ወደ እግዚአብሔር ተመልከቱ እና በህይወት ኑሩ
ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ እንዲሁም ሃገራት ሊበለጽጉ የሚችሉት ወደ እግዚአብሔር በመመልከት ብቻ ነው።
ባለፈው በሰኔ፣ በደቡብ አፍሪካ ሌሶቶ በምትባል ሃገር አሰቃቂ አደጋ ተከስቶ ነበር። ማፑትሶ ከተባለች አንዲት ቅርንጫፍ ቤተክርስቲያን ትንሽዮ አውቶቢስ 20 ወጣት ልጃገረዶችን እና ሰባት ያህሉ የሚሆኑ መሪዎቻቸውን ይዞ ለወጣት ሴቶች መሰባሰብ ወደ ዋና ከተማው፣ ማሴሩ፣ እየተጋዘ ነው። በማለዳው ሰዓቶች ውስጥ ባለሁለት መስመር የፍጥነት መንገድ ላይ እየተጓዙ እያለ፣ ከተቃራኒ አቅጣጫ እየመጣ የነበረ አንድ ተሽከርካሪ ሌላውን ተሽከርካሪ ለማለፍ ሲሞክር በአውቶቢሱ ተይዞ ወደነበረው መስመር መጣ። ሊከሰት የነበረውን የግጭት አደጋ ለማስቀረት በቂ ስፍራም ሆነ ጊዜ አልነበረም እና በሰከንዶች ውስጥ ተሽከርካሪዎቹ ተጋጭተው መንገዱን ስተው በመንከባለል፣ በእሳት ተሸፈኑ።
በውስጡ ከነበሩት ውስጥ፣ ስድስት ወጣት ሴቶች፣ ሁለት የወጣት ሴቶች አመራሮች እና የቅርንጫፍ ፕሬዘዳንት እና ባለቤቱን ጨምሮ አስራ አምስት ሰዎች በአደጋው ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። ከአደጋው የተረፉት የቤተሰቡ አባላት እና ጓደኞች የብስጭት፣ የድባቴ፣ እና የቁጭት ስሜትን ጨምሮ የሃዘን ስሜታቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ስሜቶች እና ያልተመለሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ አንዳቸው ሌላኛውን አፅናንተዋል እንዲሁም በተቀደሰ ዝማሬ፣ በቅዱሳት መጻህፍት፣ እና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ተመልሰዋል። ከአደጋው የተረፈች የአስራ ሰባት ዓመቷ ሴትሶአና ሴለቤሊ እንዲህ በማለት መስክራለች፣ ‘’ኢየሱስ ክርስቶስ ይወደናል ልባችን ምንም እንኳን ቢታመምም እርሱ ከእኛ ጋር ነው።’’
አንዲት ወጣት ሴት በቃጠሎ ምክንያት ለህክምና በሆስፒታል ውስጥ ክትትል ከምትወስድ አንዲት መሪ ጋር መፅሐፈ ሞርሞንን በአንድነት ታጠና ነበር። አንዷም እንዲህ አለች፣ ‘’በቅርቡ ከሞሮኒ እያነበብኩኝ ነበር፣ እናም ሞሮኒም ይሰማኝ የነበረውን በትክክል ተናግሯል። እርሱም በተናገረ ጊዜ፣ ይህንን እየተናገረ ያለ ይመስል ነበር፣ ‘’እነዚህን ቃላት ልትማሪ ይገባል ምክንያቱም በእነዚህ ነገሮች ውስጥ ለማለፍ እንዲረዳሽ የተጻፈ ስለሆነ ነው።”
ለእነዚህ ለጠፉት በተደረገ የጋራ የሃዘን ስነስርዓት፣ ሽማግሌ ሲያቦኛ መኪዜ ከአካባቢ ሰባዎቹ አንዱ እንዲህ ሲሉ መክረዋል፣ ‘’በዚህ ጊዜ ሁላችንም ወደ ጌታ ልንመለስ እና ልባችንን እንዲያጽናና ልንጠይቀው እና … እየተሰማን ያለውን ህመም እንዲያስታግስልን ልንጠይቀው ይገባል።’’ በአጎራባች ከነበረ ከሌሪቤ ቅርንጫፍ የወጣት ሴቶች ፕሬዘዳንት፣ ማምፎ ማኩራ፣ “ወደ ጌታ ተመለሱ፣ እናም ፈቃዱን ለመቀበል ብርታትን ፈልጉ’’ በማለት አጠንክረው ተናግረዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘የእምነታችን ራስና ፈጻሚ’ ነው [ዕብራዊያን 12:2]። ዞር አትበሉ ነገር ግን ወደ እርሱ ተመልከቱ።”
ወደ እርሱ ተመልከቱ። ቃላቶቿ አልማ ለልጁ ለሄለማን የመከረውን ያስተጋባሉ፦ ‘’እግዚአብሔርን በመመልከት በህይወት መኖራችሁን እዩ።’’ አልማ ሊያሆናን እንደ ምሳሌ በመጠቀም የሌሂን እና የህዝቡን አጋጣሚ ጠቀሰ፦ “እነሆም አባቶቻችንም ወደ ቃል ኪዳን ምድር በቀጥተኛው መንገድ የሚያመራቸውን ኮምፓስ እንደተከተሉት አይነት ወደ ዘለዓለማዊው ደስታ የሚያመራ ቀጥተኛ መንገድ የሆነውን የክርስቶስን ቃል እንደ መቀበል ቀላል ነው።” አልማም እንዲህ አለ፣ “እነርሱ ቢመለከቱት በህይወት ይኖሩ ዘንድ ነው። … እናም የምንመለከት ከሆነ ለዘለዓለም እንኖራለን።”
በሌላ ወቅት፣ አልማ በእባቦች ምክያት ይሰቃዩ የነበሩት የጥንት እስራኤላውያን በሙሴ ከፍ ተደርጎ የተያዘውን የነሃስ እባቡን ምሳሌ ጠቅሷል። ጌታ ለሙሴ የእባብን ምሳሌ እንዲሰራ እና በማማ ላይ እንዲሰቅለው ያዘዘው “የተነደፈ እያንዳንዱ ሰው እርሱን ባየ ጊዜ ህይወት ይኖር ዘንድ ነበር።” አልማም የነሃሱ ቅርጽ በመስቀል ላይ የተሰቀለውን የክርስቶስን ምሳሌ እንደሚያመለክት አብራርቷል። ብዙዎች አይተው በህይወት ኖሩ፣ ነገር ግን በአልማ ቃላት መሰረት ሌሎቹ፣ ማየት እስኪሳናቸው እና እስኪጠፉ ድረስ ‘’ደንዳና ነበሩ’’።
አልማ እንዲህ በማለት ጠየቀ፦
“ወንድሞቼ ሆይ፣ ትፈወሱ ዘንድ በቀላሉ በዓይናችሁ በመመልከት ለመፈወስ የምትችሉ ከሆነ፣ በፍጥነት አትመለከቱምን፣ ወይንስ ትጠፉ ዘንድ ዐይኖቻችሁን በዚያ ላይ ባለማመንስ ልባችሁን ማጠጠር፣ እናም ሰነፍ መሆን ይሻላችኋልን?”
“… በዐይናችሁ ወደዚህና ወደዚያ ተመልከቱ፣ እናም የእግዚአብሔር ልጅ ህዝቡን ሊያድን እንደሚመጣና፣ ለህዝቡ ኃጢያት ክፍያ እንደሚሰቃይና እንደሚሞት፣ እናም ሰዎች እንደስራቸው በመጨረሻውና በፍርዱ ቀን እንዲፈረድባቸው በፊቱ ይቆሙ ዘንድ ትንሳኤን ያመጣ ዘንድ በድጋሚ ከሙታን እንደሚነሳ ማመን ጀምሩ።”
በእርግጥ፣ “ወደ እግዚአብሔር ተመልከቱ እና በህይወት ኑሩ’’ የሚለው ምክር ለእኛ በዘለዓለማዊው ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በምድራዊ ህይወታችን በባህርይ እና በጥራት ሁሉንም ልዩነት የሚፈጥር ነው። ባለፈው የጠቀስናት የሌሶቶ የወጣት እህት ሰለቤሊ ቃላትን አስታውሱ—’’ምንም እንኳን ልባችን ቢታመምም ኢየሱስ ክርስቶስ ይወደናል፣ እርሱ ከእኛ ጋር ነው።”
ዲያብሎስ በክፋት በሚነሳበት እና እያንዳንዱ ሰው ፍጹም በማይሆንበት ይህ የወደቀው ዓለም ተፈጥሮ ነው፣ በዚህም ቅሬታ እና ጥቃት፣ ስቃይ እና ሃዘን፣ ውድቀት እና እጦት፣ ስደት እና የፍትህ እጦት ይገኛል። ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ እንዲሁም ሃገራት ሊበለጽጉ የሚችሉት ወደ እግዚአብሔር በመመልከት ብቻ ነው። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “በአዳኙ አማካኝነት፣ መጨረሻ በሌለው የኃጥያት ክፍያ በኩል እያንዳንዳችንን ከደካማነት፣ ከስህተቶች እና ከኃጥያት ስላዳነን እና እናንተ የነበሩባችሁን ህመሞች፣ ሀሳቦች፣ እና ሽክሞች አልማ 7፥11–13]፣ ስለተለማመዳቸው፣ እናንተ በእውነት ንስሀ ስትገቡና እርዳታውን ስትሹ ከዚህች አስጨናቂ አለም ከፍ ማለት ትችላላችሁ።”
በመፅሐፈ ሞርሞን ከዚህ የበለጠ የተስፋ ቃል በብዛት ተደጋግሞ አልተገለጸም፥ ‘’ትዕዛዛቴን እስከጠበቃችሁ ድረስ በምድሪቱ ትበለፅጋላችሁ፤ ነገር ግን ትዕዛዛቴን ባልጠበቃችሁ ጊዜ ሁሉ ከእኔ ዘንድ ትለያላቸሁ።’’ ከመቶ ዓመታት በላይ የተኖረበት የመፅሐፈ ሞርሞን ህዝቦች ልምድ የእነዚህን ቃላት እውነታ የሚያሳይ ነው። ‘’መበልጸግ’’ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የሰማያትን ምሪት እና በረከቶች በህይወታቸው ውስጥ ማግኘትን ነው። ‘’መበልጸግ’’ ማለት ማግባትን፣ ቤተሰብ ማፍራትን፣ እና የሌሎችን ፍላጎቶች ለሟሟላት ማገልገልን የሚያስችል የኢኮኖሚ ደህንነት ደረጃ ላይ መድረስ ማለት ነው። ‘’መበልጸግ’’ ከስቃይ እና ፈተና በላይ ከፍ ብሎ የመታየት ችሎታን ያጠቃልላል። በክርስቶስ ፀጋ አማካኝነት፣ ‘’ሁሉም ነገሮች ለበጎ ሆኖላቸዋል፣’’ አጥርቷቸዋል፣ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥልቅ እንዲሆን እድርጋል።
አልማ ወደ እግዚአብሔር መመልከት ትእዛዙን መጠበቅ፣ የእርሱን እርዳታ በመሻት በቀጣይነት ወደ እርሱ መጮህ፣ በሁሉም ጉዳዮቻችሁ ከእርሱ ጋር መማከር፣ እና ቀን እና ሌት ልባችሁን ለእርሱ ምስጋና ሙሉ ማድረግ እንደሆነ አብራርቷል። የእግዚአብሔር ትእዛዛት እና ምክሮች የሚገኙት በቅዱሳት መጻህፍት እና በአገልጋዮቹ ቃላት ውስጥ ነው። “ቤተሰብ፦ ለዓለም የተላለፈ አዋጅ” ላይ የሚገኘው መርህ እና ሃሳብ ዋናው ምሳሌ ነው። ሌላው ደግሞ ለወጣቶች ጥንካሬ መጽሔት ላይ ያለው መመሪያ ነው። የዚህ ዓመት የወጣት ወንዶች እና ወጣት ሴቶች መፈክር ‘’ወደ ክርስቶስ ተመልከቱ’’ የሚል ሲሆን ይህም የተወሰደው ጌታ ለጆሴፍ ስሚዝ እና ለኦሊቨር ካውድሪ፣ ‘’ባሰባችሁት ነገር ሁሉ ወደ እኔ ተመልከቱ፣ አትጠራጠሩ፣ አትፍሩ’’ በማለት ከተሰጠው የጌታ አጽናኝ ምሪት ነው። ለወጣቶች ጥንካሬ ስለ ጌታ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አያሌ ትእዛዛት እና ደረጃዎች የሚናገር ሲሆን የሚያስተምረውም መልካም ውሳኔዎችን በማድረግ እንዴት ወደ ጌታ መመልከት እንደሚቻል ነው። ይህም ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም የሚሆን መምሪያ መጽሀፍ ነው።
በወጣቶች ጥንካሬ ላይ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንደ አንድ ምሳሌ በምዕራፉ መግቢያ ላይ የተቀመጠው “ሰውነታችሁ የተቀደሰ ነው” የሚለው ነው። “የራሳችሁን— እና የሌሎችን ሠውነት— በክብር ያዙ። ስለአለባበሣችሁ፣ ስለፀጉር አሠራራችሁ እና ስለገፅታችሁ ውሳኔ በምታደርጉበት ጊዜ ‘ሠውነቴን ከእግዚአብሔር እንደተሠጠ ቅዱስ ሥጦታ አድርጌ እያከበርኩት ነውን?’” በማለት ራሣችሁን ጠይቁ።
ለወጣቶች ጥንካሬ በተጨማሪም፣ “ወሲብን እና የወሲብ ፍላጎትን በቅድስና ያዙ። እነርሱም የቀልድ ወይም የመዝናኛ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የለባቸውም። በወንድና በሴት መካከል ካለ ከጋብቻ ውጪ፣ የሌላን ሰው ግላዊ፣ ቅዱስ የአካል ቦታዎችን በልብስ የተሸፈነ ቢሆንም እንኳ መንካት ስህተት ነው። የምታደርጉትን፣ የምትመለከቱትን፣ የምታነቡትን፣ የምታዳምጡትን፣ የምታስቡትን፣ የምትለጥፉትን ወይም የምትጽፉትን በምትመርጡበት ጊዜ በሌሎች ወይም በራሳችሁ ላይ ሆን ተብሎ ጾታዊ ስሜት የሚቀሰቅስ ማንኛውንም ነገር አስወግዱ።”
ይህ በቅርቡ ፕሬዚዳንት ኔልሰን የሰጡትን ምክር እንድናስታውስ ያደርገናል፦
“ይህን መለኮታዊ [የንጽህና] ህግ እንደመጣስ ያሉ በበለጠ በፍጥነት ህይወታችሁን የሚያወሳስቡ ነገሮች ጥቂት ናቸው። ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለገባችሁ ሰዎች ንጹህ አለመሆን ምስክርነታችሁን ከምታጡባቸው ፈጣን መንገዶች አንዱ ነው።
“… ህይወትን የመፍጠር ሃይል የሰማይ አባት ምድራዊ ልጆቹ እንዲለማመዱ የሚፈቅደው ብቸኛው መለኮታዊ እድል ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ይህንን ሕያው መለኮታዊ ኃይል ለመጠቀም ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን አስቀምጧል። ጾታዊ ግንኙነት የሚፈቀደው በተጋቡ ወንድ እና ሴት መካከል ብቻ ነው።
“አብዛኛው አለም ይህንን አያምንም፣ የህዝብ አስተያየት ግን የእውነት ዳኛ አይደለም። ጌታ ንጹሕ ያልሆነ ሰው ወደ ሰለስቲያል መንግሥት እንደማይገባ ተናግሯል። እንዲሁም ንጹሕ ካልነበራችሁ ንስሐ እንድትገቡ እለምናችኋለሁ። ወደ ክርስቶስ ኑ፣ ለኃጢአታችሁ ሙሉ በሙሉ ንስሐ ስትገቡ ቃል የገባውን ፍጹም ምህረት ተቀበሉ [ኢሳይያስ 1፥16–18፣ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፥42–43 ተመልከቱ]።”
በመጽሐፈ ሞርሞን ተስፋ ውስጥ፣ የብልጽግና ተቃራኒ ድህነት ሳይሆን—ከጌታ ፊት መጣል እንደነበረ አስታውሱ። የእርሱ መገኘት የሚያመለክተው በአንድ ሰው ህይወት ውስጥ የመንፈሱን ተጽዕኖ ነው። ሁሉም ወደ ምድር በመጡ ጊዜ በክርስቶስ ብርሃን የተሞሉ ናቸው። በተጨማሪ፣ ለመጠመቅ መወሰን እና ስጦታን መቀበል እንዲሁም ተጨማሪ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን እና ተጨማሪ ብርሃንን መቀበል ነው። መነሳሳትን እና ምሪትን፣ የአንድን ሰው የተፈጥሮ ስጦታዎችን እና ችሎታዎችን ያመጣል፣ እንዲሁም ክፉ ተጽዕኖዎችን፣ መጥፎ ውሳኔዎችን፣ እና አደገኛ ውጤቶችን ለማስወገድ ይረዳል።
ልክ እንደናንተ፣ በአንድ ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ይደሰቱ የነበሩ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለማክበር ባለመቻላቸው ምክንያት ያንን በረከት ያጡ ሰዎችን አውቃለሁ። በተለይም በመተላለፍ ምክንያት የቤተክርስቲያን አባልነቱ የተወገደበት አንድ ሰው ወደ አእምሮዬ ይመጣል። እርሱ እንደሚለው የመጀመሪያ ምላሹ ቅር መሰኘት ነበር። ፍጹም ባልሆኑ መሪዎች ፍርጃ እንደደረሰበት ተሰምቶታል። የእርሱ ምግባር መልካም እንዳልነበረ ያውቅ ነበር፣ ነገር ግን በሌሎች ስህተት እና ውድቀት ላይ በማነጣጠር ያመካኝ ነበር። ከጊዜያት በኋላ፣ ከቤተክርስቲያን የጥሪ ግዴታዎች፣ የአምልኮ አገልግሎቶችን መካፈል ከሚጠበቅበት እና ሌሎችን ከማገልገል ግዴታዎች ውጪ በመሆኑ ምቾት እየተሰማው መጣ።
ይህ ለተወሰነ ጊዜ እየቀጠለ ሄደ፣ ነገር ግን በህይወቱ—የእግዚአብሔር መገኘት—የመንፈስ ቅዱስ መኖር ስሜቱ እየጠፋ መጣ። በልምምድ፣ ቀን በቀን ከመንፈስ የመወለድ ምቾት፣ ምሪት፣ እና በራስ የመተማመን ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር አውቋል ነገር ግን ይህንን አጥቶት ነብር። በስተመጨረሻ፣ ንሰሃ ለመግባት የሚያስፈልገውን አደረገ፣ እናም በመሆኑም ለውሃ እና ለመንፈስ ጥምቀት ብቁ ሆነ።
ትርጉም ላለው ነገር፣ ለደስታ፣ እና ለእርዳታ ሰዎች የተለያዩ ምንጮችን መፈለጋቸው ማለቂያ ያለው ነገር አይደለም። ብዙዎች ‘’ከሚጠበቀው በላይ ያልማሉ።’’ ነገር ግን ‘’በሃሰት ትምህርት ነፋስ ወዲህና ወዲያ እንደሚገፉ የምንገፋ ልጆች ልንሆን አይገባም።” እግዚአብሔርን በመመልከት በአስቸጋሪ ነገሮች ውስጥ ሰላምን እናገኛለን እናም በጥርጥር ጊዜያት እና በመንፈሳዊ ተግዳሮቶች ውስጥ እንኳን ሆነን እምነታችን ሊቀጥል ይችላል። በተቃውሞ እና በገለልተኝነት ፊት ሆነን ብርታትን ልናገኝ እንችላለን። በጊዜው ነባራዊ ሁኔታ እጅግ ከተመረጠው ጋር ልንስማማ እንችላለን። በእውነትም እምላክ እራሱ ከመጠው መንገድ በቀር ሌላ የመዳን መንገድ የለም፦ “ወደ እኔ ተመልከቱ፣ እና የዳናችሁ ሁኑ፣ እናንት የምድር ዳርቻ ሁሉ፤ እኔ አምላክ ነኝ፣ ከእኔ ሌላ አምላክ የለም።”
ወደ እግዚአብሔር መመልከት ማለት ከምናስቀድማቸው ነገሮች መካከል እርሱ አንዱ ነው ማለት አይደለም፤ ይህ ማለት ይልቁኑም እርሱ ከፍተኛው ቅድሚያ የምንሰጠው ነው ማለት ነው። ዳግም ባለፈው ሰኔ ወር በሌሴቶ የተፈጠረውን የመኪና አደጋ እንድታስታውሱ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ከሆስፒታል አልጋዋ ላይ፣ ከአደጋው የተረፈች አንዲት የወጣት ሴቶች መሪ፣ ቤተክርስቲያኑን ከመቀላቀሏ በፊት በእግዚአብሔር የማታምን የነበረች አሁን አላማዋ ህይወቷ የተረፈበትን ምክንያት ማወቅ እንደሆነ ተናግራለች። “ያለማሰለስ እግዚአብሔርን ማገልገል ምናልባትም ወደ መልሱ ብመጣ፣ ወደ መልሴ እንዴት እንደምመጣ የማውቅበት ነው’’ በማለት ተናግራለች። “እግዚአብሔርን የምወድ መስሎ ይሰማኝ ነበር፣ ነገር ግን አሁን በእውነት፣ በእውነት፣ በእውነት እወደዋለሁ። እርሱ አሁን ቁጥር አንድ በህይወቴ ቅድሚያ የምሰጠው ነው።”
በቃል፣ በሃሳብ፣ በአላማ፣ እና በድርጊት አንድ አምላክ ስለሆኑት ለሁሉም ነገሮች ወደ እነርሱ ስለምንመለከትባቸው ስለ አብ፣ ስለወልድ፣ እና ስለመንፈስ ቅዱስ ምስክርነቴን እሰጣለሁ። “ወደ እኔ ተመልከቱ፣ እናም እስከመጨረሻው የጸናችሁ ሁኑ፣ እናም ህያው ትሆናላችሁ፤ እስከመጨረሻው ለሚፀናም የዘላለምን ህይወት እሰጠዋለሁና” በማለት አስደናቂ የሆነውን የተስፋ ቃል ስለፈጸመው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነቴን እስጣለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።