በጎቹን ማስታወስ
የመቁጠር እና ልብ የማለት መርህ የሚሰራ ነው። የጌታ መንገድ ነው።
ክርስቶስ መልካሙ እረኛ ነው። እያንዳንዱ መንጋ በእርሱ ዘንድ ውድ ነው። እረኝነትን ምሳሌ በማድረግ በጎችን በስም በማወቅ፣ በመውደድ፣ የጠፉትን በመፈለግ፣ በመመገብ እና በስተመጨረሻም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በመምራት በቃል እንዲሁም በተግባር የመልካም እረኛን ባህሪያት አስተምሮናል። ከእርሱ ስር እንዳሉ እረኞች ይህን እንድናደርግ ከእኛ ይጠብቃል።
በጌታ መንገድ ስለማገልገል ከጥንታዊው ነቢይ እና ልዩ የሆነ እረኛ ሞሮኒ ብዙ መማር እንችላለን። ይኖር የነበረው ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ኮምፒዩተር እና ኢንተርኔት በሌለበት በጣም አስቸጋሪ በነበረ ጊዜ ነበር። ነገር ግን በጎቹን መከታተል ችሏል። ይህን እንዴት አደረገ? በሞሮኒ 6 ውስጥ የእሱን ዘዴ በጥቂቱ እናገኛለን። እዚያ አባላት “ከክርስቶስ ቤተክርስቲያን ህዝቦች ጋር ተቆጥረዋል፤ እነርሱንም በትክክለኛው መንገድ (ማለትም በቃልኪዳን መንገድ) ለማቆየት፣… እንዲሚቀጥሉ ለመጠበቅ፣ የእግዚአብሔርን መልካም ቃል በመመገብ ይታወሱ ዘንድ ስማቸው ተወስደዋል… ለመፆም እና ለመፀለይ፣ እናም እያንዳንዳቸው ለነፍሳቸው ደህንነት እርስ በርሳቸው እንዲናገሩ ዘንድ” ሁል ጊዜ በቤተክርስቲያን ይገኛሉ(ሞሮኒ 6:4–5; አቱሮት ተጨምሮበታል).የሚለውን እናነባለን።
ሞሮኒ፣ ዋጋ ይሰጥ የነበረው ለሰዎች ነበር—ለስሞች! ሁሉም እንዲታወስ “መቁጠር እና ማስተዋል” የሚለውን መርህ ይከተል ነበር። ችግር ላይ ያሉ ወይም የሚቅበዘበዙትን በመለየት ቅዱሳን ስለደህንነታቸው እንዲማከሩ እና እንዲወያዩ አስችሏል። (በእርግጥ የተጠበቁ እና ደህና የነበሩትን) ዘጠና ዘጠኙን ትቶ የጠፋውን ፍለጋ እንደሄደው እረኛ( ሉቃስ 15:4–7ተመልከቱ)፣ እኛም መንጋችንን እንድናስተውል፣ ልብ እንድንል እና እንድናስታውሳቸው እና ሄደንም እንዲሁ እንድናደርግ ተጠይቀናል።
በህንድ ውስጥ የሚሲዮን መሪ በነበርኩ ወቅት፣ ወጣት ለነበረው የቅርንጫፍ ፕሬዘዳንት ስለ መጪው አመት አንዳንድ ግቦቹን ስለመጠየቄ አስታውሳለሁ፡- “የመልከ ጼዴቅን ክህነት ለመቀበል ምን ያህል ሰዎች ታዘጋጃላችሁ?” ወዲያው የሰጠው ምላሽ “ሰባት!” የሚል ነበር።
ይህን የተወሰነ ቁጥር ከየት አመጣው ስል ተገረምኩ! መልስ ለመስጠት ከመሞከሬ በፊት በጎን ከአንድ እስከ ሰባት የተጻፈበትን ወረቀት አዘጋጀ። የመጀመሪያዎቹ አምስቱ መስመሮች እሱ እና የሽማግሌዎች ቡድን ሊጋብዟቸው እና የክህነት ስልጣን በረከት በሕይወታቸው እንዲኖር የሚያበረታቷቸው እውነተኛ ሰዎች ስሞች ነበረው። ስለስድስተኛው እና ስለሰባተኛው ባዶ መስመር በርግጥ መጠየቅ ነበረብኝ። ጭንቅላቱን እየነቀነቀ፣ “እንዴ ፕረዚዳንት፣ በዓመቱ መጨረሻ ክህነት እንዲኖራቸው በዓመቱ መጀመሪያ ቢያንስ ሁለት ሰዎችን እናጠምቃለን” አለ። ይህ ምርጥ መሪ የመቁጠርን እና የማስተዋልም መርህንም ተረድቷል።
ክርስቶስ እያንዳንዱ ሰው ለእርሱ የተወደደ ስለሆነ ነፍስን ለመርሳት በሚያስቸግር መንገድ ቤተክርስቲያኑን አደራጅቷል። በቅርንጫፍ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ እድሜ እና ጾታ ሳይለይ የመንከባከብ፣ የማስታወስ ኃላፊነት ያለባቸው ብዙ መጋቢ እረኞች አለው። ለምሳሌ አንድን ወጣት ለመርዳት እንደ ኤጲስ ቆጶስ፣ የአገልግሎት ወንድሞች፣ የወጣት ጎልማሳ አማካሪዎች፣ የሴሚናሪ አስተማሪዎች የቡድን አመራሮች የመሳሰሉ ብዙ ሰዎች ተመድበዋል፣ እሱ ሲወድቅ ሁሉም እንደ መረብ አጥብቀው ለመያዝ ሁሉም ይሰራሉ። ምንም እንኳን አንድ መረብ ብቻ በትክክል የተቀመጠ ቢሆን ወጣቱ ደህና፣ የታወቀ እና የታወሰ ይሆናል። ሆኖም ግን ብዙ ጌዜ ይህ መረብ ላይኖር ይችላል። ማንም ሳያስተውል ሰዎች በየጊዜው ወደ ጭጋጉ ይቅበዘበዛሉ። የተሻልን እረኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? መቁጠርን እና ማስተዋልን መማር እንችላለን።
ያንኑ ለማድረግ—ለማስታወስ፣ ቤተክርስቲያኗ መረጃዎችን እና ግብአቶችን ትሰጠናለች። የሩብ ዓመት ሪፖርት ዋነኛ ምሳሌ ነው። ብዙ ጊዜ እያንዳንዱን አባል ደጋግመን እንድንቆጥር እና እንድናስተውል እንዲሁም የጠፉትን ወይም የእኛን እርዳታ እና ፍቅር የሚሹትን እንድናስተውል ያስችለናል። የተግባር እና የቃለ መጠይቅ ዝርዝር ልክ እንደ ቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃድ እና ሌሎች ነገሮች በአሁን ጊዜ የእኛን ትኩረት የሚሹትን ይለያል። እነዚህ ለመቁጠር እና ለማስተዋል የተዘጋጁ መሳሪያዎች ሰዎች ላይ እንድናተኩር ያደርጋሉ። ጥሪ፣ የክህነት እድገት ወይም የቤተሰብን ስም ወደ ቤተመቅደስ ለመውሰድ እርዳታ የሚያስፈልገው ማነው? የሙሉ ጊዜ የሚስዮን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማዘጋጀት ማንን መርዳት እንችላለን? በዚህ ወር ማን ጠፋ? እነዚህ መሳሪያዎች ሰዎችን እንድናስታውስ ይረዱናል።
በአፍሪካ ውስጥ ስራ ተሰጥቶት የነበረን አንድ ከአሜሪካ የመጣ ቤተሰብ አውቅ ነበር። በመጀመሪያው እሑዳቸው በአገሪቱ ውስጥ ወደሚገኘው ብቸኛው የቤተ ክርስቲያን ክፍል ሄዱ፣ በዚያም ሞቅ ያለ ሰላምታ ቀረበላቸው። ረፋዱ ላይ የሰውየው ሚስት የሴቶች መረዳጃ ማህበር ፕሬዘደንት፣ እሱ ደግሞ የወጣቶች መሪ በመሆን ጥሪ ተሰጣቸው። የደከመ የሚመስለውን የቅርንጫፍ ፕሬዝደንት ምን ያህል ወጣት ወንዶች እንዳሉ ጠየቀ። ይህ ታማኝ በቤተክርስቲያኗ የመጀመሪያ ትውልድ የሆነ መሪ ወደ ቅዱስ ቁርባኑ አዳራሽ ጀርባ እያመለከተ “እነዚያ ሁለቱ ናቸው” አለ። ሰውዬው በእርግጥ ተጠራጥሮ ስለነበር የቅርንጫፉን ስም ዝርዝር ወደ ቤት ወሰደ፣ በፍጥነትም በዝርዝሩ ውስጥ 20 ወጣቶች መኖራቸውን አስተዋለ። ወደ ቅርንጫፉ ፕሬዘዳንት ተመለሰና የእሱ አማካሪ በመሆን እንዲያገለግሉ ሁለት የተነሳሱ፣ ሁለት ቋንቋ መናገር የሚችሉ ጎልማሶችን ጠየቀ፣ ከዚያም ከእነሱ እና ከሁለቱ ወንዶች ልጆች ጋር በመቀመጥ ስሞቹን ተመለከቱ።
ከዚያም እነዚህ ትጉ ወጣቶች ወደ ሥራ ገቡ። በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ በዝርዝሩ ላይ ያለውን እያንዳንዱን ወንድ ልጅ አገኙ። እነዚያ የጠፉትን በጎች እኩዮቻቸው አንድ በአንድ ተቀብለዋቸው መንፈሳዊና ሥጋዊ ምግብ መገቧቸው! በአንድ ዓመት ውስጥ በአማካይ 21 ወጣት ወንዶች በማንኛውም እሁድ ይገኙ ነበር። ለቆጠሩት እና ላስተዋሉት ወጣቶች ምስጋና ይግባቸው።
አንድ የምወደው ጓደኛዬ፣ በወጣትነቱ የድህረ ምረቃ ተማሪ ሳለ ትምህርቱን ለመቀጠል ከቤተሰቡ ጋር ወደ ትልቅ የአሜሪካ ከተማ ሄደ። ወዲያው የሽማግሌዎችን ቡድን እንዲመራ ተጠራ። ከካስማ ፕሬዝደንቱ ጋር ስለነበረው የመጀመርያ ቃለ መጠየቅ ትንሽ ተጨንቆ ስለነበረ ለመዘጋጀት ወሰነ። ለቀጣዩ አመት ሶስት ግቦች እንዳሉት ለካስማው ፕሬዝዳንቱ ነገረው፦ (1) አገልግሎትን 90 በመቶ ለማሳደግ (2) በየሳምንቱ ጠቃሚ የወንጌል ትምህርት ለማዘጋጀት እና (3) በየወሩ በአግባቡ የታቀደ የቡድን አክቲቪቲ ለማድረግ ነበር።
ይህ ብልህ የካስማ ፕሬዘደንት ለጓደኛዬ ፈገግታ እያሳየ “በዚህ አመት ከቤተሰቡ ጋር ወደ ቤተመቅደስ እንዲሄድ ለመርዳት የምትችለው ንቁ ተሳታፊ ያልሆነን የአንድ አባል ስም ልትጠራ ትችላለህ?” በማለት ጠየቀው። ይህ ነገር ጓደኛዬን አስገረመው። በጥንቃቄ አሰበና አንድ ስም ጠራ። የካስማ ፕሬዝዳንቱ “ጻፈው” ሲል መመሪያ ሰጠው። ከዚያም ይህ ልምድ ያለው መሪ ተመሳሳይ ጥያቄ ሶስት ጊዜ ጠየቀው—ቃለመጠይቁም ተጠናቀቀ። ይህ ወጣት በአመራር እና በአገልግሎት ላይ ከተማራቸው ታላላቅ ትምህርቶች አንዱን በመማር ከዚያ ቃለ መጠይቅ ወጣ። ወደ ቃለ መጠይቁ ሲገባ ትኩረቱ እቅዶች፣ ትምህርቶች እና አክቲቪቲዎች ላይ ነበር። በግለሰቦች ላይ በማተኮር ወጣ! እነዚያ አራት ስሞች የአገልግሎቱ እና የጉባኤው ዋና ትኩረት ሆኑ።
እንደ ሚሲዮን መሪ፣ አንድ እሁድ ጠዋት ከቅርንጫፎቼ አንዱን ጎበኘሁ። የቅርንጫፉ ፕሬዘዳንት የወረቀት ካርድ ከኪሱ በማውጣት በላዩ ላይ መፃፍ መቀጠሉን አስተዋልኩ። ከመዝጊያው ጸሎት በኋላ ስለዚህ ነገር ልጠይቀው ወሰንኩ። ስብሰባው እንዳለቀ እና ስለካርዱ ከመጠየቄ በፊት የቅርንጫፉ የሚስዮን መሪ ወደ መድረኩ በፍጥነት ቀረበ፣ ወረቀቱም እዚያው ተሰጠው። ይህንን ታታሪ መሪ ወደ ሳምንታዊው የቅርንጫፍ ሚስዮናውያን ማስተባበሪያ ስብሰባ ሲሄድ በፍጥነት ተከተልኩት። ከመጀመራቸው በፊት ወረቀቱን ከኪሱ አወጣ። በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ ባልተገኙ አባላት ስም ተሞልቶ ነበር። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እያንዳንዱ የምክር ቤቱ አባል አንድ ወይም ሁለት ስሞችን በመምረጥ በዚያው ቀን እነዚያ ሰዎች ደህና መሆናቸውን ለማረጋገጥ እና እንደታሰቡ እንዲያውቁ ለመጠየቅ ቃል ገቡ። አሁን ያ ቆጠራ እና ማስተዋል ነው።
ምንም እንኳን ፈጽሞ ጥቅም ላይ ላይውል ቢችልም ለወቅታዊ የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ፣ በአቅራቢያው ካለው ቤተመቅደስ በአውሮፕላን ሰአታት የሚፈጅበትን አውራጃ አስታውሳለሁ። በየወሩ የመጀመሪያ እሑድ መሪዎች የመቁጠሪያ መሣሪያዎቻቸውን የቤተመቅደስ ቡራኬ የተቀበሉ አባላቶቻቸው ለመለየት ይጠቀማሉ። የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ በቅርቡ ጊዜው እንደሚያልፍ ካወቁ፣ የስራ አስፈፃሚው ፀሀፊ እንዲታደስ የቃለ መጠይቅ ቀጠሮ ያስይዛል። የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበትን መታወቂያ በያዙ ሰዎች ዙርያ ይማከራሉ፣ ከዚያም ወደ ቃል ኪዳኑ መንገድ እንዲመለሱ ፍለጋ ይደረግላቸዋል። የቤተመቅደስ ቡራኬ ከተቀበሉት ውስጥ ምን ያህሉ ወቅታዊ መታወቂያ እንዳላቸው ጠየቅሁ። መልሱ በሚያስደንቅ ሁኔታ 98.6 በመቶ ነበር። ጊዜው ያለፈ መታወቂያ ስላላቸው ስለ ስድስቱ ሲጠየቅ መሪዎቹ በስም ለይተው እንደሚያውቋቸው እና እነሱን ለመመለስ እየተደረገ ስላለው ጥረት ገለጹልኝ!
ከጥቂት አመታት በፊት፣ ቤተሰቤ ወደ አሜሪካ እንደገና ተመለሰ። ከ26 አስደናቂ አመታት በኋላ ትናንሽ እና የተነጠሉ ክፍሎች ባሉበት በዚህ ቤተክርስቲያን ለመካፈል በጣም ጓግተን ነበር። የአጥቢያ ሚስዮናዊ እንድሆን ተጠራሁ። ታላቅ የአጥቢያ ሚስዮን መሪ ነበረን እንዲሁም አስደሳች ነገሮችን እየሰራን እና ድንቅ የሆኑ ሰዎችን እያስተማርን ነበር። በምንረዳቸው ጓደኞቼ ዙሪያ እርዳታ ለማግኘት በምክር ቤት ስብሰባ ላይ መገኘት እችል ዘንድ ጠየቅሁ። ውይይቱ በጠቅላላ በቅርቡ ስለሚካሄደው የአጥቢያ አክቪቲ ብቻ በመሆኑ ተገረምኩ። ወደ አጥቢያው የሚሲዮን መሪ ቀርቤ ስለሰዎቻችን ሪፖርት የማድረግ እድል እንዳላገኘ ገለጽኩለት። የእሱ ምላሽ? “ኦ፣ ሪፖርት እንዳደርግ እድሉ ተሰቶኝ አያውቅም” የሚል ነበር።
ይህንን ከጥቂት ሳምንታት በፊት በላሆር፣ ፓኪስታን ከተካሄደው የቅርንጫፍ ምክር ቤት ስብሰባ ጋር አነጻጸርኩ። ይህ ትንሽ ቡድን በአንድ ትንሽ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በጠቅላላ ሲያወሩ የነበረው ስለ ሰዎች ነበር። ስለ ስሞች። እያንዳንዱ መሪ ሲናገር የነበረው ስለ ሃላፊነቱ እና ስለሚያሳስባቸው ግለሰብ እና ቤተሰብ ነበር። ሁሉም የሚወያዩባቸውን ሰዎች ሊባርኩ በሚችሉበት ምርጥ መንገዶች ላይ ሃሳቦቻቸውን የመጨመር እድል ነበራቸው። እቅድ ወጥቶ እናም ሰራዎች ተሰጥተው ነበር። ከመጀመሪያው ትውልድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በስም ስለመለየት እና ስለማስተዋል እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው።
በኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ፣ በቀደሙት እና አሁን ላይ ባሉ ነቢያት እንዲሁም አዳኛችን ባስቀመጠው ምሳሌ እንዴት ማገልገል እንዳለብን ተምረናል። ስሞችን እንወስዳለን፣ እናስታውሳለን እንዲሁም ስለ ነፍስ ደህንነት እንመክራለን። ይህንን የሚያደርጉ መሪዎች በመማክርት ስብሰባዎቻቸው ላይ የአጀንዳ እጥረት አይገጥማቸውም! የመቁጠር እና ልብ የማለት መርህ የሚሰራ ነው። የጌታ መንገድ ነው። የተሻለ መስራት እንችላለን። አጽናፈ ሰማይን ለፈጠረው እና ሁሉንም ለሚገዛው ለእግዚአብሔር፣ ይህ ስራ—የእርሱ ስራ እና ክብር—በጣም ግላዊ ነው። በእርሱ አስደናቂ የማዳን እና ከፍ ከፍ የማድረግ ስራ በእርሱ እጆች ውስጥ መሳሪያ በመሆን ለምንሰራ ለእያንዳንዳችን እንደዚያ መሆን አለበት። በእውነተኛ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ተአምራት ይፈጠራሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።