ኑ፣ ተከተሉኝ
በአእምሮ ሊያዝ የሚገቡ ሀሳቦች፥ ድንኳኑ እና መሰዋዕቱ


“በአእምሮ ሊያዝ የሚገቡ ሀሳቦች፥ ድንኳኑ እና መሰዋዕቱ፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ ብሉይ ኪዳን 2026 (እ.አ.አ) 2026 (እ.አ.አ)

ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ ብሉይ ኪዳን 2026 (እ.አ.አ)

የሀሳቦች ምልክት

በአእምሮ ሊያዝ የሚገቡ ሀሳቦች

ድንኳኑ እና መሰዋዕቱ

ብሉይ ኪዳንን ስናነብ፣ አንዳንድ ጊዜ ለጌታ በግልጽ አስፈላጊ ስለነበሩ ነገሮች ነገር ግን ለእኛ ዛሬ አስፈላጊነታቸው ወዲያው የማይታዩን ረጅም ምንባቦችን እናገኛለን። ዘጸአት 25–3035–40ዘሌዋውያን 1–916–17 ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ ምዕራፎች በምድረ በዳ የነበረውን የእስራኤልን ድንኳን እና እዚያ የሚከናወኑትን የእንስሳት መሥዋዕቶች በዝርዝር ይገልፃሉ። ድንኳኑም በህዝቡ መካከል የጌታ ማደሪያ የነበረው ተንቀሳቃሽ ቤተመቅደስ ነበር።

የዘመናችን ቤተመቅደሶች ከእስራኤል ድንኳን ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፣ ነገር ግን በእርግጥ በዘፀአት ውስጥ ካለው መግለጫ ጋር አይመሳሰሉም። በቤተመቅደሶቻችን ውስጥ እንስሳትን አንገድልም—የአዳኙ የኃጢያት ክፍያ ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት የእንስሳት መስዋእት እንዲቀር አድርጓል። እነዚህ ልዩነቶች ቢኖሩም፣ ዛሬ ስለ ጥንታዊ የእስራኤል አምልኮ ዓይነቶች ማንበብ ታላቅ ዋጋ አለው፣ በተለይም በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንዳደረጉት የምናያቸው ከሆነ—“በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ለማጠናከር” በማሰብ (አልማ 25፥16) ማለት ነው። የድንኳኑን እና የእንስሳት መስዋእትን ምልክት ስንረዳ እምነታችንን በክርስቶስ የሚያጠነክሩ መንፈሳዊ መረዳቶችንም ልናገኝ እንችላለን።

እስራኤላዊያን ወደ ድንኳኑ በግ እያመጡ

የበግ መስዋእት ፣ በሮበርት ቲ. ባሬት

ድንኳኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እምነትን ያጠነክራል

እግዚአብሔር ሙሴን በእስራኤላውያን ሰፈር ውስጥ ድንኳን እንዲሠራ ባዘዘው ጊዜ ዓላማው “በመካከላቸው [ያ]ድር ዘንድ” እንደሆነ ተናግሯል (ዘጸአት 25፥8)። በድንኳኑ ውስጥ የእግዚአብሔር መገኘት በቃል ኪዳኑ ታቦት ይወከላል—ይህም በውስጡ እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን መዝገብን የያዘ በወርቅ የተሸፈነ የእንጨት ሳጥን ነው ታቦቱ ከድንኳኑ ሌሎች ክፍሎች በመጋረጃ በመለየት እጅግ በተቀደሰው ውስጠኛው ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጓል። ይህ መጋረጃ በውድቀት ምክንያት ከእግዚአብሔር ፊት የመለየታችንን እንዲሁም በአዳኙ አማካኝነት ወደ እርሱ የመመለስ ምልክት ሊሆን ይችላል።

ከሙሴ ሌላ ወደ “በቅድስተ ቅዱሳን” (ዘጸአት 26፥34) ውስጥ ለመግባት የሚችል የምናውቀውአንድ ሰው ብቻ ነው—ሊቀ ካህኑ። እንደ ሌሎቹ ካህናት፣ እሱ በመጀመሪያ መታጠብ እና መቀባት እንዲሁም ሀላፊነቱን የሚያመለክት ቅዱስ ልብስ መልበስ ነበረበት። በዓመት አንድ ጊዜ የሥርየት ቀን ተብሎ በሚጠራው ቀን ሊቀ ካህኑ ብቻውን ወደ ድንኳኑ ከመግባቱ በፊት ሰዎችን ወክሎ መሥዋዕትን ያቀርብ ነበር። በመጋረጃው ላይ ዕጣን ያጥናል። ወደ ሰማይ የሚያርገው መዓዛ ያለው ጭስ ወደ እግዚአብሔር የሚያርግ የሰዎችን ጸሎት ይወክላል። ከዚያ ሊቀ ካህኑ የእንስሳ መስዋዕት ደም ይዞ በመጋረጃው ውስጥ ያልፍ እና በቃል ኪዳኑ ታቦት ወደተመሰለውን የእግዚአብሔር ዙፋን ይጠጋል።

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና በሰማይ አባት እቅድ ውስጥ ስላለው ሚና የምታውቁት እንዳለ ሆኖ፣ ድንኳኑ እንዴት ወደ አዳኙ እንደሚያመለክተን ማየት ትችላላችሁን? ልክ ድንኳኑ እና በውስጡ ያለው ታቦት በሕዝቡ መካከል የእግዚአብሔርን መገኘት እንደሚያመለክት፣ ኢየሱስ ክርስቶስም በሕዝቦቹ መካከል የእግዚአብሔር መገኘት ነበር እንደ ሊቀ ካህኑ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ እና በእግዚአብሔር አብ መካከል አማላጅ ነው። እርሱ ራሱ በከፈለው የመስዋእትነት ደም ስለ እኛ ሊያማልድልን በመጋረጃው በኩል አልፏል።

አንዳንድ የእስራኤል ድንኳኖች ገጽታ በተለይም የግል ስርዓቶቻችሁን ለመቀበል ወደ ቤተመቅደስ ሄዳችሁ የምታውቁ ከሆነ ለእናንተ አዲስ ላይሆኑ ይችላሉ። ቤተመቅደስ እግዚአብሄር በህዝቡ መካከል የሚኖርበት ቤት ነው። ልክ እንደ ድንኳኑ እጅግ ቅዱስ ስፍራ፣ የቤተመቅደሱ ሰለስቲያል ክፍል የእግዚአብሔርን መገኘት ይወክላል። ለመግባት፣ መጀመሪያ መታጠብ እና መቀባት አለብን። ቅዱስ ልብሶችን እንለብሳለን። ቃል ኪዳን እንገባለን። በመሰዊያው ላይ ወደ እግዚአብሔር የሚያርጉ ፀሎቶችን እንፀልያለን። በመጨረሻ ወደ እግዚአብሔር መገኘት ለመግባት በመጋረጃ ውስጥ እናልፋለን።

ምናልባትም በዘመናዊ ቤተመቅደሶች እና በጥንታዊ ድንኳን መካከል ያለው በጣም አስፈላጊ የሆነ ተመመሳሳይነት ቢኖር ሁለቱም፣ በትክክል ከተረዳነው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩ እና ስለእርሱ ቤዛ መስዋእትነት በአድናቆት የሚሞሉ መሆናቸው ነው። እግዚአብሔር ልጆቹ ሁሉ ወደ እርሱ እንዲገቡ ይፈልጋል፤ እርሱ የሴት ካህናት እና “የካህናት መንግሥት” ይፈልጋል (ዘጸአት 19፥6)። ነገር ግን ኃጢያታችን ያንን በረከት እንዳናገኝ ያግደናል ምክንያቱም “ምንም እርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖር [ስለማይቻለው]” (1 ኔፊ 10፥21) ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ ክርስቶስን “ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት” (ዕብራውያን 9፥11)አድርጎት ላከው። እርሱ ለእኛ መጋረጃን ከፍቶ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ “ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት [እንቀርብ]” (ዕብራዊያን 4፥16) ዘንድ ሀይል ሰጠ።

ዛሬ፣ የቤተመቅደሶች ዓላማ ለራሳችን ደህንነትን ከማግኘት የበለጠ ነው። የራሳችንን ስርዓት ከተቀበልን እና ከእግዚአብሄር ጋር ቃልኪዳን ከገባን በኋላ፣ በቅድመ አያቶቻችን ቦታ በመሆን ስርአቶችን በወኪልነት መቀበል እንችላለን። ይህም ለሌሎች የእግዚአብሔርን መገኘትን መንገድ በመክፈት እኛም እንደጥንት ሊቀ ካህን—እንደ ታላቁ ሊቀ ካህን—መሆን እንችላለን እንደማለት ነው።

መስዋዕት በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እምነትን ያጠነክራል

ከሙሴ ሕግ ረጅም ጊዜ በፊት የነበረው የጥንት የእንስሳት መሥዋዕት የኃጢያትን ክፍያን እና የዕርቅ መርሆዎችን በሀይል ያስተምራል። አዳም እና ሔዋን መሥዋዕት ያቀረቡ ነበር። የአዳኙ መሥዋዕት ምልክት እንደሆነ ተረድተው ነበር። እንዲሁም ይህን ለልጆቻቸው አስተምረው ነበር።

በጥንቷ እስራኤል የሥርየት ቀን (በዕብራይስጥ “ዮም ኪፐር”) የእንስሳ መስዋእትነት ተምሳሌትነት በተለይ አሳዛኝ ሆኖ ሊታይ ይችላል። የዚህ ዓመታዊ ሥነ ሥርዓት አስፈላጊነት በዘሌዋውያን 16፥30 ውስጥ ተገልጧል፥ “በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተሰረያ ይሆንላችኋልና፣ … በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ።” ይህ የእግዚአብሔር መገኘት በሕዝቡ መካከል እንዲኖር አስችሏል። ይህ ስርየት የተከናወነው በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች ነበር። ከእነዚህ በአንዱ ውስጥ ፍየል ለሰዎች ኃጢአት መስዋእት ሆኖ ይሰዋል ከዚያም ሊቀ ካህኑ የፍየሉን ደም ወደ እጅግ ቅዱስ ስፍራ ይወስዳል። በኋላም ሊቀ ካህኑ እጆቹን ህይወት ባለው ፍየል ላይ ጭኖ በምሳሌያዊ ሁኔታ እነዚህን ኃጢአቶች ወደ ፍየል በማስተላለፍ የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት ይናዘዛል። ከዚያም ፍየሉ ከእስራኤል ሰፈር ይወገዳል።

በዚህ ሥነ-ስርዓት ውስጥ ፍየሎች በኃጢአተኛ ሰዎችን ቦታ በመሆን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታሉ። ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት መኖር የለበትም። ነገር ግን ኃጢአተኞቹን ከማጥፋት ወይም ከማስወገድ ይልቅ እግዚአብሔር ሌላ መንገድ አዘጋጀ—በምትኩ ፍየል ይገደላል ወይም ይወገዳል። “ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ … ይሸከማል” (ዘሌዋውያን 16፥22)።

የእነዚህ ሥነ-ሥርዓቶች ተምሳሌትነት እግዚአብሔር ወደ እርሱ ፊት እንድንመለስ የሰጠንን መንገድ ያመለክታሉ—እነዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ እና የእርሱ የኃጢያት ክፍያ ናቸው። አዳኙ “ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፣” እንዲሁም “የሁላችንን በደል” (ኢሳይያስ 53፥4፣ 6)። እርሱ በእኛ ቦታ ቆመ፣ የኃጢአትን ቅጣት ለመክፈል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ፣ ከዚያም በኋላ በትንሳኤው በኩል ሞትን ድል አደረገ። የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋእት “ታላቅ እና የመጨረሻ መስዋዕትነት፤ አዎን፣ የሰውም ሆነ የእንሥሳ … መስዋዕት አይደለም፣” ነገር ግን “መጨረሻ የሌለው እንዲሁም ዘለአለማዊ መስዋዕት” ነበር (አልማ 34፥10)። ወደ እርሱ የሚያመለክቱት የጥንት መስዋዕቶች ሁሉም ፍፃሜ ነበር።

ኢየሱስ መስቀል ተሸክሞ

በዚህ ምክንያት፣ መስዋዕቱ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ እንዲህ አለ፣ “ከእንግዲህ ደምን በማፍሰስ አታበርክቱልኝ፤ አዎን፣ መሥዋዕቶቻችሁ … ይቆማሉ። … ለእኔም መስዋእት የተሰበረ ልብና የተዋረደ መንፈስ ታቀርባላችሁ” (3 ኔፊ 9፥19–20)።

ስለዚህ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ መስዋዕቶች እና ስለ ድንኳኑ (ወይም በኋላ፣ ስለ መቅደሱ) ምንባቦችን ስታገኙ—እና ብዙዎቹን ታገኛላችሁ—የዚህ ሁሉ ዋና ዓላማ በመሲሁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ ላይ ያላችሁን እምነት ለማጠናከር እንደሆነ አስታውሱ። በቤቱ የምታደርጉትን አምልኮ ከምታነቡት እና ከምትማሩት ጋር አገናኙ። ልባችሁ እና አዕምሮአችሁ ወደ እርሱ ይዙር። እርሱ ወደ እግዚአብሔር ፊት እናንተን ለመመለስ ምን እንዳደረገ እና እናንተ እርሱን ለመከተል ምን እንደምታደርጉ አሰላስሉ።

ማስታወሻዎች

  1. ዘጸአት 33፥7–11 ሙሴ ከጌታ ጋር የተገናኘበትን “የመገናኛውም ድንኳን” ይጠቅሳል፣ ነገር ግን በዘጸአት እና በዘሌዋውያን ውስጥ የተገለጹት የመሥዋዕቶች ስፍራ ይህ ቦታ አልነበረም። እነዚያ መሥዋዕቶች የተከናወኑት በዘፀአት 25–30 ውስጥ በተገለጸው፣ እግዚአብሔር ሙሴ እና የእስራኤል ልጆች እንዲሠሩ ባዘዘው ድንኳን ውስጥ ነበር (ዘፀአት 35–40ን ይመልከቱ)። አሮንና ወንዶች ልጆቹ የእንስሳት መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ይህ ድንኳን ብዙውን ጊዜ “የመገናኛው ድንኳን” ተብሎም ይጠራ ነበር (ለምሳሌ ዘጸአት 28፥4338፥30ዘሌዋውያን 1፥3ን ተመልከቱ)።

  2. Jacob 4:5; Jarom 1:11

  3. ዘጸአት 25:10–22 ተመልከቱ

  4. ዕብራውያን 10:19–20 ተመልከቱ።

  5. ዘጸአት 40:12–13 ተመልከቱ።

  6. ዘጸአት 28 ተመልከቱ።

  7. ዘሌዋውያን16:12ተመልከቱ

  8. መዝሙር 141፥2 ተመልከቱ።

  9. ዘሌዋውያን 16:14–15 ተመልከቱ።

  10. ዮሐንስ 1:14 ተመልከቱ።

  11. ዕብራውያን 8–10ተመልከቱ።

  12. ሙሴ 5:4–12ዘፍጥረት 4:4 ተመልከቱ።

  13. ሞዛያ 15:8–9 ተመልከቱ።