የኃጢያት ክፍያን የሚያቀርብ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር
ፈውስ እና ይቅርታ እያንዳንዳቸው በሙላት የሚገኙት በኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢያት ክፍያ ውስጥ ነው።
ለፕሬዚደንት ራስል ኤም. ኔልሰን ያለኝን ፍቅር እና በእያንዳንዳችን ላይ ስላሳደሩት አስደናቂ ተጽእኖ አመስጋኝ መሆኔን እገልጻለሁ። እንዲሁም፣ የፕሬዚዳንት ዳልን ኤች. ኦክስን ክቡር ህይወት ስለጠበቀ እና ስላጎላ እግዚአብሔርን ስለሁላችንም አመሰግናለሁ።
በእያንዳንዱ የሚያልፉ ዓመታት፣ ለአዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ለምህረት የሃጢያት ክፍያው ትልቅ የፍቅር ስሜት አለኝ። የእርሱ የላቀ ፍቅር፣ በሞት እና ሃጢያት ላይ ድል ማሳካቱ የሰብአዊ ታሪክ ዋናው አስተዋጸኦ ውጤት ነው። የእርሱን መለኮታዊ ስጦታ መረዳት ለእኔ ከመቃብር በላይ ቀጣይነት ያለው ማብቂያ የሌለው ሰማያዊ ትሩፋት ነው።
የሃጢያት ይቅርታ እና በሌሎች ሃጢያት ምክንያት የተፈጠረን ቁስል መፈወስ የእግዚአብሄር ፍቅር የተገለጠበት ዋናው ተዓምራዊ የአዳኙ ሃያል ርህራሄ ነው።
የእኔ ምኞት በጣም አሳሳቢ በሆነ ሃጢያት ምክንያት ይቅርታን ለሚሹ ተስፋን መስጠት እና በሌሎች ሃጢያት ምክንያት ለተፈጠረ አሰቃቂ ቁስል ፈውስን ለሚሹ መጽናናትን መስጠት ነው።
ፈውስ እና ይቅርታ እያንዳንዳቸው በሙላት የሚገኙት በኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢያት ክፍያ ውስጥ ነው።
በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት
ምናልባት ከባድ ሃጢያትን አድርጋችሁ ከሆነ እና ሙሉ ለሙሉ ንሰሃ ልትገቡ የምትወዱ ከሆነ እንዲሁም የይቅርታን የማይነገር ሃሴት እንዲሰማችሁ የምትሹ ከሆነ፣ እባካችሁ ይህ ተዓምር እየጠበቃችሁ እንደሆነ እወቁ። አዳኙ ያለማቋረጥ ፣ “ወደእኔ ኑ” በማለት ይጣራል።
እምነታችሁን በአዳኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ማጠናከር እርሱን ለማወቅ፣ በእርሱ ለማመን፣ ልባችሁን ለእርሱ ለመስጠት የነፍሳችሁን መሻት ያበረታታል። ኢኖስ፣ “ጌታ፣እንዴት ሊሆን ቻለ?’’ በማለት ስለራሱ ይቅርታ ጠየቀ። ጌታም እንዲህ መለሰ፥ “ባላየኸውና ሰምተህ በማታውቀው በክርስቶስ ባለህ እምነት ምክንያት ነው።”
ሞሮኒ እንዲህ ሲል አከለ፣ ‘’እናም ለራሳችሁ ኃጢአተኝነትን በሙሉ ከካዳችሁ፣ እናም በሙሉ ኃይላችሁ እና አዕምሮአችሁ እና ጉልበታችሁ እግዚአብሔርን ከወደዳችሁ፣…በክርስቶስ…ጸጋው በቂ ይሆንላችኋል።”
ከሃጢያት ዘወር ማለት፣ ወደ እግዚአብሔር መመለስ፣ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላችሁን እምነት ማጠናከር ውብ ጅማሬዎች ናቸው። በትህትና ፈቃዳችሁን ለእግዚአብሄር ማስገዛት ከባድ ሃጢያታችሁን ለኤጲስ ቆጶሳችሁ ወይም ለቅርንጫፍ ፕሬዚዳንታችሁ ማሳወቅን ያካትታል። ነገር ግን ሙሉ ይቅርታችሁ ከጌታ ይመጣል። ይቅርታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አማካይነት የሚሰጥ መለኮታዊ ስጦታ ነው።
ታማኝነት
በእውነተኛነት ወደ እግዚአብሔር የመመለስ ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ከሰማዩ አባታችሁ፣ ከራሳችሁ፣ ጉዳት ከደረሰባቸው፣ እና ከክህነት አመራሮቻችሁ ጋር ታማኝ ከመሆን ቁርጠኝነት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። የሰማይ አባት ወደ እርሱ ለመምጣት ባላችሁ፣ እንዲሁም በተሰበረ ልብ እና በተዋረደ መንፈስ ለመምጣት ባላችሁ ቁርጠኝነት ይደሰታል። የተዋረደ መንፈስ ማግኘት ማለት በትህትና ራስን በእግዚአብሄር እጅ ላይ ማስቀመጥ ነው፤ የተሰበረ ልብ ሃዋርያው ጳውሎስ “አምላካዊ ሃዘን፣” በማለት የገለጸውን ያመጣል ምንም የሚያስከፍል ቢሆን ወደ እርሱ ለመመለስ የጠለቀ የነፍስ መቃተት ነው።
የተሰበረውን መጠገን
ናፍቆታችሁ የሰበራችሁትን ለመጠገን እንድትፈልጉ ይመራችኋል። ሆኖም፣ አንዳንድ ነገሮችን ለመጠገን በአናንተ ሃይል ውስጥ እንዳልሆኑ በመገንዘብ፣ ጌታ በጸጋው፣ በድርጊታችሁ ምክንያት የተጎዱትን እንዲፈውስ በትጋት ጸልያችኋል።
በሌሎች ላይ የደረሰን የከባድ ሃጢያት ጠባሳ ለመቋቋም ብዙ ጊዜ ህመሙ ከበድ ያለ ነው። እናንተ “ያደረሱትን ቁስል ለመጠገን በቅናት የጣሩትን” የሞዛያን ልጆች ምሳሌ ትከተላላችሁን? ምናልባት እያያችሁት ስላልሆነው ነገር ከምታከብሯቸው ጋር ተነጋገሩ።
ይህንን ንግግር እያዘጋጀሁ ሳለሁ፣ በንሰሃ እና ወደ ቤተክርስቲያን በመመለስ ሂደት ላይ ከነበረ ከአንድ ግለሰብ ያልተጠበቀ ኢሜይል ደረሰኝ። የቀድሞ ባለቤቱ “ከዘለዓለማዊ ጋብቻቸው፣ [ከልጆቻቸው ጋር ከነበራቸው ችግር]፣ ከገንዘብ እጦት፣ …ወጪዎችን ለማስተካከል ካለመቻል፣ [እና] ከመከዳት ጥልቅ አስጨናቂ ስሜት” ጉዳት ምክንያት አሁንም በማዘን ላይ ነበረች።
የክህነት አመራሩ እንዴት “[ለቀድሞ ባለቤቱ እና ልጆቹ ይበልጥ ምን] ማድረግ እንዳለበት በጸሎት እንዲያስብ [ለመጠየቅ] እንዴት እንደተሰማው” አካፈለኝ። በፍቃድም፣ ይህን ኤሜሉን አካፍላለሁ።
“[በመጀመሪያ] እኔ በፍቺው ውሳኔ የሰጠሁት [ገንዘብ] የበዛ ልግስና መስሎኝ ነበር፣ ነገር ግን የቅርንጫፍ ፕሬዘዳንቴ ስለጉዳዩ ለሁለት ሳምንታት ያህል እንድጾም እና እንድጸልይ አበረታታኝ። …
“በመጀመሪያ፣ ተጨማሪ ካሳ በመስጠቱ ሀሣብ ተቸግሬ ነበር። “ኃጢአቶቼ ገንዘብ ነክ ስላልሆኑ፣ ‘ለጋስ ማካካሻ’ በእውነት ምን ማለት እንደሆነ አሰብኩ … [ነገር ግን] ብዙም ሳይቆይ በገንዘብ ላይ ብቻ እንዳልሆነ ተረዳሁ።
“የክህነት አመራሮቼ [ከቀድሞዋ ባለቤቴ] እና ልጆቼ ጋር ተገናኙ እናም አሁንም ችግር ላይ እንደሆኑ እና እንዳልተፈወሱ ተገነዘቡ።’’
‘’አዲሱ ግቤ በእምነት ወደፊት መቀጠል ነበር… እኔም በቀላሉ ያለምንም ግዴታ የመርዳት ፍላጎቴን ገለጽኩ። … ከተጣራ ገቢዬ ትርጉም ያለውን ድርሻ [ለቀድሞ ባለቤቴ የተወሰነ መጠን ያለውን] ቼክ ለመላክ ወሰንኩ። ልክ የመጀመሪያውን ክፍያ ከመፈጸሜ በፊት፣ ጌታ [የዚያን ሁለት እጥፍ] መክፈል [እንደሚገባኝ በአእምሮዬ አሳሰበኝ]።
‘’ካሳው ስለገንዘብ ብቻ እንዳልነበረ አወቅሁ። ህይወቴን በትህትና ለጌታ ስለማስገዛት ነው።… ገንዘቡ በከንቱ ምርጫዬ ምክንያት ከቤተሰቤ የወሰድኩትን ለመተካት የሚረዳ ነው። በምላሹ ምንም ሳትጠብቅ እና መንፈስን እንድትሻ ስለሚከፈሉ ክፍያዎች እንዳታስብ ለመርዳት ቃልኪዳንን ስለማድረግ እና ስለመጠበቅ ነው።’’
የሰበራችሁትን ለመመለስ የምታደርጉት ጥረት ከገንዘብ ጋር የሚገናኝ አይደለም፣ ነገር ግን ከጌታ ጋር በትህትና ስትመካከሩ፣ ምናልባትም ተጨማሪ የምታደርጉት ነገር እንዳለ ታውቃላችሁ።
ቀስ በቀስ የሚመጣ መለኮታዊ ማረጋገጫ
የጌታን ምህረት ስትሹ፣ የእርሱን ሙሉ ተቀባይነት በምትጠብቁበት ትእግስተኛ ሁኑ። ይህን የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅስ አስቡበት፦
“በጠለቀ ትህትና ራሳቸውን አዋረዱ፤ እናም … በብርቱ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ አዎን፣ ቀኑን በሙሉ። … [ነገር ግን] በክፋታቸው የተነሳ ጌታ ጩኸታቸውን ለማዳመጥ ዘግይቷል።”
“ይሁን እንጂ፣ ጌታ ፀሎታቸውን ሰምቷል፣ ሸክማቸውንም ማቃለል እንዲጀምሩ፤ …እና በመጠን መበልጸግ ጀመሩ።”
በመጠን ጌታ በረከቱን እና ማረጋገጫውን ሲሰጣችሁ፣ ታገሱ።
በጌታ ጊዜ፣ አልማ ለልጁ እንደተናገረው፣ ድምጹ ፣ “እነዚህ ነገሮች እንዲያስቸግሯችሁ አትፍቀዱ።“ ብሎ ሲናገራችሁ ትሰማላችሁ ጌታ ህያው እንደሆነ፣ አንድ ቀን፣ ወደ አዳኙ ለመመለስ በቀጠላችሁ ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ ‘’በልጁ ስራ ምክንያት [ከልባችሁ] ወቀሳን ያስወግዳል።”
መጎዳት እና መሰቃየት
በሌላ ሰው ከባድ ኃጢአት ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ለተጎዳችሁ፣ የአዳኙን ፍቅር እና ርህራሄ፣ መጽናናቱን እና ሰላምን ለመካፈል እጓጓለሁ።
የተሰማችሁን ሃዘን፣ የልብ ስብራታችሁን፣ ማጣታችሁን፣ የመከዳትን አሰቃቂ ስሜት፣ በገመታችሁት መጠን የህይወታችሁን መመሰቃቀል—፣ጌታ እንደሚያውቃችሁ እና እንደሚወዳችሁ ፍጹም የሆነውን ማረጋገጫዬን እሰጣችኋለሁ። ወደ እርሱ ቅረቡ። እርሱ መጽናናታችሁ እና ሃይላችሁ ነው፤ ከፍ ሊያደርጋችሁ መላእክቱን ይልካል። ህመማችሁ የሚጠፋው፣ ሃዘናችሁ የሚሽረው፣ አላስፈላጊ ትውስታዎች የሚረሱት መቼ ነው? እኔ አላውቅም። ነገር ግን ይህን አውቃለሁ፤ እርሱ ከስቃያችሁ ትቢያ ውስጥ ውበትን ለማምጣት ሃይል አለው።
ውድ የግራንድ ብላንክ ሚቺጋን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው የማይበገር እምነት፣ በድፍረት እና ከራስ ወዳድነት ነፃ በመሆን የአዳኙን አቻ የሌለው ፍቅር እና ፀጋ ተቀብለዋል እንዲሁም በመጪዎቹ ሳምንታት እና ወራት ውስጥ ይቀበላሉ።
በእርሱ ላይ እምነታችሁን ማድረግን በቀጠላችሁ ጊዜ፣ የጨለማው ጭጋግ እና የምሽቱ መራራ እንጉርጉሮ በማለዳ ብርሃን ወደ ደስታ እና ሰላም የእንባ ፏፏቴ ይለወጣል። ሀዘናችን ወደ ደስታ ይለወጣል። … ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ [ማንም] የለም።” ያም ቀን ይመጣል። ያም እንደሚመጣ እመሰክራለሁ።
የኃጢያት ክፍያን የሚያቀርብ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመገኘት ይቻላል፣ ነገር ግን ሁላችንም የአዳኝ የኃጢያት ክፍያ ጸጋ ሁልጊዜ ያስፈልገናል። ፕሬዘደንት ዳሊን ኤች ኦክስ እንዳስተማሩት፦ “በሟችነት ውስጥ ባለው የኃጢያት ክፍያ ልምዱ ምክንያት፣ አዳኛችን በሁሉም ቦታ ያሉትን ወንዶች እና ሴቶች ማፅናናት፣ መፈወስ እና ማጠናከር ይችላል፣ ነገር ግን ይህን የሚያደርገው እሱን ለሚፈልጉ እና የእርሱን እርዳታ ለሚጠይቁት ብቻ እንደሆነ አምናለሁ። ሐዋርያው ያዕቆብ እንዳስተማረው፣ ‘በጌታ እይታ እራሳችሁን ትሁት አድርጉ፣ እናም እርሱ ከፍ ያደርጋችኋል’ (ያዕቆብ 4፥10)። በእርሱ ስናምን እና ለእርሱ እርዳታ ስንጸልይ ለበረከቱ ብቁ እንሆናለን።”
ሽማግሌ ሮበርት ኢ. ዌልስ
አሁን 97 አመት ከሆናቸው፣ከውድ ጓደኛዬ እና ከተከበሩት አጠቃላይ ባለስልጣን፣ ሽማግሌ ሮበርት ኢ ዌልስ፣ ከ60 ዓመታት በፊት የነበራቸውን ልምድ እንዳካፍል ፈቃድ አገኘሁ።
በ1960 (እ.አ.አ) በፓራጓይ እየኖሩ በአለም አቀፍ የባንክ ሰራተኛነት ተቀጥረው በነበሩበት ወቅት፣ የ32 ዓመቱ ሮበርት ዌልስ እና ባለቤቱ ሜሪል እያንዳንዳቸው በሁለት የተለያዩ አውሮፕላኖች አብራሪ ሆነው ከኡራጓይ ወደ ፓራጓይ ይበሩ ነበር። ጥቅጥቅ ደመና ስላጋጠማቸው፣ ሮበርት እና መሪል የእይታ እና የሬድዮ ግንኙነታቸው ተቋረጠ። የባለቤቱ አውሮፕላን የተከሰከሰበትን ባወቀበት ስፍራ ሮበርት በፍጥነት ሊያርፍ ቻለ። ባለቤቱም ሆነ ከእርስዋ ጋር ይበሩ የነበሩ ሁለት ጓደኞቿ ሊተርፉ አልቻሉም። በአሱንሲዮን በቤቱ የነበሩ ልጆቹ ሰባት፣ አምስት፣ እና ሁለት ዓመታቸው ነበር።
ሽማግሌ ወልስ ስለሃዘኑ ሲናገር፤
“ስሜቶቼን የበላውን በውስጤ የተከመረን ህመም ለመግለጽ ቃላቶች ለዘለለም በቂ ሊሆኑ አይችሉም። ከፍተኛ የሃዘን እንባ በቀላሉ መፍሰሱን ሊያቆም አይችልም። ይባስ ብሎ፣ አእምሮዬ ከባለቤቴ ህልፈት አሰቃቂ እውነታ ጋር ለመታገል እየሞከረ ባለበት ወቅት፣ ለመከስከሷ እራሴን ተጠያቂ በማድረግ ከፍተኛ በሆነ የጸጸት ልምምድ ውስጥ ራሴን አገኘሁት።’’
ሮበርት ይበልጥ ትኩረት በሚፈልግ ሁኔታ አውሮፕላኑ ፍተሻ እንዲደረግለት ባለማድረጉ እና ለባለቤቱም በቂ የሆነ የበረራ መመሪያን ባለመስጠቱ ራሱን ጥፋተኛ አድርጓል። የቸልተኛነት የጸጸት ስሜት ተሰምቶታል።
ሮበርት እንዲህ አለ፦
“አዕምሮዬ ወደ ጨለማ ዳመና ውስጥ ገባ።” … በተራ ነበር የምኖራው … [ለልጆቼ ጥቅም] እንጂ ለምንም አልነበረም።”
“ለመቀጠል…ፍላጎት አጥቻለሁ።”
በጊዜ ሂደት፣ ሮበርት ጥልቅ በሆነ መንፈሳዊ ልምምድ ተባርኳል። እንዲህ ያስታውሳል፤
“በአንድ ምሽት፣ በግምት ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ለጸሎት በጉልበቴ ተንበርኬ ሣለሁ፣ አንድ ተዓምር ተከሰተ። ወደ ሰማይ አባቴ እየጸለይኩ እና እየተማጸንኩ በነበርኩበት ወቅት፣ ልክ አዳኙ ከጎኔ መጥቶ ለነፍሴ እና ለጆሮዬ እነዚህን ድምጾች ጉልህ በሆነ ድምጽ ሲናገር ሰማሁ፤ ‘ሮበርት፣ የሃጢያት ክፍያዬ ለሃጢያትህ እና ለስህተቶችህ ዋጋን ከፍሏል። ባለቤትህ ይቅር ትልሃለች። ጓደኞችህ ይቅር ይሉሃል። ሸክምህን አነሳልሃለሁ። …’
‘’ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ የጸጸት ሸክም [እና ተስፋ መቁረጥ] በሚገርም ሁኔታ ከላዬ ተነሳ። እኔም ማዳን ሆነልኝ! ወዲያውኑም የጌታ የሃጢያት ክፍያው ሃይል የከበበኝ መሆኑን ተረዳሁ እናም … ይህም በቀጥታ ከእኔ ጋር የተያያዘ ነበር። ከዚህ ቀደም በፍጹም የማላውቀውን ብርሃን እና ሃሴት… ተለማመድኩ። የማይገባኝን—የጌታን የጸጋ ስጦታ ተቀበልኩ… የማይገባኝ ነበር—ልቀበለው የሚያስችለኝን ምንም ነገር አላደረግሁም፣ ነገር ግን ይሁን እንጂ እርሱ ለእኔ ሰጠኝ።’’
ወንድሞች እና እህቶች እያንዳንዳችን “በእግዚአብሔር ጸጋ በክርስቶስ ደም በፈሰሰው በክርስቶስ እንቀደስ፣ ነውርም የሌለን እንሁን።”
የአዳኛችንን እና ቤዛችንን ፍቅር፣ ምህረት እና ጸጋ እመሰክራለሁ። እርሱ ህያው ነው። እኛ የእርሱ ነን፤ እኛ የቃል ኪዳን ልጆች ነን። እሱን አምነን ስንከተለው እና እሱን ስንታመን ከሀዘናችን እና ከኃጢአታችን ያነሳናል። ከዚያ፣ ከዚህ ሟች ህይወት ባሻገር፣ በአባታችን ቤት፣ ከእርሱ ጋር ለዘላለም እና ለዘላለም እንኖራለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።