ቤተሰብ ወደ ብርሃን እየተየመለከተ፣ በሎቬታ ሬይስ ካይሮ። በሄቭንላይት የቀረበ
10.
ሰውነታችሁ ቅዱስ ነው
1 ቆሮንቶስ 6፥18–20
ሰውነታችሁ የሰማይ አባታችሁ ድንቅ ስጦታ ነው። አካል መኖሩ ትክክልና ስህተት መካከል የመምረጥ ነፃነትዎን ለመጠቀም የበለጠ ኃይል ይሰጣችኋል። ዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሰውነታችሁን በእግዚአብሔር አይን እንድታዩ ሊረዳችሁ ይችላል። ይህ ደግሞ በሰውነታችሁ ላይ ምን ስለማድረግ እና እንዴት እንደምትንከባከቡት በምታደርጉት ምርጫ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።
ዘለአለማዊ እውነቶች
ሰውነታችሁ የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነውእርሱም በአጽናፈ ዓለም እጅግ የከበረ፣ ግርማ ሞገስ ያለው ፍጥረት ነው። ቅዱሳት መጻህፍት ሰውነታችንን ከቅዱስ ቤተመቅደስ ጋር ያመሳስሉታል፣ በዚህም መንፈስ ሊኖርበት ይችላል። በእርግጥም፣ ሰውነታችሁ አሁን ፍጹም አይደለም። ነገር ግን በሰውነታችሁ የሚኖሯችሁ ልምዶች አንድ ቀን ፍጹም የሆነ፣ ከሞት የተነሳ፣ ክብር ያለው አካል ለመቀበል እንድትዘጋጁ ይረዳችኋል።
ነፍሳችሁ በሰውነታችሁ እና በመንፈሳችሁ የተዋቀረች ናት። በዚህ ምክንያት፣ አካላዊ ጤንነት እና መንፈሳዊ ጤንነት በቅርበት የተሳሰሩ ናቸው። አዳኙ ሰውነታችሁን የመንከባከብ መርሆዎችን ለማስተማር እና ስጋዊ እና መንፈሳዊ በረከቶችን ለመስጠት የጥበብን ቃልን ገልጧል።
ደስተኛ ትዳርን እና ዘለአለማዊ ቤተሰቦችን ለመፍጠርፆታዊ ስሜቶች የእግዚአብሔር እቅድ አስፈላጊ አካል ነው። እነዚህ ስሜቶች ኃጢአት አይደሉም—እነርሱ የተቀደሱ ናቸው። ፆታዊ ስሜት በጣም የተቀደሰ እና በጣም ሀይለኛ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር ባሰበው መንገድ እነዚህን ስሜቶች እንድትጠቀሙ እንዲያዘጋጃችሁ የንፅህና ህግን ሰጥቷችኋል። የንጽሕና ሕግ ፆታዊ ግንኙነትን እግዚአብሔር የሚፈቅደው በጋብቻ ውስጥ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የብቻ እንደሆነ ይገልጻል። ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ ችላ ይላሉ አልፎ ተርፎም ያፌዙበታል፣ ነገር ግን ጌታ የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን እና ከፍ ያለ ደረጃ እንድንኖር ይጋብዘናል።
ግብዣዎች
“የራሳችሁን—እና የሌሎችን ሠውነት—በክብር ያዙ። ስለአለባበሣችሁ፣ ስለፀጉር አሠራራችሁ እና ስለገፅታችሁ ውሳኔ በምታደርጉበት ጊዜ “ሠውነቴን ከእግዚአብሔር እንደተሠጠ ቅዱስ ሥጦታ እያከበርኩት ነው?” ብላችሁ ራሣችሁን ጠይቁ። የሠማይ አባት፣ አንዳችን የሌላችንን እውነተኛ ማንነት እንድናይ ይፈልጋል፦ ሥጋዊ አካልን ብቻ ሳይሆን መለኮታዊ ዕጣ ፈንታ ያለን የተወደድን ልጆቹ መሆናችንን እንድናይ ይፈልጋል። ከእግዚአብሔር ልጅነት ማንነታችሁ ይልቅ ሥጋዊ አካላችሁን የሚያጎሉ ወይም ተገቢ ያልሆነ ትኩረትን የሚስቡ ዘይቤዎችን አስወግዱ። የስነምግባር ንጽህና እና ለእግዚአብሔር ያላችሁ ፍቅር ምርጫችሁን ይምራ። ከቤተሰብህ ምክር ጠይቁ።
ሰውነታችሁን የሚያጠናክሩ ነግሮችን አድርጉ፣ የሚጎዳውን ወይም የሚያጠፋችሁን አታድርጉ። እግዚአብሔር ባዘጋጃቸው ብዙ መልካም ነገሮች በአመስጋኝነት ተደሰቱ። ግን አልኮል፣ ትምባሆ፣ ቡና፣ ሻይ እና ሌሎች ጎጂ እጾች እና ንጥረ ነገሮች ለሰውነታችሁ ወይም ለመንፈሳችሁ እንደማይጠቅሙ አስታውሱ። ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን፣ ለምሳሌ በሀኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶች፣ እንኳን በትክክል ካልተጠቀማችሁ ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ።
ፆታዊ ግንኙነትን እና ፆታዊ ስሜትን የተቀደሱ አድርጉ። እነርሱም የቀልድ ወይም የመዝናኛ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የለባቸውም። በወንድና በአንዲት ሴት መካከል ከሚሆን ጋብቻ ውጪ፣ የሌላን ሰው ግላዊ፣ ቅዱስ የአካል ቦታዎችን በልብስ ላይ ቢሆንም እንኳ መንካት ስህተት ነው። የምታደርጉትን፣ የምትመለከቱትን፣ የምታነቡትን፣ የምታዳምጡትን፣ የምታስቡትን፣ የምትለጥፉትን ወይም የምትጽፉትን በምትመርጡበት ጊዜ በሌሎች ወይም በራሳችሁ ላይ ሆን ተብሎ ፆታዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ማንኛውንም ነገር አስወግዱ። ይህም ማንኛውንም አይነት የብልግና ምስሎችን ያካትታል። ሁኔታዎች ወይም ተግባሮች ፈተናን የበለጠ እንደሚያጠናክሩ ካወቃችሁ ራቋቸው። እነዚህ ሁኔታዎች እና ተግባሮች ምን እንደሆኑ ታውቃላችሁ። እርግጠኛ ካልሆናችሁ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ ወላጆቻሁ እና መሪዎቻችሁ ለማወቅ ሊረዷችሁ ይችላሉ። ህይወትን የመፍጠር ቅዱስ ኃይልን አንደምታከብሩ ለሰማይ አባታችሁ አሳዩ።
ቃል የተገቡ በረከቶች
በባህሪያችሁ፣ በመልካችሁ እና በአለባበሳችሁ ሰውነታችሁን ስታከብሩ ለራሳችሁ እና ለሌሎች ያላችሁ ክብር ይጨምራል።
የጥበብን ቃል ለሚጠብቁት እግዚአብሔር ታላቅ የእውቀትን ሀብት ቃል ገብቷል። ከሱስ የጸዳ ጤናማ አካል፣ የግል መገለጥን የመቀበል፣ በግልፅ የማሰብ እና ጌታን የማገልገል ችሎታን ይጨምራል።
የንጽሕና ሕግን በማክበር መኖር የእግዚአብሔርን ሞገስ እና የግል መንፈሳዊ ኃይል ያስገኛል። እናንተን እና የወደፊት ቤተሰባችሁን ይጠብቃል። በትዳር ውስጥ ስትሆኑ፣ ይህ ህግ ለትዳራችሁ የበለጠ ፍቅርን፣ መተማመንን እና አንድነትን ያመጣል። ይህንን ህግ ማክበር ለዘለአለም እድገት እንዲኖራችሁ እና የሰማይ አባታችሁን እንድትመስሉ ያስችላችኋል። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር በመሆን ስትኖሩ እምነታችሁ ያድጋል።
ጥያቄዎች እና መልሶች
ጌታ ስለአለባበስ፣ ስለአጋጌጥ፣ ስለንቅሳት እና ስለመበሳት ያለው መስፈርት ምንድን ነው? የሰውነታችሁ ቅድስና የተለያችሁ መሆን ማለት ቢሆንም፣ የጌታ መስፈርት የሰውነታችሁን ቅድስና ማክበር ነው። ውሳኔዎችን፣ በተለይ በሰውነታችሁ ላይ ዘላቂ ተጽእኖ ያላቸውን ውሳኔዎች፣ በምታደርጉበት ጊዜ ይህ እውነት እና ቅዱስ መንፈስ መሪያችሁ ይሁን። ብልህ እና ታማኝ ሁኑ፣ እንዲሁም ከወላጆቻችሁ እና ከመሪዎቻችሁ ምክር ፈልጉ።
ፈተናዎችን እና መጥፎ ልማዶችን እንዴት ማሸነፍ እችላለሁ? የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተን ለመርዳት ኃይል አላቸው። እንደ ጸሎት፣ የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት እና ሌሎች፣ በማገልገል አይነት ያን ሃይል ወደ ህይወታችሁ በሚጋብዙ ነገሮች ህይወታችሁን ሙሉ። ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ወደ ወንጌሉ ስትዞሩ ድክመቶች ጥንካሬዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ትገነዘባላችሁ። እንደ አስፈላጊነቱ ከቤተሰብ፣ ከመሪዎች እና ከታመኑ ሙያዊ አማካሪዎች እርዳታ ጠይቁ። ሕይወታችሁን እንደገና ለመቆጣጠር ይረዳችኋል። ይህም ጊዜ ቢወስድም፣ ታገሱ እንዲሁም በምንም ተስፋ አትቁረጡ።
ተመሳሳይ ጾታ ያላቸውን ሰዎች ይስቡኛል። እነዚህን መስፈርቶች እንዴት ተግባራዊ አደርጋለሁ? በተመሳሳይ ጾታ መሳብ ኃጢአት አይደለም። እነዚህ ስሜቶች ካሏችሁ እና እዚህን ስሜቶች ካልተከተላችሁ ወይም ካላደረጋችሁ፣ የሰማይ አባትን የንጽህና ህግ አልጣሳችሁም። እናንተ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች እና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ናችሁ። አዳኙ የሚያጋጠማችሁን ሁሉ እንደሚረዳ አስታውሱ። ከእርሱ ጋር ባላችሁ የቃል ኪዳን ግንኙነት፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመጠበቅ እና ቃል የገባላችሁን በረከቶች ለመቀበል ብርታት ታገኛላችሁ። በእርሱ እና በወንጌሉ እመኑ።
ጥቃት ደርሶብኛል፣ እንዲሁም ሃፍረት ይሰማኛል። እኔ እንደ ኃጢአተኛ እቆጠራለሁ? አይደለህም/ነሽም። የማንኛውም ጥቃት ወይም ጉዳት ሰለባ መሆን ኃጢአተኛ አያደርግም። አዳኙ ይወዳችኋል። እርሱ የእናንተ ጥንካሬያችሁ ነው። ሊረዳችሁ፣ ሊፈውሳችሁ እና ሰላም ሊሰጣችሁ ይፈልጋል። የታመኑ ባለሙያዊ አማካሪዎች፣ የቤተሰብ አባላቶቻችሁ እና መሪዎቻችሁ እንዲሁ ሊረዷችሁ ይችላሉ።
ዘፍጥረት 1፥27 (የተፈጠርነው በእግዚአብሔር መልክ ነው)፤ ዮሐንስ 14፥18 (አዳኙ መጽናኛን ቃል ገብቷል)፤ ፊልጵስዩስ 4፥7 (የእግዚአብሔር ሰላም ማስተዋልን ያልፋል፤ ሞዛያ 2፥41 (የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁ በጊዜያዊና በመንፈሳዊ የተባረኩ ናቸው)፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥15 (መንፈስ እና ሥጋ ነፍስ ናቸው)፤ 89 (የጥበብ ቃል)፤ 121፥45(ምግባረ በጎነት አስተሳሰብን ያሳምር) ተመልከቱ።
የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ ጥያቄዎች
-
ጌታ እንዲህ ብሏል ሁሉም ነገሮች በፊቴ “በንጽህና ይሰሩ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፥41). በአስተሳሰብህ/ሽ እና በባህሪህ/ሽ ውስጥ የሥነ–ምግባር ንጽህና እንዲኖርህ/ርሽ ጥረት ታደርጋለህ/ታደርጊያለስሽ?
-
የንጽህና ህግን ታከብራለህ/ታከብሪያለሽ?
-
የጥበብ ቃልን ትረዳለህ/ትረጃለሽ እና በዚህም ትታዘዛለህ/ትታዘዣለሽ?