ወጣቶች
ተነሳሽነት ያላቸውን ምርጫዎች አድርጉ


ተነሳሽነት ያላቸውን ምርጫዎች አድርጉ

ለወጣቶች ጥንካሬ ውስጥ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን እና የነቢያቱን ትምህርቶች ታገኛላችሁ። በእነዚህ እውነቶች መመሪያነት አሁን እንዲሁም ለዘለአለም የሚባርኳችሁን ተነሳሽነት ያላቸውን ምርጫዎች ማድረግ ትችላላችሁ።

እናንተ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር የመንፈስ ልጆች ናችሁ። የእርሱ ታላቅ የደስታ እቅድ በመንፈሳዊ መልኩ እንድታድጉ እና መለኮታዊ አቅማችሁን እንድታዳብሩ ያስችላችኋል። ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝዎ እንዲሆን ልኮታል።

የሰማይ አባታችሁ ያምናችኋል። የወንጌልን ሙላት እና ከእርሱ ጋር የሚያስተሳስሩ እና ኃይሉን ወደ ህይወታችሁ የሚያመጡትን የተቀደሱ ስርአቶችን እና ቃል ኪዳኖችን ጨምሮ ታላቅ በረከቶችን ሰጥቷችኋል። ከእነዚህ ቃል ኪዳኖች ጋር ተጨማሪ ደስታ እና ኃላፊነት ይመጣል። በአለም ላይ ለውጥ ማምጣት እንደምትችሉ ያውቃል፣ ይህ ደግሞ በብዙ ሁኔታዎች ከአለም የተለየ መሆንን ይጠይቃል። ምርጫ በምታደርጉበት ጊዜ የሰማይ አባታችሁን ምሪት ፈልጉ። እርሱ በመንፈስ ቅዱስ መነሳሳት በኩል ይባርካችኋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የዘለአለም ደስታ መንገድ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ነፃነታችሁን ስትጠቀሙ፣ ወደ ዘለአለማዊ ደስታ በሚወስደው መንገድ ላይ ትሆናላችሁ። ኢየሱስ ክርስቶስን መመዘኛችሁ፣ ጠንካራ መሰረታችሁ አድርጉ። ህይወታችሁን በእርሱ ትምህርቶች ላይ ገንቡ እንዲሁም ምርጫችሁን በእነርሱ ለኩ። በጥምቀት፣ በቅዱስ ቁርባን ጊዜ እና በቤተመቅደስ ውስጥ የምትገቧቸው ቃል ኪዳኖች በክርስቶስ ላይ ላላችሁ ፅኑ መሠረት የመገንቢያ አለት ናቸው። አሁንም ቢሆን ችግሮችን እና ፈተናዎችን ትጋፈጣላችሁ፣ ነገር ግን የሰማይ አባት እና አዳኙ በሁሉም ነገሮች ይረዷችኋል።

ለወጣቶች ጥንካሬ አላማ ሊያጋጥሟችሁ ስለሚችሉት ምርጫዎች ሁሉ “አዎ” ወይም “አይ” የሚል መልስ መስጠት አይደለም። ይልቁንም ጌታ ከፍ ባለና በተቀደሰ መንገድ ትኖሩ ዘንድ ይጠራችኋል—ይኸውም በዘለዓለማዊ እውነቶች ላይ ያተኮረ ሕይወትና ጌታ ቃል የገባቸው በረከቶች ናቸው። መንገዱ ይህ ነው። ይህ መመሪያ ስለ መንገዱ ያስተምራችኋል። እርሱ የገለጠውን እውነት ያስረዳል። እነዚህን እውነቶች ምርጫ ለማድረግ መመሪያዎ አድርጉ—እንደ በቤተመቅደስ ውስጥ ቃል ኪዳኖችን መግባት እና በምስዮን ማገልገል ያሉ ትልልቅ ምርጫዎች፣ እንዲሁም ሰዎችን እንዴት እንደሚይዙ ወይም ጊዜዎን እንዴት እንደሚያሳልፉ ያሉ የእለት ተእለት ምርጫዎች አድርጉ።

ሌሎች ሊረዷችሁ ቢችሉም፣ መንፈሳዊ እድገታችሁ የግል ነው። የእናንተ ኃላፊነት ነው። በየቀኑ ለመሻሻል፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመጠበቅ እና ቃል ኪዳኖቻችሁን ለማክበር እና ሌሎች ወደ አዳኙ እንዲቀርቡ ለመርዳት የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።

ሞዛያ 4፥29–30 (የኃጢአት መንገዶች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ናቸው፣ ስለዚህ ራሳችንን መጠበቅ አለብን)፤ ሔላማን 5፥12 (በክርስቶስ ላይ መሠረታችሁን ገንቡ)፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 45፥57 (መንፈስ ቅዱስን እንደ መመሪያ ውሰዱ)፤ 25፥13 (ራሳችሁን በቃል ኪዳኖች ከጌታ ጋር እሰሩ) ተመልከቱ።

ይህ መመሪያ እንዴት ተደራጀ

እያንዳንዱ ርዕስ ሦስት ክፍሎች አሉት፦

  1. የዘለአለም እውነቶች፣ ወይም ዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ትምህርት

  2. እነዚያን እውነታዎች ለመተግበር የሚቀርቡ ግብዣዎች

  3. በእርሱ አስተምህሮቶች ለሚኖሩ ጌታ ለመስጠት ቃል የገባው በረከቶች