አጠቃላይ ጉባኤ
አዳኙን ለመገናኘት ግላዊ ዝግጅት
የሚያዝያ 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:10

አዳኙን ለመገናኘት ግላዊ ዝግጅት

የአዳኙን አስተምህሮቶች ተከተሉ። የእርሱ መመሪያዎች ሚስጥራዊ ወይም ውስብስብ አይደሉም። እነሱን ስንከተላቸው መፍራት ወይም መጨነቅ አይገባንም።

ባለፈው ጥቅምት ፕሬዚዳንት ኔልሰን “አሁን እኔ እና እናንተ ለጌታችንና ለአዳኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት የምንዘጋጅበት ጊዜ ነው” በማለት አስተምረው ነበር። ፕሬዚዳንት ኔልሰን ስለ ዳግም ምፅዓት ሲናገሩ ሁል ጊዜም ደስታ በተሞላበት ተስፋ ነው። ሆኖም፣ በመጀመሪያ ክፍል የምትገኝ አንዲት ልጅ ስለ አዳኙ ዳግም ምፅዓት በተነሳ ቁጥር እንደምትጨነቅ ነገረችኝ። “የምፈራበት ምክንያት ኢየሱስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት መጥፎ ነገሮች ስለሚከሰቱ ነው” ብላለች።

እንዲህ ሊሰማቸው የሚችለው ልጆች ብቻ አይደሉም። ለእሷ፣ ለእናንተ እና ለእኔ በጣም ጥሩው ምክር የአዳኙን ትምህርቶች መከተል ነው። የእርሱ መመሪያዎች ሚስጥራዊም ውስብስብም አይደሉም። እነሱን ስንከተላቸው መፍራት ወይም መጨነቅ አይገባንም።

በምድራዊ አገልግሎቱ መጨረሻ ላይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ መቼ ዳግም እንደሚመጣ ተጠይቆ ነበር። በዳግም ምጽአቱ ወይም ከዚህ ዓለም በምንለይበት ጊዜ እርሱን ለመገናኘት እንዴት መዘጋጀት እንዳለብን መልስ ሲሰጥ፣ በማቴዎስ 25 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ሦስት ምሳሌዎች አስተምሯል። ከእርሱ ጋር ለመገናኘት የሚደረግ የግል ዝግጅት የህይወት አላማ ማዕከል ስለሆነ እነዚህ ትምህርቶች ወሣኝ ናቸው።

በመጀመሪያ አዳኙ የአሥሩን ደናግላን ምሳሌ ተናገረ። በዚህ ምሳሌ አሥር ደናግላን ወደ ሰርግ ግብዣ ይሄዳሉ። አምስቱ በልባምነት ለመብራታቸው የሚሆን ዘይት ገዝተው የነበረ ሲሆን አምስቱ በስንፍና ሳይገዙ ቀሩ። ሙሽራው እንደሚመጣ በተነገረ ጊዜ ሰነፎቹ ደናግላን ዘይት ለመግዛት ሄዱ። ሲመለሱ በጣም ዘግይተው ስለነበር የግብዣው ቤት በር ተዘግቶ ነበር።

ኢየሱስ እኛን ለመርዳት የምሳሌውን ሦስት ገጽታዎች ገልጿል። እንዲህም ሲል አብራርቷል፦

“እናም በክብሬ በምመጣበት በዚያም ቀንም፣ ስለ አሥሮቹ ደናግል የተናገርኩት ምሳሌም ይፈጸማል።

“እነርሱ ጥበበኛ ናቸው እናም እውነትን ተቀብለዋልና፣ እና እንደ መሪያቸውም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፣ እና አልተታለሉም—በእውነት እንዲህ እላችኋላሁ፣ ቀኑን ይዋጃሉ እንጂ ተቆርጠው ወደ እሳቱ አይጣሉም።”

በሌላ አነጋገር፣ እነርሱ አይፈሩም ወይም አይጨነቁም ምክንያቱም ይድናሉ እንዲሁም ይበለፅጋሉ። ያሸንፋሉም።

ልባሞች ከሆንን በክህነት ሥርዓቶች እና በቃል ኪዳኖች አማካኝነት የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመቀበል እውነትን እናገኛለን። በመቀጠልም፣ መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ይሆን ዘንድ ብቁ በመሆን ለመቀጠል እንጥራለን። ይህን አቅም እያንዳንዳችን በግል ቀስ በቀስ ማግኘት ይኖርብናል። ቋሚ፣ ግላዊ የአምልኮ ተግባራት መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን ይጋብዛሉ።

ኢየሱስ ጎላ አድርጎ የገለጸው ሦስተኛው ነገር መሳትን ማስወገድ ነው። አዳኙ፦

“ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤

“ብዙዎች በስሜ—እኔ ክርስቶስ ነኝ—በማለት ይመጣሉና፣ እና ብዙዎችንም ያስታሉ።” በማለት አስጠንቅቋል።

አዳኙ፣ አስመሳዮች የተመረጡትን ለማታለል እንደሚሞክሩ እና ብዙ ደቀመዛሙርት እንደሚያስቱ ያውቃል። በሐሰት መለኮታዊ ሃይል እንደተቀበሉ የሚናገሩትን ወይም ጥበብን ወይም ምሪትን አስተማማኝ ካልሆነ ቦታ ወይም ከሚያስቱ ምንጮች የሚቀበሉትን ማመን የለብንም።

መፅሐፈ ሞርሞን አታላዮችን ከደቀመዛሙርት እንዴት መለየት እንደምንችል ያስተምረናል። ደቀ መዛሙርት ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ማመንን፣ እርሱን ማገልገልን እና መልካም ማድረግን ያበረታታሉ። ከሚታመኑ የአዳኙ ደቀመዛሙርት፣ ራሳቸውም ታማኝ ከሆኑ ሰዎች ምክርን ስንፈልግ እና ስንቀበል አንስትም።

በቤተመቅደስ ውስጥ አዘውትረን በማምለክ ከመሣት መጠበቅ እንችላለን። ይህ ዘላለማዊ አመለካከትን እንድንይዝ ይረዳናል እንዲሁም ከቃል ኪዳኑ መንገድ ሊለዩን ወይም ዞር ሊያደርጉን ከሚችሉ ተጽእኖዎች ይጠብቀናል።

የዚህ የአስር ደናግላን ምሳሌ አስፈላጊ ትምህርት ወንጌልን ስንቀበል፣ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር እንዲሆን ስንፈልግ እና ከመሳት ስንጠበቅ ልባሞች እንሆናለን የሚል ነው። አምስቱ ልባም ደናግላን ዘይት የሌላቸውን መርዳት እንዳልቻሉት ሁሉ ማንም ሰው በእኛ ፈንታ ወንጌልን ሊቀበል፣ መንፈስ ቅዱስን እንደ መሪ ሊወስድ እና ከመሳት ሊጠብቀን አይችልም። ይህንን ራሳችን ማድረግ አለብን።

ቀጥሎም አዳኙ የመክሊቶቹን ምሳሌ ተናገረ። በዚህ ምሳሌ፣ አንድ ሰው መክሊት ተብሎ የሚጠራን የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ለሦስት አገልጋዮች ይሰጣል። ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለሦስተኛው ደግሞ አንድ ይሰጣል። በጊዜ ሂደት፣ የመጀመሪያዎቹ ሁለት አገልጋዮች የተቀበሉትን በእጥፍ አሳደጉ። ሦስተኛው አገልጋይ ግን አንዷን መክሊት ወስዶ ቀበረ። መክሊታቸውን እጥፍ ላደረጉት ለሁለቱም አገልጋዮች ሰውዬው ለእያንዳንዳቸው፡-“መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” ይላቸዋል።

ከዚያም መክሊቱን የቀበረውን አገልጋይ “ክፉ እና ሃኬተኛ” በማለት ይናገረዋል።” የዚህ አገልጋይ መክሊት ተወሰደበትና ተባረረ። ሆኖም፣ ይህ አገልጋይ መክሊቱን እጥፍ አድርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ልክ እንደሌሎቹ አገልጋዮች ምስጋናንና ሽልማትን ባገኘ ነበር።

የዚህ ምሳሌ አንዱ መልእክት እግዚአብሔር የተሰጠንን ችሎታ እንድናጎላ ይጠብቅብናል፣ ነገር ግን እርሱ አቅማችንን ከሌሎች ጋር እንድናነጻጽር አይፈልግም። የ18ኛው መቶ ዘመን የአኒፖል የሃሲዲክ ምሁር ዙስያ ያቀረበውን ይህን መረዳት ተመልከቱ። ዙስያ የሚሞትበት ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ መፍራት የጀመረ ታዋቂ አሰተማሪ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም፣ “መምህር ሆይ፣ ለምን ትፈራለህ? ጥሩ ሕይወት ኖረሃል፣ በእርግጥ እግዚአብሄር ታላቅ ሽልማት ይሰጥሃል” አሉት።

ዙስያ እንዲህ አለ:- “እግዚአብሔር ‘ዙሲያ፣ ለምን ሌላኛው ሙሴ አልሆንክም?’ ቢለኝ ‘ለሙሴ የሰጠኸውን ታላቅ ነፍስን ስላልሰጠኸኝ ነው’ እለዋለሁ። በእግዚአብሔር ፊት ብቆም እርሱም ደግሞ፦ ዙሲያ፡ ለምን ሌላኛው ሰሎሞን አልሆንክም? ቢለኝ ‘የሰለሞንን ጥበብ ስላልሰጠኸኝ ነው’ እለዋለሁ። ነገር ግን በፈጣሪዬ ፊት ብቆምና ‘ዙስያ፣ ለምን ዙስያን አልሆንክም? እንድትሆን አቅም የሰጠሁህን ሰው ለምን አልሆንክም?’ ቢለኝስ በዚያ ምክንያት ነው የምፈራው” አላቸው።

በእርግጥ፣ ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸውን ችሎታዎች ለማጉላት በአዳኙ ጥበብ፣ ምህረት እና ጸጋ ካልተደገፍን እግዚአብሔር ያዝንብናል። በእርሱ የፍቅር እርዳታ፣ የራሳችን ምርጥ ስሪት መሆን እንድንችል ከእኛ ይጠብቃል። በተለያዩ ችሎታዎች መጀመራችን ለእርሱ ምንም ማለት አይደለም። ለእኛም እንደዚያው መሆን አለበት።

በመጨረሻም፣ አዳኙ የበጎችን እና የፍየሎችን ምሳሌ ይናገራል። በክብሩ ሲመለስ “አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።”

በቀኙ ያሉት በመንግሥቱ ወራሾች ሲሆኑ በግራው ያሉት ግን ርስት ሳያገኙ ቀሩ። የለያቸው ባህሪ ሲራብ ማብላታቸው፣ ሲጠማ ማጠጣታቸው፣ እንግዳ ሳለ ወደ ቤታቸው መቀበላቸው፣ ራቁቱን ሳለ ማልበሳቸው እና ሲታመም ወይም ሲታሰር መጠየቃቸው ወይም ይህን ሳያደርጉ መቅረታቸው ነበር።

በቀኝ እጅ እናም በግራ እጅ ያሉት ሁሉ ግራ ተጋብተው ነበር። ምግብ፣ የሚጠጣ ነገር እና ልብስ መቼ እንደሰጡት ወይም ተቸግሮ በነበረ ጊዜ መቼ እንደረዱት ወይም ይህን ሳያደርጉ እንደቀሩ ጠየቁ። አዳኙ “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” በማለት መለሠላቸው።

የምሳሌው መልዕክት ግልጽ ነው፡- ሌሎችን ስናገለግል፣ እግዚአብሔርን እናገለግላለን፤ ይህን ካላደረግን፣ እናሳዝነዋለን። የሰማይ አባትን ልጆች ህይወት ለመባረክ ስጦታችንን፣ ተሰጥኦችንን እና ችሎታችንን እንድንጠቀም ይፈልጋል። ሌሎችን ለማገልገል ያለው መለኮታዊ ግፊት በፊንላንዳዊው ገጣሚ በጆሃን ሉድቪግ ሩንበርግ በ19ኛው መቶ ዘመን በተጻፈው ድንቅ ግጥም ላይ ተገልጿል። እኔና ወንድሞቼ እና እህቶቼ በልጅነታችን ጊዜ ሁሉ “ገበሬ ፓቮ” የተሰኘውን ግጥም ደጋግመን ሰምተናል። በግጥሙ ውስጥ ፓቮ ከሚስቱ እና ከልጆቹ ጋር በማዕከላዊ ፊንላንድ ሀይቅ አካባቢ ይኖር የነበረ ድሃ ገበሬ ነበር። በፀደይ በረዶ መቅለጥ፣ በበጋ በረዶ ወይም በመጸው መጀመሪያ ላይ በመጣው ውርጭ ምክንያት በተከታታይ ለብዙ ዓመታት አብዛኛው ሰብሎቹ ይወድማሉ። አነስተኛው ምርት በገባ ቁጥር የገበሬው ሚስት “ፓቮ፣ ፓቮ፣ አንተ ያልታደልክ ሽማግሌ፣ እግዚአብሔር ትቶናል” ስትል በምሬት ትናገር ነበር። ፓቮ በተራው በቁጣ እንዲህ ይላል፡- “ህፃናቱ እንዳይራቡ ዳቦ ለመስራት የግንድ ቅርፊትን ከአጃው ዱቄት ጋር ቀላቅዪ። ረግረጋማ ቦታዎችን ለማፍሰስ ጠንክሬ እሰራለሁ። እግዚአብሔር እየፈተነን ነው፣ እርሱ ግን ያዘጋጃል።”

አዝመራው በጠፋ ቁጥር ፓቮ ረሃብን ለመከላከል በዱቄት ውስጥ የተቀላቀለውን የግንድ ቅርፊት በእጥፍ እንድትጨምር ለሚስቱ መመሪያ ይሰጥ ነበር። እንዲሁም የመሬቱን ውሃ ለማፍሰስ እና የእርሻ መሬቶቹን ለበልግ ፍሳሽ እና ለበልግ መጀመሪያ ውርጭ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጉድጓዶችን በመቆፈር ጠንክሮ ሰራ።

ከአመታት ችግር በኋላ ፓቮ በመጨረሻ የበለጸገ ሰብል ሰበሰበ። ሚስቱ በጣም ተደሰተች፣ “ፓቮ፣ ፓቮ፣ እነዚህ አስደሳች ጊዜያት ናቸው! የዛፍ ቅርፊትን የምንጥልበት እና በአጃ ብቻ የተሰራ ዳቦ የምንጋግርበት ጊዜ አሁን ነው።” ነገር ግን ፓቮ የሚስቱን እጅ ያዘና፣ “የጎረቤታችን ማሳ ደርቆአልና ግማሹን ዱቄት ከግንድ ቅርፊት ጋር ቀላቅዪ” አላት። ፓቮ የተጎዳውን እና የተቸገረውን ጎረቤቱን ለመርዳት የእሱን እና የቤተሰቡን ችሮታ ሠዋ።

የአዳኙ የበጎች እና የፍየሎች ምሳሌ ትምህርት የተሰጡንን ስጦታዎች—ጊዜን፣ ችሎታዎችን እና በረከቶችን—የሰማይ አባትን ልጆች በተለይም በጣም ተጋላጭ የሆኑትን እና የተቸገሩትን ለማገልገል መጠቀም እንዳለብን ነው።

ቀደም ብዬ ለጠቀስኩት ለተጨነቀችው የመጀመሪያ ክፍል ልጅ እና ለእያንዳንዳችሁ ግብዣዬ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድትከተሉ እና ውድ ጓደኛችሁን እንደምታምኑ ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንድታምኑ ነው። በሚወዷችሁ እንዲሁም አዳኙን በሚወዱ ላይ ተደገፉ። ልዩ ችሎታችሁን ለማዳበር እና ቀላል ባይሆንም፣ ሌሎችን ለመርዳት የእግዚአብሔርን መመሪያ ፈልጉ። ከአዳኙ ጋር ለመገናኘት ዝግጁ ትሆናላችሁ እንዲሁም ፕሬዘዳንት ኔልሰንን በደስታ እና ተስፋ በማድረግ መቀላቀል ትችላላችሁ። ይህን በማድረግ፣ ዓለምን ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት በማዘጋጀት ትረዳላችሁ እንዲሁም ወደ ጌታ እረፍት ለመግባት አሁን እና ወደፊት በበቂ ተስፋ ትባረካላችሁ።

ከአዲስ መዝሙራችን በአንዱ ላይ እንዲህ እንዘምራለን፡

ተደሰቱ! ለዚያም ቀን ተዘጋጁ!…

ዳግም የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ማንም አያውቅም፣

ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ይመለሳል፣ የደስታም ቀን ይሆናል

የምንወደው አዳኛችን እንደገና ሲመጣ።

በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ይመጣል፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2024 (እ.አ.አ)፣ 121

  2. እርሱን ለመገናኘት ዝግጁ እንድንሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚለውጠን መጨነቅ አይገባንም። ያለማቋረጥ ቃል ኪዳኖቻችንን ስናከብር እና ትእዛዛቱን ስንጠብቅ፣ በጸጋው እና በበረከቶቹ አማካኝነት ቀስ በቀስ እንደ አዳኙ እንሆናለን። ይህን ስናደርግም፣ ለዳግም ምጽአቱ የተዘጋጀን እንሆናለን። 1 ዮሐንስ 3፥2–3 ላይ እንደተናገረው፦

    “ወዳጆች ሆይ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም፡፡ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፡፡” (1 ዮሀንስ ወንጌል 3፡2)

    በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።”

  3. የጌታ ዳግም ምጽአት የሚፈጸመው በክብር በሚመለስበት ጊዜ እና ሁሉም እርሱ ተስፋ የተደረገለት መሲህ እንደነበረ እና መሆኑን በሚገነዘቡበት በሺህ ዓመቱ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው። (see ኢሳይያስ 45:23; ዘካርያስ 12:10; ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88:104ይመልከቱ)።

  4. ራስል ኤም ኔልሰን “የመክፈቻ ንግግር፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2020 (እ.አ.አ)፣ 6–8 ተመልከቱ።

  5. የጆሴፍ ስሚዝ ትርጉም፣ ማቴዎስ 25፡1 (በ ማቴዎስ 25:1፣ የግርጌ ማስታወሻ) )፤ ማቴዎስ 25:1–4, 6–13.

  6. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 45፥56-57

  7. ዴቪድ ኤ.ቤድናር፣ “Converted unto the Lord፣” Liahona፣፣ ሕዳር 2012 (እ.ኤ.አ)።

  8. 2 ኔፊ 32፥5ይመልከቱ።

  9. ማቴዎስ 24፥4–5

  10. See Joseph Smith—Matthew 1:5–6, 8–9, 21–22, 25–26.

  11. ሞሮኒ 7:13፣ 15–17 ይመልከቱ። በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ያሉት አስተምህሮቶች ከመፅሃፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ጋር ይገናኛሉ እንዲሁም “የውሸት ትምህርቶች ሀሰት መሆናቸውን” (2 ኔፊ 3፡12) ያስረዳሉ። ምናልባት ይህ “መፅሐፈ ሞርሞን አለምን ለዳግም ምፅአት የሚያዘጋጅ የእግዚአብሔር መሳሪያ ነው” በማለት የፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን የሰጡት ምላሽ አካል ነው (“The Book of Mormon, the Gathering of Israel, and the Second Coming [መፅሐፈ ሞርሞን፣ የእስራኤል መሰብሰብ እና የዳግም ምጽአት]፣” ሊያሆና፣ ሰኔ 26፣ 2013 (እ.አ.አ)፣ 27)።

  12. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ስለ ሰለስቲያል አስቡ!፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2023 (እ.አ.አ)፣ 119–20 ተመልከቱ። ፕሬዚዳንት ኔሰን በዳግም እንዳስተማሩትም፣ “[ምስክራችሁን] በማያምኑት ወንዶች እና ሴቶች የውሸት ፍልስፍና አታበክሉት” (“Overcome the World and Find Rest,” Liahona, Nov. 2022, 97)። ጥያቄአችሁን ወደ ጌታ እና ወደ ሌላ የእምነት ምንጮች ውሰዱ። … የሌሎችን ጥርጣሬዎች በመደጋገም የራሳችሁን ጥርጣሬ አታሳድጉ።” (“Christ Is Risen; Faith in Him Will Move Mountains,” Liahona, May 2021, 103)። የመጽሃፈ ሞርሞን ነቢያ ታላቁ አልማ እንዳለው፡ “እናም ደግሞ የእግዚአብሔር ሰው ሆኖ በእርሱ ጎዳና የሚራመድና ትዕዛዛቱን የሚጠብቅ ካልሆነ በቀር ማንም የእናንተ መምህርም ሆነ አገልጋይ እንዲሆን አትፍቀዱ” (ሞዛያ 23፥14)። በዚህ ዘመን፣ አዳኙ “መንፈሱ ትሁት … ቋንቋውም ቅንና በሚያንፅ … በሀይሌ በሚንቀጠቀጠውም … በምሰጣችሁ ራዕዮች እና እውነቶች በኩልም የምስጋና እና የጥበብ ፍሬዎችን”(ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥14–19) በሚያመጣ እንድንደገፍ አስተምሮናል።

  13. ረስል ኤም ኔልሰን “The Lord Jesus Christ Will Come Again [ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ይመጣል”፣ 121።

  14. በሞቱ አባቶች ምትክ ሥርዓቶች ሲፈጸሙ፣ እነዚያ ቅድመ አያቶች ወንጌልን ለመቀበል እና ታማኝ ሆነው እንደሚቀጥሉ ወይም እንደማይቀጥሉ ራሳቸው ይወስናሉ። በእነዚያ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ማንም ለሌላው አይወስንም።

  15. ማቴዎስ 25፥14–30ይመልከቱ።

  16. የቅዱሳን ጽሑፎች መመሪያ “ችሎታዎች” የሚለውን ይመልከቱ። መክሊት በጥንታዊ ግሪክ እና ሮማውያን ዘመን የነበረ የክብደት እና የገንዘብ ዋጋ መለኪያ ነበር። አንድ መክሊት 6,000 ዲናር ያህል ዋጋ እንዳለው ይገመታል፤ አንድ ዲናር ለአንድ ሠራተኛ የቀን ደሞዝ ያህል ይሆናል፤ አንድ መክሊት ለአንድ ሠራተኛ የ20 ዓመት ያህል ደሞዝ ይሆናል።

  17. ማቴዎስ 25፥21፤ እንዲሁም ቁጥር 23 ይመልከቱ።

  18. ማቴዎስ 25፥24-26 ይመልከቱ።

  19. ምሳሌውን በማስፋት፣ በዘላለማዊው የነገሮች እቅድ፣ እያንዳንዱ አገልጋይ ወደ ጌታው ደስታ ሲገባ እና ጌታ ያለውን ሁሉ ወራሽ ሲሆን፣ እያንዳንዱ አገልጋይ መጀመሪያ ላይ የነበረው ጥቃቅን ልዩነቶች እዚህ ግባ የማይባሉ ይሆናሉ።

  20. በተጨማሪም፣ ጌታ በዚህ ምሳሌ የተገለጹትን መክሊቶች እውቀትን እና ምስክርነትን ጨምሮ ከተለያዩ የህይወት እና የወንጌል ዘርፎች ( ኤተር 12:35; ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 60:2, 13) እንዲሁም ንብረት እና መጋቢነት ጋር ያመሳስላቸዋል( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 82:18ይመልከቱ)።.

  21. ሃሮልድ ኤስ ኩሽነር፣ Overcoming Life’s Disappointments (2006 እ.አ.አ)፣ 26 ተመልከቱ።

  22. ወንጌሌን ስበኩ፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የማካፈል መመሪያ—ምዕራፍ 48፡ “በህይወት ውስጥ ፍትሃዊ ያልሆነው ነገር ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ሊስተካከል ይችላል።”

  23. ማቴዎስ 25፥31-46 ይመልከቱ።

  24. ማቴዎስ 25:32–33

  25. ማቴዎስ 25፥37–39፣ 44 ይመልከቱ።

  26. ማቴዎስ 25፥40፤ እንዲሁም ቁጥር 45 ይመልከቱ።

  27. ሞዛያ 2፥17 ይመልከቱ። ወንጌሉን ስንካፈል፣ ልባቸው የተሰበረውን ለመፈወስ ስንረዳ ( ኢሳይያስ 61፥1–3ሉቃስ 4፥16–21 ይመልከቱ)፣ ደካሞችን ስናግዝ፣ የደከሙ እጆች ስናነሳ እና የደከሙ ጉልበቶችን ስናበረታ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 81፥5 ይመልከቱ) በአዳኙ ተልእኮ ውስጥ እንሳተፋለን።

  28. የፈረንጅ ልምጭ ዛፍ ውስጥ ያለው የዛፉ ውስጠኛ ሽፋን አንዳንድ ካርቦሃይድሬትስ እና ፋይበር ይዟል። እንደ የመጨረሻ አማራጭ ሊበላ ይችላል።

  29. See Johan Ludvig Runeberg, “Högt Bland Saarijärvis Moar,” Idyll och epigram Dikter (1830), nummer 25; Suomen kansalliskirjallisuus (Helsinki, 1941), 9:50–52; sv.wikisource.org/wiki/Högt_bland_Saarijärvis_moar. ከስዊድን ቋንቋ እኔ የተረጎምኩት ነው።

  30. ይህም እግዚአብሔር የጥንት እስራኤላውያን እንዲያደርጉ የሰጣቸውን መመሪያ ይወክላል፡- “ድሆች ከምድሪቱ ላይ አያልቁምና ስለዚህ እኔ በአገርህ ውስጥ ላለው ድሀ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህንትከፍታለህ ብዬ አዝሃለሁ።” ዘዳግም 15፡11 )።

  31. ስለ ዳግም ምጽአት እና ለዚያ ለመዘጋጀት መንገዶችን አስደናቂ ንግግር ዳሊን ኤች ኦክስን፣ “Preparation for the Second Coming,” ሊያሆና 2004፣ ይመልከቱ።

  32. ራስል ኤም.ኔልሰን፣ “አለምን ማሸነፍ እና እረፍትን ማግኘት፣” 95–98 ይመልከቱ። ፕሬዚዳንት ኔልሰን አስተምረዋል፣ “የዚህ መሰብሰብ አንዱ ወሳኝ አካል ጌታ በዳግም በሚመጣበት ጊዜ ለመቀበል የሚችሉ፣ ዝግጁ እና ብቁ የሆኑ ሰዎችን፤ በዚህ በወደቀው ዓለም ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን የመረጡ ህዝቦች፤ ከፍ ያለ፣ ቅድስተ ቅዱሳን የሆኑትን የኢየሱስ ክርስቶስ ህግጋትን ለመኖር በመረጣቸው የሚደሰቱ ሰዎችን ማዘጋጀት ነው” (“Overcome the World and Find Rest,” 98)።

  33. ሞሮኒ 7፥3 ተመልከቱ። ፕሬዘደንት ጆሴፍ ኤፍ. ስሚዝ እንዲህ አስተምረዋል፡ “የተጠቀሰው እረፍት አካላዊ አይደለም።… [ይህ] እውነትን በማመን የሚወለደድ መንፈሳዊ ዕረፍትና ሰላም ነው። … የወንጌልን እውነት ወደ መረዳት በመምጣት ዛሬ ወደ ጌታ ዕረፍት መግባት እንችላለን። [ወደዚህ ዕረፍት የገቡት] አእምሮዋቸው የረካ እና ዓይኖቻቸውን ወደ ከፍተኛው ጥሪ ምልክት ያደረጉ እና በማይበገር ቁርጠኝነት በልባቸው ለእውነት ጸንተው የቆዩ እና በትህትና እና በጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች መንገድ ላይ የሄዱ ናቸው። ነገር ግን ወደዚህ የፅኑ እምነት ደረጃ ላይ ሳይደርሱ በትምህርት ንፋስ የተወሰዱ፣ ምቾት የማይሰማቸው፣ ያልተረጋጉ፣ እረፍት የሌላቸው ብዙዎች አሉ። እነዚህ በቤተክርስቲያን እና በሀገር ውስጥ በሚፈጠሩ ክስተቶች እና በሰዎች ግርግር ተስፋ የሚቆርጡ ናቸው። … እነሱ የጥርጣሬ፣ የያለመረጋጋት እና እርግጠኛ ያለመሆን ስሜት ይሰማቸዋል። ሐሳባቸው የተረበሸ ነው እንዲሁም በባሕር ላይ እንደጠፋ ሰው በትንሽ በመለወጥ በጣም ደስ ይላቸዋል፣” (የወንጌል ትምህርት፣ 5ኛ እትም [1939 (እ.አ.አ)]፣ 126)።

  34. ሌን ጆንሰን፣ “When the Savior Comes Again,” መዝሙር— ለቤት እና ለቤተክርስትያን፣ የወንጌል ቤተመጻሕፍት።