አጠቃላይ ጉባኤ
በቃልኪዳን ደቀመዝሙርነት የሚገኝ ደሥታ
የሚያዝያ 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:58

በቃልኪዳን ደቀመዝሙርነት የሚገኝ ደሥታ

እንደ ቃልኪዳን ደቀመዛሙርት ለማድረግ ራሳችንን ባስተሳሰርን ጊዜ፣ ባለን የብቃት ደረጃ ሁሉ፣ ከአባታችን ከአብ እና ከልጁ ጋር ያለን ግንኙነት እየጎለበተ ይሄዳል፣ ደስታችን እየጨመረ እና ዘለአለማዊ እይታችንም እየሰፋ ይሄዳል።

በ 2023 (እ.አ.አ) አንድ ቀን ፣ የሞንጎሊያ የሚስዮን ፕሬዚዳንት ወደ ስራ ቦታዋ በምትገባበት ጊዜ ኡያንጋ አልታንሱክ በሰሜናዊ ሞንጎሊያ ከተማ በዳርካን በስራ ላይ ነበረች። በራሷ ቃላት፦

‘’አይቼዋለሁ እናም በፊቱ ገጽታ ላይ ይህን ብሩህ የሆነ ብርሃን ያየሁ ይመስለኛል። እርሱ በጣም ደግ እና በዙሪያው ላሉ የደስታ ምንጭ ነበር፣ እናም የጋለ ስሜት ተሰማኝ። ከመሄዱ በፊት፣ ጥቂት ጥያቄዎችን ጠየቅሁት። ከጥቂት ቀናት በኋላም፣ እንደገና ወደ ስራ ቦታዬ መጣና በእርሱ ቤተክርስቲያን መካፈል እችል እንደሆነ ጠየቀኝ። ይህ የሚረዳ ሊሆን እንደሚችል አሰብኩኝ። ማህበረሰቡ በጭንቀት እና በጭለማ የተሞላ የሚመስል ስለነበረ፣ ለልጆቼ የወደፊት ሁኔታ ተጨንቄ ነበር። ልጆቼ እንደዚህ ሰው የፊታቸው ገጽታ በብርሃን የተሞላና በዙሪያቸው ላሉ ለሌሎችም ደሥታን የሚያሠራጩ እንዲሆኑ ፈለግሁ።

‘’አንድ ቀን ሚስዮናውያን ስለ አስራት ህግ አስተማሩን። ልጆቼም በጉጉት፣ ‘’እማዬ፣ አስራታችንን ልንከፍል ይገባል’ አሉ። በዚያም ወቅት የልጆቼን እምነት ማየት ችያለሁ። ቤተክርስቲያኗን ከመቀላቀሌ በፊት፣ አጠቃላይ ጉባኤን በተመለከትኩ ጊዜ ፕሬዘዳንት ራሰል ኤም ኔልሰን ሲናገሩ ሰማሁ። እርሳቸውም በአለም ዙሪያ አዲስ ቤተመቅደሶች እንደሚገነቡ አበሰሩ ከዚያም በኡላንባታር፣ ሞንጎሊያም አዲስ ቤተመቅደስ እንደሚገነባ ተናገሩ። እኔም ሃሴት አደረግሁ እንዲሁም ለምን እንደሆነ ባላውቅም፣ አነባሁኝ። ሃሴት ስላደረኩም፣ እምነቴ እና ምስክርነቴ እያደገ እንደሆነ ማወቅ ችያለሁ።

ኡያንጋም፣ እንደሌሎቹ ሚሊዮኖች፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት በመዘጋጀት ላይ ያለች የታላቁ የእስራኤል መሰባሰብ አካል ነች። በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ ጉዞዋን ጀምራለች እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆናለች። የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ጃፓኖች ደቀ መዝሙር ለማለት የሚጠቀሙትን ቃል እወደዋለሁ—ደሺ ማለት ታናሽ ወንድም፣ እንዲሁም ማለት ልጅ ማለት ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር፣ ‘’በመጀመሪያም ከአብ ዘንድ ነበርኩኝ፣ እና በኩርም ነኝ።’’ በእርሱ ማንነትምክንያት፣ እና እርሱባደረገውነገርእናመልከዋለን፣ በጣም እናከብረዋለን፣ ክብርን እንሰጠዋለን፣ እንዲሁም እንከተለዋለን። ክርስቶስ ተቤዥቶናል፣ እና ወሰን ስለሌለው የሃጢያት ክፍያው ለዘለአለም እናመሰግነዋለን።

እንደ ልጆቹ የሚወደን የሰማይ አባት አለን። እርሱ ለእኛ ያለው ፍቅር ፍጹም ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እና የእርሱ ተልእኮ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሣያል። ዮሐንስ እንደጻፈው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።’’

የማናውቀውን ለማወቅ በምናደርገው ፍለጋ፣ አንዳንድ ጊዜ በለመድናቸው ምድራዊ ልምምዶች ላይ ወይም በምናውቃቸው ነገሮች ላይ እንደገፋለን፣ ። ለምሳሌ፣ ስለእግዚአብሄር አብ ከራሳችን የልጆች አስተዳደግ እና ምድራዊ በሆነው የቤተሰብ ግንኙነት አማካይነት በመጠኑ ልንማር እንችላለን። ይሁን እንጂ፣ የሰማይ አባታችንን ለመረዳት እነዚህን ማነጻጸሪያዎች በጥልቀት ለመጠቀም ስንሞክር ጥንቃቄ ልንወስድ ይገባል። የእግዚአብሔር አብ ባህርይ የማንኛውንም ከፍጹምነት በታች የሆነውን የወደቀውን ሰው ባህርይ የሚያስንቅ ነው። እግዚአብሔር አብ ፍጹም የሆነ አባት ነው። እርሱ በፍጹም በሆነ መልክ የሚወድ፣ ደግ፣ ትእግስተኛ፣ የሚረዳ፣ እና ፍጹም ግርማን የተላበሰ ነው። ሙሉ ለሙሉ ልናምነው እንችላለን። የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር የእግዚአብሔርን ፍቅር ያንፀባርቃል እንዲሁም የዚያ ፍቅር ተምሳሌት ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌም መፍትሄም ነው። ክርስቶስ፣ የአብን ፍጹም ባህርይ እና የእርሱን ዕቅድ የበለጠ ልናውቅ እንችላለን። በክርስቶስአማካይነት፣ አብን እየመሰልን እንሄድ ዘንድ የተፈጥሮአዊውን የወንዶች እና የሴቶች ዝንባሌ ለመቋቋም የሚያስችለንን ሃይል እንቀበላለን።

እንደ ሰማያዊ አባታችን ሁሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም ፍጹም ምህረትን የተሞላ እንዲሁም ጻድቅ ነው። እነዚህ መለኮታዊ የፍትህ እና የምህረት ባህርያት የሚቃረኑ አይደሉም። የሚደጋገፉ ናቸው። ፍትህ እና ምህረት ሁለቱም እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለውን ፍቅር የሚገልጹ ናቸው። ለሁላችንም በጽድቅ እና በፍትሃዊነት ስለሚፈርዱ እግዚአብሄር አብን እና ኢየሱስ ክርስቶስን ልናምናቸው እንችላለን።

እግዚአብሔር አብ እና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በአላማ እና በፍቅር ፍፁም በሆነ መልኩ የተስማሙ ናቸው። እግዚአብሔር አብ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚወዱን፣ ከእነርሱ ጋር ቃልኪዳን ለማድረግ እድል እና መብት ተሰጥቶናል። ይህን በማድረግም፣ ከክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት ሠፍቷል፤ ‘’እናም አሁን፣ በገባችሁት ቃል ኪዳን የተነሳ የክርስቶስ ልጆች፣ ወንዶችና ሴት ልጆቹ፣ ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ እነሆም በዚህ ቀን እናንተን በመንፈስ ወልዷችኋል፤ ልባችሁ በስሙ በማመን ተለውጧል ብላችኋልና፤ ስለዚህ እናንተ ከእርሱ ተወልዳችኋል እናም የእርሱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ሆናችኋል።’’

እንደ ደቀመዛሙርት፣ ቅዱስ ቃልኪዳኖችን ስንገባ እና ስንጠብቅበመንፈሳዊ ሃይል እንባረካለን። ከክርስቶስ እና ከእግዚአብሄር አብ ጋር ልዩ በሆነ ግንኙነት ተሳስረናል እንዲሁም ቃልኪዳኖችን ለገቡ እና ለጠበቁ በሚሰጥ መመዘኛ የእነርሱን ፍቅር እና ሃሴት መለማመድ እንችላለን የእግዚአብሄርን የፍቅር ሙላት የማወቅ፣ ወይም በፍቅሩ የመቀጠል ችሎታ፣ ባለን የጽድቅ ፍላጎት እና ድርጊት ላይ የተመሰረተ ነው።

ዮሐንስ፣ ምእራፍ 15፣ ቁጥር 9፣ “አብ እንደወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ።’’ የሚለውን እናነባለን። ከዚያ በመቀጠልም ‘’በፍቅሬ ኑሩ’’ የሚል ግብዣ ተሰጥቶናል።

አዳኙ እንዳለውም፣ “እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፤ ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።”

ከዚያም በቁጥር 11 ላይ ትዛዛቱን የመጠበቅን አላማ እናያለን፤ ‘’ደስታዬ በእናንተ ይሆን ዘንድ፣ እናም ደስታችሁም ፍጹም ይሆን ዘንድ፣ እነዚህን ነገሮች እነግራችኋለሁ።’’

እውነተኛ በሆነ ደቀመዝሙርነት አማካይነት፣ የእግዚአብሄርን ተፈጥሮ እና ሁሉም ልጆቹ እንዲለማመዱት የሚፈልገውን ሃሴት በይበልጥ መረዳት እንጀምራለን። ስንጀምራቸው ግራ የሚያጋቡ ይመስሉን የነበሩ አንዳንድ መርሆችን እንዲሁ መረዳት ልንጀምር እንችላለን። ለምሳሌ፣ አንዳንዶቹ ልጆቹ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እያሉ እግዚአብሔር እንዴት ሙሉ የሆነ ደስታ ሊኖረው ይችላል? መልሱም ያለው በእግዚአብሄር ፍጹም የሆነ እይታ እና ፍጹም በሆነው እቅዱ ውስጥ ነው። እርሱ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ ወደፊቱ ታላቅ ዓቅማችን ድረሥ ያየናል። እርሱ፣ ህመምን፣ ስቃይን፣ ሃጢያትን፣ ወቀሳን፣ እና የምድራዊ ህይወታችንን ብቸኝነት የምንቋቋምበትን መንገድ በልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ልጆቹ ለሆንነው ለሁላችንም አዘጋጅቷል። እግዚአብሔር ለእኛ መንገዱን እና ምርጫውን አዘጋጅቷል።

በደቀመዝሙርነት በኩል ሃሴትን የተለማመዱ የእነርሱ ምሳሌነት ይህንን ሃሳብ በተሻለ ሁኔታ እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል። ምናልባትም፣ እኛ ደስተኛ የምንሆነው እጅግ ደሥተኛ ያልሆነው ልጃችን ደሥተኛ የሚሆነውን ያህል ብቻ ነው የሚለውን አባባል ሰምታችሁ ይሆናል። ይህ ጉዳይ ሊሆን እንደማይገባ ተመልክቻለሁ። የ94 አመቷ እናቴ ወደ 200 የሚጠጉ የልጅ ልጆች አሏት። በአንድ በተወሰነ ወቅት፣ ቢያንስ ከ200ዎቹ አንዱ ደስተኛ የማይሆንበት ጊዜ አለ። ይህ አረፍተ ነገር እውነት ቢሆን ኖሮ፣ የእኔ እናት በማያሰልስ ደስታ የሌለው ሁኔታ ውስጥ ትሆን ነበረ ማለት ነው፣ ሆኖም በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ አይደለችም። የምታውቋት ምን ያህል ደስተኛ እንደሆነች ታውቃላችሁ።

አሁን ሌላ ተሞክሮ ላካፍላችሁ እወዳለሁ። ጥር 2019 (እ.አ.አ)፣ ባለቤቴ ዴቢ እና እኔ ወደ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ቢሮ ተጋበዝን። እርሳቸውም ወንበሩን ወደ እኛ ጠጋ አድርገው ተጠጋግተን ተቀመጥን። የወቅቱን ጥሪያችንን ከሠጡን በኋላ፣ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ወደ ዴቢ ዘወር አሉና በእርሷ ላይ አተኮሩ። እርሳቸውም ልክ እንደ ፍጹም አባት ወይም አያት ደግ፣ አፍቃሪ፣ ረጋ ያሉ፣ እና በሃሴት የተሞሉ ነበሩ። የዴቢን እጅ በመያዝ መታ መታ አደረጉት፣ መልካም እንደሚሆን እና ቤተሰባችንም እንደሚባረክ አረጋገጡልን። በዚያ ቅፅበት እኛ ለእርሳቸው በጣም አስፈላጊ ሰዎች የሆንን እና በአለም ላይ ያለውን ጊዜ ሁሉ ለእኛ የመደቡ ያህል ተሰማን። በዚያ አርብ ረፋድ ላይ ማረጋገጫ የማግኘት ሥሜት ተሠምቶን፣ ተወደን እና ሃሴት እያደረግን ከቢሯቸው ወጣን።

ሰኞ እለትም ዜናውን አየን። ፕሬዘዳንት ኔልሰን ከእኛ ጋር ጊዜአቸውን ባሳለፉበት በዚያ ተመሳሳይ ቀን፣ ከሴቶች ልጆቻቸው አንዷ በካንሰር ህመም ህይወቷ አለፈ። ደነገጥን። ለእርሳቸው እና ለቤተሰባቸው ባዘንን ጊዜ ልባችን በጥልቅ ተነክቶ ነበር። ስትሰቃይ ለነበረችውልጃቸው እያዘኑ ሣለ ለእኛ ሲያደርጉልን ስለነበረው ክርስቶስን መሰል አትኩሮት ልባችን በምስጋና ተሞልቶ ነበር።

ይህንን ልምድ ስናሠላስል፣ ራሳችንን እንዲህ በማለት ጠየቅን፣ ‘’እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ጊዜ እንዴት ደግ፣ አፍቃሪ፣ እና ሃሴት የሞላባቸው ሊሆኑ ቻሉ?’’ ምክንያቱም መልሱ እርሳቸው ስለሚያውቁ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ አሸናፊ እንደሆነ ያውቃሉ። ከሴት ልጃቸው ጋር ዳግም አብረው እንደሚሆኑ እና ለዘለአለምም ከእርስዋ ጋር እንደሚያሳልፉ ያውቃሉ። ሃሴት እና ዘለአለማዊ እይታ የሚመጣው ቃል ኪዳን በመግባት እና በመጠበቅ እንዲሁም ክርስቶስን በሚመስል ደቀመዝሙርነት ከጌታ ጋር በመተሳሰር ነው።

ፕሬዘዳንት ኔልሰን እንዳስተማሩት፤ ‘’አዳኙም ‘አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ’ ሰላም እንደሚሰጥ [ፊሊጵሲዩስ 4፥7]፣ እርሱ ሰብአዊ አመክንዮን ወይም ምድራዊ አስተሳሰብን የሚጥስ የላቀ፣ እና የጠለቀ እና ሠፊ ሃሴትንም ያጎናጽፈናል። ለምሳሌ፣ ልጃችሁ በማይድን ህመም ሲሰቃይ፣ ወይም ስራችሁን ስታጡ ወይም የትዳር ጓደኛችሁ ሲከዳችሁ ደስታ ሊሰማችሁ የሚችል አይመስልም። ሆኖም በእርግጠኝነት አዳኝ የሚሰጠው ያንን ደስታ ነው።’’

ቃል ኪዳኖችን በገባን እና በጠበቅን ጊዜ፣ በተፈጥሮ ወደ ውጪ በማተኮር ሌሎች ተመሳሳይ የሃሴት መለኪያ ላይ እንዲደርሱ እና በቃልኪዳኑ ግንኙነታችን ውስጥ የሚሠማን ደስታ እና ፍቅር እንዲሰማቸው የመርዳት ፍላጎት ያድርብናል። ዛሬ በምድር ላይ ባለው እስራኤልን የማሰባሰብ ታላቅ ስራ አካል መሆን እንችላለን። የእግዚአብሔርን ልጆች ወደ ክርስቶስ ለማምጣት መርዳት እንችላለን። ነቢዩ ያዕቆብ እንዳስተማረው፣ ‘’እናንተም የተባረካችሁ ናቸሁ፤ በወይኑ ስፍራዬ ከእኔ ጋር በትጋት በመስራታችሁ፣ ትዕዛዛቴንም በመጠበቃችሁና፣ የወይኑ ስፍራዬ ከእንግዲህ እንዳይበሰብስ፣ በድጋሚ ተፈጥሮአዊ ፍሬን በማምጣታችሁና፣… እነሆ በወይን ስፍራዬ ፍሬ የተነሳ እናንተ ከእኔ ጋር ደስታ ይኖራችኋል።’’

እንደ ቃልኪዳን ደቀመዛሙርት ለማድረግ ራሳችንን ባስተሳሰርን ጊዜ፣ ባለን የብቃት ደረጃ ሁሉ፣ ከአባታችን ከአብ እና ከልጁ ጋር ያለን ግንኙነት እየጎለበተ ይሄዳል፣ ደስታችን እየጨመረ እና ዘለአለማዊ እይታችንም እየሰፋ ይሄዳል። ከዚያም ሃይልን እንሞላለን እንዲሁም ለእግዚአብሔር እውነተኛ የቃልኪዳን ደቀመዛሙርት በተቀመጠ መለኪያ አይነት ሃሴት ሊሰማን ይችላል። ቅዱስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 93፣21

  2. ማቴዎስ 1፥21; 2 Nephi 2:6 ይመልከቱ።

  3. ዮሀንስ 3፥16

  4. ሞዛያ 5፥7

  5. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ዘለአለማዊው ቃል ኪዳን፣” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2022 (እ.አ.አ)፣4–11።

  6. ዴል ጂ. ረንላንድ፣ “የእግዚአብሔርን ፍቅር ተለማመዱ” [Brigham Young University devotional, ታህሳስ 3፣ 2019 (እ.ኤ.አ)]፣ 4፣ speeches.byu.edu ተመልከቱ።

  7. ዮሐንስ 15፥9–11

  8. አልማ 7፥11-13

  9. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ደስታ እና መንፈሳዊ ደህንነት፣” Liahona፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 82።

  10. Russell M. Nelson, “Hope of Israel [የእስራኤል ተስፋ]” [worldwide youth devotional [የአለም አቀ የወጣቶች ትመንፈስ ስብሰባ]፣ ሰኔ 3፣ 2018 (እ.ኤ.አ)]፣ የወንጌል ቤተመጻህፍት።

  11. ያዕቆብ 5፥75

  12. ‘’ሄሰድ፣ የእግዚአብሄር የቃልኪዳን ፍቅር፣ ቤተመቅደስ የምንገነባበት እና ቅዱስ ስርአቶችን የምንፈጽምበት ምክንያት፤ ከፕሬዘዳንት ራሰል ኤም ኔልሰን መመሪያ፣’’ የጠቅላላ ጉባኤ አመራር ስብሰባ ጥቅምት 2024፣ (እ.ኤ.አ)፣የወንጌል ላይብረርይ