ሂዱ እና እንዲሁ አድርጉ
ለአገልግሎት ስራ የተጠሩ ሚስዮናውያን ላይ ትኩረት ላደርግ እፈልጋለሁ። እነርሱ ለእኛ ምሳሌዎች ናቸው።
አዳኙ በቤተሳይዳ አልፎ ይሄድ በነበረበት ጊዜ፣ የተወሰኑ ሰዎች አንድን አይነ ስውር ወደ እርሱ አመጡ። ምናልባትም በተጨባጭ ተዓምር ለማየት ተስፋ አድርገው ነበር። አዳኙም በግል ሊፈውሰው ስለወደደ “አይነ ስውሩን ሰው እጁን ያዘው፣ እናም ከከተማው ውጪ እንዲሄድ መራው።” አስቀድሞ፣ ፈውሱ እምብዛም ውጤታማ አይመስልም ነበር። ሰውየውም “አሻቅቦ አየ እናም ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ አለ።” ኢየሱስም በርህራሄ፣ “እጆቹን እንደገና በአይኖቹ ላይ አድርጎ ወደ ላይ እንዲመለከት አደረገው።” በዚያም ተጨማሪ የአዳኙ የእጅ ዳሰሳ፣ አይነስውሩ ሰው አሁን “አጥርቶ አየ።”
ይህ እንዴት የአዳኙ ህይወት ትሁት በሆነ የአገልግሎት ስራ የተገለጠ መሆኑን የሚያሳይ አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው። እርሱም “የመጣሁት ልገለገል ሳይሆን ነገር ግን ላገለግል መጥቻለሁ” እንዳለ ያስታውሰናል እና ተጨማሪ ርቀቶችን በመሄድ የእርሱን ምሳሌ እንድንከተል ይጋብዘናል፣ ለሚጠይቁንም በመስጠት፣ እና ባልንጀራችንንም በመውደድ። ባልንጀራዬ ማነው? የሚለውን ሲጠየቅ “ሂድ እና እንዲሁ አድርግ” በማለት ክርስቶስ የመልካሙን ሳምራዊ ምሳሌ አካፈለ።
የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሚስዮናውያን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንሆን የሚፈልገው የዘመኑ የመልካሙ ሳምራዊ ምሳሌዎች ነን። ለአገልግሎት ስራ የተጠሩ ሚስዮናውያንን ትኩረት ላደርግ እፈልጋለሁ። እነርሱ አገልግሎት ምን ያህል (1) ልብን ለወንጌል እንደሚከፍት የሚያሳዩን ምሳሌዎቻችን ናቸው፣ (2) በምንም ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ብንሆን ሁላችንም እንድናገለግል የሚያደርገን፣ እና (3) ወደ ህይወታችን የክርስቶስን ሃይል እንደሚያመጣ የሚያሳዩን ምሳሌዎቻችን ናቸው።
በመጀመሪያ፣ አገልግሎት ልብን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ይከፍታል።
በ91 ምዕተ ዓለም ገደማ፣ የመጽሐፈ ሞርሞን ሚስዮን አሞን ራሱን ለንጉስ ላሞኒ እንዲህ በማለት አስተዋወቀ፣ “ለተወሰነ ጊዜ ከዚህ ህዝብ ጋር ለመሰንበት እፈልጋለሁ፤ … [እናም] አገልጋይህም እሆናለሁ።” ለንጉሱ ባደረገው አገልግሎት ምክንያት፣ አሞን “በድፍረት እንዲናገር፣ … እና ለ [ንጉስ ላሞኒ] በምን ሃይል አገልግሎቱን እንደፈጸመ እንዲናገር እድል ተሰጠው። በምላሹም፣ ንጉሱም “[አሞን] የሚፈልገውን ማንኛውንም ነገር … [ንጉሱ] እንደሚሰጠው ቃል ገባለት።” የአሞን ብቸኛ ጥያቄ ንጉሱ የኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል መልእክት እንዲሰማ ነበር። የአሞን አገልግሎት “በሺዎች የሚቆጠሩ ነፍሳት ወደ ንሰሃ [እንዲመጡ] አደረገ።”
በጊዜያችን፣ አገልግሎት ሌሎች ወደ ወንጌል እንዲመጡ ማድረጉን ቀጥሏል። እህት ቤቨን በአስተማሪነት ሚስዮናዊ ሆና እያገለገለች በነበረችበት ጊዜ ወደ ቤቷ ለህክምና እንድትመለስ የዳረጋት፣ የጤና እክል አጋጥሟት ነበር። አቋርጣ ከመሄድ ይልቅ፣ በቤቷ ሆና እንደ አገልጋይ ሚስዮናዊ በመሆን አገልግሎቷን ለመቀጠል ችላለች።
አንድን መናፈሻ እየጎበኘች በነበረችበት ጊዜ፣ እህት ቤቨን እና ጓደኛዋ አንዲትን እናት ከአራት ልጆቿ ጋር ለማናገር ተነሳሱ፣ ነገር ግን በመጠራጠራቸው ቤተሰቡ በመኪናቸው ሄዱ። በቀጣዩ ቀን፣ ይህ ቤተሰብ በዚያ እንዲሆን በመጸለይ ወደ መናፈሻው ተመለሱ። በተዓምር፣ እናት ከአንድ ቀን በፊት ተቀምጣ በነበረችበት ተመሳሳይ ቦታ ተቀምጣ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ እህት ቤቨን እና ጓደኛዋ እናትየውን ቀረቧት፣ ተዋወቋት፣ እናም በጊዜያዊ ችግር አስከፊ ሁኔታ ላይ የነበረች መሆኑን ሊያውቁ ቻሉ። እርዳታን አደረጉላት ከዚያም ስለወንጌል እንድትማር ጋበዟት።
በዚያ አገልግሎት እና ጉብኝት ምክንያት እናትየው እና ትልቁ ልጇ፣ ሁለተኛው ትልቅ ልጅም እንዲሁ ከዓመት በኋላ ተከትሎ ተጠመቁ። ዛሬ ንቁ አባላት ሆነው ይገኛሉ። እህት ቤቨን ይህ ልምድ መለኮታዊ መነሳሳት እንደሆነ አውቃለች እናም “እግዚአብሔርም [እርስዋን] የት ጋር መሆን እንዳለባት ያስመሰከረላት ነበር።”
እንደ አሞን እና እህት ቤቨን፣ ሌሎችን ባገለገልን ጊዜ፣ “መልካም ምሳሌ እንሆንላቸዋለን” እና በእኛ ውስጥ ያለውን “የተስፋ ምክንያት ለማወቅ ይሻሉ።”
ኢየሱስ “ሂዱ እና እንዲሁ አድርጉ” በማለት ይጋብዘናል፡፡
ሁለተኛ፣ አገልግሎት ሁላችንንም በምንም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንድናገለግል ያደርገናል።
ፕሬዘዳንት ራሰል ኤም ኔልሰን “እያንዳንዱን ብቁ፣ ለማድረግ ችሎታ ያለውን ወጣት ለሚስዮን እንዲዘጋጅ እና እንዲያገለግል” እና ለእያንዳንዱ ችሎታ ላላቸው ወጣት እህቶች “ጌታ ምናልባት ሚስዮን እንዲያገለግሉ የሚፈልግ መሆኑን ለማወቅ እንዲጸልዩ” ጥሪ ያቀርባሉ። እሳቸወ እንዲህ ቃል ገቡ፣ “የተጓዥነትም ሆነ የአገልግሎት፣ ሚስዮን ለማገልገል መወሰናችሁ እናንተንም ሆነ ሌሎችን እንደሚባርክ” ቃል ገብተዋል። የአገልግሎት ሚስዮን መቻል የሚለውን ቃል ትርጉም ቀይሮታል። አሁን ጌታን በሙሉ ጊዜው ለማገልገል የሚፈልግ እያንዳንዱ ብቁ ወጣት ወንድ እና ሴት በጣም ጥቂት ሁኔታዎች ካልሆኑ በስተቀር ሊከለከል አይችልም።
ሽማግሌ ሆልጋዶ የግል ሁኔታዎች ምንም አይነት በሆኑበት ውስጥ ማገልገል የመቻል ምሳሌ ነው። እርሱ የተለመደ ባልሆነ የዘር መዛባት ጋር የተወለደ ሲሆን ይህም የአስተማሪነት ሚስዮን እንዳያገለግል የከለከለው ነበር። ሽማግሌ ሆልጋዶ እንደ አገልጋይ ሚስዮናዊ በመሆን ተጠራ እናም ሌሎች ሰዎችን በሚፈልጉት ነገር በመርዳት በኤጲስ ቆጶስ የክምችት ክፍል ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ ሆነ። እርሱም መደርደሪያዎችን ማከማቸት፣ አትክልቶችን ማሸግ እና አገልግሎታቸው ያበቃ ሳጥኖችን ያስወግድ ነበር።
ሽማግሌ ሆልጋዶ ከሚስዮን አገልግሎቱ በኋላ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ወቅት ሲናገር፣ “እግዚአብሔር የአገልግሎት ሚስዮናዊ ይፈልግ እንደነበር አካፍሏል። እርሱ ሰዎች ሌሎችን መውደድ እና ማገልገል እንዳለባቸው ይፈልጋል። እነዚህ ሰዎች የመጸዳጃ ቤት ወረቀቶችን፣ ብሮኮሊ ያሽጉ፣ እና የቤት እና የቢሮ እቃዎችን ያመርቱ ነበር እና ለሰዎችም መልካም ነበሩ።”
መልካምን ለማድረግ የአገልግሎት ጥሪን መቀበል ወይም የስም መለያ ማድረግ አይጠበቅባችሁም። እያንዳንዱ አገልግሎት በአዳኙ ተቀባይነትን ያገኛል። ሁላችንም ፍቅር በተሞላበት ደግነት ሌሎችን ወደ ክርስቶስ ለማምጣት መርዳት እንችላለን። ሁላችንም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት በክርስቶስ ስም ማገልገል እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የእምነት ምሳሌ በመሆን መኖር እንችላለን። አገልግሎት እራሳችንን በእግዚአብሄር ዘንድ የተወደዱ ህያው መስዋእት በማድረግ እንድናቀርብ ያደርገናል።
ኢየሱስ “ሂዱ እና እንዲሁ አድርጉ” በማለት ይጋብዘናል፡፡
ሶስተኛ፣ አገልግሎት የኢየሱስን ሃይል ወደ ህይወታችን ያመጣል
ከአስተማሪነት አገልግሎት ወደ አገልግሎት ጥሪ የተዛወረ አንድ ወጣት ሚስዮን የክርስቶስ የፈውስ ሃይል በሚያስፈልገው በግል ተግዳሮቶች ውስጥ ሲታገል ቆየ። የተቀደሰ አገልግሎት ያንን ሃይል ወደ ህይወቱ አመጣለት። እንዲህ አለ፣ “እየታገልኩ በነበረበት ጊዜ፣ ኢየሱስ እያነሳኝ እንደነበር ተሰምቶኛል። እርሱ ሰዎችን በምግብ ጓዳ፣ በቤተመቅደስ፣ እና በወንጌሉ አማካይነት ሲባርክ ማየት እንድ የተለየ ነገር አለው።”
ይህ ወጣት ጥልቅ የሆነ ሃሴት ይሰማው ጀመር፣ እናም አዲስ ያገኘው ጥማት እርሱን እና መላውን ቤተሰቡን ባርኳል። መንፈስ በበዛ ሁኔታ ቤታቸው ውስጥ ገብቷል፣ ቤተመቅደስንም በጋራ በመደበኛነት ተሳትፈዋል፣ እናም በቤተሰባቸውም ክርስቶስ ታላቅ አትኩሮት ሆኖላቸዋል። ሚስዮናዊውም ክርስቶስ ህይውቱን እንዳዳነ እና በአገልግሎት ምክንያትም ቤተሰቡን እንደባረከለት ያምናል።
ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳስተምሩት፣ “ለሎችን የማገልገል እና የማጠንከር ፍቃደኝነት የአንድን ሰው ለመፈወስ ያለውን ዝግጁነት ይወክላል፣” ማላትም በአዳኙ የቤዛነት ሃይል አማካኝነት ።
ኢየሱስ “ሂዱ እና እንዲሁ አድርጉ” በማለት ይጋብዘናል፡፡
የአገልግሎት ሚስዮናውያን የኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደሱ የደቀመዝሙር ምሳሌዎች ናቸው።
እናንተም ሆናችሁ የቤተሰባችሁ አባል የአገልግሎት ሚስዮናዊ ሆኖ በመጠራት ሲባረክ፣ ያ ልትደሰቱበት የሚገባ ጊዜ ነው። አሁን ቤተሰባችሁ በጌታ የተለየ የኢየሱስ ክርስቶስ ተወካይ በቤታችሁ እየኖረ እንዳለ ያውቃል። ያ ሁላችሁንም በዘላቂነት የሚቀይር ነው። በየትኛውም የአገልግሎት ጥሪ ላይ ቅሬታ ሊኖር አይገባም። እንዲህ እያልን እንዘምራለን፣ “ወደምትፈልገው እሄዳለሁ” እና “እንድሆን የምትፈልገውን እሆናለሁ።” የምንናገረውን የምንሆንበትን የምናሳይበት እውነተኛ አጋጣሚ ይህ ነው!
ለምታገለግሉ ለሁላችሁ፣ እና በተለይም ከ 4000 በላይ የሆናችሁ የአገልግሎት ሚስዮናውያን፣ እንወዳችኋለን! የማስተማሩ ሚስዮናውያን የጌታ አንደበቶች ከሆኑ፣ እናንተ የአገልግሎት ሚስዮናውያን የጌታ እጆች ናችሁ፣ እና ሁለተኛ ደረጃ ሚስዮናውያን አይደላችሁም። እያንዳንዳችሁ ለእስራኤል መሰባሰብ አስፈላጊዎች ናችሁ። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳስተምሩት፣ “በማንኛውም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ እና እንዲጠብቁ ማንንም የሚረዳ ነገር ስናደርግ፣ እስራኤልን ለማሰባሰብ እየረዳን ነን።”
እናንተ የአገልግሎት ሚስዮናውያን በእያንዳንዱ ቀን በተለያየ መንገድ እስራኤልን እየሰባሰባችሁ ነው፣ እናም አገልግሎታችሁ ህይወትን ይቀይራል። እናንተ የአገልግሎታችሁ ተጠቃሚ ማን እንደሆነ አታውቁም፣ ነገር ግን እግዚአብሄር ያውቃል። ዘወትር ማስታወስ ያለባችሁ “ከነዚህ ከታናናሾች አንዱን ባገለገላችሁ ጊዜ፣ … እርሱን እያገለገላችሁ ነው።” በቤተክርስቲያን የጥሪ ማእከል ፈቃደንነታችሁን ስትገልጹ ድምጻችሁን እንሰማለን፤ በማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ እርዳታን ስታደርጉ ፈገግታችሁን እናያለን፤ እናም በቤተመቅደስ ውስጥ ስታገለግሉ ብርሃናችሁ ይሰማናል። የተራበን ታበላላችሁ፣ የተራቆተን ታለብሳላችሁ፣ እንዲሁም ለተጠማው የሚጠጣ ትሰጣላችሁ።
ሁላችንም ልናደርግ የሚገባው “ሂዱ እና እንዲሁ አድርጉ” የሚለውን ነው፡፡
አገልግሎት የክርስቶስ ደቀመዝሙር የህይወት ደም ነው
አገልግሎት ልብን ለወንጌል የመክፈት ሃይል አለው እናም ሁላችንም ሙሉ ነፍሳችንን ለክርስቶስ እንድንሰጥ ያደርገናል። ይበልጥ እርሱን እንድንመስል ልባችንን ይለውጣል እና በሂደት ሌሎችን ከፍ እናደርጋለን። ፕሬዘዳንት ኔልሰን በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት ጠይቀዋል፣ “በዚህ መንፈሳዊ መበስበስ ባጠቃው ዓለም ውስጥ፣ ግለሰቦች … ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉን?” የእርሱም መልስ፣ “አዎን! … ‘የጌታ የቃል ኪዳን ህዝቦች፣… በታላቅ ክብር የእግዚአብሔርን ሃይል ታጥቀው’ … የሁሉንም የሰው ዘር ህይወት ከፍ ማድረግ ይችላሉ።” በአገልግሎት ልብን እና ዓለምን እንቀይራለን።
ክርስቶስ “መልካም እያደረገ ዞረ።” ህመምተኞችን አገልግሏል፣ ለአይነ ስውራን ብርሃንን ሰጥቷል፣ የተገፉትን ጎብኝቷል። ምግብን አዘጋጅቷል፣ በሰርግ ስፍራ እርዳታን ለግሷል፣ እና ተርበው የነበሩትን በሺህ የሚቆጠሩትን መግቧል። አንድን ሰው በክርስቶስ ስም ባገለገልን ጊዜ፣ በይበልጥ ቅድስናችን እየጨመረ እና ለዘለዓለም ህይወት ስጦታ ብቁ እንሆናለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው ነው። እርሱ የእኔ እና የእናንተ አዳኝ ነው። እርሱ ቤዛችን ነው። እርሱ የአገልግሎት ታላቁ ምሳሌያችን ነው። እያንዳንዳችን ሄደን እንደዚሁ እንድናደርግ እጋብዛለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።