አጠቃላይ ጉባኤ
በራሳቸው ላይ ፈራጅ ይሆናሉ
የጥቅምት 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:26

በራሳቸው ላይ ፈራጅ ይሆናሉ

(አልማ 41፥7)

በኢየሱስ ክርስቶስ አምነን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገብተን ከጠበቅን፣ እንዲሁም ለኃጢአታችንም ንስሐ ከገባን፣ የፍርድ ወንበሩ ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።

መጽሐፈ ሞርሞን የሚደመደመው ሞሮኒ ”ወደ ክርስቶስ ኑ፣” “በእርሱም ፍፁማን ሁኑ፣” “ኃጢአተኝነትን በሙሉ [ከራሳችንን] እንካድ፣” እናም “በሙሉ ኃይላ[ችን]፣አዕምሮአ[ች]ን እና ጉልበታ[ችን] እግዚአብሔርን [እንውደድ]” በሚል የሚያበረታታ ግብዣ ነው። የሚገርመው፣ ትምህርቱ የመጨረሻ አረፍተ ነገር ትንሣኤውንና የመጨረሻውን ፍርድ አስቀድሞ የሚናገር መሆኑ ነው።

እንዲህም አለ፣ “መንፈስና ስጋዬም በአንድነት እስኪገናኝ፣ እናም ለህያዋን እና ለሙታን ዘለዓለማዊ ዳኛ በሆነው በታላቁ ያህዌህ አስደሳቹ የፍርድ ወንበር ፊት እናንተን ለመገናኘት ድል አድርጌ ወደ ሰማይ እስከምመጣ ድረስ፣ በቅርብ ወደ እግዚአብሔር ገነት ለማረፍ እሄዳለሁ።”

ሞሮኒ የመጨረሻውን ፍርድ ለመግለጽ “አስደሳቹ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ በጣም አስገርሞኛል። ሌሎች የመጽሐፈ ሞርሞን ነቢያትም በተመሳሳይ የፍርድ ቀን “ታላቁ ቀን” እና “በእምነት ዓይን [መመልከት]” የሚገባን እንደሆነ ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ የፍርድ ቀንን ስንጠባበቅ ብዙውን ጊዜ ሌሎች ትንቢታዊ መግለጫዎች ወደ አዕምሯችን ይመጣሉ፤ ለምሳሌ “እፍረትና መጥፎ ጸጸት፣” “ስጋትና ፍርሃት፣” እንዲሁም “ዘለዓለማዊው ስቃይ”።

ይህ ታላቅ የቋንቋ ልዩነት የሚያመለክተው፣ የክርስቶስ አስተምህሮ ሞሮኒ እና ሌሎች ነቢያት ያንን ታላቅ ቀን በመንፈሳዊ ባልተዘጋጁ ሰዎች ላይ ከሚሰነዝሩት ፍርሃት ይልቅ በጉጉት እና በተስፋ እንዲጠብቁ አስችሏቸዋል የሚል እምነት አለኝ። ሞሮኒ እናንተም ሆናችሁ እኔ መማር የሚያስፈገንን ምን ነገር ተገንዝቧል?

የሰማያዊ አባታችንን የደስታ እና የምህረት እቅድን፣ አዳኛችን በአብ እቅድ ውስጥ ስላለው የማስተሰረያ ሚና፣ እና እና እንዴት እኛ “[ለራሳችን] ኃጢአቶች በፍርድ ቀን [ተጠያቂ]” እንደምንሆን ስናስብ፣ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ለማግኘት እጸልያለሁ።

የአብ የደስታ እቅድ

የአብ ዕቅድ ዋና አላማዎች የመንፈስ ልጆቹ ስጋዊ አካልን እንዲቀበሉ፣ በምድራዊ ተሞክሮ “መልካሙን ከክፉ” ለመለየት እንዲማሩ፣ በመንፈሳዊ እንዲያድጉ እና ለዘለአለም እያደጉ እንዲሄዱ ዕድሎችን መስጠት ነው።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች የሥነ ምግባር ምርጫ በማለት የተጠቆመው የወንድ እና ሴት ልጆቹን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት በሚያመጥው የእግዚአብሄር ዕቅድ ውስጥ ዋነኛ አካል ነው። ይህ መሰረታዊ መርህ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እንደ የመምረጥ ነፃነት እና የመምረጥ እና የመተግበር ነፃነት ተደርጎ ተገልጿል።

“የሥነ ምግባር ምርጫ” የሚለው ቃል ጠቃሚ ትምህርት ይዟል። ሥነ ምግባር፣ ለሚለው ተመሳሳይ ቃላት “መልካም፣” “ሐቀኛ” እና “በጎ” የሚሉትን ቃላት ሊያካትት ይችላል። ነጻ ምርጫ ለሚለው ቃል ያሉት ተመሳሳይ ቃላት “ተግባር፣” “እንቅሥቃሴ” እና “ሥራ” የሚሉትን ቃላት ሊያካትት ይችላል። ስለዚህ “የሥነ ምግባር ምርጫ” ሲባል መልካም፣ ሀቀኛ፣ በጎና እውነተኛ የሆነውን ነገር የመምረጥ ችሎታና መብት አለን ማለት ነው።

የእግዚአብሄር ፍጥረት “ተፅዕኖ የሚያደርጉ ወይም ተፅዕኖ የሚደረግባቸውን” ያካትታል። እንዲሁም የሥነ ምግባር ምርጫ በፈጣሪ የተዘጋጀ “በራስ ምርጫ የመተግበር ኃይል” ሲሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ተፅዕኖ የምናደርግ አካላት እንጂ በቀላሉ ተፅዕኖ የምንደረግ ግዑዛን እንዳንሆን ኃይሉን ይሰጠናል።

ምድር የተፈጠረችው የሰማይ አባት ልጆች “ጌታ አምላክ የሚያዛቸውን ማናቸውንም ነገሮች ሁሉ እንደሚያደርጉ“ ለመፈተን ነው። የፍጥረት እና የሟች ህልውናችን ዋነኛ ዓላማ እግዚአብሔር እንድንሆን የሚጋብዘንን እንድናደርግ እንዲሁም እንድንሆን እድል መስጠት ነው።

አምላክም ሄኖክን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦

“እነሆ፣ እነዚህ ወንድሞችህን እይ፤ እነርሱ የእጅህ ስራዎች ናቸው፣ እና በፈጠርኳቸው ቀንም እውቀታቸውን ሰጠኋቸው፤ እና በዔደን ገነትም ለሰው ነጻ ምርጫውን ሰጠሁት፤

“እና ለወንድሞችህም ይህን ብያለሁ፣ እና ደግሞም እርስ በርስ እንዲዋደዱ፣ እና እኔ አባታቸውን ይመርጡ ዘንድ ትእዛዝን ሰጠኋቸው።

የመምረጥ ነጻነትን የመጠቀም መሰረታዊ ዓላማ እርስ በእርስ መዋደድና እግዚአብሔርን መምረጥ ነው። እነዚህ ሁለት ዓላማዎች እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችን እና አዕምሯችን መውደድ፣ እና ባልንጀራችንን እንደራሳችን መውደድ ከሆኑት ከመጀመሪያውና ከሁለተኛው ታላላቅ ትእዛዛት ጋር በትክክል ይጣጣማሉ።

እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እና እግዚአብሔርን እንድንመርጥ እንደተገሰፅን፣ እንደተበረታታን፣ እንደተመከርን ሳይሆን እንደታዘዝን አስቡ። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ሥነ ምግባር” ተብሎ የተተረጐመው ቃል እንደ ቅጽል ብቻ ሳይሆን የመምረጥ ነፃነታችንን እንዴት ልንጠቀምበት እንደሚገባ የሚገልጽ መለኰታዊ መመሪያም ሊሆን እንደሚችል ልጠቁም እወዳለሁ።

አንድ የታወቀ መዝሙር “ትክክለኛውን ምረጡ” የሚል ርዕስ ያለው አለምክንያት አይደለም። የሥነ ምግባር ምርጫ በረከት የተሰጠን በፈለግን ጊዜ የፈለግነውን ለማድረግ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የሥነ ምግባር ምርጫ የተሰጠን በአብ ዕቅድ መሠረት ዘለዓለማዊ እውነትን እንድንፈልግ እና በእርሱ መሠረት እንድንተገብር ነው። “[ራሳችንን በመወከል]፣” መልካም ስራን በጉጉት ማከናወን አለብን፣ “ብዙ ነገሮችን በራሳ[ችን] ነጻ ምርጫ ማድረግ፣ እናም ብዙ ጽድቅንም መስራት አለ[ብን]።”

የሥነ ምግባር ምርጫ አስፈላጊነት የቅድመ ምድራዊ ሕይወት ሸንጎ ላይ አስመልክቶ በሠፈረው የቅዱሳት መፃሕፍት ዘገባ ላይ ተገልጿል። ሉሲፈር አብ ለልጆቹ ባለው ዕቅድ ላይ አመፀ እና የገለልተኛ እርምጃ ኃይልን ለማጥፋት ፈለገ። ጉልህ ሆኖ የሚታየውም፣ የዲያብሎስ ተቃውሞ ያተኮረው በቀጥታ በሥነ ምግባር ምርጫ መርህ ላይ ነበር።

እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ሰይጣን ስለዐመፀብኝና እኔ እግዚአብሔር አምላክ የሰጠሁትን የሰው ነጻ ምርጫ ለማጥፋት ስለፈለገ፣ … [እርሱ] እንዲጣል አደረግሁኝ።”

የጠላት ራስ ወዳድ ሴራ የእግዚአብሔር ልጆች በጽድቅ የሚንቀሳቀሱ “ራሳቸውን [የሚወክሉ]” የመሆን አቅም እንዲያጡ ማድረግ ነበር። የእሱ ዓላማ የሰማይ አባት ልጆች ላይ ተፅዕኖ የሚደረግባቸው ግዑዛን ብቻ እንዲሆኑ ነበር።

ማድረግና መሆን

ፕሬዚዳንት ዳለን ኤች. ኦክስ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አንድን ነገር እንድናውቅ እና በሥነ ምግባር አመራር አማካኝነት አንድ ነገር እንድንሆን እንደሚጋብዘን አጽንኦት ሰጥተዋል። እንዲህም አሉ፦

“ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ እና በአሁን ዘመን ያሉ የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶች፣ ሁሉም ሰዎች እንደ ሥራቸው ወይም እንደ ልባቸው ምኞት ወሮታ ስለሚከፈላቸው የመጨረሻው ፍርድ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሌሎች ጥቅሶችም በምናደረገው ሁኔታ ላይ ተመስርተን እንደምንፈረድ ይገልጻሉ።

ነቢዩ ኔፊ የመጨረሻውን ፍርድ የገለጸው እኛ ከሆንንበት ሁኔታ አንጻር ነው፦ ‘እናም ስራቸው የረከሰ ከሆነ እነርሱም የረከሱ መሆን አለባቸው፤ የረከሱ ከሆኑም ደግሞ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር አይችሉም’ (1 ኔፊ 15፥33፤ አጽንኦት ተጨምሯል)። ሞሮኒ እንዲህ ይላል፦ ’ንፁህ ያልሆነውም አሁን ንፁህ ሳይሆን የሚቀርበት ጊዜ ይመጣል፤ እናም ፃድቅ የሆነው አሁንም ፃድቅ ይሆናል’ (ሞርሞን 9፥14፤ አጽንኦት ተጨምሯል)።”

ፕሬዚዳንት ኦክስ በመቀጠል እንዲህ ብለዋል:- “ከእነዚህ ትምህርቶች በመነሳት የመጨረሻው ፍርድ የመልካም እና የክፋት ተግባራት ድምር፣ ወይም እኛ ያደረግነው፣ ግምገማ ብቻ አይደለም በማለት ለመደምደም እንችላለን። ይህም የድርጊታችን ወይም የሀሳቦቻችን ፣ወይም ምን አይነት ሰው እንደሆንን፣ የመጨረሻው ውጤትን የሚያስታውቅ ነው።”

የአዳኙ የኃጢያት ክፍያ

ሥራችንና ምኞታችን ብቻውን አያድነንም እናም ሊያድነን አይችልም። “የምንችለውን ካደረግን በኋላ” ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቀው በአዳኛችን ማለቂያ በሌለውና ዘላለማዊ በሆነው የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አማካኝነት በሚገኘው ምሕረትና ጸጋ ብቻ ነው።

አልማ እንዲህ ብሏል፣ “እናም የእግዚአብሔር ልጅ ህዝቡን ሊያድን እንደሚመጣና፣ ለህዝቡ ኃጢያት ክፍያ እንደሚሰቃይና እንደሚሞት፣ እናም ሰዎች እንደስራቸው በመጨረሻውና በፍርዱ ቀን እንዲፈረድባቸው በፊቱ ይቆሙ ዘንድ ትንሳኤን ያመጣ ዘንድ በድጋሚ ከሙታን እንደሚነሳ ማመን ጀምሩ።”

“የወንጌሉን ህግጋትና ስርዓቶችን በማክበር፣ የሰው ዘር ሁሉ በክርስቶስ የኃጢአት ክፍያ አማካይነት መዳን እንደሚችሉ እናምናለን።” በእውነተኛ ሁኔታ “[በዳግም ከተወለድን]፣” በቤዛው ላይ እምነት ካሳደርን፣ “በቅንነት ልብ” እና “በእውነተኛ ዓላማ” ንስሐ ከገባን፣ እና “እስከ መጨረሻው [ከጸናን]” ኃጢአታችን እና ክፉ ሥራዎቻችን በእኛ ላይ እንደ ምስክርነት የማይቆሙ በመሆናቸው ምንኛ አመስጋኞች መሆን አለብን።

እግዚአብሔርን መፍራት

ብዙዎቻችን በዘላለማዊው ዳኛ ፊት የምንቀርበው ዓለማዊ ፍርድ ቤት ውስጥ ከሚካሄድ የፍርድ ሂደት ጋር ይመሳሰላል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። ዳኛው ይመራል። ማስረጃዎች ይቀርባሉ። ፍርድ ይሰጣል። መጨረሻው ምን እንደሚሆን እስክናውቅ ድረስ ጥርጣሬና ፍርሃት ያድርብናል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ መግለጫ ትክክል አይደለም የሚል እምነት አለኝ።

ቅዱሳት መጻሕፍት “[አምላካዊ] ፍርሀት” ወይም “እግዚአብሔርን መፍራት” በማለት የሚገልጹት ነገር ብዙውን ጊዜ ከምናገኛቸው ከሟች ፍርሐቶች የተለየ ቢሆንም ከእነሱ ጋር የተያያዘ ነው። ድንጋጤን እና ጭንቀትን ከሚፈጥረው ከዓለማዊ ፍርሃት ይልቅ፣ [አምላካዊ] ፍርሀት በህይወታችን ውስጥ ሰላምን፣ ማረጋገጫን እና መተማመንን ይጋብዛል።

ጻድቃዊ ፍርሀት በጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ላይ የሚገኝ አክብሮትን እና ጥልቅ አድናቆትን፣ ትዕዛዛቱን ማክበርን፣ እንዲሁም በእርሱ እጅ ለየሚሰጡትን የመጨረሻው ፍርድ እና ፍትህ በጥልቅ ስሜት መጓጓትን ይይዛል። [አምላካዊ] ፍርሀት የሚመነጨው ስለ አዳኙ መለኰታዊ ተፈጥሮና ተልዕኮ ትክክለኛ ግንዛቤ ካለን፣ ፈቃዳችንን ለፈቃዱ ለማስገዛት ፈቃደኝነት ካለን እንዲሁም እያንዳንዱ ወንድና ሴት ስለራሱ ወይም ስለሟች ፍላጐቶች፣ ሃሳቦች፣ ቃላትና ድርጊቶች በፍርድ ቀን ተጠያቂ እንደሚሆን እውቀት ካለን ነው።

እግዚአብሔርን መፍራት ወደ እርሱ በመምጣት የሚፈረድበትን የሚፈራ ስሜት ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ ነገሮች በእርግጥ እንዳሉ፣ እናም ነገሮች በእርግጥ እንደሚሆኑ የሚያሳይ ራሳችንን የማወቅ ተስፋ ነው።

ከዚህ በፊት የኖረ፣ አሁን የሚኖርና ወደፊት በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው “[እንደስራው ወይም ስራዋ] መሰረት እንዲፈረድባቸው በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት ይቆማሉ።”

ምኞታችን ለጽድቅ፣ ሥራችን ለበጐነት ከሆነ—ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ አምነናል፣ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገብተን ጠብቀናል፣ እንዲሁም ለኃጢአታችንም ንስሐ ገብተናል ማለት ከሆነ—የፍርድ ወንበሩ ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ኤኖስ እንዳወጀው፦ “በ[ቤዛችን] ፊት [እንቆማለን]…፤ ከዚያም[ ] ፊቱንም በደስታ [እናያለን]።” በመጨረሻውም ቀን “የጽድቅን ዋጋ ይቀበላል።”

በተቃራኒው ደግሞ ምኞታችን ለክፋት፣ ሥራችንም ለክፋት ከሆነ የፍርድ ወንበር አስፈሪ ይሆናል። “ፍጹም እውቀት፣” “ብሩህ ትውስታ፣” እንዲሁም “[ ሀይለኛ የሆነ የጥፋተኛነ[ታችን] ስሜት” ይኖራል። “እናም በዚህ አስከፊ ሁኔታ ወደ አምላካችን ለመመልከት አንደፍርም፤ እናም አለቶቹንና ተራራዎቹን ከእርሱ ፊት እንዲደብቁን በላያችን ላይ እንዲወድቁ ብናዛቸው እጅግ እንደሰታለን።” በመጨረሻው ቀን “[የክፋት ብድራችንን እንቀበላለን]።”

ከዚያም፣ በመጨረሻ በራሳቸው ላይ ፈራጅ ይሆናሉ። የት መሄድ እንዳለብን የሚነግረን ሰው አይኖርም። በጌታ ፊት፣ በሟችነት ውስጥ ምን ለመሆን እንደመረጥን እንዲሁም ለዘላለም የት መሆን እንዳለብን ለራሳችን እናውቃለን።

የተስፋ ቃል እና ምስክርነት

የመጨረሻው ፍርድ ደስ የሚያሰኝ ሊሆን እንደሚችል መረዳት ለሞሮኒ ብቻ የተጠበቀ በረከት አይደለም።

አልማ ለአዳኙ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ተስፋ የተደረገላቸውን በረከቶች ገልጿል። እንዲህም አለ፦

“ነገር ግን የዳግሞ መመለስ የቃል ትርጉም መጥፎን ለመጥፎ፣ ስጋን ለስጋ ወይንም ዲያብሎስን ለዲያብሎስ መልሶ ማምጣት ነው—መልካም ለሆነው መልካምን፣ ፃድቅ ለሆነው ፅድቅን፤ ፍትሃዊ ለሆነው ፍትህን፤ መሃሪ ለሆነው ምህረትን ማምጣት ነው።

“…ለሰዎች ፍትሃዊ ሁን፣ በትክክል ፍረድ፣ እናም ያለማቋረጥ መልካምን ስራ፤ እናም ይህንን ሁሉ የምታደርግ ከሆነ ደመወዝህን ታገኛለህ፤ አዎን፣ ምህረት በድጋሚ ይመለስልሃል፤ በድጋሚም ፍትህ ይመለስልሃል፣ በድጋሚም ጻድቃዊ ፍርድ ይመለስልሃል፣ እናም በድጋሚ መልካም ደመወዝ ታገኛለህ።”

ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው አዳኛችን መሆኑን በደስታ እመሰክራለሁ። የአልማ ቃል ለእኔ እና ለእናንተ ዛሬ፣ ነገ እንዲሁም ለዘለዓለም እውነትና ተፈጻሚነት አለው። እንዲህ የምመሰክረውም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።