በሙሉ ልባችሁ ድርሻችሁን ተወጡ
በትዕግስት እና በትጋት፣ በሙሉ ልብ የድርሻችንን ለማከናወን አዳኝን በብቃት እመኑ።
ባለፈው አመት ወደ አውሮፓ በሄድኩበት ወቅት የቀድሞ የስራ ቦታዬ የሆነውን በፍራንክፈርት አየር ማረፊያ የሚገኘውን ሉፍታንዛ የጀርመን አየር መንገድ ጎበኘሁ።
የአውሮፕላን አብራሪዎቹን ለማሰልጠን ማንኛውንም ሊባል የሚችል መደበኛ እና ድንገተኛ የበረራ ሁኔታን የሚፈጥሩ በርካታ የተራቀቁ ሙሉ ለሙሉ የሚንቀሳቀሱ ምስለ በረራዎችን ይጠቀማል። የአየር መንገድ አብራሪ ሆኜ ባሳለፍኳቸው በርካታ ዓመታት የአብራሪነት ፍቃዴን ወቅታዊ ለማድረግ በየስድስት ወሩ የሙከራ በረራ በምስለ በረራ ማድረግ ነበረብኝ። የእነዚያን ከባድ የጭንቀት እና የውጥረት ጊዜያት ብቻ ሳይሆን ፈተናውን ካለፍኩ በኋላ ይሰማኝ የነበረውን የስኬታማነት ስሜት በደንብ አስታውሳለሁ። በዚያን ጊዜ ወጣት የነበርኩኝ ሲሆን ፈተናውንም እወደው ነበር።
በጉብኝቴ ወቅት፣ ከሉፍታንዛ ስራ አስኪያጆች አንዱ የቢ747 ምስለ በረራን አንድ ጊዜ እንደገና ማብረር መሞከር እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ።
በጥያቄው ላይ ሙሉ በሙሉ ለማሰብ ጊዜ ከማግኘቴ በፊት፣ በሚያስገርም ሁኔታ የራሴ የሚመስል ድምፅ፣ “አዎ፣ በጣም ደስ ይለኛል” ሲል ሰማሁት።
ቃላቱን አንደተናገርኩኝ የሀሳብ ናዳ አእምሮዬን አጥለቀለቀው። 747 አውሮፕላንን ካበርኩኝ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል። በዚያን ጊዜ ወጣት እና በራስ መተማመን የነበረኝ አብራሪ ካፒቴን ነበርኩ። አሁን፣ እንደቀድሞ ዋና አብራሪነቴ የምጠብቀው መልካም ስም ነበረኝ፡፡ በእነዚህ ባለሙያዎች ፊት ራሴን አሳፍር ይሆን?
ሆኖም ወደ ኋላ ለማለት በጣም ዘግይቼ ነበር፣ ስለዚህ በአብራሪው ወንበር ላይ ተቀምጬ፣ እጆቼን በተለመዱት እና በተወዳጆቹ መቆጣጠሪያዎች ላይ አደረኩኝ ከዚያም፣ ትልቅ ሰማያዊ አውሮፕላን በማኮብኮቢያው ላይ ሲያጓራ እና በሰማያዊ የነፃነት አየር ሲያኮበኩብ እንደገና ተሰማኝ።
በረራው የተሳካ ነበር ለማለት ያስደስተኛል፣ አውሮፕላኑም በጥሩ ሁኔታ ላይ ነበር፣ ለራሤ የነበረኝ አመለካከትም እንዲሁ።
ያም ሆኖ ልምዱ ለእኔ ትሁት የሚያደርግ ነበር። ብቃቴ ከፍተኛው ደረጃ ላይ በነበረበት ወቅት ማብረር እንደ ሁለተኛ ተፈጥሮዬ ቀላል ነበር። አሁን፣ ቀላሉን ነገር ለማድረግ ሙሉ ትኩረቴ አስፈልጎት ነበር።
ደቀ መዝሙርነት ራስን መግዛትን ይጠይቃል
በምስለ በረራው ውስጥ የነበረኝ ተሞክሮ በማንኛውም ነገር ብቁ መሆን— መብረርም ሆነ፣ መቅዘፍ፣ ልብስ ስፌት፣ ወይም እውቀት ማግኘት — የማያቋርጥ ራስን መግዛት እና ልምምድን እንደሚጠይቅ አስፈላጊ ማሳሰቢያ ነበር።
ክህሎትን በማግኘት ወይም ተሰጥኦን በማዳበር አመታትን ልታሳልፉ ትችላላችሁ። እንደ ሁለተኛ ተፈጥሯችሁ ቀላል እስኪሆንላችሁ ድረስ በጣም ጠንክራችሁ ትሰሩ ይሆናል። ሆኖም ይህ ማለት ልምምድ ማድረግ እና ማጥናት ማቆም እንችላለን ብላችሁ ካሰባችሁ፣ ቀስ በቀስ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ያገኛችኋቸውን እውቀት እና ችሎታዎች እያጣችሁ ትሄዳላችሁ።
ይህ ቋንቋን እንደ መማር፣ የሙዚቃ መሳሪያን እንደ መጫወት እና የአየር መንገድ አውሮንን እንደማብረር ባሉ ክህሎቶች ላይም ይሠራል። የክርስቶስ ደቀ መዝሙር በመሆን ላይም ይሠራል።
በቀላል አነጋገር ደቀ መዝሙርነት ራስን መግዛትን ይጠይቃል።
ይህ ተራ ጥረት በማድረግ እንዲሁም በአጋጣሚ የሚመጣም አይደለም።
በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ስጦታ ነው፣ ሆኖም እሱን ለመቀበል የሁላችንን “ሃይል፣ አእምሮ እና ጉልበት” ቁርጠኝነት የሚጠይቅ የታሰበበት ምርጫ ነው። በየዕለቱ የሚደረግ ልምምድ ነው። እንዲሁም በየሰዓቱ። የማያቋርጥ ትምህርት እና የማያወላውል ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። እምነታችን፣ ለአዳኙ ያለን ታማኝነት፣ በዚህ በምድራዊ ህይወት ውስጥ በሚገጥመን ተቃውሞ ሲፈተን እየጠነከረ ይሄዳል። መንከባከባችንን ስለምንቀጥል፣ በንቃት መተግበራችንን ስለምንቀጥል ይጸናል እንዲሁም ተስፋ አንቆርጥም።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ እምነትንና የዚህን አሳማኝ ኃይል መጠቀም ካልቻልን፣ በአንድ ወቅት ቅዱስ አድርገን ለያዝናቸው ነገሮች ያለን እርግጠኛነት ይቀንሳል፤ ይህም ቀደም ሲል እውነት እንደሆኑ ስለምናውቃቸው ነገሮች እርግጠኝነታችን ይቀንሳል።
በአንድ ወቅት እኛን የማይስቡን ፈተናዎች ብዙም የማያስጠሉ እና ይበልጥ የሚማርኩ ሆነው መታየት ይጀምራሉ።
የትናንትናው ጠንካራ ምስክርነት ሊያሞቀን የሚችለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። በድምቀት መብራቱን እንዲቀጥል የማያቋርጥ እንክብካቤ ያስፈልገዋል።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ ለእያንዳንዱ አገልጋዮቹ የተቀደሰ አደራ ይኸውም መክሊት የሚባል የገንዘብ መጠን ስለሰጠ ጌታ የሚናገር ምሳሌ አዳኙ አስተምሯል። መክሊታቸውን በትጋት የተጠቀሙ አገልጋዮች አበዟቸው። መክሊቱን የቀበረው አገልጋይ መጨረሻ ላይ ጠፋበት።
እዚህ የምንማረው ትምህርት? እግዚአብሔር የእውቀት፣ የችሎታ፣ የእድል ስጦታዎችን ይሰጠናል እንዲሁም እኛን እና ሌሎች ልጆቹን ይባርኩ ዘንድ እንድንጠቀምባቸው እንድናሳድጋቸው ይፈልጋል። እነዚያን ስጦታዎች በየጊዜው እንደምናደንቀው የስኬት ሽልማት መደርደሪያ ላይ ብናስቀምጠው ይህ ሊሆን አይችልም። ስጦታዎቻችን የሚያጎሉት እና የሚበዙት ስንጠቀምባቸው ብቻ ነው።
ተሰጥኦ አላችሁ
“ነገር ግን ሽማግሌ ኡክዶርፍ፣ ቢያንስ ያን ያህል ዋጋ ያላቸው ምንም ስጦታዎች ወይም ተሰጥኦዎች የሉኝም” ልትሉ ትችላላችሁ። ምናልባት ግልጽ እና አስደናቂ የሆኑ የሌሎችን ስጦታዎችን ልትመለከቱ እና በንፅፅር የእናንተ ተራ እንደሆኑ ይሰማችሁ ይሆናል። በቅድመ ምድር ህይወታችን፣ ታላቁ የስጦታ እና የተሰጥኦ አይነቶች በተሰጡበት ቀን፣ የእንናንተ ሳህን በተለይ ከሌሎች ከሞሉና ከተትረፈረፉ ሳህኖች ጋር ሲወዳደር በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ትንሽ እንደሆኑ ታስቡ ይሆናል።
እናንተን አቅፌ ይህን ታላቅ እውነት እንድትረዱ እንዴት ባደርግ ምንኛ ደስ ባለኝ፤ እናንተ ማለቂያ የሌለው የአምላክ የመንፈስ፣ የተባረካችሁ የብርሃን ልጅ ናችሁ። እንዲሁም ልታስቡት ከምትችሉት በላይ የሆነ አቅም በውስጣችሁ ተሸክማችኋል።
ባለቅኔዎች እንዳስተዋሉት ወደ ምድር የመጣችሁት “የክብር ደመና እየተከተላችሁ ነው” !
መነሻ ታሪካችሁ መለኮታዊ ነው፣ ፍፃሜያችሁም እንዲሁ ነው። ሰማያትን ትታችሁ ወደዚህ መጣችሁ ነገር ግን ሰማያት አልተዋችሁም!
እናንተ ተራ አይደላችሁም።
ተሰጥኦ አላችሁ!
በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ፣ እግዚአብሔር እንዲህ አውጇል፦
እያንዳንዱም ሰው አንድ ስጦታ በእግዚአብሔር መንፈስ ተስጥቶታል።
ሁሉም በዚህም እንዲጠቀሙበት፣ ለአንዳንዶቹ አንድ ተሰጥቷል፣ እና ለሌሎችም ሌላ ተሰጥቷል።”
አንዳንድ ስጦታዎቻችን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተዘርዝረዋል። ብዙዎቹ አልተዘረዘሩም።
ሞሮኒ እንደተናገረው፣ “የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንዳትክዱአቸው አጥብቄ እመክራችኋለሁ፣ ብዙ ናቸውና፤ እና እነርሱም የሚመጡት ከአንድ እግዚአብሔር ነው። የሚገለጡበት “የተለያዩ መንገዶች አሉ ነገር ግን ሁሉን በሁሉ የሚያደርገው እግዚአብሔር አንድ ነው”
መንፈሳዊ ስጦታዎቻችን ሁል ጊዜ የሚስቡ አለመሆናቸው እውነት ነው፣ ይህ ማለት ግን አስፈላጊነታቸው ያነሰ ነው ማለት አይደለም። በዓለም ዙሪያ ባሉ አባላት ላይ ያስተዋልኳቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎች ላካፍላችሁ? እንደዚህ ባሉ በአንድ ወይም በብዙ ስጦታዎች እንደተባረካችሁ አስቡ፡-
-
ርህራሄ ማሳየት።
-
ልብ ያተባሉ ሰዎችን ማስተዋል።
-
ደስተኛ ለመሆን ምክንያቶችን መፈለግ
-
ሰላም ፈታሪ መሆን።
-
ትናንሽ ተዓምራትን ማስተዋል።
-
ከልብ የመነጨ ምስጋና ማቅረብ
-
ይቅር ማለት።
-
ንስሃ መግባት።
-
መፅናት።
-
ነገሮችን በቀላሉ ማብራራት።
-
ከልጆች ጋር መግባባት።
-
የቤተክርስቲያን መሪዎችን መደገፍ።
እነዚህ ስጦታዎች በአጥቢያው የተሰጣኦ ትርኢት ላይ ላይታዩ ይችላሉ። ሆኖም ለጌታ ስራ ምን ያህል ውድ እንደሆኑ እና ከእግዚአብሔር ልጆች አንዱን በስጦታዎቻችሁ እንደነካችሁ፣ እንደባረካችሁ ወይም እንዳዳናችሁ ማየት እንደምትችሉ ተስፋ አደርጋለሁ። አስታውሱ፤“በትንሽና በቀላል ነገሮች ታላቅ ነገሮች ይፈፀማሉ።”
ትንሹን ድርሻችሁን ተወጡ
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ የተወደዳችሁ ጓደኞቼ፣ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ስጦታዎች እና ተሠጥዖኦዎች እንድታውቁ መንፈስ እንዲረዳችሁ እጸልያለሁ። በጌታ ምሳሌ ውስጥ እንደተጠቀሱት ታማኝ አገልጋዮች፣ እናሳድጋቸው እንዲሁም እናጉላቸው።
ለሃላፊነታችን መልስ ለመስጠት በሰማይ ባለው ርኅሩኅ አባታችን ፊት የምንቆምበት ቀን ይመጣል። በሰጠን ስጦታዎች ምን እንዳደረግን —በተለይም ልጆቹን ለመባረክ እንዴት እንደተጠቀምንባቸው ማወቅ ይፈልጋል። እርሱ በእውነት ማን እንደሆንን፣ ማንን እንድንሆን እንደተፈጠርን ያውቃል፣ ስለዚህም ከእኛ ብዙ ነገር ይጠብቃል።
ሆኖም እዚያ ለመድረስ ታላቅ፣ ጀብደኛ ወይም ከሰው በላይ የሆነ እርምጃ እንድንወስድ አይጠብቅም። እርሱ በፈጠረው ዓለም ውስጥ፣ እድገት ቀስ በቀስ እና በትዕግስት—ነገር ግን በዘላቂነት እና ያለማቋረጥ ይመጣል።
ሞትንና ኃጢአትን ድል ባደረገበት ጊዜ ከሰው በላይ የሆነውን ድርሻ የተወጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
የእኛ ድርሻ ክርስቶስን መከተል ነው። ከኃጢአት መራቅ፣ ወደ አዳኙ መመለስ እና በመንገዱ በአንድ ጊዜ አንድ እርምጃ መራመድ የእኛ ድርሻ ነው። ይህንን በትጋት እና በታማኝነት ስንወጣ፣ በእርሱ ፍፁም እስከምንሆንበት እስከዚያ ፍጹም ቀን ድረስ ፍፁም አለመሆንን እና የጉድለቶችን ሰንሰለት ጥለን ቀስ በቀስ የጠራን እንሆናለን።
በረከቶቹ የሚደረስባቸው ናቸው። ቃልኩዳኖቹ በቦታቸው ናቸው። በሩ ወለል ብሎ ተክፍቷል። መግባትና መጀመር የኛ ምርጫ ነው።
መጀመሪያው ትንሽ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ያ ምንም አይደል።
እምነታችሁ ደካማ በሚሆንበት ጊዜ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ተስፋና በማንጻት እና በማጥራት ሃይሉ ጀምሩ።
አባታችን ይህንን የእምነት እና የደቀመዝሙርነት ፈተና እንደ ተራ ቱሪስቶች ሳይሆን ባቢሎንን ትተው ልባቸውን፣ አእምሯቸውን እና እርምጃቸውን ወደ ጽዮን እንዳደረጉ እንደ ሙሉ ልብ አማኞች እንድንሆን ይጠይቀናል።
ጥረታችን ብቻውን ለሰስቲያል ሊያበቃን እንደማይችል እናውቃለን። ነገር ግን ለኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ እና ቁርጠኛ ሊያደርጉን ይችላሉ፣ እርሱም ለሰስቲያል እንድንበቃን ያደርገናል።
በተወደደው አዳኛችን ምክንያት፣ አለማሸነፍ የሚባል ነገር የለም። ተስፋችንን እና እምነታችንን በእርሱ ላይ ካደረግን ድል ማድረጋችን የተረጋገጠ ነው። ጥንካሬውን፣ ኃይሉን፣ የተትረፈረፈ ጸጋውን እንደምናገኝ ቃል ገብቷል። ደረጃ በደረጃ፣ ቀስ በቀስ ከእርሱ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር በዘላለማዊ ክብር ወደምንኖርበት ወደዚያ ታላቅ እና ፍጹም ቀን ይበልጥ እንቀርባለን።
እዚያ ለመድረስ፣ ዛሬ እና በየቀኑ የእኛን ድርሻ መወጣት አለብን። ትናንት ለወሰድናቸው እርምጃዎች እናመሰግናለን፣ ሆኖም በዚያ አናቆምም። የምንሄደው ገና ብዙ እንደሚቀረን እናውቃለን፣ ግን ያ ተስፋ እንድንቆርጥ እንዲያደርገን አንፈቅድም።
የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን የማንነታችን አስፈላጊ ክፍል ያ ነው።
እያንዳንዱ የቤተክርስቲያኑ አባል እና የእርሷ አካል ለመሆን የሚፈልጉ ሁሉ በአዳኝ እንዲታመኑ እና በትዕግስት እና በትጋት፣ በሙሉ ልባችሁ የበኩላችሁን እንድትወጡ—ደስታችሁ ሙሉ እንዲሆን እና አንድ ቀን፣ አብ ያለውን ሁሉ እንድትቀበሉ አሳስባለሁ እና እባርካለሁ። ስለዚህ የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።