የምህረት እቅድ
ጌታ መሀሪ ነው እናም የሰማይ አባታችን የደህንነት ዕቅድ በእውነትም የምህረት እቅድ ነው።
የነቢይ ግብዣ
ባለፈው ሚያዝያ፣ ቤተክርስቲያኗ የከርትላንድን ቤተመቅደስ እንዳገኘች ከተነገረው አስደሳች ዜና በኋላ፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 109 ላይ የሚገኘውን የከርትላንድ ቤተመቅደስ ምረቃ ጊዜ የተደረገውን ጸሎት እንድናጠና ጋብዘውን ነበር። ፕሬዚዳንት ኔልሰን የምረቃው ጸሎት፣ “ቤተመቅደስ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እኔ እና እናንተ የህይወት ፈተናዎችን መቋቋም እንችል ዘንድ መንፈሳዊ ሃይልን” እንዴት እንደሚሠጠን የሚያስተምር ነው” ብለዋል።
የክፍል 109 ጥናታችሁ የባረኳችሁ ግንዛቤዎችን እንዳስገኘላችሁ እርግጠኛ ነኝ። ዛሬ ምሽት፣ የነብያችንን ግብዣ ስከተል የተማርኳቸውን ሁለት ነገሮች አካፍላለሁ። ጥናቴ የመራበት ሰላም ሰጪ መንገድ ጌታ መሐሪ እንደሆነ እና የሰማይ አባታችን የደንነት እቅድ በእውነት የምሕረት እቅድ እንደሆነ አስታውሶኛል።
በቤተመቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ አዲስ የተጠሩ ሚስዮናውያን
እንደምታውቁት፣ “አዲስ የተጠሩ ሚስዮናውያን የቤተ መቅደስ ቡራኬን በተቻለ ፍጥነት እንዲቀበሉ እና ሁኔታዎች በሚፈቅዱት መጠን በቤተመቅደስ እንዲገኙ ይበረታታሉ።” አንዴ ቡራኬ ከተቀበሉ በኋላ “የሚስዮናዊነት አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት የቤተመቅደስ … ሰራተኞች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።”
ወደሚስዮን ማሰልጠኛ ቦታ (MTC) ከመግባታቸው በፊት በቤተመቅደስ ውስጥ ያላቸው ጊዜ የለአዲስ ሚስዮናውያን አስደናቂ በረከት ሊሆን ይችላል፣ ምክንያቱም እነዚያን ቃል ኪዳኖች ለአለም ከማካፈላቸው በፊት ስለ ቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች የበለጠ ይማራሉና።
ነገር ግን ክፍል 109ን በማጥናቴ፣ በቤተመቅደስ ውስጥ፣ እግዚአብሔር አዳዲስ ሚስዮናውያንን—በእርግጥም ሁላችንንም—በተጨማሪ በተቀደሰ መንገድ ኃይል እንደሚሰጥ ተምሬያለሁ። በራዕይ በተሰጠው የምረቃ ጸሎት፣ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ “… ስለ ስምህ ምስክርነት ለመስጠት አገልጋዮችህ ከቤትህ በሚወጡበት ጊዜ፣” “የሰው ልጆች ሁሉ” “የምድር ታላላቆችም” ሆኑ “ድሆች፣ ችግረኞች፣ እና [የተጠቁት]” “ልባቸው እንዲራራ” በማለት ጸለየ። “አገልጋዮችህ ስለስምህ ለመመስከር ከቤትህ የሚወጡትን ልባቸው ያሰላስል ዘንድ፣ ጥላቻቸውም በእውነት ፊት ይከሰም ዘንድ፣ እና ህዝብህም በሁሉም አስተያየት ሞገስን ያገኙ ዘንድ፤ እኛ ባሪያዎችህ ድምፅህን እንደ ሰማን አንተም እንደላከን የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያውቁ ዘንድ” በማለት ጸለየ።
ይህ አዲስ ለተጠራ ሚስዮናዊ— “ህዝብህም በሁሉም አስተያየት ሞገስን ያገኙ ዘንድ” ጥላቻን” “በእውነት ፊት ይከሰም ዘንድ”፣የሚያደርግ ቃል ኪዳን ነው። ያለጥርጥር እያንዳንዳችን እነዚህ ተመሳሳይ በረከቶች ያስፈልጉናል። ከጎረቤቶች እና ከስራ ባልደረቦች ጋር በምንገናኝበት ጊዜ ልቦች መሰላሰላቸው ምን አይነት በረከቶች ይሆናሉ። የመመረቂያው ጸሎት በቤተመቅደስ ውስጥ ያለን ጊዜ እንዴት የሌሎችን ልብ እንደሚያራራ አይገልጽም፣ ነገር ግን በጌታ ቤት ውስጥ ያለው ጊዜ ኢየሱስ በክርስቶስ እና በምህረቱ እኛን በማማከል የራሳችንን ልብ እንደሚያራራ እርግጠኛ ነኝ።
ጌታ ለጆሴፍ ስሚዝ የምሕረት ልመና መልስ ሰጠ
የከርትላንድን የምረቃ ጸሎት ሳጠና፣ ጆሴፍ ለቤተክርስቲያኗ አባላት፣ ለቤተክርስቲያኗ ጠላቶች፣ ለአገሪቱ መሪዎች፣ ለምድር ህዝቦች ምህረትን ደጋግሞ መለመኑ አስገረመኝ። በግል፣ ጌታን እንዲያስታውሱት እና ለሚወዳት ኤማ እና ለልጆቻቸው እንዲራራላቸው ለምኗል።
ከአንድ ሳምንት በኋላ፣ በሚያዚያ 3፣ 1836 (እ.አ.አ)፣ በፋሲካ፣ በከርትላንድ ቤተመቅደስ፣ አዳኙ ለእሱ እና ለኦሊቨር ካውደሪ ሲገለጥ እና በትምህርተ እና ቃል ኪዳኖች ክፍል 110 ላይ እንደተመዘገበው፣ “እነሆ፣ ይህን ቤት ተቀብዬዋለሁ፣ እና ስሜም በዚህ ይሆናል፤ እና በምህረትም ራሴን ለህዝቤ አሳያለሁና” ሲል ጆሴፍ ምን ተሰምቶት ይሆን? ይህ የምሕረት ቃል ኪዳን ለጆሴፍ የተለየ ትርጉም ሳይኖረው አልቀረም። ፕሬዚዳንት ኔልሰን ባለፈው ሚያዚያ እንዳስተማሩት፣ ይህ ቃል ኪዳን እንዲሁ “ዛሬ ተመርቀው ለሚከፈቱ ቤተመቅደሶችም ሁሉ ይሠራል።”
በጌታ ቤት ምህረትን ማግኘት
እያንዳንዳችን በጌታ ቤት ውስጥ ምሕረት የምናገኝባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ጌታ ለመጀመሪያ ጊዜ እስራኤልን ድንኳን እንዲሠሩ እና “የምሕረት መቀመጫውን” በመካከሉ እንዲያስቀምጡ ካዘዘ ጊዜ ጀምሮ አሁንም ይህ እውነት ነው። በቤተመቅደስ ውስጥ በገባናቸው ቃል ኪዳኖች ውስጥ ምሕረትን እናገኛለን። ከጥምቀት ቃል ኪዳኑ በተጨማሪ እነዚያ ቃል ኪዳኖች ከአብ እና ከወልድ ጋር በማስተሣሰር ፕሬዚዳንት ኔልሰን በዕብራይስጥ “ሄሴድ የተባለ ልዩ ዓይነት ፍቅር እና ምህረት” እንደሆነ ያስተማሩትን በላቀ ደረጃ እንድናገኝ ያደርጉናል።
ለዘለአለም ከቤተሰቦቻችን ጋር ለመታተም ባለን እድል ምህረትን እናገኛለን። በቤተመቅደስ ውስጥ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ የደሕንነት እቅድ ክፍል—ፍጥረት፣ ውድቀት፣ የአዳኙ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት እና እንደገና ወደ የሰማይ አባታችን መገኘት የመግባት ብቃታችን የምሕረት መገለጫ እንደሆነ ይበልጥ በግልጽ እንረዳለን። በትክክል “የምሕረት ዕቅድ” በመሆኑ ምክንያት የደህንነት እቅድ የደስታ እቅድ ነው ሊባል ይችላል።
ይቅርታን መፈለግ ለመንፈስ ቅዱስ በር ይከፍታል።
በክፍል 110 ጌታ በቤተመቅደሶቹ እራሱን በምሕረት እንደሚገልጥ ለሰጠው ውብ ቃል ኪዳን አመስጋኝ ነኝ። እኛም ልክ እንደ ጆሴፍ ምህረትን በምንለምንበት ጊዜ ጌታ ራሱን እንዴት በምሕረት እንደሚገልጥ ስለሚገልጸው ነገር አመስጋኝ ነኝ።
በክፍል 109 ላይ የሠፈረው የጆሴፍ ስሚዝ የምህረት ልመና፣ ልመናዎቹ ራዕይን ሲያነሳሱ የመጀመሪያ ጊዜ እንዳልነበረ ያሣያል። በተቀደሠ ጫካ ውስጥ፣ ወጣቱ ጆሴፍ የጸለየው የትኛው ቤተክርስቲያን እውነት እንደሆነ ለማወቅ ብቻ አልነበረም ነገር ግን “የምሄድበት ሌላ ማንም አልነበረውምና ወደ ጌታ ምሕረትን ለማግኘት” እንዳለቀሰ ተናግሯል።” በሆነ መንገድ ጌታ ብቻ የሚሰጠው ምህረት እንደሚያስፈልገው መገንዘቡ የሰማይ መስኮት እንዲከፈት ረድቶታል። ከሶስት አመታት በኋላ፣ ጆሴፍ “ሁሉን ወ[ደ]ሚገዛ እግዚአብሔር ለኃጢአቶ[ቹ] እና ለጥፋቶ[ቹ] ይቅርታ” ጠየቅኩበት ካለበት ጸሎት በኋላ መልአኩ ሞሮኒ ተገለጠ።
የምሕረት ልመናን ተከትሎ የሚመጣው ይህ የመገለጥ ንድፍ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የታወቀ ነው። ሄኖስ የጌታን ድምፅ የሰማው ለይቅርታ ከጸለየ በኋላ ነበር። የንጉሥ ላሞኒ አባት መለወጥ “አንተን ለማወቅ ኃጢያቴን በሙሉ እተዋለሁ” በሚል ጸሎቱ ይጀምራል። በእነዚህ አይነት ተመሳሳይ አስደናቂ ልምዶች ላንባረክ እንችላለን፣ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ለጸሎት መልስ እንዲሰማቸው ለሚቸገሩ፣ የጌታን ምሕረት መፈለግ የመንፈስ ቅዱስን ምስክርነት እንዲሰማን ከምናደርግባቸው በጣም ኃይለኛ ከሆኑ መንገዶች መካከል አንዱ ነው።
የእግዚአብሔርን ምሕረት ማሰላሰል ለመፅሐፈ ሞርሞን ምስክርነት በር ይከፍታል።
በሞሮኒ 10፥3–5 ላይ ተመሳሳይ ውብ የሆነ መርህ እንማራለን። ከልብ በሆነ ጸሎት፣ መፅሐፈ ሞርሞን እውነት መሆን አለመሆኑን ማወቅ እንደምንችል ለማስተማር ብዙ ጊዜ እነዚህን ጥቅሶች እናሳጥራቸዋለን። ነገር ግን እንዲህ ማሳጠር ለምሕረት ጠቃሚ ትኩረት እንዳይሰጥ ሊያደርግ ይችላል። ሞሮኒ ማሳሰቢያውን እንዴት እንደጀመረ አድምጡ፥- “እነዚህን ነገሮች በምታነቡበት ጊዜ፣…ከአዳም መፈጠር ጀምሮ እነዚህን ነገሮች እስከምትቀበሉበት ጊዜ ድረስ ጌታ ለሰው ልጆች ምን ያህል መሃሪ እንደነበረ እንድታስታውሱ እመክራችኋለሁ እናም በልባችሁ አስቡበት።”
ሞሮኒ እነዚህን ነገሮች ሊዘጋቸው የነበሩትን መዝገቦች እንድናነብ ብቻ ሳይሆን መፅሐፈ ሞርሞን “ጌታ ለሰው ልጆች ምን ያህል መሐሪ እንደነበረ” በልባችን እንድናሰላስል ያሳስበናል። “እነዚህ ነገሮች ሃሰት እንደሆኑ የዘላለም አባት እግዚአብሔርን በክርስቶስ ስም እንድንጠይቅ” የሚያዘጋጀን በጌታ ምሕረት ላይ ማሰላሰላችን ነው።
በመፅሐፈ ሞርሞን ላይ ስናሰላስል፣ እንዲህ እንጠይቅ ይሆናል፥ አልማ እንዳስተማረው፣ የእግዚአብሔር የምሕረት እቅድ በዚህ ምድር ላይ የኖረ ሰው ሁሉ እንደሚነሳ፣ በራሳቸው ላይ ያለው ፀጉር እንደማይጠፋ እና ወደ ፍፁም ሰውነታቸው እንደሚመለሱ የሚያረጋግጥ እውነት ነው?አሙሌክ የአዳኙ ምሕረት በእውነት እኛ መክፈል ያለብንን እና “በደህንነት እቅፍ ውስጥ እንድንከበብ የሚያስችለውን የፍትህ ጥያቄ ሁሉ ማርካት ይችላል” ያለው ትክክል ነው?
እውነት አልማ እንደመሰከረው ክርስቶስ ለኃጢአታችን ብቻ ሳይሆን [“ለህመማችን እና በሽታችን]” የተሰቃየው ህዝቡን በድካሙ እንዴት እንደሚረዳ ያውቅ ዘንድ ነው? ንጉሥ ቢንያም እንዳስተማረው፣ እንደ ነፃ ስጦታ፣ “… ለኃጢአተኞች፣ እነርሱን በተመለከተ ያለውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሳያውቁ ለሞቱት፣ ወይም ባለማወቅ ኃጢያትን ለፈፀሙት”31 በእውነት መሃሪ ነው?
ሌሂ “ሰዎች እንዲኖሩ፣ አዳም ወደቀ፤ እና ሰዎች የሚኖሩትም ደስታም እንዲኖራቸው ዘንድ ነው” ያለው እውነት ነው? አቢናዲ ኢሳይያስን ጠቅሶ እንደመሰከረው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን” የሚለው በእርግጥ እውነት ነው?
በጥቅሉ፣ በመፅሐፈ ሞርሞን እንደተገለጸው የአብ እቅድ በእርግጥ የምህረት ነው? እንደዚያ እንደሆነ እና በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ያሉት ሰላም እና ተስፋ ሰጪ የምሕረት ትምህርቶች እውነት እንደሆኑ እመሰክራለሁ።
አሁንም፣ የሰማይ አባት “በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እውነቱን ይገልፅላችኋል” የሚለውን የሞሮኒን ተስፋ ምንም እንኳን እናንተ በታማኝነት ብታነቡም እና ብትጸልዩም ለመረዳት አንዳንዶቻችሁ እንደምትቸገሩ እገምታለሁ። ይህን ትግል የማውቀው ከብዙ አመታት በፊት የራሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት የመፅሐፈ ሞርሞን ክፍሎች ለጸሎቶቼ ፈጣን እና ግልጽ መልስ ባልሰጡበት ጊዜ ስለተሰማኝ ነው።
እየታገላችሁ ከሆነ፣ መፅሐፈ ሞርሞን “ጌታ ምን ያህል መሐሪ እንደሆነ” በሚያስተምርባቸው ብዙ መንገዶች ላይ እንድታሰላስሉ የሞሮኒ ምክር እንድትከተሉ እጋብዛችኋለሁ። ካለኝ ልምድ በመነሳት፣ ይህን ስታደርጉ የመንፈስ ቅዱስ ሰላም ልባችሁ ውስጥ ይገባና መፅሐፈ ሞርሞን እና የሚያስተምረው የምሕረት እቅድ እውነት መሆኑን ማወቅ፣ ማመን እንዲሁም ሊሰማችሁ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ።
ለአብ ታላቅ የምሕረት እቅድ እና አዳኙም በፈቃደኝነት ስለፈጸመው ምስጋናዬን እገልጻለሁ። እርሱን ከፈለግን በቅዱስ መቅደሱ እና በሁሉም የሕይወታችን ክፍል በምሕረቱ ራሱን እንደሚገለጥ አውቃለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።