ማንም ብቻውን አይቀመጥም
በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መኖር በዳግም በተመለሰችው ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ለሁሉም ቦታ ማግኘትን ይጨምራል።
፩.
ለ50 አመታት፣ የወንጌል ባህልንም ጨምሮ ስለባህልን አጥንቼአለሁ። የጀመርኩት በእድል ብስኩቶች [በውስጡ እጣፋንታ ተጽፎበት የተጠቀለለ ስስ ወረቀት የሚገኝበት ብስኩት] ነበር።
በሳን ፍራንሲስኮ ቻይናታውን ውስጥ የጎንግ ቤተሰብ እራት የእድል ብስኩቶች እና “የሺህ ማይል ጉዞ የሚጀምረው በአንድ እርምጃ ነው” በሚሉት ጥበባዊ አባባል ተጠናቋል።
ጎልማሳ ሳለሁ የእድል ብስኩቶችን እሰራ ነበር። ነጭ የጥጥ ጓንቶችን ለብሼ፣ ከምድጃው ውስጥ ሞቅ ያለ ክብ ብስኩቶችን አጣጥፌ በቅርጻቸው አዘጋጃቸው ነበር።
በሚያስገርመኝ ሁኔታ፣ የእድል ብስኩቶች በመጀመሪያ ጊዜ የቻይና ባህል አካል እንዳልሆኑ ተማርኩ። የቻይና፣ የአሜሪካ እና የአውሮፓ የእድል ብስኩቶች ባህልን ለመለየት፣ ልክ አንድ ሰው የጫካ እሳትን በሶስት ጎንዮሽ ለማስተካከል ብዙ ቦታዎችን እንደሚጠቀም ሁሉ እኔም በበርካታ አህጉራት ላይ የእድል ብስኩቶች ፈልጌ ነበር። በሳን ፍራንሲስኮ፣ ሎስ አንጀለስ እና ኒው ዮርክ ያሉ የቻይና ምግብ ቤቶች ስለወደፊት እድል የሚነግሩት ብስኩቶችን የሚሰጡ ሲሆን፣ በቤጂንግ፣ ለንደን ወይም ሲድኒ ያሉ ምግብ ቤቶች ግን አይሰጡም። ብሔራዊ የእድል ብስኩት ቀንን የሚያከብሩት አሜሪካውያን ብቻ ናቸው። የቻይና ማስታወቂያዎች ብቻ “ትክክለኛውን የአሜሪካ የእድል ብስኩቶች” ያቀርባሉ።
የእድል ብስኩቶች አስደሳች እና ቀላል ምሳሌ ናቸው። ነገር ግን የባህል ልምዶችን በተለያዩ ቦታዎች የሚያወዳድረው ተመሳሳይ መርህ የወንጌልን ባህል እንድንለይ ይረዳናል። እናም አሁን የመፅሐፈ ሞርሞን ምሳሌያዊ እና የአዲስ ኪዳን ምሳሌ ትንቢቶች እየተፈጸሙ ሳሉ፣ ጌታ የወንጌል ባህልን ለመማር አዲስ እድሎችን እየከፈተ ነው።
፪.
በሁሉም ቦታዎች ሰዎች እየተንቀሳቀሱ ናቸው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 281 ሚሊዮን አለም አቀፍ ስደተኞችን ዘግቧል። ይህ በ1990 ከነበረው በ128 ሚሊዮን ግለሰቦች ሲበልጥ፣ እና በ1970 ከነበረው ግምት በሦስት እጥፍ ከላይ ይበልጣል። በሁሉም ቦታ፣ ከቀድሞ ይልቅ ብዛት ያላቸው ወንጌሉን የተቀላቀሉ ሰዎች የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እያገኙ ናቸው። በየሰንበቱ፣ ከ195 የትውልድ ሐገሮች እና ግዛቶች የሆኑ አባላት እና ጓደኞች በ31,916 የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን አካል ሆነው ይሰባሰባሉ። 125 ቋንቋዎችን እንናገራለን።
በቅርብ ጊዜ፣ በአልባኒያ፣ በሰሜን መቄዶንያ፣ በኮሶቮ፣ በስዊዘርላንድ እና በጀርመን ውስጥ አዲስ አባላት የመፅሐፈ ሞርሞን የወይራ ዛፍ ተምሳሌትን ሲፈጽሙ አይቻለሁ። በያዕቆብ 5 ውስጥ፣ የወይኑ ቦታ ጌታ እና አገልጋዮቹ ከተለያየ ቦታ የመጡትን በመሰብሰብ እና በማዳቀል ሁለቱንም የወይራ ዛፎች ሥሮችን እና ቅርንጫፎችን ያጠናክራሉ። ዛሬ የእግዚአብሔር ልጆች በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሆነው ይሰባሰባሉ፤ ጌታ በዳግም የተመለሰውን የወንጌል ሙላትነታችንን ለማስፋት አስደናቂ የተፈጥሮ መንገዶችን ይሰጣል።
እኛን ለመንግሥተ ሰማያት እያዘጋጀን፣ ኢየሱስ ስለ ታላቁ እራት እና የሰርግ ድግስ ምሳሌዎችን ተናግሯል። በእነዚህ ምሳሌዎች ውስጥ፣ የተጋበዙ እንግዶች ላለመምጣት ሰበብ ይሰጣሉ። ጌታው አገልጋዮቹን እንዲህ በማለት አዘዛቸው፦ “ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች ፈጥነህ ውጣ” እና “ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣ” ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንና ዕውሮችንም “ወደዚህ አግባ።” በመንፈሳዊ አነጋገር፣ እነዚያ እያንዳንዳችን ነን።
ቅዱሳት መጻህፍት እንደሚያውጁት፦
ወደ “የጌታ ቤት እራት የሆነው” ወደተዘገጀበት “ሁሉም አገሮች [ይጋበዛሉ]።”
የጌታን መንገድ አዘጋጁ … በዚህ ኗሪዎችዋም እንዲቀበሉት፣ መንግስቱም በምድር ላይ እንዲሄድ፣ … ወደ ፊት ለሚመጡት ቀናትም [እንዲዘጋጁ]።
ዛሬ ለጌታ እራት የተጋበዙት ከሁሉም ቦታ እና ባህል የመጡ ናቸው። ሽማግሌ እና ወጣት፣ ሀብታም እና ድሀ፣ አካባቢያዊ እና አለም አቀፋዊ፣ የቤተክርስቲያናችንን ምዕመናኖች ከማህበረሰባችን ጋር እናመሳስላለን።
እንደ ዋና ሐዋርያነት ጴጥሮስ፣ ሰማይ በራዕይ ተከፍታ “በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማት” አየ “በዚያም … ሁሉ አራዊት … ነበሩበት።” ጴጥሮስ እንዳስተማረው፦ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ … በአሕዛብ ሁሉ [ጌታን] የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።
በደጉ ሳምራዊ ምሳሌ፣ ኢየሱስ እኛን ወደ እርስ በርሳችን እና ወደ እርሱ በእንግዳ ማረፊያው—በቤተክርስቲያኑ—እንድንመጣ ጋብዞናል። መልካም ጎረቤቶች እንድንሆን ጋብዞናል። ደጉ ሳምራዊ በእንግዳ ቤት ውስጥ ላሉት ሰዎች ለሰጡት እንክብካቤ መልሶ እንደሚከፍል ቃል ገብቷል። በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መኖር በዳግም በተመለሰችው ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ለሁሉም ቦታ መስጠትን ይጨምራል።
“በእንግዳ ማረፊያ ቤት ውስጥ ክፍል” የሚለው መንፈስ “ማንም ሰው ብቻውን አይቀመጥም” የሚለውንም ይጨምራል። ወደ ቤተክርስቲያን ስትመጡ፣ ብቻውን የሆነ ሰው ካያችሁ፣ ሰላምታ አቅርባችሁላቸው ከእነርሱ ጋር ትቀመጣላችሁን? ይህ የእናንተ ልማድ ላይሆን ይችላል። ግለሰቡ ከእናንተ ልዩ ሊመስል ወይም በተለየ መንገድ በመናገር የተለየ ሊሆን ይችላል። እና፣ በእርግጥም፣ የእድል ብስኩት፣ “የወንጌል ጓደኝነት ጉዞ እና ፍቅር የሚጀምረው በመጀመሪያ ሰላምታ በመስጠት እና አንድ ሰው ብቻውን እዳይቀመጥ ማድረግ ነው” ሊል ይችላል።
“ማንም ሰው ብቻውን አይቀመጥም” ማለት ደግሞ ማንም በስሜትም ሆነ በመንፈሳዊ መልኩ ብቻውን አይሆንም ማለት ነው። ልጁን ለመጎብኘት ልቡ ከተሰበረ አባት ጋር ሄድኩ። ከአመታት በፊት፣ ልጁ አዲስ ዲያቆን ለመሆን ጓጉቶ ነበር። ለዚህ ለመዘጋጀትም ቤተሰቦቹ የመጀመሪያውን ጥንድ አዲስ ጫማ ለሱ መግዛትን ያካተተ ነበር።
ቤተክርስቲያን ውስጥ ግን ዲያቆናቱ ሳቁበት። ጫማዎቹ አዲስ ነበሩ፣ ግን ፋሽን አልነበሩም። አፍሮ እናም ስሜቱ ተጎድቶ፣ ወጣቱ ዲያቆን ከእንግዲህ ወደ ቤተክርስቲያን እንደማይሄድ ተናገረ። አሁንም ልቤ ለእሱ እና ለቤተሰቡ ተሰብሯል።
ወደ ኢያሪኮ በሚወስዱት አቧራማ መንገዶች ላይ እያንዳንዳችን ተስቆብናል፣ አፍረናል፣ ተጎድተናል፣ ምናልባትም ንቀት ወይም እንግልት ደርሶብናል። እና፣ በተለያየ የሃሳብ ደረጃ፣ እያንዳንዳችን እንዲሁ ችላ ብለናል፣ አናይም ወይም አንሰማም፣ ምናልባትም ሆን ብለን ሌሎችን እንጎዳለን። ስለተጎዳን እና ሌሎችን ስለጎዳንም ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንንም ወደ ማረፊያው ያመጣን። በእርሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ በስርዓቶቹ እና በቃል ኪዳኖቹ በኩል፣ ወደ እርስ በራሳችን እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንቀርባለን። እንወዳለን እናም እንወደዳለን፣ እናገለግላለን እናም እንገለገላለን፣ ይቅር እንላለን እናም ይቅርታን እንቀበላለን። እባካችሁን አስታውሱ፣ “ሰማይ መፈወስ የማይችለው ሀዘን ምድር የላትም”፤ የምድር ሸክሞች ይቀልላሉ—የአዳኛችን ደስታ እውን ነው።
1 ኔፊ 19 ውስጥ፣ እንዲህ እናነባለን፦ “የእስራኤልንም አምላክ እንኳን ሰዎች በእግራቸው ይረግጡታል … ንቀውታል፣ … ስለዚህ ይገርፉታል፣ እርሱም ይህን ይቀበላል፤ እናም ይመቱታል፣ እርሱም ይህን ይቀበላል። አዎን ይተፉበታል፣ እና … ይህንንም ይቀበለዋል።”
ወዳጄ ፕሮፌሰር ቴሪ ዋርነር እንደሚለው እንደ መፍረድ፣ መግረፍ፣ መምታት እና መትፋት ያሉ ድርጊቶች በክርስቶስ ሟች ህይወት ጊዜ ብቻ አልፎ አልፎ የተፈጸሙት አልነበሩም። እርስ በርሳችን፣ በተለይም የተራቡትን፣ የተጠሙትን፣ ብቻቸውን ያሉትን፣ የምናስተናግድበት መንገድ እርሱን እንዴት እንደምናስተናግድ የሚያሳይ ነው።
ዳግም በተመለሰችው ቤተክርስቲያን ውስጥ፣ ሁላችንም የተሻልን የምንሆነው ሁሉም ሰው ከሰው ጋር ሲቀመጥ ነው። ዝም ብለን አንቀበል ወይም አንታገሥ። በቅንነት እንቀበል፣ እናስተናግድ፣ እናገልግል፣ እንውደድ። እያንዳንዱ ጓደኛ፣ እህት፣ ወንድም የውጭ ዜጋ ወይም እንግዳ አይሁን፣ ከዛ ይልቅ በቤት ውስጥ መገኘት የሚገባው ልጅ ይሁኑ።
ዛሬ፣ ብዙዎች ብቸኝነት እና መገለል ይሰማቸዋል። ማህበራዊ ሚዲያ እና artificial intelligence [ሠው ሠራሽ አስተውሎት] የሰውን መቀራረብ እና የሰውን ንክኪ በጥልቅ እንድንፈልግ ሊያደርጉን ይችላሉ። አንዳችን የሌላውን ድምጽ መስማት እንፈልጋለን። እውነተኛ ህብረተሰባዊነት እና ደግነት እንፈልጋለን።
በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ተቀባይነት የለንም ብለን እንዲሰማን የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ—በምሳሌያዊ አነጋገር ብቻችንን እንቀመጣለን። ስለ አወራራችን፣ አለባበሳችን፣ የቤተሰባችን ሁኔታ እንጨነቅ ይሆናል። ምናልባትም በቂ እንዳልሆንን ይሰማናን፤ የሲጋራ ጭስ ሽታ ይኖረን፤ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ይናፍቁን፤ ከአንድ ሰው ጋር ተለያይተን እና ጉዳት እና እፍረት ይሰማን፤ ይህ ወይም ያ የቤተክርስቲያኗ ፖሊሲ ያሳስበን ይሆናል። ያላገባን፣ የተፋታን፣ መበለት ልንሆን እንችላለን። ልጆቻችን ጸጥታን የሚረብሹ ናቸው፤ ልጆች የሉንም። በሚስዮን ተልዕኮ አላገለገልንም ወይም ቀደም ብለን ወደ ቤት መጥተናል። ዝርዝሩ ይቀጥላል።
ሞዛያ 18፥21 ልባችንን በፍቅር እንድንተሳሰር ይጋብዘናል። ባነሰ ሁኔታ እንድንጨነቅ፣ እንድንፈርድ፣ ከሌሎች በብዛት እንዳንጠይቅ—እናም በሚያስፈልግ ጊዜ፣ በራሳችን ላይ በብዛት እንዳንፈርድ እጋብዛችኋለሁ። ጽዮንን በአንድ ቀን አንፈጥርም። ግን እያንዳንዱ “ሰላም”፣ እያንዳንዱ ሞቅ ያለ ገፅታ፣ ጽዮንን ያቀራርባል። በጌታ የበለጠ እንታመን እና ሁሉንም ትእዛዛቱን ለመታዘዝ በደስታ እንምረጥ።
፫.
በትምህርት መሰረት፣ በቅዱሳን የእምነት እና የጓደኛማችነት ቤት ውስጥ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቃል ኪዳን ምክንያት ብቻውን የሚቀመጥ የለው።
ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንዳስተማረው፦ ፣ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ከሁሉም ብሔር፣ ዘመዶች እና ሰዎች በአንድነት በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ “የኋለኛው ቀን ክብር የሆነውን ‘የዘመን ፍጻሜ’ ለማየት፣ በዚህ ለመሳተፍ እና ይህን ወደፊት ለመግፋት ለመርዳት ለእኛ ተትቶልናል።
እግዚአብሔር “ለዓለም ጥቅም ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም አያደርግም፤ … ሰዎችን ሁሉ ወደ እርሱ ይስብ ዘንድ። …
“… ከቸርነቱ ይካፈሉ ዘንድ ሁሉም ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጋብዛል፤ … ሁሉም ለእግዚአብሔር አንድ ናቸው።
በኢየሱስ ክርስቶስ መቀየር የተፈጥሮአዊ ሰውን እና አለማዊ ባህልን እንድንተው ይጠይቀናል። ፕሬዚዳንት ዳለን ኤች. ኦክስ እንዳስተማሩት፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጻረር ማንኛውንም ወግ እና ባህላዊ ልምምድ መተው እና የኋለኛው ቀን ቅዱሳን መሆን አለብን። እንዲህም አብራርተዋል፣ “ለሁሉም የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት አንድ የሆኑ ልዩ የወንጌል ባህል፣ የስነምግባር ስብስብ እና የሚጠበቁ ነገሮች እና ልምዶች አሉ።” የወንጌል ባህል ንጽህናን፣ በየሳምንቱ በቤተክርስቲያን መገኘትን፣ አልኮልን፣ ትምባሆን፣ ሻይንና ቡናን መከልከልን ያካትታል። ሐቀኝነትን እና ታማኝነትን፤ በቤተክርስቲያን ሀላፊነት ወደላይ ወይም ወደታች ሳይሆን ወደ ፊት እንደምንሄድ መረዳትን ያካትታል።
በሁሉም አገር እና ባህል ካሉ ታማኝ አባላት እና ጓደኞች እማራለሁ። በተለያዩ ቋንቋዎች እና ባህላዊ አስተያየት የተጠኑ ቅዱሳት መጻሕፍት የወንጌል ግንዛቤን ይጨምራሉ። የተለያዩ የክርስቶስ መሰል ባህሪያት አገላለጾች ለአዳኝ ያለኝን ፍቅር እና ግንዛቤ ጥልቅ ያደርጉታል። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ እንደ እግዚአብሔር ልጅ፣ የቃል ኪዳን ልጅ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር በመሆን የባህል ማንነታችንን ስንገልጽ ሁሉም ተባርከዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ለእኛ በግል የታሰበ ነው። በቅርቡ፣ አንድ ወጣት፣ “ሽማግሌ ጎንግ፣ አሁንም ወደ ሰማይ መግባት እችላለሁ?” ሲል ጠየቀ። ይቅርታ ሊደረግለት ይችል እንደሆነ አሰበ። ስሙን ጠየኩት፣ በጥሞና አዳመጥኩት፣ ከኤጲስ ቆጶሱ ጋር እንዲነጋገር ጋበዝኩት፣ አቀፍኩትም። የሄደውም በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ እያለው ነበር።
ወጣቱን በሌላ ሁኔታ ጠቅሼዋለሁ። በኋላም፣ “ሽማግሌ ጎንግ፣ እኔ እና ባለቤቴ ዘጠኝ ልጆች አሳድገናል … እናም ሁለት ሚሲዮን አገልግለናል” በማለት የጀመረ ያልተፈረመ ደብዳቤ ደረሰኝ። ነገር ግን “ሁልጊዜ በሰለስቲያል መንግሥት ውስጥ ለመግባት እንደማይፈቀድልኝ ይሰማኝ ነበር … ምክንያቱም በወጣትነቴ ኃጢአቶቼ በጣም መጥፎ ነበሩ!”
ደብዳቤውም ቀጠለ፣ “ሽማግሌው ጎንግ፣ የይቅርታ ተስፋ ስላገኘው ወጣት ሲናገሩ፣ ምናልባት [ይቅርታ ሊደረግልኝ እንደምችል] በመገንዘብ በደስታ ተሞላሁ። ደብዳቤውም “አሁን ራሴን እወዳለሁ!” በማለት ይደመድማል።
በእርሱ እንግዳ ማረፊያ ውስጥ ወደ እርስ በርሳችን እና ወደ ጌታ ስንመጣ፣ በቃል ኪዳኑ አባልነታችን ጥልቅ ይሆናል። ብቻውን የሚቀመጥ ሰው ሳይኖር ሲቀር ጌታ ሁላችንን ይባርከል። እና ማን ያውቃል? ምናልባት፣ ከጎን የተቀመጥንለት ሰው የእኛ ምርጥ የእድል ብስኩት ጓደኛ ሊሆን ይችላል። በትህትና ለእርሱ እና ለእያንዳንዳችን በበጉ እራት ላይ ቦታ እናስገኝ፣ አጥብቄ እጸልያለሁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።