በእግዚአብሔር ፊት ልበ ሙሉ መሆን
ልግሥና እና በጎነት ሕይወታችንን እንዲሞላው በትጋት ስንፈልግ እግዚአብሔርን ለመቅረብ ያለን ልበ ሙሉነት ያድጋል።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ዛሬ በዚህ ጠቃሚ በሆነው አጠቃላይ ጉባኤ፣ እናንተን ስለማነጋግር አመስጋኝ ነኝ። ዓይኖቼ ይባስ እየደከሙ መሄዳቸውን ቀጥለዋል። መልእክቴንም ሳቀርብ ይህን ስለምትረዱ አመሰግናችኋለሁ።
የምንኖረው በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ታላቅ ፍጥነት በሚታይበት ቀን ውስጥ ነው። በብዙ ዘርፎች እድገትን ስመለከት በደስታ እሞላለሁ።
በተለይ በወጣቶቻችን መነሣሣት ይሰማኛል። በቁጥርም በርካታ ሆነው አገልግሎትን እየሰጡ ይገኛሉ። ቅድመ ዓያቶቻቸውን እየፈለጉና በቤተመቅደስ ውስጥ ሥርዓቶችን እየፈጸሙ ይገኛሉ። ወጣት ወንዶቻችን እና ወጣት ሴቶቻችን እስከዛሬ ታይቶ በማያውቅ ቁጥር የሚስዮናዊ አገልግሎት ለመሥጠት ማመልከቻዎችን እያቀረቡ ናቸው። በማደግ ላይ ያለው ትውልድ ደፋር የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ለመሆን በመነሳት ጥሪውን እየተቀበለ ነው።
በቅርቡ አዲስ ከተወለደችው የልጅ ልጄ ጋር ተገናኘሁ። ወደፊት በህይወቷ ስለሚያጋጥሟት ፈተናዎች ሳሰላስል፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላትን እምነት እንድታዳብር ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ። በእርሱ ወንጌል መኖር ለፊት ደስተኛ ኑሮዋ አስፈላጊ ነው።
እያንዳንዳችንን እንደሚያጋጥመን ሁሉ እሷም ፈተናዎች ያጋጥሟታል። ሁላችንም ህመም፣ ብስጭት፣ ፈተና እና የምናጣው ነገር ያጋጥመናል። እነዚህ ፈተናዎች የልበ ሙሉነት ስሜታችንን ያዳክማሉ። ሆኖም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተለየ ዓይነት ልበ ሙሉነት ሥሜት አላቸው።
ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ስንገባና ቃል ኪዳኖቹን ስንጠብቅ፣ ከመንፈስ የሆነ ልበ ሙሉነት ሥሜት ሊኖረን እንችላለን። ጌታ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ልበ ሙሉነታችን “በእግዚአብሔር ፊት እየጠነከረ” ሊሄድ እንደሚችል ነግሮታል። በእግዚአብሔር ፊት የልበ ሙሉነት ሥሜት ማግኘት ምን ያህል እንደሚያጽናና እስኪ አስቡት!
በእግዚአብሔር ፊት የልበ ሙሉነትን ሥሜት ስለማግኘት ስናገር፣ አሁኑኑ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የልበ ሙሉነት ሥሜት ስለማግኘት እየተናገርኩኝ ነኝ! የሰማዩ አባታችን እንደሚሰማን፣ ፍላጎታችንን ከእኛ በተሻለ እንደሚረዳልን በመተማመን መጸለይ ማለቴ ነው። የሰማዩ አባት እኛ ከምናስበው በላይ እንደሚወደን፣ ከእኛና ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር እንዲሆኑ መላእክትን እንደሚልክልን መተማመን ነው። እያንዳንዳችን ታላቅ አቅማችን ላይ እንድንደርስ ሊረዳን እንደሚፈልግ ልበ ሙሉነት እንዲኖረን ነው እየተናገርኩ ያለሁት።
አሁን፣ እንዲህ ዓይነቱን ልበ ሙሉነት የምናገኘው እንዴት ነው? ጌታ ይህንን ጥያቄ በሚከተሉት ቃላት መልሷል፦ “አንጀትህም ለሁሉም ሰው … በልግስና ይሞላ፣ እና ምግባረ በጎነትም ሳያቋርጥ አስተሳሰብህን ያሳምር፤ ከዚያም ልበ ሙሉነትህ በእግዚአብሔር ፊት እየጠነከረ ይሄዳል።”
ቁልፉ ይህ ነው! ጌታ በራሱ አንደበት እንደተናገረው፣ ልግስና እና በጎነት በእግዚአብሔር ፊት ልበ ሙሉነትን የምናገኝበትን መንገድ ይከፍታሉ! ወንድሞች እና እህቶች፣ ይህንን ማድረግ እንችላለን! ልበ ሙሉነታችን በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥም አሁኑኑ እየጠነከረ ይሄዳል!
ስለሁለቱ ስለልግሥና እና ስለበጎነት እናስብ።
በመጀመሪያ፣ ልግሥና። ከሁለት ዓመት በፊት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የቃል ኪዳን ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን፣ አስተራራቂዎች እንድንሆን ጥሪ አድርጌ ነበር። ያኔ የተናገርኩትን እደግመዋለሁ፦ “ቁጣ በጭራሽ አያሣምንም። ጠላትነት ማንንም አይገነባም። ጸብ ወደ ተነሳሱ መፍትሄዎች በፍጹም አይመራም።”
ለሰዎች ሁሉ እውነተኛ ልግስናን ማሣየት የአስተራራቂዎች መለያ ምልክት ነው! በአደባባይም ሆነ በግል በንግግራችን ውስጥ ልግስና ሊኖረን ይገባል። አስቀድሜ የለገስኩትን ምክሬን ከልባችሁ የተቀበላችሁትን አመሰግናችኋለሁ። ሆኖም አሁንም የተሻለ ማድረግ እንችላለን።
በአሁኑ ወቅት በህዝብ ውይይት እና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ጠላትነት የሚያሳስብ ነው። የጥላቻ ንግግሮች በሌሎች ሠዎች ላይ ሥሜታዊ እና ሥነ ልቡናዊ ጉዳት ያደርሣሉ። ጸብ መንፈስ ቅዱስ ቋሚ አጋራችን እንዳይሆን ያደርጋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን፣ አስተራራቂዎች በመሆን ረገድ መንገዱን መምራት አለብን። ልግሥና የተፈጥሯችን አካል ሲሆን፣ የሌሎችን ክብር የማሣጣት ስሜት አይኖረንም። በሌሎች ላይ መፍረድን እንናቆማለን። ከሁሉም የህይወት ጎዳና ለመጡ ሰዎች ልግሥና ይኖረናል። ለሁሉም ሰው ልግሥና ማሣየት ለዕድገታችን አስፈላጊ ነው። ልግስና የአምላካዊ ባህሪ መሠረት ነው።
የሰማዩ አባታችን ልባችንን በበለጠ የበጐነት ፍቅር እንዲሞላ እንለምነው- በተለይ ለመውደድ አስቸጋሪ ለሆኑ ሰዎች። በጐነት ከሰማያዊ አባታችን ለእውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች የተሰጠ ስጦታ ነው። አዳኙ የሰላም አለቃ ነው። የእርሡ የሰላም መሣሪያዎች ልንሆን ይገባናል።
አሁን ስለበጎነት እንነጋገር። ጌታ አስተሳሰባችንን ሣናቋርጥ በበጎነት እንድናሣምር ይነግረናል። ማንኛውንም አዎንታዊ ሀሳብ በበጎነት ስታሳድጉት የምታገኙትን ማበረታቻ አስቡት። በጎነት ሁሉንም ነገር የተሻለ እና ይበልጥ ደስተኛ ያደርገዋል! በሌላ በኩል፣ መጥፎ ሐሳብ፣ በጨካኝ ሃሳብ ወይም በሚያሣዝን ሐሳብ ላይ በጎነትን ስትጨምሩ ምን እንደሚሆን አስቡ። በጎነት እነዚያን ሀሳቦች ያስወግዳል። በጎነት ከአስጨናቂ እና አስቸጋሪ ሀሳቦች ነፃ ያወጣችኋል።
ወንድሞች እና እህቶች፣ ዓለም ይበልጥ ክፉ እየሆነ በሄደ መጠን፣ እኛም ይበልጥ ንፁህ እየሆንን መሄድ አለብን። ሀሣቦቻችን፣ ቃላቶቻችን እና ድርጊቶቻችን በአስተማማኝ ሁኔታ በጎ እና ክርስቶስ ለሰው ሁሉ ባለው ፍቅር የተሞሉ መሆን አለባቸው። ከፊታችን ያለው ታላቅ ዕድል እግዚአብሔር እንድንሆን የሚፈልገውን ዓይነት ሠዎች መሆን ነው።
ሀሳባችን፣ ቃላችንና ተግባራችን ያለማቋረጥ በጎነት የተሞላበትና ለሰዎች ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሕ ፍቅር የተሞላ መሆን አለበት። ስለዚህ፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የምናሳልፈው ጊዜ በጌታ ፊት ያለንን ልበ ሙሉነት ያሣድጋል። በቤተመቅደስ ውስጥ የምናሳልፈው ረዘም ያለ ጊዜ ለአዳኛችን፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት እንድንዘጋጅ ይረዳናል። የሚመጣበትን ቀን እና ሠዓት አናውቅም። ነገር ግን ለዚያ “ለታላቁ እና አስፈሪው ቀን” እንድንዘጋጅ አጥብቄ አሳስብ ዘንድ እግዚአብሔር እያነሣሣኝ እንደሆነ አውቃለሁ።
ልግሥና እና በጎነት ሕይወታችንን እንዲሞላው በትጋት ስንፈልግ፣ እግዚአብሔርን ለመቅረብ ያለን ልበ ሙሉነት ያድጋል። በጌታ ፊት ያላችሁን ልበ ሙሉነት ለማሳደግ አስባችሁ እርምጃዎችን እንድትወስዱ እጋብዛችኋለሁ። ከዚያም፣ በላቀ ልበ ሙሉነት ወደ ሰማይ አባታችን ስንሄድ፣ በበለጠ ደስታ እንሞላለን፣ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ያድጋል። እጅግ ተስፋ ከምናደርጋቸው ነገሮች የሚልቅ መንፈሳዊ ሃይልን ማግኘት እንጀምራለን።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ እየሆነ ስላለው የቤተመቅደስ ግንባታ መፋጠን ጌታን እናመሰግናለን። በእሱ አመራር ዛሬ በእያንዳንዳቸው በእነዚህ 15 ቦታዎች ላይ ቤተመቅደስ ለመገንባት እቅዶችን እናሳውቃለን፦
-
ሬይኖሳ፣ ሜክሲኮ
-
ቾሪሎስ፣ ፔሩ
-
ሪቬራ፣ ኡራጓይ
-
ካምፖ ግራንዴ፣ ብራዚል
-
ፖርቶ፣ ፖርቱጋል
-
ዩዮ፣ ናይጄሪያ
-
ሳን ሆሴ ዴል ሞንቴ፣ ፊሊፒንስ
-
ኑሜያ፣ ኒው ካሌዶኒያ
-
ሊቨርፑል፣ አውስትራሊያ
-
ኮልድዌል፣ አይዳሆ
-
ፍላግስታፍ፣ አሪዞና
-
ራፒድ ሲቲ፣ ደቡብ ዳኮታ
-
ግሪንቪል፣ ደቡብ ካሮላይና
-
ኖርፎልክ፣ ቨርጂኒያ
-
ስፓኒሽ ፎርክ፣ ዩታ
ኢየሱስ ክርስቶስ የእስራኤል አዳኝ ይህችን የእርሡን ቤተክርስቲያን እየመራ እንደሆነ እመሰክራለሁ። እንደገና ለመምጣት እየተዘጋጀ ነው። እኛም እንደዚያው እርሡን ለመቀበል እንዘጋጅ። ለዚህም የምጸልየው በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።