አጠቃላይ ጉባኤ
መጽሐፈ ሞርሞን—የማይለካ የጉዞአችን ሃብት
የጥቅምት 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


9:47

መጽሐፈ ሞርሞን—የማይለካ የጉዞአችን ሃብት

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የሚገኙትን የክርስቶስን ቃላት ስንመገብ፣ መንፈስ ዘላለማዊ እውነቶችን እንድንረዳ ያግዘናል።

ህይወታችሁን የሚቀይር ስጦታ አንድ ሰው የሰጣችሁን ጊዜ ታስታውሳላችሁን። የአሁኑ ጥቅምት በህይወቴ ከተቀበልኳቸው ታላላቅ ስጦታዎች አንዱ የሆነውን 40ኛ ዓመት የማከብርበት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ፣ ከክፍል ጓደኞቻችን አንዱ ከሌሎች ወጣቶች ለየት ያለ ብርሃን እንደነበረው መመልከት ችያለሁ። ከእርሱ ጋር መሆን ያስደስተኝ ነበር። አንድ ቀን እርሱ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል መሆኑን ነገረኝ። ከዚያም አንድ ስጦታ ሰጠኝ፡ የመፅሐፈ ሞርሞን ቅጂ። ጥቂት ገጾችን እንዳነብ እናም ጥያቄዎቼን ሊመልሱልኝ ከሚችሉ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር እንድገናኝ ጋበዘኝ። እነዚያ ጓደኞቹ ሚስዮናውያን ነበሩ።

ሚስዮናውያኑንም ባገኘኋቸው ጊዜ፣ የክርስቶስን ትምህርት አስተማሩኝ እናም የነቢዩ ሞርሞንን ግብዣ እንድከተል ጋበዙኝ፤ “እናም እነዚህንም ነገሮች በምትቀበሉበት ጊዜ፣ እነዚህ ነገሮች ሀሰት እንደሆኑ ዘለዓለማዊ አብ እግዚአብሔርን በክርስቶስ ስም እንድትጠይቁት አጥብቄ እመክራችኋለሁ፤ እናም በቅን ልባችሁ፤ ከእውነተኛ ፍላጎት፣ በክርስቶስ አምናችሁ ከጠየቃችሁት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እውነቱን ይገልፅላችኋል” (ሞሮኒ 10፥4)።

ከመፅሐፈ ሞርሞን አያሌ ገጾችን አነበብኩ እና ጸለይኩ። ሚስዮናውያን እያስተማሩኝ የነበሩትን ነገሮች በጥልቀት ባልረዳቸውም፣ እያነበብኳቸው የነበሩት ነገሮች መልካም እና ከእግዚአብሄር የሆኑ መሆናቸው ተሰማኝ። እናም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሞሮኒን የተስፋ ቃል ተቀበልኩ፤ “እናም በመንፈስ ቅዱስ ሃይል አማካይነት የሁሉንም ነገሮች እውነተኛነት ታውቃላችሁ።” (ሞሮኒ 10፥5)

ወደ ኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከተጠመቅሁ በኋላ፣ አንዳንድ ጓደኞቼ ስህተተኛ የሆነን ውሳኔ እንዳደረግሁ ሊያሳምኑኝ ሞከሩ። ጥርጣሬ ወይም ተቃውሞ ባጋጠሙኝ ጊዜ ሁሉ፣ ቅዱሳት መጻሐፍትን በማንበብ እና ከእግዚአብሄር ጋር ለገባሁት ቃል ኪዳን እውነተኛ ሆኖ ለመቆየት በመጸለይ የታደሰ ማረጋገጫን አግኝቻለሁ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ መጽሀፈ ሞርሞን ጓደኛዬ በመሆን ቀጥሏል እና በምድራዊ ህይወት ጉዞዬ ሁሉ የማይለካ ሃብቴ ሊሆንልኝ ችሏል።

መጽሐፈ ሞርሞን ከመጽሀፍ በላይ ነው። በትንቢት እና በራእይ መንፈስ አማካይነት በአያሌ የጥንት ነቢያት የተጻፈ ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ነው።

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የተመዘገበው ታላቁ ድርጊት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ በኔፋውያን መካከል ያደረገው የግል አገልግሎት ነው። መጽሀፈ ሞርሞን “የወንጌልን ትምህርት ይገልፃል፣ የደህንነትን ዕቅድ ይዘረዝራል፣ እናም በዚህ ህይወት ሰላምን እንዲሁም በሚመጣው ህይወት ዘለዓለማዊ ደህንነትን ለማግኘት ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይናገራል” (የመጽሀፈ ሞርሞን መግቢያ) ።

የመጀመሪያው የመጽሐፈ ሞርሞን እትም፤ ሌላው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት በኒው ዮርክ ክፍለ ግዛት በአንዲት ትንሽ ከተማ መጋቢት 1830 (እ.አ.አ) ታተመ። በ1829 (እ.አ.አ) መጽሐፈ ሞርሞንን መተርጎም ባጠናቀቀ ጊዜ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ 23 ዓመት ብቻ ነበር። አጠቃላይ መጽሀፉን 75 ባልሞሉ ቀናት ውስጥ ተርጉሟል እናም የማተሙ ሂደት ሰባት ወራትን ፈጀ።

ዛሬ፣ በግምት 80000 የሙሉ ጊዜ ሚስዮናውያን ከ150 በላይ አገሮች ውስጥ በበጎ ፈቃድ እያገለገሉ ሲሆን መጽሀፈ ሞርሞን እውነት እንደሆነ እና ስለኢየሱስ ክርስቶስም የሚመሰክር መሆኑን በበመስከር ህይወታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በዚህ ዓመት በሰኔ ወር (እ.አ.አ) ለአዳዲስ ሚስዮን መሪዎች በተደረገ የቅርብ ሴሚናር ላይ ፕሬዚዳንት ራሰል ኤም. ኔልሰን ስለመጽሀፈ ሞርሞን ሃያል የሆነ ምስክርነታቸውን እንዲህ በማለት ሰጥተዋል፤ “መጽሀፈ ሞርሞን የእግዚአብሄር ቃል ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ያስተምራል እና ስለአዳኙ የሃጢያት ክፍያ ከሌላ ከማንኛውም መጽሀፍ በበለጠ ያብራራል።”

በመጽሐፈ ሞርሞን ጥናት አማካይነት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መለወጣችንን ጥልቅ ሊያደርጉ የሚችሉ ሶስት ሃሳቦችን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ፤

1. በእለት ተእለት ጥናታችሁ ትጉህ እና የማትሰለቹ ሁኑ

ልክ እንደ አልማ እና የሞዛያ ልጆች “የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ እንድንችል እና በእውነታው የተነሳ ጠንካሮች አንድንሆን ፣ በትጋት ቅዱሳት መጻህፍትን ልንመረምር”ይገባል (አልማ 17፥2)።

በጆርጂያ አትላንታ ሚስዮን የሚስዮን መሪዎች ሆነን እያገለገልን ሳለን፣ እያንዳንዱን ሚስዮናዊ በየቀኑ ቢያንስ ለ30 ደቂቃ መጽሐፈ ሞርሞንን እንዲያጠኑ ባለቤቴ እና እኔ አበረታታናቸው። ይህ ቁርጠኝነት እምነታችንን ጨምሯል እናም ተአምራት እንድንሻ እና እንድንጠብቅ ረድቶናል።

ከሚስዮናችን በኋላ በየቀኑ ቅዱሳት መጻህፍትን ለማጥናት ተመሳሳይ ጊዜ ሊኖረን የማይችል ቢሆንም ነገር ግን በየቀኑ መጽሀፈ ሞርሞንን በጸሎት አማካይነት ለማጥናት ቅድሚያ የምትሰጡ ከሆነ በጌታ እና በተስፋ ቃሉ ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ጥንካሬ እና ልበ ሙሉነትን እንደምታገኙ ቃል እገባለሁ።

2. የክርስቶስን ቃላት በመመገብ ጥናታችሁን ይበልጥ ትርጉም ያለው አድርጉ

ኔፊም “የክርስቶስን ቃል ተመገቡ … እነሆ የክርስቶስ ቃል ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች በሙሉ ይነግራችኋልና” (2 ኔፊ 32፥3) በማለት አስተምሮናል።

መመገብ ማለት ከማንበብ በላይ ማጣጣም፣ ማሰላሰል እና መተግበር ማለት ነው። መጽሀፈ ሞርሞንን ባጠናችሁ ጊዜ፣ የቅዱሳት መጻህፍት ጥናታችሁን ይበልጥ ትርጉም ያለው የምታደርጉበትን መንገድ አስቡ። ለምሳሌ፦

  • በወንጌል ቤተመጻህፍት ውስጥ ያሉትን የጥናት እርዳታዎች ተጠቀሙ።

  • የእግዚአብሔርን እቅድ ለመረዳት እና ከሰማይ አባት ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት እና ለመጠበቅ የሚመሩንን ዘለዓለማዊ እውነቶች መለየት።

  • በጥናታችሁ ወቅት የተማራችሁትን ለመጠበቅ አስፈላጊ ሀረጎችን ማድመቅ እና የተሰማችሁን ስሜት ዘግቡ።

መፅሐፈ ሞርሞን የነፍሳችንን ጥያቄ ለመመለስ ሃይል አለው። ኔፊ “ለእኛ ጥቅምና ትምህርት ይሆኑ ዘንድ ሁሉንም ጥቅሶች ከእኛ ጋር [ማመሳሰል]” ይገባናል (1 ኔፊ 19፥23) ብሎ ተናግሯል።

የክርስቶስን ቃል ስንመገብ ለራእይ በሮችን ይከፍቱልናል እንዲሁም ወደ እርሱ እንቀርቡ ዘንድ በህይወታችን የተለያየ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ወቅት ምን ማድረግ እንዳለብን ያሳየናል።

3. ስለ መጽሐፈ ሞርሞን እውነተኛነት ምስክርነታችሁን አካፍሉ

ልክ ኔፊ የህይወትን ዛፍ ፍሬ ከቤተሰቡ ጋር ለመካፈል እንደፈለገ ( 1ኛ ኔፊ 8፥12ን ተመልከቱ)፣ እኛም የመጽሀፈ ሞርሞን ምስክርነትን ስናገኝ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በማወቅ የሚመጣውን ሃሴት ለማካፈል ፍላጎትን እናዳብራለን።

እህት ቤንሰን መፅሐፈ ሞርሞን ይዛ

ከሚስዮናውያኖቻችን አንዷ የሆነችው፣ ይህንን ስብሰባ አብራን እየታደመች ያለችው እህት ቤንሰን፣ ወንድሟን ለመርዳት የነበራትን ፍላጎት አካፈለችኝ። በዚያ ጊዜ፣ እርሱ ወደ ኮሌጅ ለመሄድ እያጠና ነበር እናም ሚስዮን ስለማገልገል እርግጥኛ አልነበረም። በመጀመሪያዎቹ አራት የሚስዮን ወራቶቿ ወቅት እህት ቤንሰንን መጽሐፈ ሞርሞንን እንድታነብ፣ የምትወዳቸውን ጥቅሶች እንድታሰምርባቸው እና ያንን ግልባጭ ለወንድሟ እንድትልክ ለመጋበዝ ተነሳሳሁ።

እህት ቤንሰን የተሰመረበትን የመጽሀፈ ሞርሞን ቅጂ ላከች እና በየምሽቱ እንዲያነበው ወንድሟን ጋበዘችው። በኋላም እንዲህ በማለት አካፈለችኝ፤ “ሚስዮን ከመሄዴ በፊት ወንድሜ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ስለመሆን እርግጠኛ አልነበረም። ከጊዜ በኋላ ቀስ በቀስ፣ መጽሐፈ ሞርሞንን ሲያነብ፣ በህይወቱ ውስጥ የላቀ ሃሴትን ሊያገኝ ቻለ እናም ሚስዮን ስለማገልገልን ማሰብ ጀመረ።”

ሽማግሌ ቤንሰን

እህት ቤንሰን የሙሉ ጊዜ አገልግሎታን ከማጠናቀቋ ሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ፣ ወንድሟ የሚስዮን ጥሪውን ተቀበለ። አሁን በሜክሲኮ ቱሽክላ ጉቴሬዝ ሚሲዮን በማገልገል ላይ ይገኛል። ሽማግሌ[ኤልደር] ቤንሰን በመጽሐፈ ሞርሞን አማካይነት፣ ጌታን እንዲያገለግል ወዳደረገው ውሳኔ ወዳመራው እና ነገሮች እንዲከናወኑ ወዳደረገው የህይወቱን መንፈሳዊ ገጽታ በግልፅ አየ። ያም ውሳኔበክርስቶስ ቃላት ሃይል አማካኝነት ተጽእኖ የተደረገበት— ተዓምር ነበር።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እያንዳንዳችሁ የመፅሐፈ ሞርሞን ጥናታችሁን ጥልቅ እንድታደርጉ አበረታታችኋለሁ። በመጽሐፈ ሞርሞን ላይ ያሉ ቃላትን በተመገብናቸው ጊዜ፣ መንፈስ ዘለዓለማዊ እውነቶችን እንድንረዳ እና ጌታ እውነቱን እንዲሰሙ ላዘጋጃቸው ምስክርነታችንን እንድናካፍል እንደሚረዳን አውቃለሁ። ጌታ እንዳለው፣ “ምርጦቼ ድምጼን ይሰማሉ ልባቸውንም አያደነድኑም” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 29፥7)። እግዚአብሔርን በእምነት የሚጠይቁ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት የመጽሀፈ ሞርሞንን እውነተኛነት እንዲሁም የመለኮታዊነቱን ምስክር እንደሚያገኙ እመሰክራለሁ። ስለዚህ የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።

ማስታወሻ

  1. ረስል ኤም ኔልሰን፣ “የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ” (ለአዲስ የሚስዮን ፕሬዚደንቶች የተሰጠ ሴሚናር፣ ሰኔ 23፣ 2025 (እ.አ.አ)።