“ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ”
በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአት ስርየት አማካኝነት ከእግዛብሔር ጋር መታረቅ የማይናወጥ እምነት ያስገኛል።
ቅዱሳን ጽሑፎችን ሳጠና ትኩረቴን የሚስቡ ቃላት ያጋጥሙኛል፤ ምክንያቱም እነዚህ ቃላት በሕይወቴ ውስጥ ካጋጠሙኝ ተሞክሮዎች የተነሣ ልዩ ትርጕም አላቸው። ሙያዬን ያሳለፍኩት ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ወንጀል መርማሪ ባለሙያ በመሆን ነው ከዚህ ጋር ተያይዞ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሳነብ ዕርቅ የሚለው ቃል ትኩረቴን ስቦ ነበር። ሥራዬ የሂሳብ አያያዝን፣ የኦዲትንና የምርመራ ችሎታን በመጠቀም ሪፖርት የተደረጉትን ገንዘቦች ከገንዘብ መዝገቦች ጋር ማስታረቅ ነበር። በሌላ አነጋገር ዓላማዬ የፋይናንስ ሪፖርቶችን ከፋይናንስ ሰነዶች ጋር በማጣጣም ፍፁም ትክክለኛነት እና ወደ ትክክለኛነት መቅረቡን ማረጋገጥ ነበር። አለመግባባቶችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት አድርጌ ነበር፤ በጣም ጥቃቅን የሆኑ አለመግባባቶችን እንኳ ለመፍታት ብዙ ጊዜ ማሳለፍ የተለመደ ነበር።
ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” በማለት ተማጽኗቸዋል። ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር እንደገና መግባባት ወይም በኃጢአታችን ወይም በድርጊታችን ምክንያት የተበላሸ ወይም የተሰበረውን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት መመለስ ማለት ነው። በቀላል አነጋገር ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ማለት ፈቃዳችንን እና ተግባራችንን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ማጣጣም ማለት ነው ወይም ፕሬዝዳንት ራስል ኤም ኔልሰን እንዳስተማሩት በሕይወታችን ውስጥ እግዚአብሔር እንዲያሸንፍ መፍቀድ ነው።
ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያስተምሩት የዘላለም ሞት መንገድ ወይም የዘላለም ሕይወት መንገድ ለመምረጥ በራሳችን መንገድ እርምጃ ለመውሰድ ነጻ ምርጫ አለን። ይሁን እንጂ በትጋት ካልሰራን ለራሳችን የመወሰን ነፃነታችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር እንዳንጣጣም ሊያደርገን ይችላል።
ነቢዩ ያዕቆብ ራሳችንን ከእግዚአብሔር ጋር አለመግባባት ወይም አለመጣጣም ውስጥ ስናገኝ ዕርቅ ማግኘት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ “በክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ከእግዚአብሔር ጋር [መ]ታረቅ” እንደሆነ አስተምሯል። ዕርቅ በምሕረት ላይ የተመሰረተ መሆኑን መገንዘብ አለብን፣ ይህም የሚያመለክተው የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ዕርቅን የሚቻል ያደርገዋል።
የራሳችሁን ህይወት ስታሰላስሉ ከሰማይ አባት እንደራቃችሁ ምክንያቱም ከእርሱ መንገድ እንደወጣችሁ ስለተሰማችሁ ጊዜ አስቡ። ለምሳሌ፣ ወደ እርሱ በምታቀርቡት ጸሎት ወይም ትእዛዙን በመጠበቅ ረገድ ትጋት እየቀነሳችሁ ሊሆን ይችላል። ራሳችንን ከእግዚአብሔር ለማራቅ እንደመረጥን ሁሉ ከእሱ ጋር ለመታረቅም መምረጥ ይኖርብናል። ጌታ “ወደ እኔ ቅረቡ እና እኔም ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ ተግታችሁም ፈልጉኝ እናም ታገኙኝማላችሁ፤ ለምኑ፣ ትቀበላላችሁ፤ አንኳኩ፣ ይከፈትላችሁማል” በማለት ኃላፊነታችንን ጎላ አድርጎ ገልጾልናል።
አዳኙ ይህንን አስፈላጊ ግንኙነት ለማደስ እና ለማስታረቅ የሚረዳን እንዴት ነው? እኔ በበኩሌ የፕሬዚዳንት ኔልሰንን ምክር በመከተል እና በየቀኑ ንስሐ በመግባት ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ በምጓዝበት ጕዞ ላይ ትልቅ እድገት አሳይቻለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ዕርቅ ማለት የኃጢአትን መሰናክል በማስወገድ በተለይም በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል ያለውን የተበላሸ ግንኙነት መልሶ ማቋቋም ማለት ነው።
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከምናነባቸው ታላላቅ ዕርቅ አንዱ የኢኖስ ነው። በሕይወቱ ውስጥ የሆነ ነገር ከእግዚአብሔር ጋር አልተጣጣምም ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ መተማመንን ምሳሌ አድርጎ ገልጿል። ንስሐ የመግባት ፍላጐቱን፣ ትህትናውን፣ ትኩረቱንና ቍርጠኝነቱን ገለጸ። “ኢኖስ ኃጢያትህ ይቅር ተብሎልሃል እናም አንተ ትባረካለህ” የሜው ድምፅ ወደእርሱ ሲመጣ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ዕርቅ ተረጋግጧል። ኤኖስ ንስሐ መግባቱና እርቁ በእሱ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ሲገነዘብ እንዲህ ብሏል፣ “እናም እኔ ኢኖስ እግዚአብሔር ሊዋሽ እንደማይችል አውቃለሁ፤ ስለሆነም፣ በደሌ ተወግዶልኛል።”
ዕርቅ መፍጠር የጥፋተኝነት ስሜትን ማስታገስ ብቻ ሳይሆን በውስጣችንም ሆነ ከሌሎች ጋር ሰላምን ያስገኛል። ግንኙነታችንን ይፈውሳል፣ ልባችንን ያለስለሳል እንዲሁም ደቀ መዝሙርነታችንን ያጠናክራል፤ ይህም በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ትልቅ ተስፋና ትምክህት የሚሰጠኝ ሌላው በኢኖስ የተገለጸው፣ “እናም እኔ ኢኖስ፣ እነዚህን ቃላት ከሰማሁ በኋላ እምነቴ በጌታ የማይናወጥ ሆነ” የሚለው የዕርቅ ፍሬ ነው።
ህጻን ሳለሁ፣ አያቴ ትልቅ የቼሪ አትክልት ነበረው። በአብዛኛው በበጋ ወቅት የቼሪ አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅት በአትክልት ስፍው ውስጥ የመስራት እድል ነበረኝ። በወጣትነቴ የነበረኝ ተሣትፎ ያጋጠመኝ ነገር ባሊ ይሰጠኝና ቼሪዎችን ለመሰብሰብ ወደዛፍ መውጣት ነበር።
አያቴ ቼሪ ሼከር የሚባል ማሽን ሲገዛ የቼሪ አዝመራ መሰብሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል። ይህ ማሽን የዛፉን ግንድ ይይዘዋል ከዚያም ያነቃንቀዋል፣ ቼሪዎቹ ከዛፉ ላይ ቼሪዎቹን ለመሰብሰብ በሚጠቀሙባቸው መረቦች ላይ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል። ዛፉን የሚነቀነቀው ዛፉን ማወዛወዝ ሲጀምር ሁሉም የቼሪ ፍሬዎች በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ከዛፉ ላይ እንደሚወድቁ አስተውያለሁ። በተጨማሪም ዛፉ ለ10 ሰከንዶች ወይም ለአንድ ሙሉ ደቂቃ ቢነቀነቅም ምንም ለውጥ እንደማያመጣ አስተዋልኩ፣ አንዳንድ የቼሪ ፍሬዎች አይወድቁም። በእርግጥም የማይነቃነቊ ነበሩ።
ቼሪዎችን ከዛፍ ላይ መንቀጥቀጥ የሚቻለው ኤቲሊን በመለቀቁ ነው። ይህ ሆርሞን በቼሪው ግንድና በዛፉ መካከል ያለው የሴል ሽፋን እንዲዳከም ያደርጋል። ስለዚህ የበሰለ የቼሪ ግንድ በቀላሉ ከዛፉ ይለያል ምክንያቱም ግንኙነቱ ስለተዳከመ።
በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የእሴይ ግንድ መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክት እንደሆነ እናነባለን፤ መሢሑ ከንጉሥ ዳዊት አባት ከእሴይ የዘር ሐረግ እንደሚመጣ ትንቢት ተነግሮ ነበር። ኤትሊን የበሰለ የቼሪ ግንድ ያለውን ትስስር እንደሚያዳክም ሁሉ አለመታዘዝ፣ ጥርጣሬና ፍርሃት ደግሞ ከእሴይ ግንድ ወይም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን ትስስር ሊያዳክሙብንና በቀላሉ እንድንናወጥና ከእሱ እንድንለይ ሊያደርጉን ይችላሉ። ታማኞች ብንሆንም እንኳ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን ዝምድና እንዳናዳክም መጠንቀቅ ይኖርብናል።
በትምህርት እና ቃልኪዳኖችውስጥ ምእመናን እንኳን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፣ “ነገር ግን ሰው ከጸጋ ወድቆ ከህያው እግዚአብሔር ለመለየት የሚያስችል ሁኔታ አለ፤” ጌታም እንዲህ ብሏል፦ “አዎን፣ እንዲሁም የተቀደሱትም ቢሆኑም እንኳን ይጠንቀቁ።” ጌታም እንዳንወድቅ ይመክረናል፦ “ስለዚህ በፈተና እንዳይወድቁ፣ ቤተክርስቲያኗ ትጠንቀቅ እና በየጊዜውም ትጸልይ፤”
አንድ ሰው በቀላሉ ሊናወጥ የሚችልበትን ሁኔታ ቅዱሳን ጽሑፎች ድርጊቱ የሚያስከትለውን መዘዝ ተከትሎ ለጥፋት እንደደረሰ አድርጎ ከሚገልጸው ሁኔታ ጋር ማመሳሰል ይችላል። ይህ አገላለጽ በስፋት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው አንድ ነገር እንዲፈርስ ወይም እንዲጠፋ የሚያደርግ የመበስበስ ሁኔታን፣ ብልሹነትን ወይም ውድቀትን ለማመልከት ነው።
ይህ ብስለት ምንን ይወክላል? ለውጥ ማድረግ የማንችልበት ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን? ከዚህ ይልቅ ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆንንበት ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል የሚጠቁም ይመስለኛል። ለጥፋት የበሰለ ከመሆን መከላከያው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ነገሮችን ማድረግ ነው። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኤኖስ ንስሐ በመግባት የማይናወጥ እምነት አሳይቷል። መደበኛ በሆነ፣ ከውስጥ በሆነ እና በተደጋጋሚ በሚደረግ ንስሐ ውስጥ ጥንካሬ አለ። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “ዘወትር እና በየቀኑ ንስሃ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይበልጥ ነጻ የሚያወጣ፣ ይበልጥ ከፍ ወዳለ ክብር የሚያደርስ እና በግለሰብ ደረጃ ለምናደርገው እድገት ጠቃሚ የሆነ ነገር የለም።”
ነቢዩ ያዕቆብ ከንስሐ በተጨማሪ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር እጅ እንዳለ ማወቃችን፣ መገለጥን መፈለግና መቀበል እንዲሁም እግዚአብሔር ሲናገር ማዳመጥ ሁላችን እንዳንናወጥ እንደሚረዳን አስተምሯል። በኋላም ያዕቆብ እንዲህ ሲል አስተምሯል፣ “ስለሆነም፣ እኛ እንመረምራለን፣ …እናም ብዙ ራዕይና የትንቢት መንፈስ አለን፤ እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ስላሉንም ተስፋን እናገኛለን፣ እናም እምነታችን የማይናወጥ ሆኗል” ነቢያትና ሐዋርያት የተናገሯቸውን ቃላትና ግብዣዎች ማዳመጥና ተግባራዊ ማድረግ በተስፋ፣ በልበ ሙሉነትና በብርታት እንድንሞላ ያደርገናል። ይህም እምነታችን እንዳይዳከም ያደርጋል።
ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅ እንዲሁም ንስሐ የመግባት ፍላጐት ሊኖረው እንደሚገባ ተምሬያለሁ። ንስሐ መግባትና የኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢአት ስርየት በረከት ማጣጣም የማይናወጥ እምነት እንዲኖረን ያደርጋል። የማይናወጥ እምነት ሁል ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅ ፍላጐትን ያነሳሳል። ይህ ክብ የሆነ ወይም ተደጋጋሚ የሆነ ንድፍ ነው።
ወንድሞችና እኅቶች፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስርየት አማካኝነት ከአምላክ ጋር እንድትታረቁ እጋብዛችኋለሁ። ቃል ኪዳኖችን መፈፀምና መጠበቅ ከአዳኙ ጋር ያለንን ግንኙነት ያጠናክረዋል፣ በዚህም ለጥፋት እንዳንበቃ እናደርጋለን ብዬ እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአት ስርየት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ያለን ዕርቅ የማይናወጥ እምነት እንዲኖረን እንደሚያደርግ እመሰክራለሁ።
የሰማይ አባት እኔንና እናንተን እንደሚወደን አውቃለሁ፣ እናም የተወደደውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን፣ ቤዛችን፣ እና ታላቁ አስታራቂ እንዲሆን ልኮታል። ስለኢየሱስ ክርስቶስ እመሰክራለሁ፤ ይህንንም የማደርገው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።