አጠቃላይ ጉባኤ
ሁለተኛውን ፈተና ተጠንቀቁ
የሚያዝያ 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


11:36

ሁለተኛውን ፈተና ተጠንቀቁ

ከሚወዷችሁ እና ከሚደግፏችሁ አትደበቁ፤ ይልቁንም ወደ እነርሱ ሩጡ።

ከሁለት አመታት በፊት፣ 12 ዓመት በሞላኝ ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያዬን የአሮናዊ ክህነት የሌሊት ካምፕ እንድሳተፍ ተጋበዤ ነበር። አባቴ የቡድኑ መሪ ስለነበር እና ብዙ ጊዜ በአጥቢያው ውስጥ ካሉ ወንዶች ጋር ወደ ካምፕ ስለሚሄድ እና እኔ ቤት ውስጥ እቀር ስለነበር ይህ ለረጅም ጊዜ ሲጠብቀው የነበረ ግብዣ ነበር።

ቀኑ ሲደርስ በጣም ተደሰትኩኝ። ከትላልቅ ወንዶች ጋር አንድ ለመሆን አጥብቄ ፈልጌ እንደነበር አልክድም። ተቀባይነት ለማግኘት ቆርጬ ነበር። በዚህ ጥረት ውስጥ ብዙም ሳይቆይ አብሬ እንደምሳተፍ እና የቡድኑ አባል እንደምሆን ማሳየት እንድችል የሚያደርገኝ ፈታኝ ነገር ገጠመኝ።

የተመደብኩበት ስራ በመሪዎቹ ላይ ለመቀለድ የአባቴን የመኪና ቁልፍ ማግኘት ነበር። አባቴን ለማሳመን የተናገርኩትን በትክክል አላስታውስም፣ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በኩራት በእጄ ቁልፍ ይዤ ወደ ወንዶች ቡድን ሮጥኩ።

ከዚያም ቀጣዩ ሥራ መጣ። የመኪናውን በር ከፍቼ በሹፌሩ መቀመጫ እና በመኪናው ክላክስ ማድረጊያ መካከል ዱላ እንዳስገባ ነበር። እናም ወደ መኪናው ለመግባት ምንም አይነት መንገድ እንዳይኖር በማድረግ እቃውን ማንሳት እንዳይቻል እና እስከ ማታ ድረስ እንዲጮህ በሩን መቆለፍ ነበረብኝ።

አሁን እዚህ ጋር ነው ታሪኩ በሚያሳምም መልኩ አሳፋሪ የሆነብኝ። አንዴ ዱላውን በቦታው ካስቀመጥኩ በኋላ በሩን ዘግቼ በአቅራቢያዬ በሚገኝ ቁጥቋጦ ውስጥ ለመደበቅ የቻልኩትን ያህል ሮጥኩ። መሬት ላይ ጎንበስ ስል፣ የሚያቃጥል ህመም ተሰማኝ። በጨለማ ውስጥ በችኮላ በሚዋጋ ቁልቋል ላይ ተቀመጥኩ።

የሚዋጋ ቁልቋል

የስቃይ ጩኸቴ በመኪናው ክላክስ ድምጽ ተዋጠ። በሃፍረት ወደ መኪናው በመመለስ “ኃጢያቴን” ከመናዘዝ እና ያልተለመደ እና አሳፋሪ የህክምና እርዳታ ከመፈለግ ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረኝም።

በተቀረው በዚያ ሌሊት በድንኳን ውስጥ በሆዴ ተኝቼ፣ አባቴ ጉጠት በመጠቀም የቁልቋል እሾሆቹን አስወገደልኝ… እንግዲህ፣ ለተወሰኑ ቀናት ተመቻችቼ መቀመጥ አልቻልኩም ልበል።

ያንን ገጠመኝ ብዙ ጊዜ አሰላስያለሁ። አንዳንድ መሰረታዊ መርሆች ለእኔ ግልጽ በሆኑበት ሁኔታ እንኳን አሁን በወጣትነቴ ሞኝነት መሳቅ እችላለሁ።

ተቀባይነት ለማግኘት መሻት፣ እንደምንችል ለማሳየት መሞከር—ያመልጠናል ብሎ ማሰብ፣ መዘዝን ለማስወገድ፣ ለመጥፋት መሞከርን፣ የመሳሰሉ በሰው ልጅ ባህሪ ውስጥ ያሉ ብዙ ነገሮች በተፈጥሮአዊ ሰው ውስጥ የተለመዱ ይመስላሉ። ዛሬ ትኩረቴን የማደርገው የማይገባንን ነገር ካደረግን በኋላ—መደበቅ በሚለው በመጨረሻው ባህሪ ነው።

አሁን፣ ሰው ላይ የመቀለድ የልጅነት ሙከራዬን ከከባድ ኃጢአት ጋር እያመሳሰልኩ አይደለም፣ ነገር ግን በምድራዊ ኑሮአችን ውስጥ ስንፈተን ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ተመሳሳይነቶችን ልናገኝ እንችላለን።

በኤደን ገነት አዳምና ሔዋን ያልተለመደ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ— የተትረፈረፈ ምግብ፣ ወደር የሌለው የአትክልቱ ስፍራ ውበት— የውበት ገነት ብቻ ሳይሆን፣ አረም ወይም የሚዋጋ ቁልቋል የሌለበት ገነት ነበር።

ሆኖም፣ የአትክልት ስፍራው ለህይወታቸው አስፈላጊ እድገታቸውን እንደገደበው እናውቃለን። የአትክልት ስፍራው የመጨረሻ መዳረሻ ሳይሆን የብዙዎች የመጀመሪያ ፈተና ነው፣ የሚፈትን፣ የሚያዘጋጃቸው እና ወደ መጨረሻው መዳረሻቸው ወደ አብ እና ወልድ መገኘት የሚመለሱበት ደረጃ እንዲደርሱ የሚያስችላቸው ፈተና ነበር።

በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ተቃውሞ እንደነበረ ታስታውሳላችሁ። ሉሲፈር አዳምና ሔዋንን እንዲፈትን ተፈቅዶላት ነበር። በመጀመሪያ መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ ፍሬ እንዲበላ አዳምን ፈተነው። አዳም አትካፈል የሚለውን ትእዛዝ በማስታወስ ተቃወመ። ከዚያም ፍሬውን መብላትን የመረጠች የተባረከችው ሔዋን መጣች፣ አዳምም እንዲሁ እንዲያደርግ አሳመነችው።

በኋላ ላይ አዳምና ሔዋን ይህ ውሳኔ የሰማይ አባትን እቅድ ለመፈጸም አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። ነገር ግን ፍሬውን በመመገባቸው ከአብ በቀጥታ የተሰጣቸውን —ህግተላልፈዋል። በውጤቱም መልካሙን እና ክፉን መረዳት ያመጣው ውጤት እና የፈጠረው ጭንቀት አብ ወደ ገነት መመለሱን የሚናገርበትን ድምጽ ሲሰሙ ሃዘን ውስጥ ጣላቸው። ያለ ልብስ፣ በንጽሕና ይኖሩ ስለነበር በእርግጥ ራቁታቸውን መሆናቸውን ተገነዘቡ። ነገር ግን በዚያ ቅጽበት ራቁታቸውን ከመሆናቸው የበለጠ ያሳመማቸው ምናልባት አሁን ላይ በደላቸው መገለጡ ነው። መከላከያ የሌላቸው እና ለአደጋ የተጋለጡ ሆኑ። በየትኛውም አባባል ራቁታቸውን ነበሩ።

አጋጣሚ የሚጠብቀው ሉሲፈር እንኳን የተጋለጠ እና የተዳከመ ሁኔታቸውን እያወቀ አሁንም እንደገና ከእግዚአብሔር እንዲደበቁ ፈተናቸው።

ከተሸነፍን እጅግ ትልቅ መዘዝ ሊያመጣ የሚችለውን ይህን ፈተና፣ “ሁለተኛው ፈተና” ብዬ እጠራዋለሁ። በእርግጥ፣ የእግዚአብሄርን ሕግ እንድንጥስ ከሚቀርቡት የመጀመሪያ ፈተናዎች ሁሉ መራቅ በጣም ጥሩ ነገር ነው፣ ነገር ግን በዚህ ምድር ላይ ሁሉም በተለያዩ የመጀመሪያ ፈተናዎች እንደሚሸነፉ እናውቃለን። በጉልምስና እና በመረዳታችን እድገት ስናሳይ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል ስንጥር የመጀመሪያዎቹን ፈተናዎች ለማስወገድ ያለን ጥንካሬ በቀጣይነት እንደሚሻሻል ተስፋ እናደርጋለን።

አንዳንዶች መገኘት ወይም መጋለጥ ስለማይፈልጉ ሃፍረት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማቸው ከእግዚአብሔር ለመደበቅ ሊሞክሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከእግዚአብሄር መደበቅ እንደማይቻል ብዙ ጥቅሶች ያስተምሩናል። ጥቂቶቹን አካፍላለሁ።

ጌታ ኤርምያስን በሚከተሉት ጥያቄዎች አስተምሮታል፡- “ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን?” ይላል እግዚአብሔር፡፡

ኢዮብም እንዲህ ተማረ፡-

“ዓይኖቹ በሰው መንገድ ላይ ናቸው፥ እርምጃውንም ሁሉ ያያል።

“ኃጢአትን የሚሠሩ ይሰወሩበት ዘንድ ጨለማ ወይም የሞት ጥላ የለም።”

ዘማሪው ዳዊት በግጥም እንዲህ ሲል በአድናቆት ተሞልቶ ተናግሯል፦

“አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም።

“አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። …

“የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ አቤቱ፥ አንተ እነሆ የቀድሞውንና የኋላውን አወቅህ። …

“ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?

“ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ።”

አዲስ ተቀያሪዎች

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በቅርብ ለተቀላቀሉት ሁለተኛው ፈተና በተለየ ሁኔታ ፈታኝ ሊመስል ይችላል። በጥምቀታችሁ ወቅት የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳችሁ ላይ ለመውሰድ ቃል ገብታችኋል፣ ይህም ለብዙዎች አስፈላጊ የሆነውን የአኗኗር ለውጥ ሊያስፈልገው ይችላል። የአኗኗር ዘይቤን መለወጥ ቀላል አይደለም። ብዙ ጊዜ ወደ አፍቃሪው የሰማይ አባታችሁ ለማደግ አመሎችን እና ልማዶችን እንዲሁም ግንኙነታችሁን እንድትቀይሩ ይጠይቃል።

ጠላት ለእርሱ ስውር ጥቃቶች ተጋላጭ ልትሆኑ እንደምትችሉ ያውቃል። በብዙ መንገድ እርካታ የሌለበት ያለፈው ህይወታችሁ አሁን ላይ ከእውነት በራቀ መልኩ ማራኪ እንዲመስል ያደርጋል። በራእይ መጽሐፍ ከሳሹ ተብሎ የተጠራው “ሕይወታችሁን ለመቀየር ጠንካሮች አይደላችሁም፣ ይህን ማድረግ አትችሉም፤ ከእነዚህ ሰዎች ጋር አትሄዱም፣ ፈጽሞ አይቀበሏችሁም፣ እናንተ በጣም ደካሞች ናችሁ” በሚሉ ሐሳቦች ይፈትናችኋል።

እነዚህ ሃሳቦች በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ አዲስ ለተተከላችሁ ለእናንተ እውነት የሚመስሉ ከሆኑ የከሳሹን ድምጽ እንዳትሰሙ እንለምናችኋለን። እንወዳችኋለን፣ ልታደርጉት ትችላላችሁ፤ እንቀበላችኋለን፤ ከአዳኙም ጋር ሁሉንም ነገር ለማድረግ ጥንካሬን ታገኛላችሁ። የእኛን ፍቅር እና ድጋፍ በጣም በምትፈልጉበት ጊዜ፣ ወደ ቀድሞው የአኗኗር ሁኔታችሁ አንድ እርምጃ ወደኋላ ከወሰዳችሁ እንደማንቀበላችሁ አድርጋችሁ አታስቡ። አቻ በሌለው የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ኃይል አማካኝነት እንደገና ልትፈወሱ ትችላላችሁ። ነገር ግን ከእርሱ የምትደበቁ ከሆነ እና ራሳችሁን ከአዲሱ እምነታችሁ ማህበረሰብ ካራቃችሁ ማሸነፍ እንድትችሉ ከሚረዳችሁ ምንጭ እየራቃችሁ ትሄዳላችሁ።

በቅርብ ጊዜ የተጠመቀ አንድ የምወደው ጓደኛዬ እምነትን በተናጠል መከተል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አጋራኝ። ሁሉም እየተሰናከለ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እየተባረከ የሚገሰግስ የድጋፍ ሰጪ ማህበረሰብ አካል በመሆን እና እዚያው በመቆየት ትልቅ ጥንካሬ አለ።

ፕሬዘዳንት ረስልኤም. ኔልሰን እንዲህ አስተምረዋል፣ “አለምን ማሸነፍ ማለት በአንድ ወይም ሁለት ቀን የሚከሰት አይደለም። የሚከሰተው የክርስቶስ ትምህርትን በተደጋጋሚ በምንቀበልበት በህይወት ሙሉ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ያለን እምነት የምናሳድገው በየእለቱ ንስሀ በመግባት እና በመንፈስ በረከት በኩል ሀይል የሚሰጡንን ቃል ኪዳኖች በማክበር ነው። በቃል ኪዳን መንገድ ላይ እንቆያለን እና በመንፈሳዊ ጥንካሬ፣ በግል ራዕይ፣ በተጨማሪ እምነት፣ እና በሚያገለግሉ መላዕክት እንባረካለን።”

አካላዊ ጉዳት አጋጥሟችሁ ከሆነ ተገቢውን የሕክምና ክትትል ካላደረጋችሁ እየተባባሰ ይሄዳል እንዲሁም ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል። ለመንፈሳዊ ቁስሎችም ይህ እውነት ነው። ያልታከሙ መንፈሳዊ ቁስሎች እንዲሁ ዘላለማዊ መዳናችሁን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ። ከሚወዷችሁ እና ከሚደግፏችሁ አትደበቁ ይልቁንም ወደ እነርሱ ሩጡ። መልካም ኤጲስ ቆጶሶች፣ የቅርንጫፍ ፕሬዘዳንቶች እና መሪዎች የኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ የመፈወስ ሃይል እንድታገኙ ሊረዷችሁ ይችላሉ።

ተደብቃችሁ ያላችሁ እንድትመለሱ እንለምናችኋለን። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና የኃጢያት ክፍያው የሚያቀርቧቸው ነገሮች ያስፈልጓችኋል፣ እናንተ የምትሰጡትም ያስፈልገናል። እግዚአብሔር ኃጢአታችሁን ያውቃል፣ ከእርሱ መደበቅ አትችሉም። ራሳችሁን ከእርሱ ጋር አስታርቁ።

እንደ እርሱ ቅዱሳን፣ ሁሉን የሚወድ፣ የሚቀበል እና የሚያበረታታ፣ እያንዳንዳችንም በመንገዱ እየተሻሻልን እንድንሄድ የሚሻ ቤተክርስቲያን አባልነትን ባህልን ማሳደግ አለብን።

ይህንን ሁለተኛ ፈተና ተጠንቀቁ! የጥንት እና የዘመናችንን የነቢያት ምክር ተከተሉ እንዲሁም ከአፍቃሪ አባት መደበቅ እንደማትችሉ እወቁ።

ይልቁንስ ለተአምራዊው የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ኃይል የተገኛችሁ ሁኑ። የመኖራችን አላማ “በሁሉም አይነት የሰውነትና የአዕምሮ ጉስቁልና ስር” የሚሆን፣ በሚያሳዝን ሁኔታ በብዙ የመጀመሪያ ፈተናዎች ውስጥ የሚወድቅ ደካማ ምድራዊ አካል ማግኘት፤ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ስንወድቅ እንኳን ማደግ፤ እንዲሁም እንደ አዳኛችን እና የሰማይ አባታችን እንድንሆን ይህን ካደረግን በኋላ መለኮታዊ እርዳታን ለመጠየቅ ነው። የእርሱ መንገድ ነው። ብቸኛው መንገድ ነው! እነዝህን እውነቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመሰክራለሁ፣ አሜን።