አጠቃላይ ጉባኤ
በመንፈሳዊነት በእርሱ ሙሉ መሆን
የሚያዝያ 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


11:29

በመንፈሳዊነት በእርሱ ሙሉ መሆን

ሙሉ መሆን ማለት በዚህ ህይወት አካላዊ እና ስሜታዊ እድሳት ማግኘት ማለት አይደለም። ሙሉ መሆን በእምነት እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በመቀየር የሚመጣ ነው።

አስር ለምጻሞች ወደ ጌታ፣ ‘’ማረን’’ በማለት ጮኹ። ኢየሱስም እንዲሁ አደረገ። እርሱም ሄደው ራሳቸውን ለካህን እንዲያሳዩ ነገራቸው፣ በሄዱም ጊዜ፣ ከደዌያቸው ነጹ።

ከእነርሱም አንዱ፣ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን በጩኸት አመሰገነ። ወደ ጌታም ተመለሰ፣ በእግሩም ላይ ወደቀና ምስጋናውንም ገለጸ።

አዳኙም አመስጋኝ ለነበረው ለእርሱ እንዲህ አለው፣ “እምነትህ አድኖሃል።”

ኢየሱስ ክርስቶስ አስር ለምጻሞችን ፈውሶ ነበር። ነገር ግን አንዱ፣ ወደ አዳኙ በመምጣት፣ ተጨማሪ ነገርን ተቀበለ። ሙሉ ጤናማ ሆነ።

ዘጠኝ ለምጻሞች በአካል ተፈውሰዋል።

አንዱ በአካል ተፈውሷል እና በመንፈስም ሙሉ ሆነ።

ይህንን ታሪክ በማስታወስ፣ ተቃራኒው እውነት ቢሆንስ በማለት ተገረምኩ። ፈውስ እና ሙሉ መሆን አንድ ካልሆኑ፣ ነገር ግን በአካል እና በስሜት ካልተፈወሰ፣ አንድ ሰው በእርሱ በመንፈሳዊነት ሙሉ ሊሆን ይችላልን?

ታላቁ ፈዋሽ--አካላዊ እና ስሜታዊ---ህመሞቻችንን በሙሉ በራሱ ጊዜ ይፈውሳል። ነገር ግን ፈውስን ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ፣ አንድ ሰው ሙሉ ሊሆን ይችላልን?

በመንፈሳዊነት ሙሉ መሆን ማለት ምን ማለት ሊሆን ይችላል?

እርሱን በእምነት ለመከተል ነጻ ምርጫችንን ስንጠቀም፣ እንዲቀይርልን ልባችንን ለእርሱ ስናስገዛ፣ ትእዛዛቱን ስንጠብቅ፣ እና ከእርሱም ጋር የቃልኪዳን ግንኙነት ስናደርግ፣ እርሱ ወዳለበት እስከምንመለስ እና በሁሉም መንገድ እስከምንፈወስ ድረስ በዚህ ምድራዊ በሆነው ማንነት ውጣ ውረዶች በየዋህነት ስንጸና እና ስንማር በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ እንሆናለን። እኔ ከእርሱ ጋር ባለኝ ግንኙነት በሙሉ ልብ ከሆንኩ፣ ፈውስን እየተጠባበቅሁ፣ ሙሉ መሆን እችላለሁ።

እምነት በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋን ይወልዳል። በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነ እምነት የተወለደን ሙሉነት---ለማግኘት በማደርገው ጥረት ተስፋን አገኛለሁ። በእርሱ ያለኝ እምነት ለፈውስ ያለኝን ተስፋ ይጨምርልኛል፣ እና ያም ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለኝን እምነት ያጠናክርልኛል። ይህም ሃይለኛ ኡደት ነው።

ጌታ ለኢኖስ እምነቱ ‘’ሙሉ’’ እንዳደረገው ነገረው። ኢኖስ ነቢይ በሆነው በአባቱ በያእቆብ ቃላት ላይ ባሰላሰለ ጊዜ፣ ለዘለዓለም ህይወት የነበረውን እድል ለመረዳት በተራበ ጊዜ፣ በታላቅ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በጮኸ ጊዜ ሙሉነት መጣለት። በዚያ የፍላጎት እና የትህትና ማንነት ውስጥ፣ ሃጢያቱ እንደተሰረየለት በማስታወቅ፣ የጌታ ድምጽ ወደ እርሱ መጣ። ኢኖስm፣ ‘’እንዴት ሊሆን ቻለ?’’ በማለት ጌታን ጠየቀ። ጌታም እንዲህ መለሰ፣ “በክርስቶስ ባለህ እምነት ምክንያት ነው። … ሂድ እምነትህ አድኖሀል።”

በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት ውስጥ፣ አካላዊ እና ስሜታዊ ፈውሶችን በመጠበቅ እና ተስፋ በማድረግ ላይ እያለን በመንፈሳዊነት ሙሉ መሆንን መፈለግ እንችላለን።

በእርሱ የሃጢያት ክፍያ መስዋእትነት አማካይነት፣ እና ከልብ ንሰሃ ስንገባ፣ ለኢኖስ እንዳደረገው፣ አዳኙ ከሃጢያት ይፈውሰናል። የእርሱ ወሰን የሌለው የሃጢያት ክፍያ ለሃዘናችን እንዲሁ ይደርስልናል።

ነገር ግን---ስር ለሰደደ ህመም፣ የአእምሮ መዛባቶች፣ ካንሰር፣ ድብርት፣ ጭንቀት፣ እና ለመሳሰሉት ህመሞች እና በሽታዎች ፈውስን ላያዘጋጅልን ይችላል። የዚያ አይነቱ ፈውስ በጌታ ጊዜ የሚሆን ነው። እና በጊዜ ሂደት፣ በእርሱ ያለንን እምነት በመለማመድ ሙሉ ለመሆን መምረጥ እንችላለን!

ሙሉ መሆን ማለት የተሟላ መሆን ማለት ነው። በአብዛኛው ሙሽራው በመጣ ጊዜ መቅረዛቸውን በዘይት ሞልተው እንደነበሩት አምስቱ ልባሞች፣ መቅረዛችንን ወደ እርሱ በሚለውጥ ተስማሚ ዘይት ስንሞላ በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ልንሆን እንችላለን። በዚያ መንገድ፣ ምሳሌያዊ ለሆነው የሰርግ እራት፣ ለዳግም ምጽአቱ እንዘጋጃለን።

በምሳሌው ውስጥ፣ ሁሉም አስሩም ቆነጃጅት በትክክለኛው አቅጣጫ፣ ሙሽራውን ሲጠባበቁ ነበር። እያንዳንዳቸው መቅረዝ ይዘው መጡ።

ነገር ግን እርሱ በመጣ ጊዜ፣ ባልተጠበቀ የእኩለ ሌሊት ሰዓት ላይ፣ አምስቱ ሰነፎች በመቅረዛቸው ውስጥ በቂ ዘይት አልነበራቸውም። እነርሱ እንደ ሃጢያተኛ አልተቆጠሩም፣ ይልቁኑም እንደ ሰነፍ ተቆጥረዋል። ሰነፎቹ በመለወጥ ዘይት መቅረዛቸው በርቶ እንዲቆይ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አላደረጉም።

እና በመሆኑም፣ ወደ ሰርጉ ግብዣ ለመግባት እንዲፈቀድላቸው ባደረጉት ልመና መሰረት፣ ሙሽራው ሲመልስ፣ ‘’አታውቁኝም’’ አላቸው።

የሚያመለክተውም፣ አምስቱ ልባም ቆነጃጅት አውቀውታል ማለት ነው። እነርሱ በእርሱ ሙሉ ነበሩ።

መቅረዛቸው ውድ በሆነ የመለወጥ ዘይት የተሞላ ሲሆን ይህም ልባሞቹን ደናግሎች ወደ ሰርጉ ግብዣ እንዲገቡ እና በሙሽራው ቀኝ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል።

በአዳኙ እንደተገለጸው፣ ’’ሙሽራው በሚመጣበት ጊዜ ዝግጁ መሆን እንድትችሉ፣ መብራታችሁን አስተካክላችሁ በመለኮስ እና ዘይታችሁን በመያዝ፣ ታማኝ ሁኑ፣ ዘውትርም ጸልዩ።’’

አምስቱ ልባም ቆነጃጅት በቤን ሐሞንድ

አምስቱ ልባም ቆነጃጅት፣ በቤን ሐሞንድ

አስደናቂ የቅርጻቅርጽ ስራ አምስቱን ቆነጃጅት የሚገልጸው በቤተመቅደሱ የሴቶች መደራጃ ህንጻ የውጪኛው በሮች ላይ እና በሶልት ሌክ ቤተመቅደስ ጥላው ላይ በቅርቡተቀምጧል።

ስፍራው ከምሳሌው ተገቢነት ጋር የሚስማማ ነው። ምክንያቱም ቃልኪዳንን ስናደርግ እና ስንጠብቅ፣ በተለይም በጌታ ቤት ውስጥ የሚገኙትን በሚመለከት፣ በመለወጥ ዘይት መቅረዞቻችንን እንሞላለን።

አምስቱ ልባም ቆነጃጅት ብርሃናቸውን ሲያካፍሉ።
አምስቱ ልባም ቆነጃጅት በቤን ሐሞንድ

አምስቱን ልባም ቆነጃጅት የሚወክሉት ሴቶች የመለወጥ ዘይታቸውን ለሌሎች ባለማካፈላቸው፣ በዘይት የተሞላውን እና በድምቀት ሲያበራ የነበረውን መቅረዛቸውን ከፍ አድርገው ለሌሎች ብርሃናቸውን አካፍለውበታል። በአስደናቂ ሁኔታ አንዳቸው ሌላውን ትከሻ ለትከሻ ሲደግፉ፣ አንድ ክንድ በሌላው ዙሪያ፣ የዓይን ግንኙነት በመፍጠር እና ሌሎችን ወደ ብርሃን እንዲመጡ በመጋበዝ ይታያሉ።

በእርግጥም፣ “እኛ የአለም ብርሀን ነን።’’ አዳኙ እንዳስተማረው፤

‘’የዚህ ህዝብ ብርሃን እንድትሆኑ አሰጣችኋለሁ። በኮረብታ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።

‘’ሻማን አብርተን ከእንቅብ በታች እናኖረዋለንን? “ አይደለም፣ በመቅረዙ ላይ እንጂ፤ እና እርሱም በቤት ላሉት ሁሉ ያበራል፤

‘’ስለዚህ ሰዎች መልካም ስራዎቻችሁን ተመልክተው፣ እናም በሰማይ ያለው አባታችሁን ያከብሩ ዘንድ ብርሃናችሁ በዚህ ህዝብ ፊት ይብራ።’’

እኛ የእርሱን ብርሃን እንድናካፍል ታዘናል። ስለዚህ መቅረዛችሁን በኢየሱስ ክርስቶስ የመለወጥ ዘይት ሙሉ እንዲሁም መቅረዛችሁን በማስተካከል እና በደማቁ እንዲበራ ለማድረግ ተዘጋጁ። ከዚያም ያ ብርሃን እንዲበራ አድርጉ። ብርሃናችንን በምናካፍል ጊዜ፣ የኢየሱስን እፎይታ ለሌሎች እናመጣለን፣ ለእርሱ ያለን መለወጥ የጠለቀ ይሆናል፣ እና ለፈውስ እየጠበቅን እያለን ሙሉ መሆን እንችላለን። እና ብርሃናችንን በደማቁ እንዲበራ ባደረግን ጊዜ፣ እየጠበቅን እያለን እንኳ ደስተኞች መሆን እንችላለን።

ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስንቀየር ሙሉ መሆን እንደምንችል እና ለፈውስ እየጠበቅንም ቢሆን፣ ከእርሱ ጉልበትን እንደምናገኝ የቅዱስ መጽሀፍ ምሳሌ ይህንን መርህ ለማጠናከር ይጠቅማል።

ሃዋርያው ጳውሎስ “ለስጋዬ መውጊያ፣” በማለት የገለጸው የተወሰነ አይነት መከራ ነበረበት በዚህም ጌታ ያስወግድለት ዘንድ ሶስት ጊዜ ጠይቋል። ጌታም ለጳውሎስ “ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ሀይሌ በድካምህ ይገለጻልና” አለው። ለዚህም ጳውሎስ እንዲህ አወጀ፦

“እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።

“ስለሆነም ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያኔ ሃይለኛ ነኝና።”

የጳውሎስ ምሳሌ የሚያሳየን በድካማችንም እንኳ ቢሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ብርታታችን ፍጹም ሊሆን ይችላል—ያም፣ ምሉ እና የተሟላ ነው። በምድራዊ ትግሎች እየተጋደሉ ያሉ እነዚያ፣ እናም በእምነታቸው እንደ ጳውሎስ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱ፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የመሆንን በረከት ሊቀበሉ ይችላሉ።

ጳውሎስ ከስቃዩ አልተፈወሰም፣ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊነት ሙሉ ነበር። እና በመከራውም እንኳ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የመለወጡ ብርሃን ያበራ ነበር እና ሃሴትንም አድርጓል። ለፊሊጵሲዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ሲናገር፣ ‘’ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ እና ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ።’’

እህቶች እና ወንድሞች፣ መልሱ አዎን ነው፣ አካላዊ እና ስሜታዊ ፈውሶችን በመጠበቅ ላይ እያለን በመንፈሳዊነት ሙሉ መሆን እንችላለን። ሙሉ መሆን ማለት በዚህ ህይወት አካላዊ እና ስሜታዊ እድሳት ማግኘት ማለት አይደለም። ሙሉነት በኢየሱስ ክርስቶስ ባለ እምነት እና መለወጥ የሚወለድ ነው እና የዚያ መለወጥ ብርሃን እንዲበራ ማድረግ ነው።

‘’ብዙዎች ተጠርተዋል፣ ነገር ግን [ለመመረጥ] የመረጡት ጥቂቶች ናቸው።’’

ሁሉም በትንሳኤ ላይ በስጋ እና በስሜት ይፈወሳሉ። ነገር ግን እናንተ አሁን በእርሱ ሙሉ ለመሆን እንመርጣለን?

እኔ፣ ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀየርኩ መሆኔን፣ በደስታ አውጃለሁ፣ በእርሱ ሙሉ ለመሆን እየጣርኩ ነው። በእርሱ ጊዜ፣ ሁሉም ነገሮች ዳግም እንደሚመለሱ እና ፈውስ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ፣ ምክንያቱም እርሱ ህያው ነውና።

መቅደላዊት ማሪያም በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈወሰች ሴት ነበረች። እና እርስዋም በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ የነበረች ሴት ነበረች። እንደ እርሱ ደቀ መዝሙር፣ በገሊላ ዙሪያ አዳኙን ተከትላለች እና እርሱንም አገልግላለች።

እርስዋ የሞቱ ምስክር በመሆን፣ ከመስቀሉ ስር ነበረች።

የቀብሩን ዝግጅት ለመፈጸም ወደ መቃብሩ ሄዳለች እና የጌታ አካል እንዳልነበረ በመቃብሩም ላይ ያኖሩት ድንጋይ እንደተወሰደ አውቃለች። በመጀመሪያ በመላእክት እና በኋላም በአዳኙ በራሱ፣ ‘’አንቺ ሴት፣ ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንን ትፈልጊያለሽ?’’ ተብላ ስትጠየቅ በመቃብሩ ስፍራ እያለቀሰች ነበር።

ማርያምም፣ ‘’ጌታዬን ወስደውታል፣ እና ወዴት እንዳኖሩት አላውቅም’’ በማለት አለቀሰች።

እና ኢየሱስም በዝግታ በስሟ፣ “ማርያም” በማለት ጠራት። እና እርሷም አወቀችው እና በአክብሮት፣ ‘’ራቦኒ … መምህር’’ በማለት መለሰች።

ስለ አዳኙ ሲተነብይ፣ ኢሳይያስ፣ ‘’እርሱ ሞትን በድል ይውጣል፤ እና ጌታ አምላክም እንባን ሁሉ ከፊታቸው ያብሳል’’ በማለት ተናግሯል።

የእርሱ ትንሳኤ የማርያም እንባዎች እንዲታበሱ አስችሏል። በርግጥም የእናንተንም እንዲሁ ያብሳል።

ማርያም የመጀመሪያዋ ያረገው አዳኝ ምስክር ነበረች። እና ያየችውንም ለሌሎች ለመመስከር የመጀመሪያዋ ነበረች።

እኔ በትህትና በማርያም ምስክርነት ላይ እጨምራለሁ። እርሱ ተነስቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው ነው። በመጨረሻም፣ ሁሉም በእርሱ፣ በአካል እና በስሜት ይፈወሳሉ። እና ያንን ፈውስ ስንጠባበቅ፣ በታላቁ ፈዋሽ ያለን እምነት በመንፈሳዊነት ሙሉ ያደርገናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ሉቃስ 17፥11–19 ተመልከቱ። ‘’ሙሉ መሆን’’ የሚለው ቃል ከግሪኩ ማዳን፣ መቤዠት፣ ወይም መፈወስ ከሚለው የተተረጎመ ነው። ያም ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል ሊፈውሰን እንደሚችል የሚያሳይ ሲሆን፣ እና በተጨማሪም እርሱ መቤዠት፣ ማዳን፣ እና በሌሎች መንገዶች ሊፈውሰን እንደሚችል የሚያመላክት ነው።

  2. Alma 40:23 ይመልከቱ፤ ‘’ነፍስ ወደ ስጋ፣ ስጋም ወደ ነፍስ በዳግም ይመለሳል፤ አዎን፣ እናም ማንኛውም እጅና እግር እንዲሁም መገጣጠሚያ ወደ ቀድሞ ቦታው ይመለሳል፤ አዎን፣ የራስ ፀጉርም ቢሆን አይጠፋም፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር ወደ ተገቢው እናም ትክክለኛ አቋሙ ይመለሳል።’’ ደግሞም ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “Jesus Christ—the Master Healer,” Liahona, ህዳር 2005 (እ.አ.አ)፣ 87፦ “የትንሳኤ ስጦታ የጌታ ፍፁም የፈውስ ተግባር ነው።”

  3. ሞሮኒ 7፥40-42 ይመልከቱ።

  4. ኢኖስ 1፥8

  5. ኢኖስ 1፥7

  6. ኢኖስ 1፥8

  7. ማቴዎስ 25፥1–13 ይመልከቱ።

  8. ሰነፎች ምክንያቱም ተጨማሪ ዘይት መያዝ አስፈላጊ ወይም ጠቃሚ መስሎ አልታያቸውም ነበርና ነው።

  9. የጆሴፍ ስሚዝ ትርጉም፣ ማቲዎስ 25:12 (በማቴዎስ 25:12, የግርጌ ማስታወሻ ውስጥ)።

  10. ስለ አሥሩ ቆነጃጅት ምሳሌ ሽማግሌው ዴቪድ ኤ ቤድናር እንዲህ በማለት አስተምሯል:-

    “እባካችሁ ቆነጃጅት የተጠቀሙትን ማሰሮ እንደ ምስክርነት ማሰሮ አስቡባቸው። አምስቱ ሰነፍ ቆነጃጅት የምስክርነት ማሰሮአቸውን ይዘዋል ነገር ግን ዘይት አልያዙም። ዘይቱንም እንደ መለወጥ ዘይት አስቡት። …

    አምስቱ ልባም ቆነጃጅት ስግብግቦች እና ለማካፈል ፈቃደኛ ያልነበሩ ነበሩን፣ ወይስ የመለውጥ ዘይት ለሌላ ሊያውሱት እንደማይቻል እያሳዩ ነበር? ለትእዛዛቱ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የሚገኝ የመታዘዝ መንፈሳዊ ጥንካሬ ለሌላ ሰው ሊሰጥ ይችላልን? በተጋ ጥናት የሚገኝ እውቀት እና የቅዱሳን መጻሕፍት እሳቤ ለአንድ ለሚያስፈልገው ሰው ሊተላለፍ ይቻላልን? ለአንድ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ወንጌል የሚያመጣው ስላም አንድ መከራ ወይም ታላቅ ፈተና ላጋጠመው ግለሰብ ሊተላለፍ ይቻላልን? ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ አይደለም ነው።’’

    እርሳቸውም በዝርዝር ሲያስረዱ ‘’የምስክርነት መቅረዛችንን ለማቀጣጠል እና የመለወጥ ዘይት የማግኘት የግል ሃላፊነት አለብን። ይህ ውድ ዘይት የሚገኘው አንድ ጊዜ ጠብታን በማድረግ ነው--’በዚህ ትንሽ [እና] በዚያ ትንሽ’(2ኛ ኔፊ 28፥30)፣በተግስት እና ባለማቋረጥ ነው። ምንም አጭር መንገድ አልነበረም፤ ምንም የመጨረሻ ደቂቃ ድንገታዊ ዝግጅት የሚቻል አልነበረም” (David A. Bednar, “Converted unto the Lord,” Liahona, Nov. 2012, 109).

  11. ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 33፣17። ፕሬዘዳንት ራሰል ኤም ኔልሰን ሲመክሩ፤ ‘’አሁን እኔ እና እናንተ ለጌታችንና ለአዳኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት የምንዘጋጅበት ጊዜ ነው። አሁን ለደቀመዝሙርነታችን ከሁሉ የላቀ ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜ ነው።’’ (‘’ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ይመጣል፣’’ ሊያሆና፣ ሕዳር 2024 (እ.አ.አ))።

  12. አምስቱን ልባም ቆነጃጅት የቀረጸው አርቲስት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀየሩ ደቀመዛሙርትን የሚወክሉትን፣ ከተለያየ እድሜ እና ዘር የመጡትን አምስት ልባም ቆነጃጅት ምስል ሰራተኛ የሆነው ቤን ሃሞንድ ነው።

  13. ቅዱስ ቁርባንን ስንካፈል፣ ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን እናድሳለን ።የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በላያችን ልንወስድ እና ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደምንሆን አዲስ ቃል እንገባለን። በክህነት ስርዓቶች ውስጥ በብቁነት መሳተፍ እና ቃል ኪዳኖችን መግባት እና መጠበቅ ሙሉ ያደርገናል። ይህ መርህ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ፣ ‘’የህይወት እንጀራ፣ ህያው ውሃ’’፤ በሚል ባማረ መንገድ ተገልጾአል።

    ‘’የሕይወት እንጀራ፣ ህያው ውሃ፣

    ነፍሴን መግባት፣ ልቤን ሙላው።

    ጌታ ሆይ፣ በአንተ አዲስ ህይወትን ስጠኝ

    እናም ሙሉ--ፍጹም እና ቅዱስ- አድርገኝ

    ከአንተም ጋር ለዘለዓለም ተጣምሬአለሁ።’’

    (መዝሙር— ለቤት እና ለቤተክርስትያን, no. 1008, የወንጌል ቤተመጻሕፍት)።

  14. (ማቴዎስ 5፥14)።

  15. 3 ኔፊ 12፥14-16

  16. በተወደደ መዝሙር ቃላቶች ውስጥ፤

    “ይህ የእኔ ትንሽ ብርሃን፣ እንዲያበራ አደርገዋለሁ…

    በሄድኩበት በየትኛውም ስፍራ፣ እንዲያበራ አደርገዋለሁ…

    ኢየሱስ ለእኔ ሰጥቶኛል፤ እንዲያበራ አደርገዋለሁ።

    እንዲበራ፣ እንዲበራ፣ እንዲበራ…

    “ይህ የእኔ ትንሽ ብርሃን፣” መዝሙር ለቤት እና ለቤተክርስትያን፣ የወንጌል ቤተመጻሕፍት።

  17. 2 ቆሮንቶስ 12፥7

  18. 2 ቆሮንቶስ 12፥8 ይመልከቱ።

  19. 2 ቆሮንቶስ 12፥9

  20. 2 ቆሮንቶስ 12፥9–10

  21. ፊልጵስዩስ 4፡4፣ እንዲሁም 2ኛ ቆሮንጦስ 1፥3-4 ተመልከቱ፤ ‘’የምህረት አባት፣ የመጽናናት ሁሉ አምላክ፣ እኛ በእግዚአብሄር በተጽናናንበት መጽናናት በችግር ያሉትን ሁሉ እናጽናና ዘንድ፣ በመከራችን ሁሉ ያጽናናን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እና አባት ይባረክ።’’

  22. ዴቪድ ኤ. ቤድናር፣ “Put On Thy Strength, O Zion, ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 82።

  23. ማቴዎስ 22:14፤ እንዲሁም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥34-35 ይመልከቱ።

  24. ሉቃስ 8፥2-3 ይመልከቱ።

  25. ዮሀንስ 19፥25ይመልከቱ።

  26. ዮሐንስ 20፥15; እንዲሁም ቁጥር 13 ይመልከቱ።

  27. ዮሀንስ 20፥13 ይመልከቱ።

  28. ዮሀንስ 20፥16 ይመልከቱ።

  29. ኢሳይያስ 25፥8