አጠቃላይ ጉባኤ
የእኛ ሰማያዊ የምሪት ስርዓት
የሚያዝያ 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:48

የእኛ ሰማያዊ የምሪት ስርዓት

ሕይወታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስናተኩር እስከመጨረሻው እየጸናን እና እየተደሰትን ወደቤት የምንመለስበትን መንገድ እናገኛለን።

በምወደው ፍሩቲላር፣ ቺሌ ውስጥ በ26 ዓመቴ በተጠመኩበት ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቴን ለወጠው። በዚያ ሰአት ሥራዬ ውቅያኖሱን፣ ወንዞችን እና ውብ የሆነውን የቺሊ ፓታጎንያ ሀይቆችን አቋርጦ ወሰደኝ። ከተጠመኩ በኋላ፣ በእውነትም “ሁሉም ነገሮች እግዚአብሔር መኖሩን እንደሚያመለክቱ፣” በመገንዘብ ሥራዬንና ሕይወቴን በአዲስና በተለየ መንገድ ተመለከትኩ።

በተፈጥሮ፣ ሳልሞን የተባሉት የአሳ ዝርያዎች፣ እንቁላላቸው የሚፈለፈለው በወንዞች ምንጭ ውስጥ ነው። በሕይወታቸው ውስጥ በተወሰነ አንድ ወቅት ላይ፣ ለዕድገታቸው አስፈላጊ የሆኑ ምግቦችን እና ሁኔታዎችን ወደሚያገኙበት ወደ ውቅያኖሱ ለመድረስ ከወንዙ በታች መዋኘት ያስፈልጋቸዋል።

ነገር ግን ውቅያኖሱ አዳኞች የሚደበቁበት እንዲሁም በሚያንጸባርቁ መንጠቆዎች ላይ ምግብ የሚመስሉ ነገር ግን ለእድገታቸው የማይጠቅሙ ምግቦችን እላያቸው ላይ በማንጠልጠል ሳልሞኖችን ለመያዝ የሚሞክሩ ዓሣ አጥማጆች ያሉበት ቦታ ነው። ሳልሞኖቹ ከእነዚህ አደጋዎች መትረፍ ከቻሉ፣ ኃይለኛ የመመሪያ ስርዓታቸውን በመጠቀም አዲስ እና አንዳንድ የተለመዱ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ፣ ወደተፈለፈሉበት ቦታ ለመመለስ ዝግጁ ይሆናሉ። ሳይንቲስቶች የስደት ባህሪያቸውን ለዓመታት ካጠኑ በሃላ ከጂፒኤስ ጋር የሚመሳሰል፣ እንደ ማግኔት አይነት ካርታ ወደ መጨረሻ መዳረሻቸው በሚያስገርም ሁኔታ በትክክል እንደሚመራቸው ደርሰውበታል።

አንድ ቀን ሁላችንም ወደመጣንበት ወደ ሰማያዊው ቤታችን መመለስ እንችላለን። እንዲሁም ልክ እንደ ሳልሞኑ የአሳ ዝርያ፣ እኛን ለመምራት የሚያገለግል፣ እንደማግኔት አይነት የራሳችን ካርታ ወይም የክርስቶስ ብርሃን” አለን። ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን እንዲህ በማለት አስተምሯል፦ “እኔ መንገድና፣ እውነት ህይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”

ሕይወታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስናተኩር እስከመጨረሻው እየጸናን እና እየተደሰትን ወደቤት የምንመለስበትን መንገድ እናገኛለን። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “የሚሰማን ደስታ ከህይወታችን ሁኔታዎች ጋር ያለው ግንኘነት አነስተኛ ነው ነገር ግን በህይወታችን ውስጥ ትኩረት ከምንሰጣቸው ነገሮች ጋር ያለው ተዛምዶ ታላቅ ነው።”

የእኛ መለኮታዊ ተፈጥሮ እና ዘላለማዊ እጣ ፈንታ

ለአለም የተላለፈ የቤተሰብ አዋጅ ላይ፣ እያንዳንዳችን በሰማይ ወላጆች የተወደድን የመንፈስ ሴት እና ወንድ ልጆች እንደሆንን እንዲሁም እያንዳንዳችን መለኮታዊ ተፈጥሮ እና ፍጻሜ እንዳለን እናነባለን። … በቅድመ ምድራዊ ህይወት ውስጥ፣ የመንፈስ ወንድ እና ሴት ልጆች እግዚአብሔርን እንደ ዘላለማዊ አባታቸው ያውቁት እና ያመልኩት ነበር፣ እንዲሁም ልጆቹ ስጋዊ አካልን አግኝተው ምድራዊ ልምዶችን በማግኘት ወደ ፍጹምነት ለማደግ እና በመጨረሻም መለኮታዊ እጣ ፋንታቸው የሆነውን የዘላለማዊ ህይወት ወራሽ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን አላማውን ተቀብለው ነበር

በሥጋ ከመወለዱ በፊት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አብን በመወከል ለሙሴ ተገልጦ አነጋግሮት ነበር። እርሡ የሚሠራው ታላቅ ሥራ እንዳለው ለሙሴ ነገረው። በተገናኙበት በዚያ ጊዜ፣ ጌታ ብዙ ጊዜ “ልጄ” ብሎ ጠራው።

ከዚያ ተሞክሮ በኋላ ሰይጣን ሊፈትነው እንዲህ በማለት መጣ፥ የሰው ልጅ ሙሴ ሆይ፣ አምልከኝ።

ሙሴ የራሱን መለኮታዊ ተፈጥሮ በማስታወስ ለዚያ ፈተና እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ “አንተ ማን ነህን? እነሆም እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ።” እውነታው ሙሴን ከጠላት ውጊያ ነጻ አወጣው።

ወንድሞች እና እህቶች፣ የሟችነት መንጠቆዎች እውን ናቸው! ብዙ ጊዜ የሚያታልሉ ናቸው፣ ነገር ግን አንድ ኢላማ ብቻ ይፈልጋሉ፣ ይህም እኛን ወደ አብ እና ወደ ዘላለማዊ ህይወት ከሚያመራው የሕይወት ውሃ መንገድ ለማውጣት ነው።

የሟችነት መንጠቆዎች ምን ያህል እውን መሆን እንደሚችሉ አውቃለሁ። አንድ እሁድ ዕለት፣ አዲስ የቤተክርስቲያን አባል ሆኜ በክህነት ክፍል እያስተማርኩኝ ሳለ እኔን የሚያሳዝን ውይይት በተማሪዎቹ መሃል ተነሳ። ትምህርቴን ለመጨረስ ተቸገርኩኝ። ተቀየምኩኝ እንዲሁም እኔ ተበዳይ እንደሆንኩኝ ተሰማኝ። አንድም ቃል ሳልናገር፣ ለተወሰነ ጊዜ ወደቤተክርስቲያን ላለመመለስ እያሰብኩኝ ወደውጪ ወደሚያስወጣው በር አመራሑኝ።

በዚያች ሰአት ነገሩ ያሳሰበው የክህነት ስልጣን ተሸካሚ ፊት ለፊቴ ቆመ። ፍቅር በተሞላ መልኩ፣ ትኩረቴን ክርስቶስ ላይ እንዳደርግ እንጂ ክፍሉ ውስጥ በተፈጠረው ነገር ላይ እንዳላደርግ ጋበዘኝ። ከእርሱ ጋር ወደነበረኝ ተሞክሮ ሳስብ፤ “ሒድ፣ ተከተለው እርሱ ለእኔ ወሳኝ ነው” የሚል ድምጽ ሰምቶ እንደነበር ነገረኝ።

ሽማግሌ ቫርጋስ እና ከእርሳቸው በኋላ የነበሩ መሪ።

ውድ ጓደኞቼ፣ እኛ ሁላችንም ለእርሱ ወሳኝ ነን። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦ “ከእግዚአብሔር ጋር በገባነው ቃል ኪዳን ምክንያት፤ እርሱ እኛን ለመርዳት በሚያደርገው ጥረት አይታክትም እንዲሁም ለእኛ ያለውን የምሕረት ትዕግሥቱን አናስጨርሰውም።” መለኮታዊ ተፈጥሮአችን እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለን የቃል ኪዳን ግንኙነት መለኮታዊ እርዳታን እንድንቀበል ያስችለናል።

የመመገብ አስፈላጊነት

ሳልሞን የተባለው የአሳ ዝርያ፣ ለማደግ በውቅያኖስ ውስጥ መመገብ እንዳለበት ሁሉ እኛም በመንፈሳዊ ምግብ እጦት እንዳንሞት ራሳችንን በመንፈሳዊ ነገሮች መመገብ አለብን። ጸሎት፣ ቅዱሳት መጻህፍት፣ ቤተመቅደስ እንዲሁም ዘወትር በእሁድ ስብሰባዎች ላይ መገኘት በመንፈሳዊ ነገሮች ዝርዝር ውስጥ በጣም አስፈላጊ ናቸው።

ህዳር 1956 (እ.አ.አ)፣ ሪካርዶ ጋርሲያ፣ በሓገሬ በቺሊ ውስጥ የቤተክርስቲያኗ የመጀመሪያ አባል በመሆን ተጠመቀ። ከመሞቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ በቤተሰቡና በጓደኞቹ ፊት እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ከብዙ ዓመታት በፊት ሚስዮናውያን ከቤተሰቤ ጋር ደስተኛ እንድሆን ጋብዘውኝ ነበር። እኔ ደስተኛ ሰው ነኝ። ለሁሉም ሰው ወንጌሉ ደስታ እንደሆነ ንገሩ።”

የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ከተመገበ በኋላ፣ ሪካርዶ መላ ህይወቱን እግዚአብሔርን እና ባልንጀራውን በፍቅር ለማገልገል ሰጠ። የእርሱ የደቀመዝሙርነት ምሳሌ እኔን ጨምሮ ትውልዶችን ባርኳል። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ሲል አስተምሮ ነበር፦ “በእግዚአብሔር ፍቅር የተሞላ ሰው፣ ቤተሰቡን በመባረክ ብቻ አይረካም፣ ነገር ግን በአለም ዙሪያ ያለውን የሰውን ዘር በሙሉ ለመባረክ በጉጉት ይዞራል።” (

ወደ ሰማያዊ ቤታችን ተመለሱ

በእያንዳንዳችን ውስጥ ወደ ሰማያዊ ቤታችን የመመለስ ፍላጎት አለ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም የሰማያዊ መመሪያ ስርዓታችን ነው። መንገዱ እርሱ ነው። የእርሱ የሓጢያት ክፍያ ከእግዚአብሔር ጋር ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን እንድንገባ አስችሎናል። ቃል ኪዳን ከገባን በኋላ አንዳንድ ጊዜ እራሳችንን አደገኛ የውሃ ግፊት ባለበት ስንዋኝ እናገኘዋለን። አደጋ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ፈተና እና መከራ እምነታችንን እና መንፈሳዊ ጥንካሬያችንን ይፈትናሉ። እርዳታን ጠይቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ይረዳልናል እንዲሁም ሸክማችንን ለመካፈል ሁልጊዜ ይጓጓል።

እርሱ “ህመምን እና ደዌን የሚያውቅ ሰው እንደሆነ” አስታውሱ። አዳኙ፣ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ሲል አስተምሯል። እርሱ ኃጢያታችንን እስከመርሳት ድረስ፣ በኃጢያት ክፍያው አማኻኝነት ይቅር መባል እንድንችል አድርጋል።

እነዚህን ሓጢያቶች መድገም እንደሌለብን ማስታወስ እንድንችል፣ በዚህ ምድራዊ ህይወት ውስጥ በምንማራቸው ትምህርቶች ውስጥ ኃጢያታችንን ሙሉ በሙሉ ላንረሳቸው እንችላለን። ከዚያ ይልቅ፣ እያንዳንዱ እሁድ በቤተክርስቲያን ቅዱስ ቁርባንን ስንወስድ እርሱን እናስታውሳለን። ይህ ሥርዓት የአምልኮ እና የመንፈሳዊ እድገት አስፈላጊ አካል ነው። ይህ አንድ ሌላ ቀን ብቻ እንዳልሆነ ስንረዳ ደስታ ይመጣል። “ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል” ይህም የሆነው፣ ከዓለም ዕረፍት ሊሰጠን እና ሥጋችንን እና መንፈሳችንን ለማደስ በማሰብ ነው።

እንዲሁም እርሱን ወደ ቤተመቅደስ—ወደ የጌታ ቤት ስንሄድ እናስታውሰዋለን። ቤተመቅደሶች ከእግዚአብሔር ስጦታዎች ሁሉ ታላቅ የሆነው፣ ወደ ዘለአለማዊ ህይወት የሚመራን የቃል ኪዳኑ ማእከል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይበልጥ ጠለቅ ያለ እውቀትን ይሰጡናል።

ወደቤተመቅደስ መሄድ መጽናናትን እና ዘለአለማዊ እጣፈንታችንን በተመለከተ ታላቅ ተስፋን ሰጥቶኛል። በመጋረጃው በሁለቱም በኩል ካሉት ሰዎች ጋር ሰማያዊ የሆነ ግንኙነቶች አጋጥመውኛል። በሰው ዘንድ ሊታዩ በማይችሉ ህመሞች ምክንያት ህይወታቸውን ሙሉ እንክብካቤ ይሹ በነበሩት፣ በትንሾቹ ሁለቱ ልጆቼ ህይወት ውስጥ ተአምራዊ ፈውሶችን አይቻለሁ።

የደህንነት እቅድን አስመልክተን በምናካፍልበት ወቅት ቤተሰባችን ይደሰታል። ልጆቼ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት “[ስቃያቸው] ለጥቂት ጊዜ ቢሆን እንደሆነ” ሲያውቁ ፊታቸው ያበራል። ልጆቻችንን በጣም እንወዳቸዋለን፣ እንዲሁም ፕሬዚዳንት ጄፍሪ አር ሖላንድ እንዳስተማሩት፣ “አንድ ቀን በፊታችን ከብረው እና አዲስ ሆነው፣ በአካል እና በአእምሮ ፍጹም በሆነ መንገድ ውብ ሆነው ፊት ለፊታችን ይቆማሉ።” ቃል ኪዳኖቻችን የማይቻለውን የሚቻል እንዲሁም እያንዳንዱን የጨለማ እና የጥርጣሬ ቦታ በብርሓን እና በሰላም በመሙላት ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ የቀረብን እንድንሆን ያደርጉናል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት፣ ማፍቀርን፣ መጸለይን እና የምናስብላቸውን ሰዎች መደገፋችንን ለመቀጠል ተስፋ እና በርከት ያሉ ምክንያቶች አሉን።

እርሱ ህያው እንደሆነ አውቃለሁ። እርሱ በግል ያውቀናል እንዲሁም ይወደናል። “እርሱ መንገድ፣ እውነት እና የዓለም ሕይወትነው።”

ዛሬ ሁላችንም “ሕይወታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በአስተምህሮቶቹ ላይ ማእከል እንድናደርግ እጋብዛችኋለሁ። ይህንን ማድረግ የፈተና፣ የቅያሜ እና ለራስ የማዘን ስሜትን መንጠቆ እንድናስወግድ ይረዳናል። እንደ ቤተመቅደሶች ቅዱስ፣ ፅኑ እና የማይለወጥ ሆነን እንቆማለን። ማእበሎቹን ተቃቁመን እስከመጨረሻው በመጽናት እና በመደሰት ወደቤት እንደርሳለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት መሐንዲስ ሆኜ ቺሊ ውስጥ የውሀ እርሻን በማልማት ሠርቻለሁ።

  2. አልማ 30፥44

  3. See Steve Lundeberg, “Magnetic Pulses Alter Salmon’s Orientation, Suggesting They Navigate via Magnetite in Their Tissue,” Oregon State University Newsroom, May 2, 2020, oregonstate.edu.

  4. ዮሐንስ 14፥6

  5. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ደስታ እና መንፈሳዊ ደህንነት፣” Liahona፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 82።

  6. ቤተሰብ፦ ለአለም የተላለፈ አዋጅ፣” የወንጌል ቤተመጽሐፍት

  7. ሙሴ 1፥4–13 ተመልከቱ።

  8. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ዘለአለማዊ ቃል ኪዳን፣” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2022 (እ.አ.አ)፣ 6።

  9. ዳለን ኤች. ኦክስ፣ “መንፈስን መመገብ፣” ኤንዛይን፣ ህዳር 1998 (እ.አ.አ)፣ 10‑19 ይመልከቱ።

  10. See Trent Toone, “Builders and Blessings: How Early Latter-day Saint Pioneers Shaped the Growth of the Church in Chile,” Church News, Feb. 18, 2025, thechurchnews.com.

  11. የሪካርዶ ጋርሲያ ሴት ልጅ ከሆነችው ከፔርላ ጋርሲያ ጋር የግል ቃለ መጠይቅ።

  12. Teachings of Presidents of the Church: Joseph Smith (2007), 426.

  13. ኢሳይያስ 53፥3

  14. ዮሐንስ 16፥33

  15. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፥42 ተመልከቱ።

  16. ኒል ኢል. አንደርሰን፣ “Repent … That I May Heal You፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2009 (እ.አ.አ)፣ 40–43 ተመልከቱ።

  17. ርዕሶች እና ጥያቄዎች፣ “ቅዱስ ቁርባን፣” የወንጌል ቤተመጽሐፍት ውስጥ ተመልከቱ።

  18. ማርቆስ 2፥27

  19. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ዘለአለማዊ ቃል ኪዳን”፣ 4–11።

  20. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 14፥7

  21. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥7

  22. ጀፍሪ አር. ሆላንድ፣“Like a Broken Vessel,” ሊያሆና፣ ህዳር 2013(እ.አ.አ.)፣ 42።

  23. ዕብራውያን 3፥6 ተመልከቱ።