ስለ ክርስቶስ እንናገራለን
እኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን ስለዚህም ብርሃኑን ለመቀበል እና ለማጋራት እንሻለን።
መግቢያ
ረጅም ጊዜ በቆየንበት የውጪ ሃገር የሥራ ምድባችን መጨረሻ ላይ እኔና ባለቤቴ ሌሳ ወደ አገር ቤት ለመመለስ አመቺ ባልሆነ ሰዓት ለሚደረግ አንድ ተጨማሪ በረራ ለመዘጋጀት ወደ አንድ አየር ማረፊያ ተርሚናል ገባን። ከብዙ ሰዎች ጋር በተንጓተተ ሠልፍ ላይ እየሄድን ሣለን ለበረራው በጊዜ ስለመድረሥ፣ ስለፓስፖርት እና ስለቪዛ ቁጥጥር እንዲሁም የደህንነት ፍተሻዎችን በተሳካ ሁኔታ ስለማለፍ የሚጨነቁ ተጓዦች እያደገ የሚሄድ ጭንቀት ተሰማን።
በመጨረሻም በክፍሉ ውስጥ ያለው ከፍተኛ ውጥረት እና ጭንቀት ተፅዕኖ ያላደረገባት የምትመሥል የጉምሩክ ሠራተኛ ወዳለችበት ክፍል ደረስን። እሷም በዘልማድ ቀና ብላ ሣታየኝ፣ ዶክመንቶቼን ወሠደች፣ ፎቶግራፌን አረጋገጠች፣ ከአንዱ ገጽ ወደሌላው በአውራ ጣቷ ገለጠች በመጨረሻም ማህተሙን ፓስፖርቴ ላይ በከባድ ምት አሣረፈች።
ከዚያም የሌሳን ሠነዶች ወሠደች። ምንም ዓይነት ስሜት ሣይታይባት አጎንብሣ ትኩረቷን ሥራዋ ላይ በማድረግ ከፊት ለፊቷ ባሉት ሠነዶች ዝርዝር ነገሮች ላይ በማተኮር በባለሙያ ዓይን ገጾቹን በዘዴ ገለጥ ገለጥ አደረገች። በድንገት አቁማ ጭንቅላቷን ቀና አድርጋ በታሠበበት እና ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ከሌሳ ጋር ዓይን ለዓይን ስትተያይ ትንሽ ተደነቅን። የሌሳን ፓስፖርት ፈገግ ብላ በእርጋታ ማህተም ካደረገች በኋላ ሠነዶቹን መልሣ ሰጠቻት። ባለቤቴም በምላሹ ፈገግ በማለት ሠነዶቹን ተቀበለች እንዲሁም ሞቅ ያሉ የመሠነባበቻ ቃላት ተለዋወጡ።
“አሁን ምንድን ነው የሆነው?” ማመን እንዳልቻልኩኝ በሚጠቁም ሁኔታ ጠየቅኩኝ።
ከዚያም ሌሳ ሠራተኛዋ ያየችውን አሳየችኝ—እሱም የአዳኙ ምስል ያለበት ትንሽ ካርድ ነበር። በድንገት ከሌሳ ቦርሳ ወድቆ ወደ ፓስፖርቷ እጥፋት ውስጥ ገብቶ ነበር። የጉምሩክ ሠራተኛዋ አግኝታው የነበረው ይህንን ነበር። መላ ባህርይዋን የቀየረው ይህ ነበር።
Grace and Truth በሣይምን ዲዊ፣ በ altusfineart.com፣ © 2025፣ በፍቃድ ጥቅም ላይ የዋለ።
ይህች ትንሽ የአዳኙ ምሥል እነዚህ የማይተዋወቁ ሠዎች የሚተዋወቁ እንደሆኑ እንዲሠማቸው ረዳቻቸው። የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን ውበት፣ ተዓምራት እና እውነት በመያዝ ለሌሎች ሠዎች ሥሜት ግድ የሌለበትን ግንኙነት የሠውን ሥሜት የሚረዳ ወደመሆን ለወጠችው። በዚያ ቀን በቀሪው ጊዜ እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ያንን አስደሣች፣ ቀላል ጊዜ በአድናቆት አስበዋለሁ እንዲሁም የክርስቶስ ብርሃን በእግዚአብሔር ልጆች ላይ በሚያስከትለው አስደናቂ ውጤት ተደስቻለሁ።
ስለ ክርስቶስ እንናገራለን
እኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን ስለዚህም ብርሃኑን ለመቀበል እና ለማጋራት እንሻለን። በቤተክርስቲያኗ ሥም በግልፅ እንደተመለከተው “ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የማዕዘን ድንጋይ ነው” የሚለው የሃይማኖታችን የሥነ መለኮት ትምህርት ነው። በጥንት ጊዜ በነበሩ እና በሕይወት ባሉ ነቢያት በኩል የሰማይ አባታችን “እርሱን እንድንሰማው!” እና “ወደ ክርስቶስ እንድንመጣ” አዝዞናል። “ስለክርስቶስ እንናገራለን፣ በክርስቶስ እንደሠታለን፣ ስለክርስቶስ እንሠብካለን፣ [እንዲሁም] ስለክርስቶስ ትንቢት እንናገራለን።
ኢየሡስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ እና በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ኢየሱስ ወንጌሉን እንዳስተማረ እንዲሁም ቤተክርስቲያኑን እንዳቋቋመ እናስተምራለን
የምንመሰክረውም ኢየሱስ በህይወቱ መጨረሻ ላይ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ መከራን በተቀበለ፣ በመስቀል ላይ በተሰቀለ፣ ከዚያም ትንሣኤን ባገኘ እና ከሞት በተነሳ ጊዜ የኃጢአት ክፍያችንን እንደከፈለ ነው።
በአዳኙ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት ምክንያት ንስሀ በምንገባባበት ጊዜ ይቅር ልንባል እና ከኃጢአታችን ልንነፃ ስለምንችል እንደሠታለን። ይህ ሰላምን እና ተስፋን ያመጣልናል እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር መገኘት እንድንመለስ እና የደስታን ሙላት እንድንቀበል ያስችለናል።
በኢየሱስ ትንሳኤ ምክንያት ሞት የመጨረሻው ሳይሆን ወደፊት የሚያራምድ አንድ ጠቃሚ እርምጃ እንደሆነ እንተነብያለን። “ከሞትን በኋላ ሁላችንም ከሞት እንነሣለን። ይህ ማለት የእያንዳንዱ ግለሠብ መንፈስ እና አካል እንደገና ተገናኝተው ለዘላለም ይኖራሉ ማለት ነው።”
ወደ ክርስቶስ ኑ
እኛን ለማስተማር እና ለመምራት ከእግዚአብሔር መገለጥን የሚቀበሉ በዘመናችን በሕይወት ያሉ ነቢያት ወደ ክርስቶስ እንድንመጣ እየጋበዙን ይገኛሉ። ልባችንን፣ ጆሮአችንን እና ዓይኖቻችንን የበለጠ በእርሱ ላይ እንድናተኩር እየረዱን ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እናተኩር ዘንድ በቀዳሚ አመራር የተቀየሡ እና የተዋወቁ በርካታ ማስተካከያዎችን እና ማሻሻያዎችን እንደምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
-
“የሞርሞን ቤተክርስቲያን” የሚለውን ስም ለመተው እና የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በሚለው በትክክለኛው ሥም ለመተካት የተላለፈው ውሳኔ።
-
የወጣት ሴቶች እና የወጣት ወንዶች ጭብጦች እና እንደ “የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነኝ” እና “ክርስቶስን ተመልከቱ” ያሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮሩ ሙዚቃዎች።
-
የኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ እና ቃል በቃል የተከናወነውን ትንሳኤ፣ በታሪክ ውስጥ እጅግ የከበሩ ክስተቶች አድርጎ የበለጠ ትኩረት መሥጠት
-
ትንሳኤን እንደ አንድ ቀን በዓል ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማተኮር ለአንድ ሰሞን ማክበር።
አንዳንዶቹ ያሳደሩትን ተፅእኖ በጥልቀት እንመርምር። በመጀመሪያ የቤተክርስቲያኗ ምልክት።
የቤተክርስቲያኗ ምልክት
በ 2020(እ.አ.አ)ፕሬዚዳንት ኔልሰን የቤተክርስቲያኗን አዲስ የምስል መለያ አስተዋወቁ፡፡ ይህ ምልክት ክርስቶስ የእርሡ ቤተክርስቲያን ማዕከል እንደሆነና የህይወታችንም ማዕከል መሆን እንዳለበት ያሳያል። አሁን ይህን የተለመደ ምልክት በቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃድ፣ በቤተክርስቲያኗ ድረ ገጾች እና መጽሔቶች ላይ፣ በቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃድ ላይ፣ በወንጌል ላይብረሪ መተግበሪያ ምልክት ላይ እና ሌላው ቀርቶ በጦር ሰራዊት ውስጥ በሚያገለግሉ የቤተክርስቲያኗ ብዙ አባላት ወታደራዊ መታወቂያ መለያዎች ላይ እናየዋለን። ምልክቱም ኢየሱስ ክርስቶስ የማዕዘን ራስ ድንጋይ መሆኑን እንድናስታውስ የሚያደርግ በካምቦዲያ እና በ145 ቋንቋዎች ጥቅም ላይ የዋለውን በእዚህ የማዕዘን ድንጋይ ውስጥ የሚገኘውን የቤተክርስቲያኗን ስም ያካትታል።
በምልክቱ መካከል የአልበርት ቶርቫልድሰን ክርስተስ የተሠኘ ተወዳጅ የእምነበረድ ሐውልት የሚገኝ ሲሆን ከቤተክርስቲያኗ ጋር በስፋት እየተያያዘ ነው እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የጎብኚዎች ማዕከላት እና የቤተመቅደስ ግቢዎች ውስጥ ይገኛል። በቤተክርስቲያኗ ምልክት ውስጥ በጉልህ የሚታይ መሆኑ ክርስቶስ የምንሰራው ነገር ሁሉ ማዕከል መሆን እንዳለበት ይጠቁማል። ለማቀፍ የተከፈቱት ክንዶቹ ጌታ ወደ እርሱ የሚመጡትን ሁሉ ለመቀበል የገባውን ቃል ኪዳን ያሳያል። ይህ ምልክት የአዳኙ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ምስላዊ መግለጫ ሲሆን ሕያው የሆነውን ክርስቶስን ያለማቋረጥ የሚያስታውስ ነው።
ለማወቅ ከነበረኝ ጉጉት የተነሳ የቤተክርስቲያኗ ምልክት አንድ አስፈላጊ አካል ምን እንደሆነ ብዙ ቤተሰቦችን እና ጓደኞቼን ጠይቄ ነበር። በሚገርም ሁኔታ ብዙዎች የያዘውን የተቀደሰ ገፅታ አያውቁትም። ኢየሱስ ክርስቶስ የቆመው ከቅስት ሥር ነው። ይህ ከመቃብር እየወጣ ያለውን ከሞት የተነሳውን አዳኝ ይወክላል። በቤተክርስቲያኗ ምልክትም ጭምር ከሙታን የተነሣውን ሕያው ክርስቶስን እናከብራለን።
የላቀ የተቀደሠ ትንሣኤ
አሁን የትንሣኤን አስፈላጊነት እናስብ። ትንሣኤን አስመልክቶ በተሠጠ የቅርብ ጊዜ የቀዳሚ አመራር መልዕክት “የእርሱን ትምህርቶች በማጥናት እና በመላው ህብረተሰባችን በተለይም በቤተሰባችን ውስጥ የትንሣኤ ባህልን ለማቋቋም በመርዳት የሕያው አዳኛችንን ትንሣኤ ማክበር [እንዳለብን]” ተነግሮናል። ባጭሩ ወደላቀ እና የተቀደሰ የትንሣኤ በዓል እንድንሸጋገር ተበረታተናል።
ትንሣኤን አስመልክተው የሚመጡትን መገለጦች እወዳቸዋለሁ እንዲሁም ትንሣኤን ቅዱስ የሆነ እና የተቀደሰ ወቅት ለማድረግ ላሣያችሁት ብዙ ጥረቶች ደስተኛ ነኝ። በትንሣኤ ዕለት በሚውለው እሁድ የአንድ ሰአት የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ከማድረግ በተጨማሪ ሊደረጉ የሚችሉ ሌሎች ብቁ የሆኑ ተግባራት ምሳሌዎች በአጥቢያ እና በካስማ አምልኮዎች እንዲሁም በሆሣዕና በዓል እና በሰሙነ ሕማማት ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ያካትታሉ። እነዚህ አከባበሮች ከልጆች እና ከወጣቶች ጋር የሚደረጉ አክቲቪቲዎችን ያካትታሉ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከተለየዩ የእምነት ተቋማት የመጡ ሃይማኖቶች መዘምራንን ያካትታሉ። ሌሎች ደግሞ የህያው ክርስቶስ የጉብኝት ክፍለ ጊዜን ለአባላት እና ለጓደኞቻቸው ክፍት ያደረጉ ሲሆን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያካትቱ የትንሳኤ ዝግጅቶችን አካሂደዋል።
እንደዚህ ያሉ አክቲቪቲዎች አዳኙ በድል በገባበት ወቅት ድምፃቸውን በአንድነት በማድረግ ያወደሡትን በኢየሩሳሌም ከተማ የነበሩትን ህዝቦች ያንፀባርቃሉ። ይህን በጣም አስፈላጊ የሆነ በዓል ለማክበር እንደ ቤተሰብ በቤት እንድታመልኩ የቀዳሚ አመራር ላቀረቡት ግብዣ የሰጣችሁት ምላሽ ሪፖርቶችም እንዲሁ አስደናቂ ናቸው።
ትንሣኤን አስመልክቶ የሚደረገው የቤተሰብ አምልኮ በሚያስደንቅ ሁኔታ ከፍ እንዳለ አምናለሁ። ከሁለት አመት በፊት፣ ቤተሰባችን ትንሣኤን የሚያከብርበትን መንገድ ለማሻሻል ስላለው ቁርጠኝነት ተናግሬ ነበር። ይህ አሁንም በሂደት ላይ ያለ ነገር መሆኑን እቀበላለሁ። ልዩ የሆነ የትንሣኤቀን ምግብ፣ የትንሳኤ ቅርጫቶች እና የፋሲካ የእንቁላል አደን ሁሌም ያስደስተናል፣ ስለዚህም አሁንም እንደዚያ እናደርጋለን። ነገር ግን፣ በዓሉን ስናከብር ሆን ብለን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በኃጢያት ክፍያው ላይ የሚያተኩር መንፈሳዊ ነገር መጨመራችን እጅግ ቅዱስ ለሆኑት ለእነዚህ ዝግጅቶች አከባበር አስደሣች ሚዛን አምጥቷል።
ይህ ዓመት፣ ትንሣኤ ይበልጥ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ለማድረግ ሦስተኛው ሙከራችን ይሆናል። ልክ እንደ ገና በዓል የቤተሰባችን የፋሲካ ቀን ጨዋታ ከአዲስ ኪዳን እና ከመፅሐፈ ሞርሞን ቅዱሳት መጻህፍትን ማንበብን፣ ሙዚቃን፣ የትንሣኤ ምስሎችን፣ የዘንባባ ዝንጣፊዎችን እና ሙሉ ለሙሉ እውነት ለመናገር ትንሽ ትርምስን ያካትታል። ልጆች እና የልጅ ልጆች የሆሳዕና እሁድ ምስጋና የሆነውን “ሆሳዕና … በጌታ ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፤ ሆሳዕና በዓርያም” እና “ይህ ከገሊላ … የመጣ … ኢየሱስ ነው” ማንበብ “ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” የሚለውን ከማንበብ ጋር ተቀባይነት ያለው ይመስላል።
አሁን በተለያዩ ማስዋቢያዎች እንደሠታለን። በአንድ ወቅት ጥንቸሎች እና የትንሳኤ እንቁላሎች ብቻ በሚባል ደረጃ የሚከበረው አሁን በክርስተስ እና በባዶ መቃብር፣ ከሞት የተነሳውን አዳኝ ከመቃብሩ ውጭ ባለው የአትክልቱ ስፍራ በሚያሣይ እና አዳኙ ለኔፋውያን ተገልጦ በሚያሣዩ ምስሎች ሚዛኑን የጠበቀ ነው። ትንሣኤ የአንድ ቀን በዓል ከመሆን ይልቅ የአንድ ሠሞን አከባበር እንዲሆንም እየጣርን ነው። የሆሣዕናን በዓል እና የሥቅለትን ቀን እንዲሁም በመላው ሠሙነ ሕማማት ስለተከናወኑት ቅዱስ ክስተቶች የበለጠ ለመነጋገር፣ ለማሰብ እና ለማክበር እየሞከርን ነው።
ትንሣኤ፣ የኢየሡስ ክርስቶስን የሃጢያት ክፍያ መስዋዕት እና ቃል በቃል የተከናወነውን የእርሱን አስደሣች ከሞት መነሣት ሁለቱንም እንድናከብር ያስችለናል። በአትክልቱ ሥፍራ እና በቀራንዮ ላይ የነበረውን የአዳኙን ሥቃይ በምናስብበት ጊዜ ልባችን ያዝናል፣ ነገር ግን ባዶውን መቃብር ስንመለከት እና “እርሱ ተነስቷል!” የሚለውን ሰማያዊ አዋጅ ስንሰማ ልባችን ደስ ይለዋል።
ቃል በቃል የተከናወነ ትንሣኤ
ቀዳሚ አመራር “ለሰው ልጆች ከተላለፉት መልዕክቶች ሁሉ እጅግ የከበሩትን ፋሲካን እና የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ ጠብቁ” ሲሉ የሠጡት የቅርብ ጊዜ ማበረታቻ የዚህን ወቅት ታላቅነት ያጎላል። በተለያዩ የክርስትና የነገረ መለኮት ምሁራን ዘንድ ትንሣኤን እንደ ምልክትና ምሳሌያዊ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ “ትንሣኤ ማለት እስከዛሬ በሕይወት የኖሩት ሁሉ ይነሳሉ፣ ትንሣኤያቸው ደግሞ ቃል በቃል የሚፈፀም ነው” የሚለውን ትምህርታችንን እናረጋግጣለን። “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።” አዳኙ የእያንዳንዱን ሕያው ነፍስ የሞት እስር ይበጥሣል።
ኢየሱስ ባቀረበልን ፍቅር ላይ በመገረም እንቆማለን። “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም”ሲል የሠጠውን ቃል እንቀበላለን።
ሲ. ኤስ. ሌዊስ እንደተናገረው፣ “ክርስትናን መስበክ ማለት [ለሐዋርያት] በዋነኝነት ትንሳኤን መስበክ …ማለት ነው። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ በተዘገበው በእያንዳንዱ የክርስቲያን ስብከት ውስጥ ትንሣኤ ዋናው ጭብጥ ነው። ትንሣኤና ውጤቶቹ ክርስቲያኖች ያመጡት ‘ወንጌል’ ወይም የምሥራች ነው።”
“ትንሳኤ አለ፣ … ሞት ድል አይኖረውም፤ እናም የሞት መውጊያ በክርስቶስ ተውጧል።”በማለት አውጃለሁ።
መደምደሚያ እና ምስክርነት
ሳጠቃልለው፣ ትንሳኤን የሚወክሉትን የተቀደሡ ዝግጅቶች ይበልጥ ሆን ብለው እንዲያከብሩ ከህያው ነቢያችን እና ከአማካሪዎቹ የቀረበላቸውን ግብዣ የሚቀበሉ ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸው ትስስር ይበልጥ እየጠነከረ እንደሚሄድ እመሰክራለሁ።
የመቃብሩን፣ መቃብሩን የሸፈነውን ድንጋይ፣ የኢየሱስን፣ የማርያምን፣ የደቀ መዛሙርቱን እና የመልዓኩን ቀላል ምሥል በመጠቀም የትንሣኤን ታሪክ በቃል ለማስታወሥ ከአራት ዓመት የልጅ ልጇ ጋር ስለተለማመደች አንዲት አያት ከቀናት በፊት ሠማሁኝ። ትንሹ ልጅ፣ አያቱ ቀብሩን፣ የመቃብሩን መዝጊያና መክፈቻ እንዲሁም በአትክልት ሥፍራው የተካሄደውን የትንሳኤውን ክንውን ስታካፍል በትኩረት እየተመለከተ እና እያዳመጠ ነበር። ከዚያም ምሥሎቹን እራሱ በማንቀሳቀስ፣ በሚያስገርም ሁኔታ ታሪኩን በጥንቃቄ ለወላጆቹ ደገመው። ከዚህ አስደሣች ጊዜ በኋላ፣ ፋሲካ ለምን እንደምናከብር ተጠየቀ። ልጁ ቀና ብሎ ተመለከተና ህፃናት በሚሠጡት አመክንዮ መንገድ “ምክንያቱም ስላለ ነዋ ” ሲል መለሰ።
እርሱ እንደተነሣ እና ሕያው እንደሆነ በእርሱ፣ በእናንተ እና በመላዕክት እንዲሁም በነቢያት ምስክርነት ላይ የእኔን ምስክርነት እጨምራለሁ፣ ይህንንም የምመሠክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።