አጠቃላይ ጉባኤ
ልግስና— የእውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ምልክት
የሚያዝያ 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


11:29

ልግስና— የእውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ምልክት

የደቀ መዝሙርነት እውነተኛው መዳረሻ ቃል በቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን መሆን ነው።

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በቅርቡ “ደቀ መዝሙርነታችንን ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሠጠው” እንድናደርግ ጋብዘውናል።” ይህ ኃይለኛ ግብዣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የግል ደቀ መዝሙርነት በጥልቅ እንዳሰላስል አነሳስቶኛል።

ደቀ መዝሙርነት ታስቦበት የሚደረግ ነው

ደቀ መዝሙር የሌላ ሰው ተከታይ ወይም ተማሪ ማለት ነው። ደቀ መዛሙርት እንደ መምህራቸው ለመሆን ሕይወታቸውን የሚያውሉ “ሰልጣኞች” ናቸው። ስለዚህም፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን አስተምህሮቶቹን እና ትምህርቱን ከማመን የበለጠ ነገር መሆኑን ያሳያል። የእርሱን መለኮትነት እውቅና ከመሥጠት እና እርሡን እንደ አዳኛችን እና ቤዛችን አድርገን ከመቀበል የበለጠ ነገርንም ያመለክታል—ያም እጅግ አስፈላጊ ነው።

ፕሬዚዳንት ዳለን ኤች. ኦክስ እንዳብራሩት፥ “ክርስቶስን መከተል የተለመደ ወይም አልፎ አልፎ የሚደረግ ልምምድ አይደለም። በማንኛውም ጊዜ እና በሁሉም ቦታ ሊመራን የሚገባው ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት እና የህይወት መንገድ ነው።” ደቀ መዝሙርነት በጌታ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት እና በሚያስችል ሃይሉ ለመለወጥ ሆን ብለን የምናደርገው ጉዞ ነው። የደቀ መዝሙርነት እውነተኛው መዳረሻ የእርሱን “መልክ [በፊታችን] እስከምንቀበል ድረስ” ቃል በቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን መሆን ነው

የጌታ ደቀ መዛሙርት ለመሆን በየእለቱ ሆን ብለን ሀሳቡን እና ተግባራቶቹን መምሰል አለብን—ለምሳሌ፣ ታዛዥነቱን፣ ትህትናውን እና ታጋሽነቱን። እነዚህን ባህሪያት ቀስ በቀስ ወደ ማንነታችን ስናካትት፣ “የ[እርሱን] የመለኮታዊ ተፈጥሮ ተካፋዮች” እንሆናለን። ይህንን የአዳኙን ባህሪ ማስመሰል ማለት እርሱን ከልብ ማምለክ ማለት ነው። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “ለኢየሱስ ያለን መውደድ የሚገለጸው ኢየሱስን በመምሰላችን ነው። ብለዋል።”

እውነተኛው የደቀ መዝሙርነት ምልክት

ልንከተላቸው ከሚገቡን የኢየሱስ ክርስቶስ በርካታ መለኮታዊ ባህሪያት መካከል፣ አንደኛው ከሁሉም የበለጠ የሚያስፈልግ እና ሁሉንም የሚያካትት ነው። ያም ባህሪ ንጹህ ፍቅሩ ወይም ልግስናው ነው። ነቢዩ ሞርሞን እና ሐዋርያው ጳውሎስ ሁለቱም ያለ ልግሥና “[እኛ] ምንም እንዳልሆንን ያስታውሱናል።” ወይም፣ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንደተገለጠው፣“ ያለልግስና፣ [እኛ] ምንም ማድረግ አንችልም።”

አዳኙ ራሱ እንደሚከተለው በተናገረ ጊዜ ፍቅር እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ የሚለዩበት ምልክት ወይም መገለጫ እንደሆነ ለይቶታል፦

“እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።

“እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”

ልግስናን ለማብራራት አስቸጋሪ ሊሆን ይችልላ ነገር ግን በዚያ ባህሪ ለሚነኩ ሰዎች ሁሉ በቀላሉ የሚገባ ግልጽ የሆነ ፅንሰ ሀሳብ ነው። ወንጌሌን ስበኩ የሚለው መጽሃፍ “ልግስና ልክ እንደ እምነት ወደ ተግባር ይመራል” በማለት ያስተምራል። በእርግጥም ልግስና “በድርጊት ላይ ያለ ፍቅር” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ይህ “መልካም እያደረገ ሄደ የሚለው መግለጫ በአዳኙ ህይወት ማጠቃለያ ላይ ታላቅ ማስተዋልን ይሰጣል።”

የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ጌታችን ለሌሎች ያለውን ንፁህ ፍቅር ያሳየበትን መንገድ ለመምሰል ጥረት ማድረግ አለብን። ምንም እንኳን አዳኙ ልግስናን በብዙ መንገዶች ቢገልጽም፣ በእውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ ውስጥ በቀላሉ ለሚታዩት ሶስት ልዩ የልግስና መንገዶች ትኩረት መስጠት እፈልጋለሁ።

ልግስና ማለት ርህራሄን ማሳየት ማለት ነው

በመጀመሪያ፣ አዳኙ ርህሩህ በመሆን ልግስናን አሳይቷል። በመፅሐፈ ሞርሞን እንደተመዘገበው በኔፋውያን መካከል ባከናወነው አገልግሎት ጌታ ህዝቡን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እና ባስተማራቸው ነገሮች ላይ እንዲያሰላስሉ እንዲሁም በሚቀጥለው ቀን ተመልሶ ሲመጣ እንዲዘጋጁ ጋብዟቸዋል። መዝገቡ እንዲህ ይላል፥

“እንባ እያነቡ መሆናቸውንና፣ እርሱ ከእነርሱ ጋር ትንሽ እንዲቆይ የሚፈልጉ በመምሰል በእርሱ ላይ ያተኮሩ ይመስሉ እንደነበር ተመለከተ።

“እናም እርሱ እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ ስለእናንተ አንጀቴ በርህራሄ ተሞልቷል።”

ርህራሄ ማለት መከራን ለማስታገስ የሚያስፈልግ የልግስና አንዱ ክፍል ነው። በርኅራኄ ተሞልቶ፣ ጌታ በሕዝብ መካከል የታመሙትንና የተጨነቁትን ፈውሷል። ከዚህም በኋላም፣ መላእክት ከሰማይ ወርደው ከበዋቸው ሳለ ልጆቻቸውን ባረካቸው። እርሱ እነዚህን የርኅራኄ፣ የፍቅር ተግባራትን እና ሌሎችንም ፈጽሟል፣ ምክንያቱም እርሱ “በርኅራኄ ስለተነካ” ነበር።

በደቡብ አሜሪካ ወጣት ሚስዮናዊ ሆኜ ሳገለግል፣ እኔም የምወደው ጓደኛዬ ባሳየኝ ርኅራኄ ተጠቅሜ ነበር። አንድ ቀን ምሽት ከጓደኛዬ ጋር ወደ ሚሲዮን ፕሬዘዳንታችን ቤት በመኪና እየሄድኩ ሳለሁ፣ አንድ ወጣት በብስክሌት በድንገት ከመኪናው ፊት ለፊት ታጠፈ። በፍጥነት ስለተከሰተ ግጭቱን ማስቀረት አልቻልኩም። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ይህ ወጣት በተፈጠረው አደጋ ህይወቱ አለፈ። በህይወቱ መጥፋት ክፉኛ አዘንኩ። የተከሰተው አሰቃቂ እውነታ በራሴ የሰቀቀን ቀንበር ሲያወርድብኝ ፈራሁኝ እንዲሁም ድንጋጤ ወረረኝ፣ ወደ እስር ቤትም ተወሰድኩ እናም ታሠርኩኝ። እንዲህ ያለ ፍርሃትና ብቸኝነት መቼም ተሰምቶኝ አያውቅም። ቀሪውን ሕይወቴ በእስር የማሳልፍ መስሎኝ ተስፋ በመቁረጥ እና በፍርሃት ስሜት ተሞላሁ።

ሽማግሌ ብራየን ኮቸቨር የተባለ ሚስዮናዊ ጓደኛዬ ስለአደጋው አውቆ ነበርና በርህራሄ ተነካ። ወደ እስር ቤት መጥቶ ብቻዬን እንዳልሆን በክፍሉ ውስጥ ከእኔ ጋር እንዲቆይ እንዲፈቀድለት ፖሊሶቹን ተማጸነ። በሚያስደንቅ ሁኔታ፣ ተስማሙ። እስከ ዛሬ ድረስ፣ በህይወቴ ውስጥ በነበረኝ ታላቅ የጭንቀት ጊዜ ውስጥ ይህ ደቀመዝሙር ላደረገው የክርስቶስ አይነት ፍቅር ጥልቅ አድናቆት ይሰማኛል። የልግስናው ርህሩህነት የደቀ መዝሙርነቱ ማሳያ ምልክት ነበር። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተዋሉት፣ “የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ ተከታይ ለመለየት ከሚያስችሉት መንገዶች በጣም ቀላሉ መንገድ አንድ ሰው ለሌሎች ሰዎች በሚያሳየው ርህራሄ ነው።

ልግስና ላልተገለፁ ፍላጎቶች የምንሰጠው አገልግሎት ነው

አዳኙ ፍቅሩን ከሚገልጽባቸው መንገዶች ውስጥ ሌላኛው ምሳሌ የሌሎችን ያልተገለፁ ፍላጎቶች መገንዘብ እና ማገልገል ነው። ለ38 ዓመታት ሲያነክስ የነበረውን ማንም የሚረዳው የሌለውን ሰው ጌታ ፈወሰው በጽድቅም እንዲኖር አበረታታው። ዝሙት ስትፈፅም በተያዘችው ሴት ላይ ከመፍረድ ይልቅ ተስፋን እና መጽናኛን ሰጣት። በጣሪያው በኩል ለወረደው ሽባ ለሆነ ሰው ጌታ የሰውነትን ፈውስ ብቻ ሳይሆን የኃጢአትን ስርየት ሰጥቶታል።

ኤጲስ ቆጶስ ሆኜ እንዳገለግል በተጠራሁበት ወቅት፣ ስድስቱ ትናንሽ ልጆቻችን የቅዱስ ቁርባን ስብሰባችንን ለባለቤቴ ክሪስቲን ፈታኝ አድርጋውባት ነበር፣ እኔ በመነጋገሪያውመድረክ በምቀመጥበት ጊዜ ብቻዋን ትቆጣጠራቸው ነበር። ልትገምቱ እንደምትችሉት ልጆቻችን ብዙውን ጊዜ የጥልቅ አክብሮት እርጋታ የላቸውም። የእርሷን ሁኔታ በመመልከት፣ ጆን እና ዴቢ ቤኒች የተባሉ ሁለት የአጥቢያችን አባላት እርሷን ለመርዳት በየእሁዱ አብረዋት መቀመጥ ጀመሩ። ደግነታቸው ለዓመታት የቀጠለ ሲሆን ለቤተሰባችንም ምትክ አያቶች ሆኑ። ልክ እንደ ጌታ፣ እነዚህም ደቀ መዛሙርት የማይነገረውን ፍላጎት በራሳቸው በማስተዋል—የደቀ መዝሙርነታቸውን ጉልህ ምልክት በፍቅር ተገበሩት።

ልግስና ማለት ሌሎችን በቃል ኪዳኑ ጎዳና እንዲራመዱ ማገዝ ነው።

በመጨረሻም፣ የአዳኙ ፍጹም ፍቅር ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች መለኮታዊ አቅማቸውን እንዲፈፀሙ በማስቻል ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህም “ከማዳኑ እና ከቤዛነቱ ኃይል እንድንካፈል ነው።” ይበልጥ እንደ መምህራችን ስንሆን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ የመርዳት ፍላጎታችን ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ይጨምራል።

ለምሳሌ፣ የተቀየሙትን ወይም የተረሱትን ማበረታታት እና ወዳጅ ልንሆናቸው እንችላለን፣ ለጉባኤያችን አዲስ የሆኑትን በእንክብካቤ በመቀበል ልንረዳቸው፣ ወይም ጓደኞቻችንን በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ እንዲያመልኩ መጋበዝ እንችላለን—ምናልባትም በዚህ በመጪው ፋሲካ። ለማየት ዓይን እንዲኖረን እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነርሱ ያለውን አመለካከት እና ስሜት እንዲሰማን ሆን ብለን እና በጸሎት የሰማይ እርዳታን ከፈለግን ሌሎችን ለማበረታታት እና ለመርዳት ስፍር ቁጥር የሌላቸው መንገዶች አሉ።

በቃል ኪዳን መንገዳቸው ላይ ሌሎችን መርዳት ያልተለመደ የአገልግሎት ተግባር ሊመስል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በአሁኑ የፊሊፒንስ የሥራ ምደባዬ ወቅት ስለ አጋማታ ቤተሰብ አወኩኝ። የተጠመቁት በ2023 (እ.አ.አ) ነበር፣ ከዚያም በአቅራቢያው በሚገኘው በኡርዳኔታ ፊሊፒንስ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደ ቤተሰብ የሚታተሙበትን ቀን በጉጉት ወሰኑ። ይሁን እንጂ፣ ከቤተሠቡ ቀጠሮ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ አካባቢው በብዙ አውሎ ነፋስ ተመታ። የሩዝ እርሻ ያለው ገበሬ የሆነው ወንድም አጋማታ በከባድ አውሎ ነፋሱ ወቅት እህሉን መትከል አልቻለም ነበር። አውሎ ነፋሱ በመጨረሻ ካለፈ በኋላ መሬቱ በውሃ ሲርስ— ለመትከል ተስማሚ በሆነ ሁኔታ፣ ሩዙን በፍጥነት መትከል አስፈልጎት ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ የቤተመቅደስ ጉዞውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ነበረበት።

ሚስዮናውያን ሩዝ በመትከል ረዱ።
ሚስዮናውያን ሩዝ እየተከሉ።

ሁለት ደቀ መዛሙርት፣ ሽማግሌ ካውላን እና እህት ካውላን ከሦስት ወጣት የአገልግሎት ሚስዮናውያን ጋር ስለ አጋማታ ቤተሰብ ችግር ሰምተው ምንም የእርሻ ልምድ ባይኖራቸውም እርዳታ ሰጡ። በጠራራማ ጸሃይ ስር በመስራት ችግኞችን በመትከል እነ አጋማታስ ተግባራቸውን እንዲያጠናቅቁ እና የቤተመቅደሥ መታተም ሥርዓታቸውን በታቀደላቸው ቀጠሮ መሰረት እንዲገኙ አስችለዋቸዋል። ሽማግሌ ካውላን እንዳስተዋሉት “[የአጋማታስ ቤተሠብ] በጌታ ቤት ነጭ ልብስ ለብሰው ስናይ ፊቶቻቸው ያበሩ ነበር። እነሱን ስናገለግል የተሰማን ደስታ አቻ የሌለው ደስታ ነው!” ብለዋል

የአጋማታ ቤተሰብ ከቤተመቅደስ ውጪ

የአጋማታስ ቤተሰብ አሁን እንደ ዘላለማዊ ቤተሰብ በመታተማቸው የበለጸገ በረከቶችን ያገኛሉ ምክንያቱም በልግሥና የተሞሉ ጥቂት ደቀ መዛሙርት —በደቀ መዝሙርነታቸው መገለጫ— ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን በእነሡ የቃል ኪዳን ጎዳና እንዲራመዱ ለመርዳት ወስነዋል።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ዘላቂ ደስታን የምናገኝበት ብቸኛው መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት ነው። የታሠበበት እና ለሌሎች ሰዎች በሚሠጥ ዓላማ ያላቸው የፍቅር ተግባራት የተሞላ መንገድ ነው። የደቀ መዝሙርነት መንገድ አስቸጋሪ እና ፈታኝ ሊሆን ቢችልም እና አንዳንድ ጊዜ ልንቸገር እና ልንወድቅ ብንችልም፣ እግዚአብሔር እንደሚያስብልን እና በምንሞክርበት ጊዜ ሁሉ ሊረዳን እንደሚፈልግ መጽናኛን ማግኘት እንችላለን። ኢሳይያስ ፣ “እግዚአብሔር፣ … ፣ አትፍራ፣ እረዳሃለሁ በማለት እጃችንን እንደሚይዝ።” ያስታውሰናል።

ይህንን የሰማይ አባታችንን ማረጋገጫ በልቦናችን ይዘን ለደቀ መዝሙርነት ቅድሚያ እንሰጥ ዘንድ የፕሬዚዳንት ኔልሰንን ግብዣ እንድንከተል አጥብቄ እጸልያለሁ። “በልባችን ሙሉ ሃይል ወደ አብ እንጸልይ ዘንድ በዚህ” ”በእርሱ ፍቅር ልባችን እንዲሞላ፣ ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ለሆኑት ሁሉ የሰጣቸውን ፍቅር እናድርግ፥ … እርሱም በሚገለጥበት ጊዜ እርሱን እንድንመስል፣ “ ምክንያቱም የእውነተኛ ደቀመዝሙርነትን ምልክት ስለምንይዝ፣ እርሱም “ልግስና… የክርስቶስ ንጹሕ ፍቅር ነው።”

ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው ክቡር አዳኛችን፣ ቤዛችን፣ ዓርአያችን እና ወዳጃችን እንደሆነ እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ይመጣል፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2024 (እ.አ.አ)፣ 121

  2. Merriam-Webster.com Dictionary፣ “relief” ይመልከቱ።

  3. ዳለን ኤች ኦክስ፣ “ክርስቶስን መከተል፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2024 (እ.አ.አ)፣ 23

  4. አልማ 5፥14፤ እንዲሁም አልማ 5፥19 ይመልከቱ።

  5. 2 ጴጥሮስ 1፥3-8 ይመልከቱ።

  6. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ፍጹምነት በመጠባበቅ ላይ”፣ ሊያሆና፣ ህዳር 1995 (እ.አ.አ)፣ 87።

  7. ሞሮኒ 7፥45፤ በተጨማሪም 1 ቆሮንቶስ 13፥3 ይመልከቱ።

  8. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 18፥19፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል።

  9. ዮሀንስ 13፥34-35፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል።

  10. ወንጌሌን ስበኩ፦ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የማካፈል መመሪያ [2023 (እ.አ.አ)]፣ 127።

  11. የሐዋሪያት ስራ 10፥38

  12. 3 ኔፊ 17፥3ን ይመልከቱ

  13. 3 ኔፊ 17፥5-6

  14. Merriam-Webster.com Dictionary፣ “relief” ይመልከቱ።

  15. 3 ኔፊ 17፥7-25 ይመልከቱ።

  16. ማቴዎስ 9፥3614፥14ማርቆስ 1፥416፥34

  17. ለሞት ሚዳርግ አደጋ በመሆኑ ምክንያት የፖሊስ መኮንኖቹ በመደበኛው አሰራር መሰረት ወደ እስር ቤት አስገቡኝ። ሹፌሩ እኔ ስለነበርኩኝ ከጓደኛዬ ለዩኝ። ለሁለት ቀናት እስር ቤት ነበርኩ። ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ይህ ወጣት አደጋው በደረሰበት ወቅት ሰክሮ እንደነበርና ይህም እየተንቀሳቀሰ ከነበረው ተሽከርካሪያችን ፊት ለፊት እንዲታጠፍ ተጽእኖ እንዳደረገበት ደርሰውበታል። በመደበኛ ችሎት ዳኛ ፊት ቀርቤ ነበር፣ ምንም አይነት የስህተት ወይም የቸልተኝነት ማስረጃ እንደሌለ ነገር ግን ይህ በቀላሉ አሳዛኝ እና አስከፊ አደጋ እንደሆነ ተረጋገጠ።

  18. ማቴዎስ 25፥31-40፣ በተለይ ቁጥር 36 ይመልከቱ።

  19. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “አስታራቂዎች ይፈለጋሉ፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2023 (እ.አ.አ.)፣ 98።

  20. ዮሀንስ 5፥2-9፣ 14 ይመልከቱ፥

  21. ዮሐንስ 8፥1–11 ይመልከቱ።

  22. ማርቆስ 2፥1–12 ይመልከቱ።

  23. ኦምኒ 1፥26

  24. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥12 ይመልከቱ።

  25. 2 ኔፊ 26፥24 ይመልከቱ።

  26. ከዳርዊን ሴራኖ ካውላን ጋር ካደረኩት የግል ግንኙነት፣ ታህሳስ 1፣ 2024 (እ.አ.አ.)።

  27. ኢሳይያስ 41፥13

  28. ሞሮኒ 7፥48

  29. ሞሮኒ 7፥47