አጠቃላይ ጉባኤ
እግዚአብሔር ልብን ያያል
የጥቅምት 2025 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:41

እግዚአብሔር ልብን ያያል

እግዚአብሔር አላማዎቹን ለማሳካት እና እርሱ እንደሚፈልገን እንድንሆን እኛን ለመርዳት እያንዳንዳችንን በሙሉ ልብ ወደ እርሱ መመለስ እንዳለብን ነው።

ከእሴይ ልጆች መካከል አዲሱን የእስራኤል ንጉስ እንዲመርጥ በታዘዘ ጊዜ፣ ነቢዩ ሳሙኤል የእሴይን ታላቁን ልጅ፣ ኤሊያብን በማየት፣ ‘’በእውነት በጌታ የተቀባው እርሱ በፊቱ ነው’’ በማለት ከፍ ባለ ድምጽ እንዲሁም በጉጉት ተናገረ። ነገር ግን ኤሊያብ በጌታ የተመረጠ ባሪያ አልነበረም። ይህም የተሳሳተ መደምደሚያ ሆኖ ተገኘ፣ ጌታም ሳሙኤልን እንዲህ ሲል አስተማረው፦ “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ምክንያቱም እኔ አልተቀበልኩትም፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና … ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።”

ዳዊት ከወንድሞቹ ይልቅ በአካል የበረታ ወይም ብዙ ችሎታ የነበረው ባይሆንም፣ በእግዚአብሔር እይታ ልቡ የበረታ ነበር። እግዚአብሔርን በሙሉ ልቡ የሚወድ እና እርሱንም ለመታዘዝ ጥልቅ የሆነ ፍላጎት ነበረው። በእግዚአብሔር ፍቅር፣ ሃይል እና የተስፋ በረከቶች የማይናወጥ እምነት ነበረው፣ በኋላም በጌታ እርዳታ ጎልያድን ያለፍርሃት በመፋለም እና በማሸነፍ ይህንን አሳይቷል።

ይህ ታሪክ የሚያስተምረን እግዚአብሔር አላማዎቹን ለማሳካት እና እርሱ እንደሚፈልገን እንድንሆን እኛን ለመርዳት እያንዳንዳችንን በሙሉ ልብ ወደ እርሱ መመለስ እንዳለብን ነው። ለአንድ ጠበቃ፣ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ ውደድ” በማለት አዝዟል። ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ፣ እንዲህ አለው፣ “እነሆ፣ ጌታ ልብን እና መልካም ፈቃድ ያለውን አዕምሮ ይሻል።” ለኔፋዊያንም፣ ትንሳኤን ያደረገው አዳኝ “ለእኔም መስዋእት የተሰበረ ልብና የተዋረደ መንፈስ ታቀርባላችሁ” የሚል ግብዣ አቅርቧል።

ያየሆነው ለምንድን ነው? አዳኙ እንዳስተማረው በሙሉ ልብ ወደ እርሱ ብንመለስ፣ በሃጢያት ክፍያው ምክንያት፣ ምድራዊ ተግዳሮቶቻችንን ለመቋቋም፣ ፈተናዎችን ለማሸነፍ፣ ምሪትን እና መረዳትን ለመቀበል፣ እና በህይወታችን ሃሴት እና ሰላም እንዲሰማን በሚያስችለን ጥንካሬ እና መንፈሳዊ ስጦታ ልንባረክ እንችላለን። “ከትንንሾቹ ነገሮች ታላቅ ነገሮች ይወጣሉ።” እርሱም ደካማዎቹን ነገሮች ወደ ጥንካሬ’’ መለወጥ እንደሚችል እና በምድራዊ ህይወት ስኬታማ ለመሆን በሚያስፈልገን ነገር እንዲሁም ዘለዓለማዊ ህይወት እንድናገኝ ሊባርከን እንደሚችል ተናግሯል። “ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና” አለ።

በከፊልም ቢሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ጸሃፍት እና ፈሪሳውያንን ሲገስጻቸው የነበረው ለዚህ እንደሆነ አምናለሁ። ምንም እንኳ የእርሱን ህግ በመጠበቅ ይተጉ የነበረ ቢሆንም፣ ያንን ሲያደርጉ የነበረው በተሳሳተ ምክንያት ነበር። “ይህ ህዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው’’ በማለትም ይገስጻቸው ነበር።

ይህ ስለምናደርገው ነገር ብቻ ሳይሆን—ስለ ቃላቶቻችን እና ድርጊቶቻችን ሳይሆን—ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድናደርግ ያዘዘንን ለምን እንደምናደርገው ጭምር—ፍላጎቶቻችንን እና ዋና ትኩረታችንን የሚሻ መሆኑን የእርሱ ደቀ መዛሙርት ለሆኑት ሁሉ ትሁት ማሳሰቢያ ነው። እርሱም “እኔ ጌታ ሁሉንም ሰዎች በስራዎቻቸው መሰረት፣ እንደልባቸውም ምኞት እፈርድባቸዋለሁና” በማለት ተናግሯል። የሰማይ አባታችን ከልጆቹ ከይስሙላ የመታዘዝ እና የአገልግሎት ድርጊት በላይ ይፈልጋል። እነዚህን ነገሮች በሙሉ ልባችን እንድናደርጋቸው የሚፈልገው በሙሉ ልባችን ስለምንወደው እንዲሆን ነው። እንደ እርሱ መሆንን እንድንሻ ይፈልጋል።

አሁን፣ የልባችን መንፈሳዊ ጤንነት ለጌታ ዋናው አሳሳቢ ጉዳይ ከሆነ—ከአንድ እውነተኛ ደቀመዝሙር ምን እንደሚጠብቅ—ልባችንን በእግዚአብሔር ፊትም ትክክል መሆኑን በማወቅ እንዴት ልንመረምር እንችላለን?

በቅርቡ፣ እኔና ባለቤቴ ከፖርቹጋል የሚስዮን አገልግሎት ከተመለስን በኋላ የአካላዊ ጤንነታችንን ጉዳይ ለመገምገም ተከታታይ የጤና ምርመራ አድርገን ነበር። አንዳንዶቹ ምርመራዎች በልባችን ጤንነት ላይ ያተኮሩ ነበሩ—እንደደም ምርመራ፣ በልብ ሁለንተናዊ ጤንነት ላይ ያተኮሩ ምርመራዎች ነበሩ። አዳኛችንም እንዲሁ የልባችንን የጤንነት ሁኔታ ለመከታተል መንፈሳዊ የምርመራ ሁኔታዎችን እንዳዘጋጀልን አምናለሁ። ጥቂቶቹን ለእናንተ ላካፍላችሁ።

ልባችሁን በመንፈሳዊ ምርመራዎች መፈተሽ

በመጀመሪያ፣ ትኩረታችን፣ቅድሚያ የምንሰጣቸው እና ዝንባሌያችን

“መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና፣” በማለት ኢየሱስ አስተምሯል። መዝገብ ለእኛ ውድ የሆነ ነገር ነው፣ ጥረታችንን እና ትኩረታችንን የምንሰጠው ነገር ነው። ጊዜያችንን የምንሰጠው እና ትጉረታችንን የምናደርግበት፣ የምናደርገውን እንድናደርግ የሚያነሳሳን እርሱ ስለልባችን ብዙ ይናገራል። “ልባቸውን በአለም ነገሮች ላይ ስለሚያደርጉ እና በሰዎች ይሞገሱ ዘንድ ስለሚነሳሱ” ብዙዎች እንደተጠሩ እና ጥቂቶች ብቻ እንደተመረጡ ጌታ አስጠንቅቋል። በህይወቴ ለአዳኙ ቅድሚያ እሰጣለሁ? የማደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ለእርሱ ክብር ብቻ አደርጋለሁ?

ሁለተኛ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለማክበር ያለን ፈቃደኝነት

በቅዱሳን መጽሐፍት በሙሉ፣ ጌታ እና የእርሱ ነቢያት ትእቢትን እና አለመታዘዝን ከደንዳና ልብ ጋር ያያይዙታል። ኔፊ “እናንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የማታከብሩትት እንዴት ነው? በልባችሁስ ደንዳናነት ምክንያት የምትጠፉት እንዴት ነው?” በማለት ወንድሞቹን መክሯል። በሚዙሪ የነበሩትን ቅዱሳን ጌታ ‘’ነገር ግን እስኪታዘዝ ድረስ ምንም የማያደርግ፣ እና ትእዛዝን በሚጠራጠር ልብ የሚቀበል እና በስንፍና የሚጠብቅ፣ እርሱ ይፈረድበታል’’ በማለት አስጠንቅቋል። ትዕዛዛቱን በማክበር ላይ ጌታ ፍጹምነትን የሚጠብቅ ባይሆንም፣ እርሱ በሙሉ ልባችን ለመጠበቅ የልባችንን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ይጠይቃል።

ሶስተኛ፣ ቅዱሳን መጽሐፍትን ለማጥናት እና ራእይን ለመሻት ያለን ትጋት

ጌታ ኦሊቨር ካውድሪን “ስለዚህ እነዚህን ቃላት በልብህ አከማች” ሲል አሳስቦታል። ቅዱሳን መጻህፍትን በትጋት እንድንመረምር እና በመንፈስ ቅዱስ ሃይልም አማካኝነት በልባችን የወንጌልን እውነተኛነት፣ እንዲሁም መረዳትን እና ምስክርነት ለማግኘት ተጋብዘናል።

ነቢዩ አቢናዲ ክፉ የሆነው የንጉስ ኖህን ቀሳውስት ያንን ባለማድረጋቸው ‘’ልባችሁን ለመረዳት ያዘጋጃችሁ አይደላችሁም፤ በመሆኑም ጥበበኞች አልሆናችሁም’’ በማለት ይገስጻቸዋል። ቅዱሳን መጽሐፍትን በየእለቱ ለማጥናት እና በጸሎት አማካኝነት እነርሱንም ለመረዳት ልቤን ለመጠቀም እውነተኛ የሆነ ጥረት እያደረግሁ ነው?

አራት፣ ሃሳባችን እና ቃላቶቻችን

አዳኙ “ክፉ ሃሳብ ከልብ ይወጣልና” እንዲሁም“በልብ ሞልቶ የተረፈው በአንደበት ይገለጣል” በማለት አስተምሯል። የሃሳባችን እና የቃላቶቻችን ጥራት የልባችን ንጽህና መልካም አመላካች ነው። እኔ ስለሌሎች ወይም ስለራሴ ተግባራት ወይም ዝንባሌ አያሌ እኩይ የሆኑ ሃሳቦችን እያበረታታሁ ነው? ሌሎችን ለመፈረጅ እና ለመኮነን ፈጣን ነኝ? ለጥፋቶቼ ማመካኛ ወይም ምክንያት እፈልጋለሁ? ቃላቶቼስ እንዴት ናቸው? ቃላቶቼ በዙሪያዬ ያሉትን ከፍ የሚያደርጉ እና የሚያነሳሱ ናቸው? ወይስ በአብዛኛው ግጭትን እና ቅሬታን የሚፈጥሩ ናቸው?

አካላዊ ምርመራዬ እንዳለቀ፣ ሃኪሜ በአጠቃላይ ልቤ ጤነኛ መሆኑን ነገረኝ—ነገር ግን የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት አሁኑኑ ሊስተካከሉ የሚገቡ ጥቂት አሳሳቢ ጉዳዮች ነበሩ። ከዚያም የህይወት ዘይቤ ለውጦችን አዘዘልኝ። በተመሳሳይ መልኩ፣ የልባችሁን መንፈሳዊ ሁኔታ በምትገመግሙበት ጊዜ እና አንዳንድ እኩይ የሆኑ ምልክቶች መግባት ሲጀምሩ፣ እባካችሁ አትሸበሩ! አዳኙ እናንተን ለመርዳት ድንቅ የሆነ መንፈሳዊ መድሃኒት እና ህክምና አዘጋጅቷል። እንዲያውም አዲስ ልብ ሊሰጣችሁ ቃል ገብቷል! የልባችሁን መንፈሳዊ ጥንካሬ ሊያሻሽሉ የሚችሉ አንዳንድ ድርጊቶች የሚከተሉት ናቸው፥

የልባችሁን መንፈሳዊ ጤና ማሻሻል

በመጀመሪያ፣ ከክርስቶስ ጋር ግንኙነታችሁን አጠናክሩ

በየቀኑ ወደ ክርስቶስ ለመምጣት ጊዜያችንን በሰጠን ጊዜ፣ ልባችን ይቀየራል። ከልብ በሆነ ጸሎት እና በመደበኛ ጾም የታገዘ የእለት ተእለት የቅዱሳን መሳህፍት ጥናት፣ ለአዳኙ ያላችሁን ፍቅር ይጨምራል እንዲሁም እምነታችሁን እና ንሰሃ ለመግባት ያላችሁን ፍላጎት ይጨምራል፣ ልባችሁንም በትህትና ወደ እግዚአብሔር ይማርካል። “ወደ ጌታ ጮህኩ፤ እነሆ እርሱም ጎበኘን፣ እኔም አባቴ የተናገራቸውን ቃላት ሁሉ እንዳምን ልቤን አባባው“ የሚለውን ይህን የኔፊን ምሳሌ አስቡ።

የእምነትን ዘር ጻድቅ በሆነ ፍላጎት እና ድርጊት ለመንከባከብ በቀጠልን ጊዜ፣ እንደኔፋውያን ተመሳሳይ የሆነ የልብ መቀደስን እንለማመዳለን፤ “ይሁን እንጂ ዘወትር ፆሙ፣ እንዲሁም ፀለዩ፣ ነፍሳቸውንም በደስታና በመፅናናት እስከሚሞሉ ድረስ፣ አዎን፣ ልባቸውን ለእግዚአብሔር በፍቃዳቸው በመስጠት በሚመጣው ቅድስና ልባቸው እንዲጸዳና እንዲቀደስ እስከሚያደርጉ ድረስ በትህትና እየጠነከሩ፣ በክርስቶስም እምነታቸውን እያጸኑ ሄዱ። በሃሴት እና በመጽናናት ነፍሳቸው እስኪሞላ ድረስ፣ አዎን ልባቸው እስኪጸዳ እና እስኪቀደስ ድረስ ይህም ልባቸውን ለእግዚአብሄር በመስጠታቸው ምክንያት የሆነ ነው።”

ሁለተኛ፣ ፍላጎታችሁን ከእርሱ ፍቃድ ጋር ማስማማት

አዳኙም ሲያስተምር፣ “ብትወዱኝ ተዛዛቴን ጠብቁ’’ ብሏል። ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እና በመጠበቅ ፍቅራችንን እንድናሳይ ይጋብዘናል። በየእለቱ ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ በጣርን ጊዜ፣ ከልብ ለሃጢያታችን ንሰሃ ስንገባ፣ እና የእርሱንም ስም በላያችን ላይ ለመውሰድ በተጋን ጊዜ እና ፈቃዳችንን ከእርሱ ፈቃድ ጋር ስናስማማ፣ ቋሚ በሆነ የመንፈስ ቅዱስ ህብረት ልንባረክ እንችላለን።

ኔፊ ‘’ስለዚህ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ በሙሉ ልባችሁ አላማ፣ በእግዚአብሔር ፊት ባለማስመሰልና ያለግብዝነት፣ ነገር ግን በእውነት ፍላጎት፣ ለኃጢአታችሁ ንስሀ በመግባት፣ በጥምቀት የክርስቶስን ስም በራሳችሁ ላይ መውሰዳችሁን ለአብ በመመስከር ወልድን ብትከተሉ—አዎን፣ እንደቃሉ ጌታችሁንና አዳኛችሁን ወደ ውኃው ብትከተሉ፣ እነሆ፣ መንፈስ ቅዱስን እንደምትቀበሉ አውቃለሁ’’ ሲል መስክሯል። መንፈስ ቅዱስ ይመራችኋል፣ የጌታንም ፈቃድ እንድታውቁ እና መልካም ምርጫዎችን እንድታደርጉ ይረዳችኋል።

በመጨረሻ፣ በሙሉ ልባችሁ እግዚአብሔርን እና ሌሎችን አገልግሉ

አዳኙ ሁሉን ሰዎች “በሙሉ ልባቸው [እንዲያገለግሉት]” ጋብዟል። ጌታ ያዘዘንን እያንዳንዱን ነገር ለማድረግ ስንመረጥ—ትእዛዛቱን ማክበር፣ ቅዱስ ቁርባንን መካፈል፣ በቤተመቅደስ አምልኮ፣ እና ሌሎችን ማገልገል—በሙሉ ልብ እና በእውነተኛነት ካደረግን እያንዳንዱ የአገልግሎት ስራ እምነታችንን እና ምስክርነታችንን የሚያጠናክር ሃያል መንፈሳዊ ልምምድ ይሆናል እንዲሁም ለእግዚአብሄር እና ለባልንጀሮቻችን ልባችንን በሃሴት እና በፍቅር ይሞላዋል።

ዛሬም የነቢዩ አልማ ጥያቄ ያስተጋባል፣ “በመንፈስ ከእግዚአብሔር የተወለዳችሁ ናችሁን? በፊታችሁስ ምስሉን ተቀብላችኋልን? በልባችሁስ ይህንን ታላቅ ለውጥ ተለማምዳችኋልን?’’

ወንድሞች እና እህቶች፣ ዛሬ ሙሉ ልባችሁን ለአዳኙ እንድትሰጡ እጋብዛችኋለሁ። እያንዳንዱ የአምልኮ እና የአገልግሎት ድርጊት ልባዊ እና የታሰበበት ይሁን። ከዓለም የሆኑ ሃሳብን የሚበትኑትኑ ነገሮችን ወደ ጎን ተዉ እና በየእለቱ በህይወታችሁ ለጌታ ትርጉም ያለው ጊዜ እንዲኖራችሁ ጣሩ። ንሰሃ ግቡና በሙሉ ልባችሁ ወደ እርሱ ተመለሱ፣ እርሱም ይቅር ይላችኋል፣ በፍቅሩም እቅፍ ይይዛችኋል። የዚህን አለም ነገሮች አትፈልጉ ነገር ግን በትኩረት የእርሱን ክብር እና የተሻለውን ነገር ምረጡ። እርሱ ሃሳባችሁን እና የልባችሁን ምኞት ያውቃል፣ ወደ እርሱም በመጣችሁ ጊዜ፣ በብርታት፣ በራስ መተማመን፣ በሰላም እና በደስታ በዚህ ህይወት እና በዘለዓለም የሰለስቲያል መንግስቱ ውስጥ ስፍራን በመስጠት ይባርካችኋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው እንደሆነ አውቃለሁ። እርሱ ቤዛችን ነው። እርሱ እናንተን እና እኔን በሙሉ ልቡ ይወደናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።