እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ፍቅር
አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን በደስታ እመሰክራለሁ። ለእኛ ያለው ፍቅር ፍጹም፣ ግላዊ እና ዘለአለማዊ ነው።
አንድ የበጋ ወቅት ራቅ ወዳለ አካባቢ ስንጓዝ፣ ቤተሰባችን ደመና በሌለው ሰማይ ስር ከቤት ውጭ ተኝተው አሳለፉ። ከላያችን ላይ በግልጽ የሚታየው ድንቅ የሰማይ ጠፈር፣ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ክዋክብቶች የተሞላ እና አልፎ አልፎ ተወርዋሪ ኮከብም ይታይበት ነበር። በእግዚአብሔር ግርማዊ የሆነ አፈጣጠር እየተደነቅን፣ ከእርሱም ጋር የአክብሮት ግንኙነት ተሰማን። በሆንግ ኮንግ ያደጉት ትናንሽ ልጆቻችን ከዚህ በፊት እንደዚህ ያለ ነገር አጋጥሟቸው አያውቁም ነበር። በንጹህ አንደበታቸው እኛም የምንኖርበት ቦታ እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ሰማይ ስር እንደምንኖር ጠየቁ። ሰማይ አንድ አይነት መሆኑን ነገር ግን እኛ የምንኖርበት ቦታ እነዚህን ከዋክብት ቢኖሩንም እንኳ የአየር እና ሰውሰራሽ የብርሃን ብክለት እንዳናይ ይከለክሉናል ብዬ ልገልጽላቸው ሞከርኩ።
ቅዱሳት መጻሕፍት “እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ብለው አስተምረውናል። ትኩረታችንን የሚከፋፍሉ ነገሮች እና ምድራዊ ፈተናዎች መንፈሳዊ ራዕያችንን ቢያጨልሙትም፣ በእግዚአብሔር እና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነታችንን ስንለማመድ፣ ስለእነርሱ እውነኛነት እና ለእኛ እንደሚያስቡልን ግልጽ ማረጋገጫን እናገኛለን።
በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ፣ ነቢዩ ሌሂ “[ከሁሉ] በላይ ጣፋጭ” የሆነችውን እና “አንድን ሰው ደስተኛ ለማድረግ መልካም የሆነችን ዛፍ” አየ። ፍሬውንም በቀመሰ ጊዜ ነፍሱ በታላቅ ደስታ ተሞላች እና ቤተሰቡም እንዲካፈሉለት ፈለገ። ይህ ዛፍ “የእግዚአብሔርን ፍቅር” እንደሚወክል ተምረናል፣ እናም ልክ እንደ ሌሂ እኛም ወደ ህይወታችን ስንጋብዘው አስደሳች የሆነውን የእግዚአብሔርን ምስክርነት መቀበል እንችላለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይ አባት ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል። በእርሱም የቤዛ መስዋዕትነት፣ ኃጢአታችንን በራሱ ላይ ወሰደ እናም ስለ በደላችንም ደቀቀ። እርሱ ሀዘናችንን አዝሎ፣ ጭንቀታችንን ተሸክሞ፣ ህመማችንን እና ደዌያችንን በራሱ ላይ ወሰደ። መንፈስ ቅዱስን እንዲያጽናናን እና የመንፈስ ፍሬዎች እንደ ደስታ፣ ሰላም እና እምነት ያሉትን በተስፋ ይሞሉን ዘንድ ይልክልናል።
የእግዚአብሔር ፍቅር ለሁሉም የሚደርስ ቢሆንም፣ ብዙዎች አጥብቀው ይፈልጉታል፣ ሌሎች ግን የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲሰማቸው ይፈልጋሉ ነገር ግን ይገባኛል ብለው አያምኑም። ሌሎች ደግሞ አጥብቀው ለመያዝ እየጣሩ ይገኛል። በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ደጋግመን ንስሀ ስንገባ፣ በግልፅ ይቅር ስንል፣ ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ስንጥር እና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ሌሎችን ለማገልገል ስንችል የእግዚአብሔርን ፍቅር ያለማቋረጥ መለማመድ እንደምንችል ቅዱሳት መጻህፍት እና የጌታ ነቢይ፣ ያስተምሩናል። የእግዚአብሔር ፍቅር የሚሰማን ወደ እርሱ እንድንቀርብ የሚያደርጉንን ነገሮች ስናደርግ፣ ለምሳሌ፣ በየቀኑ ከእርሱ ጋር ያለንን ቀረቤታ በጸሎት እና በቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት ስናጠብቅ፣ እና ኩራት፣ ጠብ እና አመጸኛነት አይነት ከእርሱም የሚያርቁንን ነገሮችንም ባለማድረግ ነው።
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን “በአዳኙ እርዳታ በህይወታችን ውስጥ ያሉትን አሮጌ ፍርስራሾች እንድናስወግድ” እና “ምሬትን ወደ ጎን እንድንተው” ጋብዘውናል። ህይወታችንን በአዳኙ እና በቤተመቅደሱ ስነስርዓቶች እና ቃል ኪዳኖች ላይ በማተኮር መንፈሳዊ መሰረቶቻችንን እንድናጠናክር አበረተውናል። እንዲህም የተስፋ ቃል ሰጥተዋል፣ “የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖቻችንን ስንጠብቅ፣ የጌታን የብርታት ሀይል ይበልጠ ለማግኘት እንችላለን። … የኢየሱስ ክርስቶስን እና የሰማይ አባታችንን ንፁህ ፍቅር በብዙ መትረፍረፍ እንለማመዳለን!”
በሚያምር ቤተሰብ እና ተስፋ ሰጪ በሆነ ስራ የተባረከ አንድ ጓደኛ አለኝ። ይህም በህመም ምክንያት ስራ መስራት እንዳይችል ከሆነ በኋላ ነገሮች ተቀየሩ፣ ያም የትዳር ፍቺን አስከተለ። ከዚያ በኋላ ያሉት ዓመታት አስቸጋሪ ነበሩ፣ ነገር ግን ለልጆቹ ያለው ፍቅር እና ከእግዚአብሔር ጋር የገባው ቃል ኪዳን ደግፎታል። አንድ ቀን የቀድሞ የትዳር ጓደኛው ዳግም ማግባቷን እና የቤተመቅደስ ትስስር ቃል ኪዳናቸው እንዲሰረዝ እንደጠየቀች ተረዳ። እጅግ ተቸገረ እናም ግራ ተጋባ። በእግዚአብሔርም ቤት ሰላምንና ማስተዋልን ፈለገ። ከጉብኝቱም ማግስት የሚከተለውን መልእክት ከእርሱ ደረሰኝ፦
“ትላንትና ማታ በቤተመቅደስ ውስጥ አስደናቂ ልምድን አገኘው። አሁንም ትንሽ ቂም እንደያዝኩ ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። … መለወጥ እንዳለብኝ አውቅ ነበር እና ይህን ለማድረግ ሳምንቱን ሙሉ እየጸለይኩ ነበር። … ትናንት ማታ በቤተመቅደስ ውስጥ መንፈስ ከልቤ ውስጥ ቂምን እንዳስወገልኝ ተሰማኝ። … ከዚህ ነፃ መውጣቴ በጣም እፎይታ ነበር። … በላዬ ላይ የተጫጫነኝ አስከፊ የሆነ አካላዊ ሸክም ተራግፏል።”
አሁንም ድረስ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም፣ ጓደኛዬ በጌታ ቤት ያገኘውን ያን ልምድ እንደ እንቁ ጠብቆታል ነፃ አውጪ የሆነው የእግዚሃብሄር የፍቅር ሃይል ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርብ፣ ለህይወቱ የበለጠ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረው እና ስለወደፊቱም ብዙ መጨነቅ እንዳይኖርበት አድርጎታል።
የእግዚአብሔርን ፍቅር ስንለማመድ፣ ሸክማችንን በጽናት መሸከም እና በትዕግስት እና በደስታ ለፈቃዱ መገዛት እንችላለን። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንደሚያስታውስ፣ በመከራችን እንደሚጎበኘን፣ እና ከባርነት እንደሚያድነንም እንተማመናለን። እንዲሁም የተሰማንን ደስታ ከቤተሰባችን እና ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ለመካፈል እንፈልጋለን። እንደ ሌሒ ቤተሰብ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው ከፍሬው ለመብላትም ሆነ ላለመብላት የመምረጥ ነጻነት አለው፣ ነገር ግን እኛ የምንወዳቸው ሰዎች የእግዚአብሔርን ፍቅር ሊሰማቸው በሚችልበት መንገድ ለመውደድ፣ ለማካፈል እና ለመጋበዝ ዕድላችን ነው።
ሌሎች የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲሰማቸው ለመርዳት፣ እንደ ትህትና፣ ልግስና፣ ርህራሄ እና ትዕግስት የመሳሰሉ የክርስቶስን አይነት ባህሪያትን በራሳችን ውስጥ ማዳበር፣ እንዲሁም እግዚአብሔርን መውደድ እና ባልንጀሮቻችንን መውደድ በሆኑት ሁለቱ ታላቅ ትእዛዛት ሌሎችን ወደ አዳኝ እንዲመልሱ መርዳት አለብን።
አንዱ ልጃችን በጉርምስና ዕድሜው ከሌሎች ጋር ግንኙነትን ለመፍጠር እና ባለው በራስ መተመማን ጉድለት ይቸገር ነበር። እኔና ባለቤቴ እርሱን እንዴት እንደምንረዳው ለማወቅ ጸለይን፣ እና ጌታ እንድናደርግ የሚፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኞች ነበርን። አንድ ቀን ከልጄ ጋር አብሬ መጎብኘት የምችለው ሰው እንዳለ የሽማግሌዎች ቡድን ፕሬዚዳንቴን ለመጠየቅ ተነሳሳሁ። ትንሽ ካሰበ በኋላ፣ ከባድ የጤና እክል ያለባትን አንዲት ሴት እንድንጎበኝ፣ እና በቅርንጫፍ ፕሬዚዳንቱም ፈቃድ መሰረት በየሳምንቱ ቅዱስ ቁርባንን ወደ እርሷ እንድናመጣ ጠየቀን። ልጄ በዚህ ሳምንታዊ ቁርጠኝነት ላይ ምን ምላሽ እንደሚሰጥ በማሰብ በጣም ተደስቼ ነበር ግን ደግሞ ተጨንቄ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሄድንበት ወቅት፣ ይህቺ ውድ ሴት የማያቋርጥ ህመም ውስጥ ሆና ስለነበር ልባችን በጣም አዘነ። ለቅዱስ ቁርባኑ በጣም አመስጋኝ ነበረች፣ እናም እርሷን እና ባለቤቷን መጎብኘት መቻላችን አስደስቶናል። ከጥቂት ጉብኝቶች በኋላም፣ አንድ እሁድ ሩቅ ቦታ ነበርኩና ከልጄ ጋር አብሬው መሄድ አልቻልኩም፣ ነገር ግን ስለሃላፊነታችን አንዲያስታውስ አደረኩት። ቤት ስደርስም፣ ጉብኝቱ እንዴት እንደነበር ለመስማት መጠበቅ አልቻልኩም። ልጄ የክፍል ጓደኞቹ እንደዚህ ዓይነት መልካም ነገሮችን ያደርጋሉ ብሎ አላሰበም ሲል መለሰለት። እናም ወንድሙን ይዘው መጥተው እንዲረዳቸው እና ቅዱስ ቍርባኑ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንደተከናወነ በመግለጽ ያብራራል፣ ነገር ግን ይህች ውድ እኅት በሳምንቱ ውስጥ በቤት ውስጥ ፊልሞችን ለመመልከት ጓደኞችን ስለጋበዘች እና የቪዲዮ ማጫወቻዋ ስለማይሰራ በሳምንቱ ውስጥ አዘነች። ልጄ በይነመረብ ላይ መፍትሄን እንደፈለገ፣ ችግሩን እንዳገኘው እና በዛው ቦታ እንዳስተካከለላት ተናገረ። እርሱ ጠቃሚ፣ ደስተኛ እና ቀኗን ብርህ ለማድረግ የታመነ ዓይነት ሰው እንደሆነ ተሰማው። እግዚአብሔር ለእርሱ ያለውን ፍቅር ተሰማው።
ምንም ያህል ጥረት ብታደርጉም ህይወት ከባድ ናት፣ ጸሎቶችሁም እንዳልተሰሙ ከተሰማችሁ፣ ወይም የእግዚአብሔርን ፍቅር ሊሰማችሁ ካልቻለ፣ ባይታዩንም ከእኛ በላይ ያሉት ክዋክብት እንደሚኖሩ እርግጠኛ እንደሆኑም፣ እያንዳንዱ ጥረታችሁ ዋጋ ያለው መሆኑን እና የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያውቁት፣ እንደሚሰሙ እና እንደሚወዷችሁ እባካችሁ እወቁ።
በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ውስጥ “በማዕበል እየተናወጡ” ሳሉ፣ አዳኙ በውሃው ላይ ወደ እነርሱ በመራመድ፣ “አይዟችሁ፣ እኔ ነኝ፣ አትፍሩ” በማለት አረጋጋቸው። ጴጥሮስ በውሃ ላይ ተራምዶ ወደ አዳኙ መሄድ በፈለገ ጊዜ፣ ኢየሱስ፣ “ና” ብሎ ተናገረው። እና ጴጥሮስ ትኩረቱን አጥቶ መስጠም በጀመረ ጊዜ፣ አዳኙ ወዲያውኑ ለመያዝ እጁን ዘርግቶ እንዲህም በማለት አዳነው፣ “አንተ እምነት የጎደለህ፣ ለምን ተጠራጠርህ?”
በሕይወታችን ውስጥ ነፋሶች በእኛ ላይ ሲነፍሱ፣ ደስተኛ እና ደፋር ለመሆን ፈቃደኞች ነን? አዳኝ እንደማይተወን እና ምናልባት እኛ ገና በማናውቃቸው መንገዶች በአቅራቢያችን እንዳለ እንዴት መለየት እንችላለን? በተለይ ከፊታችን ያለው መንገድ የማይቻል በሚመስልበት ጊዜ በእምነት ወደ እርሱ ለመሄድ ፈቃደኞች ነን? ለደህንነታችን በምንፍጨረጨር ጊዜስ በምን ዓይነትስ መንገዶች ወደ ደኅንነት ያስጠጋናል? በሁሉም ሃሳቦች ያለ ጥርጥርና ፍርሃት እንዴት ነው በታማኝነት ወደ እርሱ መመልከት የምንችለው?
በሕይወታችሁ ውስጥ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲሰማችሁ ከፈለጋችሁ የሚከተሉትን እንድታስቡት እጋብዛችኋለሁ፦
-
በመጀመሪያ፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆናችሁን ለማስታወስ በተደጋጋሚ አሰላስሉ እና የምታመሰግኑበትን ነገሮች አስቡ።
-
ሁለተኛ፣ በየዕለቱ ጸልዩ፣ የሰማይ አባት በአጠገባችሁ ማን የእርሱ ፍቅሩ እንዲሰማቸው እየፈለጉ እንደሆነ ታውቁ ዘንድ እንዲረዳችሁ ጠይቁ።
-
ሦስተኛ፣ ግለሰቡ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲሰማው ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምትችሉ በትህትና ጠይቁ።
-
እና አራተኛ፣ በተቀበላችሁት መነሳሳት መሰረት ወዲያውኑ በምሪት እርምጃን ውሰዱ።
እኛ ያለማቋረጥ የምንጸልይ እና ሌሎችን ወክለን ከጠየቅን እግዚአብሔር ልንረዳቸው የምንችላቸውን ሰዎች ያሳየናል። ፈጣን እርምጃ ከወሰድን እርሱ ጸሎታቸውን የሚመልስበት መንገድ መሆን እንችላለን። ይህን በማድረግ፣ ከጊዜ በኋላ፣ ለጸሎታችን መልስ እናገኛለን፣ እና የእግዚአብሔር ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ ይሰማናል።
ከጥቂት ወራት በፊት በቬትናም እየተጓዝን ሳለ እኔና ባለቤቴ በከባድ አውሎ ነፋስ በተከሰተ ጊዜ በተነሳ የበረራ አውሮፕላን ላይ ነበርን። ሁከቱ ከባድ ነበር፣ እና ጥቁር ደመና፣ ከባድ ዝናብ እና መብረቅ በመስኮታችን በኩል ይታይ ነበር። ከረዥም እና ተፈራራቂ መናወጦች በኋላ፣ አውሮፕላናችን በመጨረሻ ከአውሎ ነፋሱ ደመና በላይ ተነስቶ ወደዚህ ወደ ከበረ ገጽታ ወጣ። በድጋሚም ስለሰማይ አባታችን እና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አስታወስን እናም ለእኛ ያላቸውንም ታላቅ ፍቅር ተሰማን።
ውድ ጓደኞቼ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንደ ተለማመድ ሰው፣ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን በደስታ እመሰክራለሁ። ለእኛ ያለው ፍቅር ፍጹም፣ ግላዊ እና ዘለአለማዊ ነው። እርሱን በታማኝነት ስንከተል፣ በፍቅሩ እንሞላ እና ሌሎችንም ወደ ፍቅሩ የምንመራ የብርሃን ማማ እንሁን። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።