አጠቃላይ ጉባኤ
ቅዱሥ ለሆኑ ነገሮች የሚሠጥ ጥልቅ አክብሮት
የሚያዝያ 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:49

ቅዱሥ ለሆኑ ነገሮች የሚሠጥ ጥልቅ አክብሮት

ቅዱስ ለሆነ ነገር ጥልቅ አክብሮት ማሣየት እውነተኛ ምስጋናን ማዳበርን ያበረታታል፣ እውነተኛ ደስታን ያሰፋል፣ አዕምሯችንን ወደ መገለጥ ይመራል እንዲሁም በህይወታችን ውስጥ ታላቅ ደስታን ያመጣል።

በዘፀዓት መጽሐፍ ውስጥ፣ ሁላችንም ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን የሚገባንን የዕለት ተዕለት ጉዳዮቹን ወደ ጎን አድርጎ በእሳት የሚነደውን የማይቃጠለውን ቁጥቋጦ ለማየት ወደ ኮሬብ ተራራ ከሄደው ከሙሴ ጋር እንጓዛለን። እንደቀረበም፣ “እግዚአብሔር ከቁጥቋጦው ውስጥ እርሡን ጠርቶ ሙሴ፡ ሙሴ ሆይ፡ አለ። እና እርሱም እነሆኝ አለ። [እግዚአብሔርም]፣ የቆምክባት ሥፍራ የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ”አለው። በታላቅ ጥልቅ አክብሮት፣ ትህትና እና አድናቆት፣ ሙሴ ጫማውን አወለቀና የጌታን ቃል ለመስማት እንዲሁም የእርሱን ቅዱስ መገኘት ለመለማመድ ራሱን አዘጋጀ።

ያ በተቀደሰው ተራራ ላይ በጥልቅ አክብሮት የተሞላ የጌታ መገለጥ ተሞክሮ፣ ሙሴን ከመለኮታዊ ማንነቱ ጋር ያገናኘው በርግጥም ይህ በሕይወቱ የተለየ ጥሪ እንዲመርጥ ያደረገውከተራ እረኝነት ወደ ታላቅ ነቢይነት የመቀየሩ ቁልፍ ክፍል ነበር። በተመሳሳይ መልኩ፣ እያንዳንዳችንም የጥልቅ አክብሮትን በጎነት የመንፈሳዊ ባህርያችን ቅዱስ ክፍል በማድረግ ደቀመዝሙርነታችንን ከፍ ወዳለ መንፈሳዊነት መቀየር እንችላለን።

ጥልቅ አክብሮት የሚለው ቃል የመጣው ሪቨሪ[revereri]፣ ከተሠኘ ከአንድ የላቲን ግሥ ሲሆን ትርጉሙም “በአክብሮታዊ ፍርሃት መቆም” ማለት ነው። ከወንጌል አንፃር ሲታይ፣ ይህ ትርጉም ጥልቅ አክብሮትን፣ ፍቅርን እና የምስጋና ስሜትን ወይም አመለካከትን ቀላቅሎ ይይዛል። ልባቸው በተሰበረ እንዲሁም ለእግዚአብሄር እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ባደሩ ሰዎች ለቅዱሱ የሚገለፀው እንዲህ ያለው አገላለፅ በነፍሣቸው ውስጥ የላቀ ደስታን ይፈጥራል።

ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች የሚሠጥ ጥልቅ አክብሮት የአንድ ወሣኝ መንፈሳዊ ብቃት ትልቁ መገለጫ ነው፤ ከቅድስና ጋር ያለን ቁርኝት ውጤት ሲሆን ለሰማይ አባታችን እና ለአዳኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ፍቅር እና ቀረቤታ ያንፀባርቃል። በተጨማሪም በጣም ከላቁ የነፍስ ተሞክሮዎች አንዱ ነው። እንደዚህ ያለው በጎነት ሀሣባችንን፣ ልባችንን እና ህይወታችንን ወደ አምላክ ይመራል። እንደ እውነቱ ከሆነ ጥልቅ አክብሮት የመንፈሳዊነት አንዱ ገጽታ ብቻ አይደለም፤ ልክ ልጆቻችን “ጥልቅ አክብሮት ሣሣይ የሠማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ በቅርብ እንዳሉ በልቤ አውቃለሁ”፣ የሚለውን መዝሙር ሲዘምሩ እንዳስተማሩን መንፈሳዊነት የተገነባበት መሠረትና ከአምላክ ጋር የግል ግንኙነትን የሚፈጥር ዋናው ነገር ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ከእግዚአብሔር እና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ጥልቅ ኅብረት ለመመሥረት ራሳችንን ዝግጁ እናደርግ ዘንድ በዚያውም መንፈሳዊ ባህርያችንን እንድናጠናክር የጥልቅ አክብሮት ስጦታን በሕይወታችን እንድናሳድግ ተጋብዘናል። በልባችን ውስጥ እንደዚህ ዓይነት በዛ ያሉ ስሜቶች ቢኖሩን ኖሮ ያለ ጥርጥር በህይወታችን ውስጥ ታላቅ ደስታ እና ሃሴት ይኖር ነበር፣ እንዲሁም ሀዘን እና መከፋት ቦታ አይኖራቸውም ነበር። ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ጥልቅ አክብሮት ማሳየት በየቀኑ ለምናደርጋቸው ለአብዛኞቹ ነገሮች ትርጉም እንደሚሰጥ እና ከፍ ላሉ እና ለተቀደሱ ነገሮች ፍርሃት፣ አክብሮት እና ፍቅር እንዲኖረን በማድረግ የአመስጋኝነት ስሜታችንን እንደሚያጠናክርልን ማስታወስ አለብን።

እንደ አለመታደል ሆኖ፣ የምንኖረው ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንግዳ ነገር እየሆነ መምጣቱ እየጨመረ በመጣበት ዓለም ውስጥ ነው። በርግጥ የትኛውም የሚነበብ የታብሎይድ መጽሔት፣ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ወይም የኢንተርኔት ጉብኝት እንደሚመሰክረው ዓለም አክብሮት የሚጎድለውን ታከብራለች። ቅዱስ ለሆነው ነገር ክብር አለመስጠት እያደገ የሚሄድ የአመለካከት ፍላጎት ማጣትን እንዲሁም የባሕርይ ቸልተኝነትን ይፈጥራል፣ ይህም አንድን ትውልድ በፍጥነት ወደ ግዴለሽነት የሚያሸጋግር ሲሆን ቀጣዩን ትውልድም ወደ ሰቆቃ ሊያስገባው ይችላል።

በተጨማሪም ጥልቅ አክብሮት ማጣት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረጉ ቃል ኪዳኖች ከሚፈጥሩት ጥምረት ሊያርቀን እና በአምላክ ፊት ያለብንን የተጠያቂነት ስሜት ሊያጠፋው ይችላል። በውጤቱም ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ፍላጎቶቻችንን በማርካት ስለራሳችን ምቾት ብቻ የምንቆርቆር የመሆን አደጋ ውስጥ እንገባለን፤ በመጨረሻም እግዚአብሔርን ጨምሮ ቅዱስ የሆኑ ነገሮችን ወደምንንቅበት ሥፍራ እንደርሳለን፣ በዚህም ምክንያት የሠማይ አባት ልጆች በመሆናችን ያለንን መለኮታዊ ተፈጥሮ እንንቃለን። ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ጥልቅ አክብሮት አለማሣየት በዚህ በምንኖርበት ዘመን ለመንፈሳዊ ህልውናችን እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን የራእይ መንገዶቻችንን በማስተጓጎል የጠላትን ዓላማ ያራምዳል።

ቅዱስ ለሆነ ነገር ጥልቅ አክብሮት የመሥጠት ትርጉም እና አስፈላጊነት በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ በደንብ በዝርዝር ተቀምጧል። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ ያለ አንድ ምሳሌ ለሰማይ አባታችን እና ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስጥልቅ አክብሮት ማሣየት የሠለስቲያል መንግሥትን ለሚቀበሉ ሠዎች አስፈላጊ ምግባር መሆኑን የሚያሣይ ይመስላል።

የቤተክርስቲያን አባላት ሁላችንም የአብን እና የወልድን ምስሎች የምንገልፅበትን መንገድ ጨምሮ በሁሉም ረገድ በፍፁም ቅድስና እና በክብር ልንይዛቸው እንጥራለን። የመንፈስ ቅዱስ ምሪት እነዚህ ምስሎች የአብን እና የወልድን ቅዱስ ተፈጥሮ፣ ባህርይ እና አምላካዊ ባህርያት እንዴት እንደሚያንጸባርቁ በመወሰን ረገድ ወሳኝ ክፍል ነው። ይዘትን እና ምስሎችን ለማመንጨት የሚውሉ ሠው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) መጠቀምን ጨምሮ በቴክኖሎጂ የሚቀርቡ የረቀቁ መሳሪያዎችን በመጠቀም በሰማዩ አባታችን እና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በትምህርታቸው ላይ ያለንን ዋነኛ ትኩረት ሊከፋፍሉ የሚችሉ በስእል ገላጭ የሆኑ ነገሮችን እናስወግዳለን።

ይኸው መርህ በቤተክርስቲያኗ ሕጋዊ የመገናኛ መንገዶች በሚቀርብ በማንኛውም የመረጃ ምንጭ ላይ ተግባራዊ ይሆናል። እያንዳንዱ ትምህርት፣ መጽሐፍ፣ መምሪያ እና መልዕክት የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ቅዱስ ምግባር፣ እሴቶች እና ደረጃዎች መጠበቃችንን ለማረጋገጥ በመንፈስ መሪነት በጥንቃቄ የተዘጋጀ እና የጸደቀ ነው። ሽማግሌ ዴቪድ ኤ. ቤድናር፣ በቅርብ ጊዜ ለወጣት ጎልማሶች በሠጡት መልዕክት ላይ “በመንፈሳዊነት እና በቴክኖሎጂ መካከል ያለውን ውስብስብ የሆነ የጋራ መገናኛ በጥንቃቄ ለመምራት፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን በትህትና እና በጸሎት፦(1) ለሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀማቸው መመሪያ ሊሆኑ የሚችሉ የወንጌል መርሆችን መለየት እና (2) የመንፈስ ቅዱስን ጓደኝነት እና መንፈሳዊ የራእይ ስጦታን ለማግኘት በቅንነት መጣር አለባቸው”፣ ሲሉ አስተምረዋል።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውስብስብ እየሆነ የመሄዱን ያህል፣ በቀላሉ ከመንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ በሚመጣው ጥልቅ አክብሮት ውስጥ የሚገኘውን መደነቅ፣ አክብሮታዊ ፍርሃት እና መገረም መምሰል አይችልም። የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን፣ በሠው ሠራሽ አስተውሎት AI የመነጩ ይዘቶችን እና ምስሎችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም ከእግዚአብሔር እና ከልጁ ጋር ያለንን ግንኙነት እንዳናዳክም መጠንቀቅ ይኖርብናል። በዘመናዊ የቴክኖሎጂ “የሥጋ ክንድ” ላይ መታመን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ ሊገኝ ለሚችለው ማነሳሻ፣ እነፃ እና ምስክርነት በቂ ያልሆነ እና አክብሮት የጎደለው መተኪያ መሆኑን ማስታወስ አለብን። ኔፊ እንደተናገረው፦ “አቤቱ ጌታ፣ በአንተ ታምኛለሁ፣ እንዲሁም ለዘለዓለም በአንተ እታመናለሁ። እምነቴን በስጋ ክንድ ላይ አላደርግም።”

በሌላ ራዕይ፣ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ለጌታ የተገነቡ ቤተመቅደሶች ለእርሱ የጥልቅ አክብሮት ስፍራ መሆን እንዳለባቸው መመሪያን ተቀብሏል። ውድ ነቢያችን ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን በአገልግሎታቸው በሙሉ በቅዱስ ቤተመቅደስ ውስጥ የምናቀርበው አምልኮ በጥልቅ አክብሮት የተሞላ መሆን እንዳለበት አበክረው ገልፀዋል። በጌታ ቤት ውስጥ ወደ አብ እና ወደ ወልድ ቅዱስ መገኘት ስለመግባት ተምረናል። ወደ ቤተመቅደስ ስንገባ እና እዚያ ባሉት ቅዱስ ሥርዓቶች ለመሳተፍ እራሳችንን ስናዘጋጅ ከምናደርጋቸው የመጀመሪያዎቹ ነገሮች አንዱ ጫማችንን ማውለቅ እና ነጭ ልብሳችን መልበሥ መሆኑ ሁልጊዜ አስተማሪ እና የሚያነሣሣ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እንደ ሙሴ፣ በዓላማ ከተንቀሣቀስን፣ ምድራዊ ጫማችንን ማውለቅ ቅዱስ መሬትን ለመርገጥ እና ከፍ ወዳሉ እና ቅዱስ ወደሆኑ መንገዶች የመሸጋገር መጀመሪያ መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ያለንን ጥልቅ አክብሮት ለማወቅ እና ደቀ መዝሙርነታችንን ጥልቅ ወደ ሆነ መንፈሳዊነት እና ቁርጠኝነት ለመቀየር ልክ እንደ ሙሴ ወደ ተራራ ጫፍ መውጣት አያስፈልገንም። ለምሳሌ ያህል የቤት አካባቢያችንን ከዓለማዊ ተጽዕኖዎች ለመከላከል ስንጥር ልናገኘው እንችላለን። ይህ በቅንነት እና በሙሉ መንፈሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለሠማዩ አባታችን በመጸለይ እና አዳኛችንን በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ የሚገኙትን እና የነቢያቶቻችንን ትምህርት በትጋት በማጥናት እርሱን የበለጠ ለማወቅ በመፈለግ ሊደረግ ይችላል። በተጨማሪም ትዕዛዛቱን በመጠበቅ ከጌታ ጋር የገባናቸውን ቃል ኪዳኖች ለማክበር ስንጥር እንደዚህ አይነት መንፈሳዊ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። እነዚህ ጥረቶች ጸጥ ያለ እና እርግጠኛ የሆነ ሠላምን ወደ ልባችን ያመጣሉ። በእንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ላይ ማተኮር ቤቶቻችንን ጥልቅ አክብሮት ወደተላበሠ የመንፈሳዊ መሸሸጊያ ቦታ—ልክ ሙሴ በተራራው ላይ እንደነበረው ተሞክሮ፣ መንፈሡ ወደሚያድርበት የግል የእምነት የተቀደሠ ቦታ ወደመሆን ለመለወጥ ይረዳል።

እንዲሁም ልባችንን ወደ ጌታ መመለስን ጨምሮ በቤተክርስቲያኗ የአምልኮ አገልግሎት ላይ በታማኝነት ስንሣተፍ፣ ቅዱስ መዝሙሮችን በቅንነት ስንዘምር እንደዚህ ዓይነት መንፈሳዊ እመርታን ልናገኝ እንችላለን። ልክ እንደ ሙሴ—ዓለማዊ የሆኑ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን፣ በተለይም የሞባይል ስልኮቻችንን ወይም ከዚህ የተቀደሰ ጊዜ ጋር የማይስማማ ነገርን ማስወገድ፣ አእምሮአችንን እና ልባችንን በአዳኙ እና ከቃል ኪዳኖቻችን ጋር በሃጢያት ክፍያው ላይ በማድረግ ትኩረታችንን ቅዱስ ቁርባንን ወደመካፈል እንድንመልስ ያስችለናል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ቅዱስ ቁርባን ላይ ትኩረት ማድረግ ከአዳኙ ጋር በጥልቅ አክብሮት ቃልኪዳናችንን የሚያድስ የግንኙነት ጊዜ እንዲኖረን እንዲሁም ሰንበትን አስደሳች ያደርጋል ህይወታችንንም በአስደናቂነት ይለውጣል።

በመጨረሻም በጌታ ቤት ተራራ—በቅዱስ ቤተመቅደሳችን—ዘወትር ስናመልክ እና በተለይም የሥጋዊ ህይወት ፈተናዎች ሲያጋጥሙን በቃል ኪዳን መተማመን ለመኖር ስንጥር ይህንን መንፈሳዊ ለውጥ ደቀመዝሙርነታችን ላይ ልናይ እንችላለን።

እኔና ባለቤቴ እነዚህን መመሪያዎች በህይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ስንጥር በግለሠብ ደረጃ የተወሰነ የተቀደሰ የተራራ ላይ ጊዜዎችን በጥልቅ አክብሮት አሳልፈናል፣ ይህም በደቀመዝሙርነታችን ላይ ትርጉም ያለው አስደናቂ ለውጥ አምጥቷል። ባለቤቴ ገና በሆስፒታል እያገገመች እያለች ያለጊዜው ተወልዶ ያረፈውን ሁለተኛ ልጃችንን ሣንቀብር በመቃብር ስፍራ ውስጥ በእግር የሄድነው ትናንት የሆነ ያህል ትዝ ይለኛል። ያንን አስቸጋሪ ፈተና መቋቋም እችል ዘንድ እንዲረዳኝ ለመጠየቅ ወደ እግዚአብሄር በጥልቅ አክብሮት አጥብቄ መጸለዬን አስታውሳለሁ። በዚያ ቅጽበት እኔና ባለቤቴ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመኖር የሚገኘውን ደስታ በመያዝ ብንጸና በህይወታችን ሁሉም ነገር መልካም እንደሚሆን በልቤ ግልጽ እና ጠንካራ መንፈሳዊ ማረጋገጫ አገኘሁ። በዚያን ጊዜ ከአቅም በላይ የሆነ፣ የሚያሳዝን ፈተና የነበረ የሚመስለው ነገር ወደ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮታዊ ተሞክሮ፣ እምነታችንን ወደሚደግፍ እና ከጌታ ጋር በገባናቸው ቃል ኪዳኖች እና ለእኔ እና ለቤተሰቤ በገባው ቃል ኪዳኖች ላይ መተማመንን የሰጠን ጥልቅ ተሞክሮ ወደመሆን ተለወጠ።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ቅዱስ ለሆነ ነገር ጥልቅ አክብሮት ማሣየት እውነተኛ ምስጋናን ማዳበርን ያበረታታል፣ እውነተኛ ደስታን ያሰፋል፣ አዕምሯችንን ወደ መገለጥ ይመራል እንዲሁም በህይወታችን ውስጥ ታላቅ ደስታን ያመጣል። እግሮቻችንን በተቀደሰ መሬት ላይ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋን እና ልባችንንም በእግዚአብሄር ላይ እንዲያተኩር ያደርጋል።

እንዲህ ያለውን በጎነት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ለማካተት ስንጥር ትሕትናን ማሳደግ፣ እግዚአብሔር ለእኛ ስላለው ፈቃድ ግንዛቤ ማስፋት እንዲሁም ከጌታ ጋር በገባናቸው የቃል ኪዳን ተስፋዎች ላይ ያለንን መተማመን ማጠናከር እንደምንችል እመሰክርላችኋለሁ። ለተቀደሱ ነገሮች የሚሠጥን ይህንን የጥልቅ አክብሮት ሥጦታ የራሳችን ስናደርግ—በጌታ ቤት ተራራም ሆነ፣ በመሠብሠቢያ አዳራሽ ወይም በራሳችን ቤቶች ከሠማይ አባታችን እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅር ጋር ስንገናኝ በሚያስገርም መደነቅ እና አክብሮታዊ ፍርሃት እንደምንሞላ እመሰክራለሁ። እነዚህን እውነቶች በቅዱስ አዳኛችን እና በቤዛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በጥልቅ አክብሮት እመሠክራለሁ፣ አሜን።