1 ቆሮንቶስ 12–13
ጳውሎስ ቤተክርስቲያኗን ከክርስቶስ አካል ጋር አነጻጸረ
ስለመንፈሳዊ ስጦታዎች፣ አንድነት እና ልግስና ማስተማር
ቆሮንቶስ ትልቅ እና ጥድፊያ የበዛባት ከተማ ነበረች። አያሌ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት በዚያ ይኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከተለያየ ስፍራ የመጡ እና አንዳቸው ከሌላው የተለያዩ ነበሩ። ጳውሎስ በአንድነት እንዲኖራቸው እና አንዳቸው የሌላውን መልካም እንዲፈልጉ ሊረዳቸው ይፈልግ ነበር። ስለዚህ ደብዳቤ ጻፈላቸው።
1 ቆሮንቶስ 1፥11–13
በደብዳቤውም ሁሉም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተለያየ ስጦታ እንዳላቸው ጳውሎስ ለቅዱሳን ነገራቸው። አንዳንዶቹ የእምነት ስጦታ ነበራቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ተአምራትን የማድረግ ስጦታ ነበራቸው። አንዳንዶቹ ጥበበኞች ነበሩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሌሎችን ይፈውሱ ነበር። አንዳንዶች የተለየ ቋንቋን ይናገሩ ነበር። ሁሉም ቅዱሳን የተለያየ ስጦታ ነበራቸው፣ ነገር ግን ሁሉም የተገኙት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበር።
1 ቆሮንቶስ 12፥3–11፣ 29–30
ምንም እንኳን ቅዱሳን አንዳቸው ከሌላው የተለዩ ቢሆኑም፣ በኢየሱስ ያላቸው እምነት አንድ እንዳደረጋቸው ጳውሎስ አስተማረ። የኢየሱስን ትምህርት ለመከተል፣ ለመጠመቅ እና የእርሱን ቤተክርስቲያን ለመቀላቀል ሲወስኑ፣ በኢየሱስ በመተባበር አንድ ቡድን ሆነዋል።
1 ቆሮንቶስ 12፥27
ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ራስ፣ እጆች እና እግሮች እንዳሉት አካል ነች አለ። እያንዳንዱ የአካል ክፍል የተለያየ ስራን ያከናውናል። ጆሮ ከአይን የተለየ በመሆኑ መጥፎ ስሜት ሊሰማው አይገባውም። ራስም ለእግር፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። እያንዳንዱ ክፍል አስፈላጊ ነው፣ ሁሉም በአንድነት ይሰራሉ።
1 ቆሮንቶስ 12፥12–14።
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን የነበሩትን ቅዱሳን “የክርስቶስ አካል” በማለት ጠርቷቸዋል። የተለያዩ ስጦታዎቻቸውን በመጠቀም አንዳቸው ሌላውን በመርዳት እና በመባረክ፣ እንደተለያየ የአካል ክፍል በአንድነት እንዲሰሩ ይፈልግ ነበር።
1 ቆሮንቶስ 12፥15–27።
ይህን ለማድረግ፣ ሰዎች ልግስና የተባለ የተለየ አይነት ፍቅር ያስፈልጋቸዋል። ይህም ኢየሱስ ለእያንዳንዱ ሰው የነበረው አይነት ፍቅር ነው። ጳውሎስ፣ ልግስና ማለት ሌሎች መጥፎ ቢያስቡም አንዱ ለሌላኛው ትዕግስትን ማሳየት ማለት ነው አለ። ክፉ፣ ራስ ወዳድ፣ ወይም ቀናተኛ አለመሆን ማለት ነው። እውነትን መውደድ እና ተስፋ ያለው መሆን ማለት ነው።
(1 ቆሮንቶስ 13፥1–7፤ ሞሮኒ 7፥47
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ቅዱሳን ልግስና ለዘለኣለም እንደሚኖር ነገራቸው። ምንም የተለያየ ስጦታ ቢኖረን፣ ሁላችንም ልግስና ያሰፈልገናል። ሁላችንም በሙሉ ልባችን የሰማዩ አባታችንን ብንጠይቅ እና እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን ብንሞክር ልግስና ሊኖረን ይችላል።
1 ቆሮንቶስ 13፥1–3፣ 8፤ ሞሮኒ 7፥48