የምስራች የአሰራር መመሪያ
ስለዚህ፣ በበለጠ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ህይወታችሁ መጨመር ምን ሊመስል ይችላል?
መኖሪያዬ የሆነችውን የሉዊዚያናን ክፍለ ግዛት ጎብኝታችኋት ከሆነ፣ ምናልባትም ጣእም ያላቸውን አያሌ ምግቦቻችንን ታውቋቸው ይሆናል—ጋምቦ፣ ጃምበላያ፣ ኤቶፌ፣ እና ዝርዝሩ ይቀጥላል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ከእነዚያ የምግብ እሰራርመመሪያዎች ውስጥ የሚገኘውን አንዱን ለማብሰል በመፈለግ ራሴን በድፍረት ስሜት ውስጥ አገኘዋለሁ። ሁሉም ቅመማ ቅመሞች ከተዋሃዱ በሃላ እና በዝርዝር የተቀመጠውን መመሪያ ከመከተል በኋላ ያለው የመጨረሻው ደረጃ መቅመስ እና የጎደለ ነገር አለመኖሩንለ ማረጋገጥ ነበር። በዚያ ቅጽበት፣ ክሪዮል በተሰኘ ቅመም የአበሳሰል ዘይቤ የሚነገር አፈ ታሪክ በጆሮዬ በለሆሳስ ድምጽ እንዲህ ሲል ተሰማኝ፣ “በዛ ያለ የቶኒ ጨምርበት።” የቶኒ በኦፕሉሳስ፣ ሉዊዚያና፣ እኔ በምኖርበት ክፍለ ግዛት የሚሰራ የክሪዮል ቅመም ነው። በአብዛኛው የምግብ መመሪያውን እየተከተሉ ባለበት ጊዜ የሚፈጠርን ጉድለት ለሟሟላት የሚጠቀሙት እንደ “ሚስጢራዊ ቅመማ ቅመም” አይነቶች ነው።
ባለቤቴ፣ ሚሸል እና እኔ በሉዊዚያና የሚስዮን መሪ በመሆን የማገልገልን ክብር አግኝተን ነበር። እኛ በሚስዮን ቤት ውስጥ ሚስዮናውያን አገልግሎታቸውን ጨርሰው ወደ ቤተሰቦቻቸው ከመመለሳቸው አንድ ምሽት ቀደም ብሎ ልዩ የሆነውን የጃምቦላያ ምግብ አሰራር የማስተማር ባህል ነበረን። ዳግም ከተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በተጨማሪ፣ ሚስዮናውያኖቻችን ሚስዮኑን የሚሰናበቱት የተማሩትን የምግብ አበሳሰል በማድነቅ ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት፣ በቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙሃን ቤተመጻህፍት ውስጥ ፍለጋ ሳደርግ ከፕሬዚዳንት ራሰል ኤም. ኔልሰን ጋር የተደረገ የዳግም መመለስ ንግግሮች የሚልን የአጫጭር ቪድዮዎች ስብስብ መተግበሪያን አየሁ። ከአጫጭር ቪድዮዎች መካከል ከነበሩት ዝርዝሮች ውስጥ አንዱ ትኩረቴን ሳበው እናም ፈገግ አልኩኝ። “ቅዱሳን መጻህፍት በደስታ ለመኖር የእግዚአብሄር የምግብ አሰራር መመሪያዎች ናቸው” የሚል ነበር። ወዲያውኑ ያንን የሁለት ደቂቃ ቪዲዮ በመጫን ፕሬዚዳንት ራሰል ኤም. ኔልሰን የጀማሪ ህጻናትን እንዴት ደስተኛ መሆን እንደሚችሉ ያስተማሩበትን ቀላል እና ሃያል መልእክት ተመለከትኩ። እንዲህ ሲሉ አስተማሩ፦ “ኬክ የምታዘጋጁ ቢሆን መመሪያውን ትከተላላችሁ፣ አይደለም እንዴ? እናም ሁል ጊዜ መልካም ውጤት ታገኛላችሁ፣ አታገኙም እንዴ?”
ቀጥለውም፣ በቅርቡ 95 ዓመት እንደሚሆናቸው በመናገር፤ “ሰዎች፣ ‘ምንድነው የምትመገበው? ሚስጥርህስ ምንድነው?’ ይሉኛል” እርሳቸውም ሲመልሱ፣ “ሚስጥሩ ቅዱሳት መጻህፍት ይባላል። ምናልባትም አንብባችሁ ሞክሯቸው።”
እንግዲህ፣ ይኸውላችሁ። የደስተኛ አኗኗር ቀላሉ ሚስጥር፣ በቅዱሳት መጻህፍት እንደተዘረዘረው፣ የእግዚአብሔርን የምግብ አሰራር መመሪያ መከተል ብቻ ነው። እኔ “የምስራች የአሰራር መመሪያ” ብዬ እጠራዋለሁ።
የምግብ አሰራር መመሪያውን እየተከተላችሁ ባለበት ጊዜ ችግር ቢፈጠር ምን ታደርጋላችሁ? እንግዲህ፣ ከምስራቹ የምግብ አሰራር መመሪያ ስር ሁል ጊዜ በስተመጨረሻ የተሳካ እንዲሆንላችሁ “ሚስጥራዊ ቅመማ ቅመሞች” የሚልን ታገኛላችሁ። መልሱ ሁል ጊዜም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እኔ እንደማስበው ቅመማ ቅመሞቻችን ጥሩ የማይሆኑበት፣ ወይም መመሪያውን ለመከተል የምንቸገርበት፣ ወይም ምናልባት ቅደም ተከተሉን የምናዛባበት፣ ወይም ከቁጥጥራችን ውጪ በሆነ ሁኔታ የሆነ ነገር የሚከሰትበት ወ.ዘ.ተ ቅጽበት ያጋጥመናል።
መፍትሄው ምንድን ነው? በቀላሉ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ህይወታችሁ የሚጋብዝን ተጨማሪ ነገር ማከል ነው።
ስለዚህ፣ በበለጠ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ህይወታችሁ መጨመር ምን ሊመስል ይችላል?
እንደ ሚስዮን ፕሬዚዳንት በመሆን ባገለገልኩ ጊዜ፣ በየስድስት ሳምንቱ እያንዳንዱን ወጣት ሚስዮናዊ በግል የማግኘት መልካም ተሞክሮ ነበረኝ። አንድ ለአንድ በምንገናኝበት በዚያ ወቅት፣ ሚስዮናውያን በጥምረት ከሚያገለግሉ ጓደኞቻቸው ጋር እንዴት ውጤታማ ሆነው ማገልገል እንደሚችሉ መመሪያን መጠየቅ ለእነርሱ የተለመደ ነገር ነበር።
በአንድ ወቅት፣ አንድ ሚስዮናዊ ወደ ግል ቃለመጠይቁ መጣ እናም ተቀመጠ። በዕእምሮው ውስጥ አንዳች የከበደ ነገር እንደነበር ከሰውነት እንቅስቃሴው መረዳት ችያለሁ። እኔም “ዛሬ ስለምን ብንወያይ ትወዳለህ?” በማለት ጠየቅሁ። ከአገልጋይ ጓደኛው ጋር የነበረበትን አንዳንድ ተግዳሮቶች እና ይህም የሚስዮናዊ አገልግሎታቸውን ለማከናወን ባላቸው ችሎታ ላይ ምን ያህል ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን መግለጽ ጀመረ። አይኖቹ እንባ እያቀረሩ፣ እኔን በመመልከት እንዲህ ሲል ጠየቀ፣ “ፕሬዚዳንት፣ ምን ላደርግ ይገባኛል?”
በዚያ ቅጽበት፣ በእውነት ምን መመለስ እንደነበረብኝ አላወቅሁም። ከአጭር ቆይታ በኋላ፣ በአንድነት የመንፈስን ምሪት ለማግኘት ለጸሎት መንበርከክ የምንችል መሆኑን ጠየቅሁት። እርሱም ተስማማ፣ እናም ተንበረከክን እናም ተነሳሳሽነትን ለማግኘት ጸለይን።
ከጸሎቱም በኋላ፣ ለአጭር ጊዜ መንበርከካችንን ቀጠልን እና አንዳችን ሌላኛውን ማየት በምንችልበት ሁኔታ ወንበሮቻችን ላይ ተቀመጥን። አንድን ጥቅስ ማንበብ የምንችል እንደሆነ ጠየቅሁት። ቅዱስ መጽሃፋችንን እንደከፈትን፣ አቋርጬ እንዲህ አልኩት፣ “ይህንን ጥቅስ በምናነብበት ወቅት፣ እባክህ ራስህን ይህን ጥያቄ ጠይቅ፤ እነዚህን ባህርያት የምኖር ከሆነ፣ ከጓደኛዬ ጋር ያለኝን ግንኙነት እና የሚስዮናዊ አገልግሎታችንን ያሻሽለዋልን?”
ከዚያም ሞሮኒ 7፥45ን ከፈትን እና ከፍ ባለ ድምጽ አነበብን፤ “እናም ልግስና ትታገሳለች፣ እናም ደግ ናት፣ እናም አትቀናም፣ እናም በኩራት አትወጠርም፣ የራሷን አትፈልግም፤ በቀላሉ አትቆጣም፣ ክፉ አታስብም፣ እናም በመጥፎ ስራ አትደሰትም፣ ነገር ግን በእውነት ትደሰታለች፣ ሁሉንም ነገሮች ትታገሳለች፣ በሁሉም ነገሮች ታምናለች ሁሉንም ነገሮች ተስፋ ታደርጋለች፣ በሁሉም ነገሮች ትፀናለች።”
እርሱም እኔን በመመልከት አይኖቹ እንባ እያቀረሩ እንዲህ አለ፣ “አዎን፣ ፕሬዚዳንት፣ ነገር ግን ያንን ማድረግ ከባድ ነው።” እኔም ተስማማሁ እና እርሱ ከጌታ ጋር አብሮ ለመስራት መለኮታዊ አቅም ያለው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አስታወስኩት።
ከዚያም ካለንበት ልንነሳ እና ከጌታም ጋር ቀጥተኛ በሆነ አቅጣጫ ወደ ፊት እና ወደ ላይ መሄድ እንዳለብን የሚያስታውሰንን ሽማግሌ ክላርክ ጂ. ጊልበርት ያስተማሩትን የተዳገቱ ምሳሌ በአጭሩ ተወያየን። በቀጣዮቹ እርምጃዎች አሁንም ከባድ ስሜት እየተሰማው ያለ መሆኑን መገመት ቻልኩኝ፣ ስለዚህ “በትንሽና በቀላል ነገሮች ታላቅ ነገሮች ተፈፅመዋል” ለሚለው ጥቅስ የእርሱን መረዳት እንዲገልጽልኝ ጠየቅሁት። ትንሽ እና ቀላል የሆኑ ነገሮችን በማድረግ ታላላቅ ነገሮች ሊከናወኑ ይችላሉ የሚለውን ሃሳብ መግለጽ ጀመረ። አንድ ደቂቃ እንዲወስድ እና ለጓደኛው ደግ መሆን የሚችልባቸውን ሁለት ትንሽ እና ቀላል ነገሮችን እንዲለይ ጠየቅሁት።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሃሳቡን አካፈለ። ከዚያም አንድ ደቂቃ እንዲወስድ እና ለጓደኝው ታጋሽ መሆን የሚችልባቸውን ሁለት ትንሽ እና ቀላል ነገሮችን እንዲለይ ጠየቅሁት። ወዲያውኑ የእርሱን ሁለት ሃሳቦች አካፈለ። ከስብሰባችን ቀደም ብሎ ይህን ሲያሰላስል እንደነበር ግልጽ ነው። እቅዱን በእውነተኛነት እንዴት መፈጸም እንደሚችል እነዚያን ጥቂት ጉዳዮች ለእርግጠኝነታቸው፣ ለምሪት፣ እና ለመነሳሳት በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት እንዲወስዳቸው ጋበዝኩት። እርሱም ተስማማ። እየጨረስን ሳለ፣ በሳምንታዊ ደብዳቤውም አጭር ማስታወሻ እንዲያዘጋጅ ጠየቅሁት።
ቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት እንዳለፉ፣ በሳምንታዊ ደብዳቤዎቹ ላይ ነገሮች እየተሻሻሉ መሆኑን ለመመልከት ቻልኩ። ነገር ግን ያንን መሻሻል በእርሱ ሳምንታዊ ደብዳቤው ላይ መመልከት ብቻ ሳይሆን፣ ግን በጓደኛውም ሳምንታዊ ደብዳቤ ላይ ጭምር ለማየት ችያለሁ። በቀጣዩ የግል ቃለ መጠየቅ ላይ፣ በፊቱ ላይ ታላቅ ልዩነቶችን ተመለከትኩ። እንዲህም በማለት ጠየቅሁት፣ “ስለዚህ፣ ልግስና ለዘወትር አይወድቅም የሚለው እውነት ነውን?” በታላቅ ፈገግታ እንዲህ ሲል መለሰ፥ “አዎን እናም በትንሽና በቀላል ነገሮች ታላቅ ነገሮች ተፈፅመዋል።”
ለደስተኛ አኗኗር የምስራቹን የምግብ አሰራር መመሪያ በተከተላችሁ ጊዜ፣ የፕሬዚዳንት ኔልሰንን አስተምሮዎች አስታውሱ፣ “ምንም አይነት ጥያቄዎች ወይም ችግርች ቢኖሯችሁ፣ መልሱ ሁልጊዜም በኢየሱስ ክርስቶስ ህይወት እና ትምህርት ውስጥ ይገኛል።” ስለኃጢያት ክፍያው፣ ፍቅሩ፣ ምህረቱ፣ አስተምሮቱ፣ እና በዳግም ስለተመለሰችው የፈውስ እና የእድገት ወንጌሉ የበለጠ ተማሩ። ወደ እርሱ ተመለሱ! እርሱን ተከተሉ!”
“እርሱን መስማት” ባስፈለጋችሁ ጊዜ እና ወደ ህይወታችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት መጋበዝ እንደምትችሉ ማወቅ ባስፈለጋችሁ ጊዜ፣ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ስለግል ራእይ ያስተማሩንን ደረጃዎች መከተልን አስታውሱ።
“በመደበኛነት የምትሄዱበትን ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ ምረጡ። በእግዚአብሄር ፊት ራሳችሁን ትሁት አድርጉ። ወደ ሰማዩ አባታችሁ ልባችሁን አፍስሱ። ለመልስ እና ለመጽናናት ወደ እርሱ ዘወር በሉ።
“ስለ ጭንቀቶቻችሁ፣ ስለ ፍርሃቶቻችሁ፣ ስለ ድክመቶቻችሁ፣ ስለልባችሁ ምኞቶች፣ አዎን የልባችሁ ጉጉት ስለሆነውም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጸልዩ። ከዚያም አድምጡ! ወደ አእምሯችሁ የሚመጡትን ሀሳቦች ጻፉ። ስሜቶቻችሁን መዝግቡ እና እንድታደርጉት የተነሳሳችሁትን እርምጃዎች ተከታሉ። ይህን ሂደት ከቀን ወደ ቀን፣ ከወር ወደ ወር፣ ከዓመት ወደ ዓመት ስትደግሙት ‘ወደ ራዕይ መርህ ታድጋላችሁ።’”
ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችን እንደሆነ እመሰክራለሁ። እርሱም “ወደ ሰማዩ [አባታችን] ለመመለስ እንድንችል ሁሉን ፈጽሟል።” በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።