‘’በዚህም ደቀመዛሙርቴ መሆናችሁን ሁሉም ያውቃሉ’’
እኛ ለእግዚአብሔር እና ለልጆቹ ያለን ፍቅር ይህች በእውነት የአዳኙ ቤተክርስቲያን እንደሆነች ለአለም ሃያል የሆነ ምስክርነት ነው።
ከብዙ ዓመታት በፊት እኔና እኅት ኡክዶርፍ በደቡባዊ ጀርመን እየተጓዝን ነበር። ልክ ከፋሲካ በፊት ነበር እና አንድ የቤተክርስቲያኗ አባል ያልነበረች ጓደኛችንን በእሁድ የአምልኮ አገልግሎት ላይ እንድትሳተፍ ጋበዝናት። ይህችን ውድ ጓደኛችንን ወደድናት፣ በመሆኑም ስለአዳኙ እና ስለእርሱ ቤተክርስቲያን ምን እንደተሰማን እና እርሷ እንድትመጣ እና እንድታይ መጋበዙ የተለመደ ነበር። እርሷም ግብዣውን ተቀበለች እና በአቅራቢያው በነበረ የአንድ ቤተክርስቲያን ስብሰባ ላይ ተቀላቀለችን።
አንድን ጓደኛችሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን አምጥታችሁት ከሆነ፣ ምናልባትም በዚያ እሁድ ጠዋት ከነበረኝ ስሜት ጋር ልታያይዙት ትችላላችሁ። ሁሉም ነገር በፍጹምነት እንዲሄድ ፈለግሁ። ጓደኛችን እጅግ የተማረች፣ መንፈሳዊ ግለሰብ ነበረች። የዚህ ቅርንጫፍ ቤተክርስቲያን ስብሰባዎች በእርሷ ላይ መልካም ግምት ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ጽኑ ተስፋ ነበረኝ።
የቅርንጫፉ አባላት በአንድ ህንጻ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ጥቂት ክፍሎችን ተከራይተው እዛ ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። እዚያም ለመድረስ፣ በዚያ አካባቢ የተከማቹትን የቁሳቁሶች ጠንካራ ሽታ በማለፍ፣ ከህንጻው በስተጀርባ በኩል የነበረውን ደረጃ መውጣት ነበረብን።
የቅዱስ ቁርባን ስብሰባው እንደጀመረ፣ ይህንን ልምምድ ለመጀመሪያ ጊዜ ስላስተናገደችው ጓደኛዬ አሰብኩ፣ እና ነገር ግን ጥቂት እንድሸማቀቅ ያደረጉኝን ነገሮች አስተዋልኩኝ። ለምሳሌ፣ ዝማሬው፣ ልክ እንደ የታበርናክል ዘማሪዎች አዘማመር አይመስልም ነበር። እረፍት የሌላቸው፣ የሚጮሁ ልጆች ድምፃቸው በቅዱስ ቁርባን ስብሰባው ወቅት እየተሰማ ነበር። ተናጋሪዎቹ የሚቻላቸውን አድርገዋል፣ ነገር ግን ለህዝብ በሚደረግ ንግግር የተካኑ አልነበሩም። ምናልባትም የሰንበት ትምህርት የሚሻል ይሆናል በሚል ተስፋ፣ በስብሰባዎቹ ወቅት ምቾት በሌለው ሁኔታ ተቀምጬ ነበር።
የሚሻል አልነበረም።
ጠዋቱን ሙሉ ጓደኛችን, ልናሳያት ይዘናት ስለሄድነው ወደዚህ ቤተክርስቲያን ምን ልታስብ እንደምትችል ስጨነቅ ዋልኩኝ።
ቀጥሎም፣ ወደ ቤት በመሄድ ላይ እንዳለን፣ ጓደኛዬን ላናግራት ዘወር አልኩኝ። እኔም ይህች አንድ ትንሽ ቅርንጫፍ እንጂ መላውን ቤተክርስቲያን የምትወክል እንዳልሆነች ለማብራራት ሞከርኩ። ነገር ግን እኔ አንዲት ቃል ከመናገሬ በፊት፣ እርሷ መናገር ጀመረች።
‘’ያማረ ነበር፣’’ አለች።
እኔም ተደነቅሁኝ።
እርሷም በመቀጠል፣ ‘’ሰዎች በቤተክርስቲያናችሁ አንዱ ለአንዱ ባለው የአክብሮት ስሜት ተመስጫለሁ። ሁሉም ከተለያየ መደብ የመጡ ይመስላል፣ ይህም ሆኖ በእርግጥም ከልብ እንደሚዋደዱ ግልጽ ነው። እኔም ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑ እንዲመስል የሚፈልገው እንዲህ ነው ብዬ አስባለሁ።”
እኔም ስለፈረጅ አመለካከቴ ፈጥኜ ንሰሃ ገባሁ። እኔም ጓደኛዬን ለማስገረም ፈልጌ የነበረው ፍጹም የሆነ መልክ ባላቸው ስብሰባዎች ነበር። ነገር ግን የዚህች ቤተክርስቲያን አባላት አሳክተው የነበረው የፍጹም ልብ የፍቅር መንፈስ፣ ደግነት፣ ትእግስት፣ እና ርህራሄ ነበር።
“ይህም እምነት በምድር ይበዛ ዘንድ ነው”
ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፣ ውድ ጓደኞቼ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እወዳለሁ። ይህች የአዳኙ እውነተኛ እና ህያው ቤተክርስቲያን ናት፣ እናም ዳግም የተመለሰውን የኢየሱስ ክርስቶስን የሙላት ወንጌል የምታስተምር ናት። የእርሱ የክህነት ሀይል እና ስልጣን በዚህ አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ቤተክርስቲያን ራሱ ይመራታል፣ በተጠሩ እና በተፈቀደላቸው አገልጋዮች አማካኝነት፣ እና በሕይወት ባለ ነቢይ፣ እርሱም ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን አማካኝነት። እርሱ፣ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሰበሰቡ እና አለምንም ለዳግም ምጽአቱ ለማዘጋጀት ለኋለኛው ቀን ቅዱሳን የተለየ ተልእኮን ሰጥቷል። ይህ ሁሉ እውነት ስለመሆኑ ምስክርነቴን እሰጣለሁ።
ነገር ግን ብዙ ሰዎች የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲለማመዱ፣ እነርሱ ስለክህነት ስልጣን ወይም ስርአቶች ወይም ስለእስራኤል መሰባሰብ እያሰቡ እንዳልሆነ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። እነርሱ በአመዛኙ የሚያስተውሉት፣ ከሁሉም ነገር በላይ፣ ከእኛ ጋር ሲሆኑ ምን እንደሚሰማቸው እና እኛም አንዳችን ለአንዳችን ያለንን አክብሮት ነው።
ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፣” ብላል። ‘’በዚህም ደቀመዛሙርቴ መሆናችሁን ሁሉም ያውቃሉ።’’ በአብዛኛው፣ የአንድ ግለሰብ የመጀመሪያ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት የሚመጣው እርሱ ወይም እርሷ በኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት መካከል ፍቅር ሲሰማቸው ነው።
‘’እምነት … በምድር ያድግ ዘንድ’’ ቤተ ክርስቲያኑን ዳግም እንደመለሰ አዳኙ ተናግሯል። በመሆኑም፣ ብዙ ሰዎች የቤተ ክርስቲያናችንን ስብሰባዎች ይጎበኛሉ፣ አዳኙም በእርሱ ጠንካራ እምነት ኖሯቸው እንዲሄዱ ይፈልጋል! ጓደኞቻችን በእኛ መካከል የሚሰማቸው ፍቅር፣ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ይበልጥ የሚያቀርባቸው ይሆናል! ያም ሁልጊዜ በምንሰባሰብበት ያለን ቀላል ግብ ነው።
ማንም በኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ እምነትን፣ ወይም ለሰማይ አባት የበለጠ ቅርብ ለመሆን ሲሻ፣ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን ቤቱ ውስጥ እንዳለ ሊሰማው ይገባል። እነርሱን ወደ ስብሰባዎቻችን መጋበዝ ልክ ወደ ቤታችን እንደምንጋብዛቸው የተለመደ እና የሚገባ ሊሆን ይችላል።
ተመሳሳዩ እና እውነተኛው
አሁን፣ እኔ ተመሳሳዩን እየገለጽኩ እንደሆነ አስተውላለሁ። በዚህ ሟች ህይወት፣ ተመሳሳዩንን ለመለማመድ ያለን እድል የቀነሰ ነው። እናም ‘’ፍጹም እስከሆነው ቀን ድረስ’’ ምን ጊዜም ቢሆን በተመሳሳዩ እና በእውነተኛው መካከል ክፍተት ይኖራል። በመሆኑም ቤተክርስቲያን ፍጹም የሆነው ቀን እንደሆነ ካልተሰማን ምን ልናደርግ ይገባናል? ለየትኛውም አይነት ምክንያት፣ ቅርንጫፋችን ፍጹም እምነትን ወይም ፍቅርን ባላሳደገ ጊዜስ? ወይም ለዚያ የማንመጥን መስሎ በተሰማን ጊዜስ?
አንድ ልናደርገው የማይገባ ነገር ቢኖር፣ ተመሳሳዩ ላይ ተስፋ አለመቁረጥ ነው!
የመጽሐፈ ሞርሞን የርእስ ገጽ ይህንን አስፈላጊ ማስጠንቀቂያ ያካትታል፤ እንዲህም ይላል፣ ‘’ስህተቶች ካሉ፣ እነርሱ የሰዎች ስህተቶች ናቸው፤ በመሆኑም፣ የእግዚአብሔርን ነገሮች አትኮንኑ።’’
አንድ መጽሀፍ—ወይም አንድ ቤተክርስቲያን ወይም አንድ ግለሰብ— ‘’ስህተት’’ኖሮት የእግዚአብሔር ስራ ሊሆን ይችላልን?
የእኔ መልስ በሚያስተጋባ ሁኔታ አዎንነው!
ስለዚህ፣ እራሳችንን ለጌታ ከፍተኛ መመዘኛ ተጠያቂ የምናደርግ ከሆነ፣ አንዳችን ለአንዳችን እንዲሁ ትእግስትን እናሳይ። እያንዳንዳችን በእድገት ላይ ያለን ስራ ነን፣ እና ሁላችንም ለምናደርገው እድገት በአዳኝ ላይ የምንደገፍ ነን። ይህ እንደግለሰቦች ለእኛ እውነት ነው፣ እና ይህም በምድር የእግዚአብሔር መንግስት እውነታ ነው።
ጌታ እኛን ሲጋብዘን የእርሱ መንግስት ተካፋዮች እንድንሆን ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ገንቢዎች እንድንሆን ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡ “አንድ ልብ እና አንድ አዕምሮ“ እንዲሆኑ ይጠብቃል። እንዲሁም አንድ ልብ ለመሆን፣ የሚያስፈልገን ንጹህ ልብ፣ እና ያም ታላቅ የልብ ለውጥ እንደሚጠይቅ ነው።
ነገር ግን ያ ማለት ከእናንተ ጋር እንዲመሳሰል ልቤን መቀየር ማለት አይደለም። እናንተም፣ ልባችሁ ከእኔ ጋር እንዲመሳሰል መቀየር ማለትም አይደለም። ይህ ማለት ሁላችንም ከአዳኙ ጋር እንዲመሳሰል ልባችንን መቀየር ማለት ነው።
መካተት እና አባልነት
እና ምን ጊዜም የተካተታችሁ መስሎ የማይሰማችሁ ከሆነ፣ እባካችሁ ብቻችሁን እንዳልሆናችሁ እወቁ። ሁላችንም በክፍሉ ውስጥ እንደ እንግዳ ሆነን የመሰልንባቸው የህይወት አጋጣሚዎች አልነበሩምን? ይህ አይነቱ ተሞክሮ ከአንድ ጊዜ በላይ አጋጥሞኛል። የ11 አመት እድሜ እያለሁ፣ ቤተሰቦቼ ቤታቸውን ትተው እና ወዳልተለመደ አካባቢ ለመዛወር የተገደዱበት አጋጣሚ ነበር። ሁሉም ነገር እኔ ከለመድኩት የተለየ ነበር። እናም በአነጋገር ዘይቤዬ ለሌሎች ልጆች እኔ እነርሱ ከለመዱት የተለየሁ ነበርኩ። ጓደኝነት እና አባልነት እጅግ ባስፈለገኝ በዚያ ጊዜ፣ ብቸኝነት እና ያለቦታዬ የመሆን ስሜት ተሰማኝ።
እዚህ ምድር ላይ፣ አብዛኛውን ጊዜ የምናስተውላቸው ልዩነቶች—አንዳንዶች አንዳቸው ለአንዳቸው የሚሰጡት መስፈርት—ከምድራዊ ነገሮች ጋር የተገናኘ ነው፤ አካላዊ ገጽታ፣ ዜግነት፣ ቋንቋ፣ አለባበስ፣ ልምዶች፣ እና የመሳሰሉት። ነገር ግን ‘’እግዚአብሔር ነገሮችን ሰዎች እንደሚያዩአቸው አያይም። ሰዎች ውጫዊ ገጽታን ይመለከታሉ፣ ነገር ግን ጌታ ልብን ይመለከታል።’’
ከእርሱ እይታ አንጻር፣ ከሌሎች መስፈርቶች ሁሉ የሚቀድም አንድ ነገር አለ፤ የእግዚአብሔር ልጅ። ሁላችንም በዚህኛው ውስጥ በፍጹምነት እንካተታለን።
በአነጋገራቸው፣ በድርጊታቸው፣ እና በአስተሳሰባቸው እንደእኛ ከሚመስሉት ጋር መሆን ተፈጥሯዊ ነው። ለዚያም ስፍራ አለው።
ነገር ግን በአዳኙ ቤተክርስቲያን ውስጥ፣ ለመሰባሰብ እና እውነትን ለመፈለግ ፈቃደኞች የሆኑትን የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ እንሰባስባለን። አንድ የሚያደርገን አካላዊ መልካችን፣ የፖለቲካ አመለካከታችን፣ ባህላችን ወይም ዘራችን አይደለም። እኛን ያጣመረን የጋራ ማንነት አይደለም። ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለን ቁርጠኝነት እና ለተመለሰው ወንጌሉ ይህ የጋራ ግባችን ነው እኛ ‘’በክርስቶስ አንድ ነን።’’
እኛ የምንሻው አንድነት ሁሉም ሰው በአንድ ስፍራ እንዲቆም ሳይሆን፤ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ወደሆነ አንድ አቅጣጫ—ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ—እንዲመለከት ነው። እኛ አንድ ነን፣ ይህም ከነበርንበት የተነሳ ሳይሆን ነገር ግን ልንሄድ ከምንጥርበት የተነሳ ነው፣ ከአሁን ማንነታችን ሳይሆን ማንን ለመሆን ከምንሻው የተነሳ ነው።
እውነተኛው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ማለት ያ ነው።
አንድ አካል።
እግዚአብሔርን የምትወዱ ከሆነ፣ ልጁን በመከተል እርሱን ይበልጥ ለማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ፣ አባልነታችሁ እዚህ ነው። በቅንነት የአዳኙን ትእዛዛት ለመጠበቅ የምትሹ ከሆነ—ምንም እንኳ በእርሱ አሁንም ፍጹም ባትሆኑ—እናንተ ለኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፍጹም የተስማማችሁ ናችሁ።
እና በዙሪያችሁ ካሉት ሰዎች የተለያችሁ ከሆናችሁስ? ያ ተስማሚ ያልሆናችሁ አያደርጋችሁም—የክርስቶስ አካል ተፈላጊ ክፍል ያደርጋችኋል። ሁሉም በክርስቶስ አካል ውስጥ ተፈላጊዎች ናቸው። ጆሮዎቻችን አይኖቻችን ሊመለከቱ የማይችሏቸውን ያስተውላሉ። እግሮቻችን እጆቻችን በውጤታማነት የማያደርጓቸውን ነገሮች ያደርጋሉ።
ያ ማለት ስራችሁ ሰዎችን ሁሉ እንደ እናንተ መቀየር ማለት አይደለም። ነገር ግን ልታበረክቱት የምትችሉት አንዳች አስፈላጊ ነገር አለ ማለት ነው—እና እናንተም የምትማሩት አስፈላጊ ነገር አለ!
አንድ ድምፅ
በሁሉም የአጠቃላይ ጉባኤ ክፍለ ጊዜ፣ ተሰጥኦ ባላቸው ዘማሪዎች በሚያነሳሱ ዝማሬዎች እንባረካለን። በምታደምጡበት ጊዜ፣ ዘማሪዎቹ ሁሉም አንድን አይነት ኖታ እንደማይዘምሩ ታስተውሉ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ አንዱ ክፍል የሙዚቃውን ቃና ሲከተል፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሌላኛውን። ነገር ግን ሁሉም ውብ ለሆነው ድምጽ አስተዋጸኦ ያደርጋሉ፣ እና በተሟላ ሁኔታ የተዋሃዱ ናቸው። እያንዳንዱ የዝማሬ አባል ተመሳሳይ የሆነ ማእከላዊ ግብ አለው፤ እግዚአብሔርን ማሞገስ እና ልባችንን ወደ እርሱ ማነሳሳት። እያንዳንዱ በአንዱ መለኮታዊ አላማ ላይ ልቡን ወይም ልቧን ማጣመር ይኖርባቸዋል። ኣና ያ ሲሆን፣ በእውነትም አንድ ድምጽ ይሆናሉ።
የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ካልሆናችሁ፣ በአዳኙ ‘’የቤዛነት ፍቅር ዝማሬ’’ እየተደሰትን እያለ እንድትቀላቀሉን እንጋብዛችኋለን። እንፈልጋችኋለን። አንወዳችኋለን። ቤተክርስቲያኗ በእናንተ ጥረት ጌታን እና የእርሱን ልጆች ለማገልገል የተሻለች ትሆናለች።
‘’ወደ እግዚአብሔር መንጋ ለመምጣት፣ እና የእርሱ ህዝብ ለመባል፣’’ በጥምቀት አማካይነት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳንን በመግባት ፍላጎታችሁን አሳይታችሁ ከሆነ፣ አዳኙ የኋለኛው ቀን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንድትሆን በሚፈልገው መንገድ ለመርዳት በዚህ ታላቅ እና መለኮታዊ ስራ ስለተሳተፋችሁ እናመሰግናችኋለን።
በጀርመን ካለችው ጓደኛዬ እንደተማርኩት፣ እኛ ለእግዚአብሄር እና ለልጆቹ ያለን ፍቅር ይህች በእውነት የአዳኙ ቤተክርስቲያን እንደሆነች ለአለም ሃያል የሆነ ምስክርነት ነው።
ሁሉም የእርሱ ደቀመዛሙርት መሆናችንን ያውቅ ዘንድ-አዳኛችን፣ ታዳጊያችን፣ እና መምህራችን ባስቀመጠልን መንገድ ለመኖር እንድንሻ እግዚአብሔር በትእግስት ነገር ግን በትጋት ይባርከን። ቅዱስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።