የእግዚአብሔር ነቢያት
የነቢዩን ድምጽ ማዳመጥ እና መታዘዝ እስከ ዳግም ምጽአት ድረስ ያለውን መልካም ነገር ሁሉ ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።
ውድ ወጣቶች፣ እንዴት ያለ ውብ የጉባኤ ክፍለ ጊዜ ነው! ቀደም ሲል ሦስት የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ንግግር አድርገውልናል። እንዴት ያለ አስደናቂ በረከት ነው! በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ሄንሪ ቢ. አይሪንግ ንግግር ያደርጉልናል። መንፈሳዊ መነሳሳቱ ይቀጥላል!
ባለፈው ዓመት ባደረኩት ንግግር ላይ፣ ይህንን ዓለም እንዴት መጋፈጥ እንዳለብን ዳዊት ከጎልያድ ጋር ከነበረው አጋጣሚ ተምረናል። አምስቱን ድንጋዮች ታስታውሳላችሁ? ዛሬ፣ በእናንተ ዕድሜ በነበርኩበት ጊዜ ያነበብኩትን የብሉይ ኪዳን ታሪክ አካፍላለሁ፣ ያም እንደ ዋና ገፀ ባህሪ መሆን እንድፈልግ አድርጎኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ስሟን ስለማይነግረን፣ ትኖርበት በነበረው ከተማ ስም ሱነማዊቷ ሴት ብለን እንጥራት።
አንድ ቀን ነቢዩ ኤልሳዕ በሱነም በኩል እያለፈ ነበር፣ “ታላቅ ሴት [እንደ]ነበረች እና እንጀራ ይበላ ዘንድ [እንደጋበዘችው]። በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ [እንደነበር]” እናነባለን። ነቢዩ ኤልሳዕ በቤቷ እንዲመገብ በመጋበዙ በጣም የተደሰተ ይመስለኛል! ብዙ ጊዜም እነሱ ጋ ይሄድ ነበር፣ አንድ ቀን ሴቲቱ ለባሏ፣ “ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ” በማለት ተናገረች።
ሴቲቷ፣ “[አሁን] አውቃለሁ” አለች። ኤልሳዕን ነቢይ መሆኑን ሳታውቅ ወደ ቤቷ የጋበዘችው ይመስላል፤ ኤልሳዕ የተናገረውንና ያስተማረውን በጥሞና በማዳመጥ ምስክርነቷን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተቀበለች። (በዚያን ጊዜ ምንም ፎቶ አለመኖሩን አስታውሱ! ስለዚህ ነቢዩን ፊቱን ብቻ በማየት መለየት ከባድ ነበር።)
ታሪኩ ግን በዚያ ብቻ አያበቃም። ከእለታት አንድ ቀን ሴቲቱ ባሏን እንዲህ አለችው፣ “ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል።”
ይህች ታማኝ ሴት ነቢዩ ከተማዋን አቋርጦ ሲያልፍ የሚያርፍበት ቦታ እንዲኖረው በቤቷ ውስጥ አንድ ክፍል ለመሥራት ፈቃደኛ ነበረች!
ዛሬ ከዚህ ተሞክሮ ሃይለኛ ትምህርት መማር እንችላለን።
ጌታ ለሱነማዊቷ ሴት ኤልሳዕ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆነ መሰከረላት፣ እሷም ቤቷን በመክፈት እሱን ተቀበለችው።
እኛም ዛሬ ስለ እግዚአብሔር ነቢያት የግል ምስክርነትን መቀበል እና ልባችንን እና አእምሯችንን—ቤታችንን—በዚህ የመጨረሻ ቀናት የሰማይ አባታችን ለእኛ ላለው መልእክት መክፈት እንችላለን።
ውድ ወጣቶች፣ በህይወት ስላለ የእግዚአብሔር ነቢያት የግል ምስክርነት አለኝ ብላችሁ እራሳችሁን እንድትጠይቁ እጋብዛችኋለሁ።
ከመጀመሪያው እንጀምር።
ነቢይ ምንድን ነው? ነቢይ እግዚአብሔር ለእርሱ ይናገርለት ዘንድ የጠራው ሰው ነው። በጥንት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በምድር ላይ ነቢያት አሉ።
ነቢያት ባለራዕይ እና ገላጮች ናቸው። ይህም ሌሎች ማየት የማይችሉትን ማየት እንዲሁም ስለወደፊት ክስተቶች ትንቢት መናገር ይችላሉ ማለት ነው። ለችግሮችም ሊያዘጋጁን ይችላሉ። ነቢያት ከጌታ ትእዛዛትን እና መገለጥን ይቀበላሉ። ዘጠነኛው የእምነት አንቀፅ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ስለሚኖረው ቀጣይነት ስላለው መገለጥ ይናገራል። “እግዚአብሔር እስካሁን በገለጣቸው ሁሉ፣ አሁንም በሚገልጣቸው ሁሉ እናምናለን፣ እናም የእግዚአብሔርን መንግስት በተመለከተ ወደፊትም እርሱ በሚገልጣቸው ታላቅና አስፈላጊ ነገሮችም እናምናለን” ይላል።
ሽማግሌ ጌሪ ኢ. ስቲቨንሰን “ጌታ በዚህ ህይወት ወደ ደስታ፣ በሚቀጥለውም ህይወት ወደ ሰለስቲያል ክብር ሊመራን ስለሚፈልግ ዛሬም ትእዛዛቱን እና ፈቃዱን ለነቢያቱ መግለጥ ቀጥሏል” በማለት ተናግረዋል።
ነቢያትም ወንጌልን ያውጃሉ እንዲሁም በምድር ላይ ላሉ ሁሉ የተነሳሱ የእግዚአብሔር አስተማሪዎችና መልእክተኞች ናቸው።
እያንዳንዱ የቀዳሚ አመራር እና የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን አባል ነቢይ፣ ባለራዕይ እና ገላጭ ነው። በጌታ መሪነት በቡድን የማገልገል፣ ትምህርትን የማወጅ እና የመተርጎም እንዲሁን ለቤተክርስቲያኗ ፖሊሲ የማቋቋም ስልጣን አላቸው። እነዚህ የቡድን ውሳኔዎች አንድ ሆነው በመስማማት የሚወስኑባቸው መሆን ስላለባቸው በጥንቃቄ ይጸልያሉ እንዲሁም ያጠናሉ። በዚህ መንገድ ጌታ ፈቃዱ እንደሚፈጸም ያረጋግጥልናል።
ነቢያት ስለ ክርስቶስ ይመሰክራሉ—ስለመኖሩ፣ ስለ አገልግሎቱ እና መለኮታዊነቱ።
ከመፅሐፈ ሞርሞን የተወሰኑ የነቢያትን ምስክርነቶች እናንብብ።
አቢናዲ እንዲህ አወጀ፦
“እግዚአብሔር ራሱ በሰው ልጆች መካከል እንደሚወርድና፣ ህዝቡንም ያድናል።
“በስጋ በመኖሩም የተነሳ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ይጠራል።”
ላማናዊው ሳሙኤል ኢየሱስ ክርስቶስም “የእግዚአብሔር ልጅ፣ የሰማይና የምድር አባት፣ የሁሉም ነገር ፈጣሪ ነው” ሲል መስክሯል።
ነቢዩ ሞሮኒም “ኢየሱስን ማየቴን ታውቃላችሁ፣ እናም እርሱም ፊት ለፊት ተናግሮኛል” ብሏል።
ክርስቶስ ኔፋውያንን በጎበኛቸው ጊዜ ካደረጋቸው የመጀመሪያ ነገሮች ውስጥ አንዱ አስራ ሁለቱን ሐዋርያት መጥራቱ ነው። ሕዝቡንም “ከመካከላችሁ የመረጥኋቸውን የእነዚህን የአስራ ሁለቱን ቃላት በጥንቃቄ የምታዳምጡ ከሆነ የተባረካችሁ ናችሁ” አላቸው።
አሁን፣ ልጆችን ለሚያሳድጉ ወላጆች ወይም ለሌሎች የቤተሰብ አባላት ጥቂት ቃላትን ላካፍል። ጌታ እራሱ የደህንነት እቅድ እውነትን ለአዳምና ሔዋን አስተምሯል። ከዚያም “እነዚህን ነገሮች ለልጆቻችሁ በነጻ እንድታስተምሩ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” ብሎ ተናግሯቸዋል።
በነፃ ማስተማር ማለት ምን ማለት ነው? ይህ የወንጌልን እውነት መማር፣ ስለዚያም የግል ምስክርነትን ማግኘት እና ያንን እውቀት ለልጆቻችን ማካፈል ማለት ነው። መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ የማስተማሪያ ጊዜዎችን ማዳበር ነው። በዚያም እውቀትና ምስክርነት መሰረት መኖር ነው።
መፅሐፈ ሞርሞን 2,060 ብላቴና ተዋጊዎችን “የእውነት እና የጥሞና ሰዎች ነበሩ፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንዲጠብቁና በፊቱም በቅንነት እንደሚራመዱ ተምረዋልና” በማለት ይገልፃቸዋል። እነዚህ ወጣቶች በዚያን ጊዜ የጦር መሪያቸው እና ነቢያቸው የነበረውን ሄለማንን በታማኝነት ታዘዙ እንዲሁም እናቶቻቸው ልባቸውን በእውነት እና በእምነት እንደሞሉ ተገንዝበው ነበር።
ወላጆች፣ ብዙ ድምፆች አንዳንዴም ብዙ ጨለማ ባለበት በዚህች ዓለም ውስጥ ልጆቻችንን በብርሃን እና በእውነት እንድናሳድግ እግዚአብሔር ራሱ አዞናል። ለልጆቻችን የሚያድኑ የወንጌል እውነቶችን እንድናስተምር አደራ ሰጥቶናል። ይህን እራሳችን ለማድረግ ካልቻልን፣ ዓለም አያስተምርልንም።
ውድ ወጣት ጓደኞቼ፣ ለእናንተ ግብዣ አለኝ፦ በመጪዎቹ ቀናት፣ እንድትንበረከኩ፣ ልባችሁን እንድትከፍቱ፣ እና በእርሱ የመረረጡት ነቢያት እና ሐዋርያቱ ዛሬ በምድር ላይ የእርሱ ድምፅ መሆናቸውን እንዲያረጋግጥላችሁ ለሰማዩ አባት በእምነት እንድትጸልዩ እጋብዛችኋለሁ።
ሱነማዊቷ ሴት ያንን ምስክርነት በመንፈስ ቅዱስ በኩል ማግኘት እንደምንችል አስተምራናለች። እነርሱ በእግዚአብሔር የተቀቡ እንደሆኑ ካወቅን፣ ድምፃቸውን በመተማመን፣ በእምነት እና በተስፋ ስንታዘዝ ተግዳሮቶቻችን በቀጣይነት ቢኖሩብንም ህይወታችን ቀላል እንደሚሆን ቃል እገባላችኋለሁ። የነቢዩን ድምጽ ማዳመጥ እና መታዘዝ አዳኛችን ዳግም እስኪመጣ ድረስ ያለውን መልካም ነገር ሁሉ ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።
የዓለም ክፋት እያደገ ነው፣ ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እና መንግስቱ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጠንካራ ናቸው። ጽዮን ጌጠኛ ልብሷን ለብሳለች፣ የክርስቶስ ዙፋን አይወድቅም። ጌታ በምስክርነታችን እንድንበረታ፣ በእምነት እንድንሞላ እና በየቀኑ ንስሀ እንድንገባ ይጠብቃል። አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራውን እንድንፈጽም በእያንዳንዳችን ላይ ይተማመናል።
አንድ ጊዜ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ፣ “ወንድሞች፣ ለዚህ ታላቅ ስራ ወደፊት አንሄድምን?” በማለት ተናግሯል። ነገር ግን የእኔ መልእክት በዋናነት ለእናንተ ለወጣቶች ስለሆነ ወንድሞች ከማለት ይልቅ ወጣቶች የሚለውን ቃል መጠቀም እፈልጋለሁ። ዝግጁ ናችሁ?
“[ወጣቶች]፣ ለዚህ ታላቅ ስራ ወደፊት አንሄድምን? ወደኋላ ሳይሆን ወደፊት ሂዱ። በርቱ፣ [ወጣቶች]፤ ወደ ድልም ሂዱ!” ልባችሁ ትደሰት፣ ሃሴትም ታድርግ”
በህይወት ስለሚገኙ ነቢያት ምሪ እና ስለተቀደሱ ጥረታቸው አመስጋኝ ነኝ። እነርሱ ዛሬ መንግሥቱን በምድር ላይ እንዲያራመዱ፣ እንዲመሰርቱ እና እንዲመሩ በእግዚአብሔር እንደተጠሩ የእኔን ጠንካራ ምስክር እሰጣችኋለሁ። ሁልጊዜም እንዲህ ይሆናል። ሁልጊዜ ባሮቹን የሚመርጠው ጌታ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።