በክርስቶስ ማረጋገጫን እና ጥንካሬን ማግኘት
እነዚህ የማረጋገጫ ጊዜያት ጌታ እንደተዋችሁ ማስረጃዎች አይደሉም። ይልቁንም፣ አንተን ለማጣራት እና ለማጠናከር በበቂ ሁኔታ እንደሚወዳችሁ ማስረጃዎች ናቸው።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ አብረን ስንሰበሰብ የጌታ ፍቅር ይሰማኛል። ከእናንተ ጋር ለመነጋገር ትህትና ይሰማኛል። እኔ ከምናገረው ቃላቶች በጣም በላቀ መልኩ፣ ጌታ እንድትሰሙ የሚፈልገውን መንፈስ ቅዱስ ወደ ልባችሁ እንዲያመጣ እጸልያለሁ።
ከረጅም ጊዜ በፊት፣ በኮሌጅ ውስጥ በነበርኩበት አመታት ፊዚክስ እና ሒሳብ ለመማር እፈልግ ነበር። ጫና በጣም ተሰማኝ። ከራሴ አቅም በላይ የሆነን ነገር ለመማር እየሞከርኩ እንደነበር ተሰማኝ። የበለጠ ጫና በተሰማኝ ቁጥር፣ የመቀጠል ፍላጎቴ እየቀነሰ መጣ። ብርታት ማጣቴ ጥረቶቼ ፍሬ አልባ እንደነበሩ እንዲሰማኝ አደረገ። ሰለመተው እና ሌላ ቀለል ያለ ነገር ስለማድረግ ማሰብ ጀምሬ ነበር።
የደካማነት ስሜት ተሰማኝ። ስጸልይ፣ ማቆም እንዳለብኝ ከጌታ ማረጋገጫ ተሰማኝ። እርሱ ለዓእምሮዬ እንዲህ ሲናገር ተሰማኝ፣ “አቅምህን እየፈተንኩኝ ነው፣ ነገር ግን እኔ ካንተ ጋር ነኝ።”
ያኔ የእንዚያ ቃላትን ትርጉም አላወኩም ነበር፡፡ ነገር ግን ምን ማድረግ እንደነበረብኝ አውቄ ነበር—ወደ ስራ ሄድኩ።
ቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ በማሰላሰልና በመስራት፣ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” የሚለውን የማበረታቻ መልእክት ተረዳሁ።
ከፊዚክስ ጋር የነበረኝ ትግል በእውነትም የጌታ ስጦታ እንደሆነ ተማርኩ። እርሱ ሊረዳኝ አብሮኝ እንዳለ እምነት ካለኝ፣ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን ማድረግ እንደምችል እያስተምረኝ ነበር። በዚህ ስጦታ አማካኝነት፣ አቅሜን ሊፈትሽ እና ሊያጠነክረኝ ጌታ እየሰራ ነበር።
መፈተሽ የሚለው ቃል ብዙ ትርጉሞች አሉት። የአንድን ነገር አቅም መፈተሽ በቀላሉ መፈተን ብቻ ማለት አይደለም። ጥንካሬውን መጨመር ነው። የብረት ቁራጭን አቅም መፈተሽ በውጥረት ውስጥ እንዲያልፍ ማድረግ ነው። እውነተኛ ተፈጥሮው እስኪገለጥ እና እስኪሻሻል ድረስ ሙቀት፣ ክብደት እና ግፊት ይጨመራል። በዚህ አቅም ፍተሻ ሂደት ውስጥ ብረቱ አይደክምም። እንዲያውም፣ ሊታመን የሚችል፣ ትልቅ ሸክሞችን ለመሸከም የሚያስችል ጠንካራ ነገር ይሆናል።
በዚያው መልኩ እኛን ለማጠንከር ጌታ አቅማችንን ይፈትሻል። ያ ማረጋገጫ በቀላል ወይም በምቾት ጊዜ አይመጣም። ልንሸከመው አስበን ከምንችለው በላይ ውጥረት በሚሰማን ጊዜ ይመጣል። ጌታ ማደግ እንዳለብን እና በጥረታችን እንዳንታክት፣ ተስፋ እንዳንቆርጥ፣ መሞከርን እንድንቀጥል ያስተምራል።
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለ እምነትን ማዳበር ከቀጠልን—በጊዜው ነገሮች ፈጽሞ የማይቻሉ ሆነው በሚሰሙን ጊዜዎች እንኳ—በመንፈስ ይበልጥ እንጠነክራለን። የቅዱሳት መጻሕፍት መዛግብት ይህንን እውነት ያጎላሉ።
ለምሳሌ፣ ነቢዩ ሞሮኒ በዚህ መልኩ አቅሙ ተፈትሻል እንዲሁም ተጠናክሯል። እርሱ የመጨረሻ አመታቶቹን ብቻውን ነበር የኖረው። ጓደኟች እንደሌሉት፣ አባቱ እንደተገደለ፣ ህዝቡ እንደጠፋ ጻፈ። ነፍሱን በሚፈልጉ ሰዎች ታድኖ ነበር።
ሆኖም ሞሮኒ ተስፋ አልቆረጠም። ይልቁንም፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ሊገድሉት የፈለጉትን የሕዝቡን ዘሮች ጨምሮ በህይወቱ ለማየት ለማይችላቸው ሰዎች፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ምስክርነት በሰሌዳዎች ላይ ቀረጸ። ለእኛ ፃፈልን። አንዳንዶች ቃላቱ ላይ እንደሚያላግጡ ያውቅ ነበር። አንዳንዶች እንደማይቀበሉት ያውቅ ነበር። ሆኖም መፃፉን ቀጠለ።
በእርሱ የአቅም መፈተሽ ሂደት ውስጥ፣ የሞሮኒ እምነት ታድሶ እና ጠንክሮ ነበር። የበለጠ የነፃ ሆነ። ቃሉ በታማኝነት እስከ መጨረሻው ድረስ የጸናውን ኃይል ይሸከማል። የእርሱን ምስክርነት ስናነብ ያ ሃይል ሊሰማን ይችላል።
“አሁን እኔ ሞሮኒ፣ መልካም የመሰለኝን በመጠኑ እፅፋለሁ፤ ለወንድሞቼ ለላማናውያንም እፅፋለሁ፤ እናም ስለክርስቶስ መምጣት ምልክት ከተሰጠ አራት መቶ ሃያ ዓመት ማለፉን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ።
“እናም እናንተን በጥብቅ በመምከር ጥቂት ከተናገርኳችሁ በኋላ እነዚህን መዛግብት አትማቸዋለሁ።
“እነሆ፣ እነዚህን ነገሮች በምታነቡበት ጊዜ፣ ይህን እንድታነቡ በእግዚአብሔር ጥበብ ከሆነ፣ ጌታም ለሰው ልጆች ከአዳም መፈጠር ጀምሮ እነዚህን ነገሮች እስከምትቀበሉአቸው ጊዜ ድረስ ምን ያህል መሃሪ እንደነበረ እንድታስታውሱ በጥብቅ እመክራችኋለሁ፣ እናም በልባችሁ ይህን አሰላስሉ።
“እናም እነዚህንም ነገሮች በምትቀበሉበት ጊዜ፣ እነዚህ ነገሮች ሀሰት እንደሆኑ ዘለዓለማዊ አብ እግዚአብሔርን በክርስቶስ ስም እንድትጠይቁት እመክራችኋለሁ፤ እናም በቅን ልባችሁ፤ ከእውነተኛ ፍላጎት፣ በክርስቶስ አምናችሁ ከጠየቃችሁት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እውነቱን ይገልፅላችኋል።
“እናም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሁሉንም ነገር እውነታ ታውቁታላችሁ።”
የሞሮኒ ምስክርነት በብቸኝነት የነጠረ ነበር፣ ነገር ግን ሁሉም ትውልዶች የሰማይ አባታችንን እና አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲፈልጉ ለመምራት በብርሃን ያበራል።
ሌላው የመፅሐፈ ሞርሞን ነቢይ ያዕቆብ በልጅነቱ መከራን እና ብዙ ሀዘንን በማሳለፍ ተረጋግጧል እና ተጠናክሯል። ነገር ግን አባቱ፣ ሌሂ፣ እግዚአብሔር በፈተናዎቹ ውስጥ እንደሚባርከው አስተምሮታል።
“እናም እነሆ በወንድሞችህ መጥፎነት የተነሳ፣ በልጅነትህ ጊዜ በመከራና በብዙ ኃዘን ተሰቃይተሀል።
“ይሁን እንጂ፣ ያዕቆብ፣ በምድረበዳ ውስጥ የተወለድክ የበኩር ልጄ፣ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ታውቃለህ፤ እናም እርሱ መከራህን ወደ ጥቅምህ ይለውጥልሃል።
“ስለዚህ፣ ነፍስህ ይባረካል፣ እናም ከወንድምህ ኔፊ ጋር በደህና ትኖራለህ፤ እናም ቀናትህን አምላክህን በማገልገል ታሳልፋለህ። ስለዚህ፣ በቤዛህ ፅድቅ ምክንያት አንተ እንደምትድን አውቃለሁ፤ ምክንያቱም በዘመኑ ፍፃሜ ለሰዎች ደህንነትን ለማምጣት እርሱ እንደሚመጣ አይተሀልና።”
ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በሊበርቲ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ እንደዚህ አይነት ማረጋገጫ እና ማጠናከሪያ አጋጥሞታል። በነበረበት አስፈሪ ጥልቀት ውስጥ ነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ሲል ጮኀ፤
“እግዚአብሔር ሆይ የት ነህ? …
ጌታ በዮሴፍ ስቃይ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ መታገስ የሚያስገኘውን የመቀደስ ውጤት አይቷል፤
“ልጄ፣ ለነፍስህ ሰላም ይኑርህ፤ ጭንቀትህ እና ስቃይህ ለጥቂት ጊዜ ቢሆን ነው፤
“ከዚያም፣ በመልካም ይህን ብትጸና፣ እግዚአብሔርም ወደ ላይ ዘለአለማዊ ክብር ይሰጥሀል፤ ጠላቶችህንም በሙሉ ታሸንፋቸዋለህ።”
ትልቁ የማረጋገጥ እና የማጠናከሪያ ምሳሌ የሚሆነው የአዳኝ የሀጢያት ክፍያ ነው። የዓለምን ኃጥያት በራሱ ለይ ወሰደ። ሕመማችንን እና ሃዘናችንን ተሸከመ። መራራ ጽዋውን ጠጥቷል። በእያንዳንዱ ወቅት መታመኑን አረጋግጧል።
በከበረው የኃጢያት ክፍያው ምክንያት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ የፈተና ጊዜ ሊያበረታን ይችላል። እርሱ እኛን እንዴት እንደሚረዳን ያውቃል ምክንያቱም በሟችነት ውስጥ የሚሰሙን ፈተናዎች ሁሉ ተሰምቶታል። “የህዝቡን ህመምና በሽታ በራሱ ላይ ይወስዳል … ህዝቡን ከድካሙ እንዴት እንደሚረዳ ያውቅ ዘንድ ይህንን ያደርጋል።”
በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እያለ አዳኙ አብን ፈተናው ከእርሱ ላይ ማለፍ ይችል እንደሆነ እንደጠየቀ እንማራለን—ነገር ግን የአብ ፈቃድ ከሆነ አዳኝ እንደሚያደርገው ተናግሯል። በሌላ አነጋገር፣ አዳኙ ጥርጣሬን እና እርግጠኛ አለመሆንን አስተናገደ፣ ነገር ግን በሰማይ አባቱ ላይ እምነት ነበረው።
ወንድሞች እና እህቶች፣ የእናንተ የአቅም መፈተሽ እና መጠናከር የሞሮኒ ወይም የያዕቆብ ወይም የነቢዩ ጆሴፍን ላይመስል ይችላል። ነገር ግን ይመጣል! በቤተሰብ ሕይወት ፈተናዎች ውስጥ በጸጥታ ሊመጣ ይችላል። በህመም ወይም በብስጭት ወይም በሀዘን ወይም በብቸኝነት ሊመጣ ይችላል።
እነዚህ ጊዜያት ጌታ እንደተዋችሁ ማስረጃዎች እንዳልሆኑ እመሰክራለሁ። ይልቁንም፣ አንተን ለማጣራት እና ለማጠናከር በበቂ ሁኔታ እንደሚወዳችሁ ማስረጃዎች ናቸው። እርሱ የዘላለምን ሕይወት ሸክም እንድትሸከሙ ብርቱዎች እያደረጋችሁ ነው።
በአገልግሎታችን በእምነት ከቀጠልን፣ ጌታ ያጠራናል። እርሱ ያጠነክረናል። እናም አንድ ቀን፣ ወደ ኋላ መለስ ብለን እናያለን እና እነዚያ ፈተናዎች የእርሱ ፍቅር ማስረጃዎች መሆናቸውን እገነዘባለን። ከእርሱ ጋር በክብር መቆም እንድንችል እየቀረጸን እንደነበረ እናያለን። የጌታ ሐዋርያ ጳውሎስ በራሱ ህይወት መጨረሻ ላይ እንዳለው፣ “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ።”
እግዚአብሔር እንደሚያቃችሁ እመሰክራለሁ። የሚያጋጥሟችሁን ፈተናዎች እርሱ ያውቃል። እርሱ ከናንተ ጋር ነው፡፡ አይተዋችሁም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እመሰክራለሁ፡፡ እሱ ጥንካሬያችን፣ ቤዛችን፣ ተስፋችን ነው፡፡ የምናምነው ከሆነ፣ መንፈሳዊ ሃይላችንን እንድንሸከመው ከተጠራነው እያንዳንዱ ፈተና ጋር እኩል ያደርጋል። ስለዚህ የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።