2020–2024
“እነሆ፣ … እናንተ ከፍ የምታደርጉት ብርሃን ነኝ”
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


13:29

“እነሆ፣ … እናንተ ከፍ የምታደርጉት ብርሃን ነኝ”

እኛ የጌታን ብርሃን ከፍ የምናደርገው ቃል ኪዳኖቻችንን ስንጠብቅ እና ህያው ነቢያችን የእግዚአብሔርን ቃል ሲናገር ስንደግፍ ነው።

በዚህ ጉባኤ ላይ በቀረቡት ብዙ ምስክርነቶች ላይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ ጌታችን እና አዳኛችን፣ የአባታችን ልጆች ሁሉ ቤዛ እንደሆነ ሐዋርያዊ ምስክርነቴን አክላለሁ ። በኃጢያት ክፍያው አማካኝነት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ብቁ ከሆንን ወደ ሰማይ አባታችን ፊት እንድንመለስ እና ከቤተሰቦቻችን ጋር ለዘለአለም እንድንሆን አስችሎናል።

አዳኙ ከምድራዊ ጉዞዎቻችን አልራቀም። ላለፉት ሁለት ቀናት በመረጣቸው መሪዎቹ አማካኝነት ወደ እርሱ እንድንቀርብ ሲናገር ሰምተናል። በህይወታችን ያለተጠበቁ ክስተቶችን ስናስተናግድ፣ በንፁህ ፍቅሩና ምሕረቱ ደግሞ ደጋግሞ ያበረታናል። ኔፊ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “እግዚአብሔር ረዳቴ ነበር፤ በምድረበዳ ውስጥ በስቃዬ መራኝ። … በፍቅሩ ሞላኝ።”

በሥራው እርስ በርሳችን ስንደጋገፍ ያ ፍቅር ማስረጃ ሆኖ ይገለጣል።

በአጠቃላይ ጉባኤ ላይ በህይወት ያሉትን ነቢያችንን፣ ቀዳሚ አመራርን፣ አስራ ሁለት ሐዋሪያት ቡድን አባላትን፣ እና ሌሎች የቤተክርስቲያኗ አጠቃላይ ባለልስጣናትና፣ አጠቃላይ መሪዎችን እንደግፋለን። መደገፍ ማለት አንድን ሰው ከፍ አድርጎ መያዝ ፣ ትኩረታችንን ለእነርሱ መስጠት፣ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን እና ቃላቸውን በተግባር ማዋል ማለት ነው። በጌታ ምሪት በመነሳሳት ይናገራሉ፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን፣ የማህበረሰቡን የምግባር ዝቅተኝነት እና የአብን እቅድ ለማጨናገፍ ጠላት በብዛት የሚደረገውን ጥረት ይረዳሉ። እጃችንን ወደ ላይ ከፍ ስናደርግ፣ ድጋፋችንን የምንሰጠው ለዚህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለየዕለት ሕይወታችንም ጭምር ነው።

ድጋፍ መስጠት ሚያካትተው፣ በአጥቢያዎቻችን እና በካስማዎቻችን ውስጥ ያሉትን የካስማ ፕሬዚዳንቶቻችን እና ኤጲስ ቆጶሶቻችን፣ የቡድን እና የድርጅት መሪዎችን፣ መምህራንን፣ እና የወጣቶች ካምፕ ዳይሬክተሮችን ከፍ ማድረግ ነው። በቤት ውስጥ፣ ከፍ የምናደርገው ሚስቶቻችንንና፣ ባሎቻችንን፣ ልጆቻችንን፣ ወላጆቻችንን፣ ሌሎች ዘመዶቻችንን እንዲሁም ጎረቤቶቻችንን ነው። ወደ ላይ እርስ በርሳችን ከፍ ስንደራረግ እንዲህ እያለን ነው፣ “‘የዛሉትን‘ ክንዶችህን እና እጆችህን ከፍ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን በጎንህ አንተን አፅናኝ እና አበረታታች በመሆን አለውልህ ለማለት ነው።”

ከፍ የማድረግ ሀሳቡ በቅዱሳት መጻህፍት ላይ የተመሠረተ ነው። በሞርሞን ውሃ ላይ፣ አዲስ የተጠመቁት የቤተክርስቲያን አባላት፣ “አንዳ[ቸው የአንዳ[ዶችን] ሸክም … ለመሸከም ፈቃደኞች በመሆን [በመፈለግ] … መፅናናትን ለሚፈልጉም [በማፅናናት፤ እናም በሁሉም ጊዜ በሁሉም ነገር … የእግዚአብሔር ምስክር በመሆን [ይቆሙ] ዘንድ” ቃል ገብተዋል።

ኢየሱስ ለኔፊያውን እንዲህ ብሏል፦ “ለዓለም ያበራ ዘንድ ብርሃናችሁን ከፍ አድርጉ። እነሆ፣ እናንተ ከፍ የምታደርጉት ብርሃን ነኝ።” እኛ የጌታን ብርሃን ከፍ የምናደርገው ቃል ኪዳኖቻችንን ስንጠብቅ እና ህያው ነቢያችን የእግዚአብሔርን ቃል ሲናገር ስንደግፍ ነው።

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ቡድን ውስጥ ሲያገለግሉ እንዳሉት፣ “ለነቢዮቻችን ድጋፍ ስንሰጥ፣ ትንቢታዊ ቅድመ ነገሮች ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ የግል ቃል ኪዳን እንገባለን።”

ነቢይን መደገፍ የተቀደሰ ስራ ነው። ዝም ብለን አንቀመጥም፤ ከዚህ ይልቅ አጥብቀን እንከላከልለታለን፣ ምክሩን እንከተላለን፣ ቃሉንም እናስተምራለን እንዲሁም ስለ እሱ እንጸልያለን።

ንጉስ ቢንያም፣ በመጽሐፍ ሞርሞን ውስጥ ለህዝቡ እንዲህ ብሏል፣ “እኔ እንደ እናንተው ነኝ፣ በሁሉም አይነት የሰውነትና የአዕምሮ ጉስቁልና ስር የሆንኩ፤ ይሁን እንጂ … ህዝብ ተመርጫለሁ፣ … በጌታ እጅ ተፈቅዶልኛል፣ እናም ጌታ በሰጠኝ በሙሉ ኃይል፣ አዕምሮና፣ ብርታት እናንተን እንዳገለግል ወደር በሌለው ኃይሉ ተቀምጫለሁ፣ እንዲሁም ተጠብቄአለሁ።”

የሙሴን እጆች መያዝ።

በተመሳሳይም በ100 ዓመታቸው ፕሬዚዳንት ኔልሰን በጌታ ተቀምጠዋል እንዲሁም ተጠብቀዋል። በወቅቱ የቀዳሚ አመራር አባል የነበሩ ፕሬዚዳንት ሃሮልድ ቢ ሊ፣ ሙሴ በራፊዲም ኮረብታ ላይ ቆሞ የነበረውን ምሳሌ ጠቅሰዋል። “[የቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንት] እጆች ሊዝሉ ይችላሉ” ብለዋል። “አንዳንድ ጊዜ በእሱ ከባድ ኃላፊነቶች የተነሳ ሊሸበሩ ይችላሉ፤ ሆኖም ምሪቱን ስንከተል እና በእሱ አመራር ሥር ስንመራ፣ የገሃነም በሮች በእናንተም ሆነ በእስራኤል ላይ አያሸንፉም። የእናንተ ደህንነት እና የእኛ ደህንነት የሚመካው ጌታ ቤተክርስቲያኑን እንዲመሩ የጠራቸውን ሰዎች መከተላችን ወይም አለመከተላችን ነው። ቤተክርስቲያኗን ማን ሊመራ እንደሚፈልግ ያውቃል፣ እናም ምንም ስህተት አይፈጽምም።”

ፕሬዚዳንት ኔልሰን እግዚአብሔርን ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉበትን ጥበብ ለመምራት ይጠቀሙበታል። የእሳቸው ብስለት፣ ሰፊ ልምድ፣ ጥበብ እና የማይለዋወጥ ራዕይ ተቀባይነታቸው በተለይ ለዘመናችን የሚጠቅም ነው። እንዲህም ብለዋል፦ “የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ዓለምን ‘ሁሉ ምድር በጌታ እውቀትም [የምትሞላበትን]’ እያዘጋጀች ነው (ኢሳይያስ 11።9)። … ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በተነገረው መለኮታዊ ማስታወቂያ ይህ ሥራ ኃይል ተሰጥቶታል። ይህም ስድስት ቃላትን ብቻ ያቀፈ ነበር፦ ‘የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስማው! (የጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥17).ይመልከቱ።”

ፕሬዚዳንት ኔልሰንም እንዲህ ብለዋል፦ “አዳኛችንን ማወቅ በግል ይበልጥ አስፈላጊ እና ለሁሉም የሰው ነፍስ አግባብ የሆነበት ጊዜ በምድር ታሪክ ውስጥ ኖሮ አይታወቅ። ሁላችንም ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተልና ትምህርቶቹን ለማድመጥ ብንመርጥ—በዓለም ዙሪያም ሆነ በግል ሕይወታችን ውስጥ የሚከሰቱትን አሳዛኝ ግጭቶች እንዴት ልንቀርፋቸው እንደምንችል አስቡ።”

ወንድሞች እና እህቶች፣ ማጉረምረምን በማሰወገድ ይበልጥ እገዛ ማድረግ፣ የእግዚአብሔርን ቃል፣ መንገዱን እና “ዛሬ ካሉን ታላላቅ ፈተናዎቻችን አንዱ በእግዚአብሔር እውነት እና በሰይጣን አስመሳይነት መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ነው፡ ለዚህ ነው ጌታ ‘ድል [እና]ደርግ ዘንድ፤ አዎን፣ ሰይጣንን ድል [እና]ደርግ ዘንድ፣ እናም የእርሱን ስራ ከሚደግፉት የጠላት አገልጋዮች እጆች እናመልጥ ዘንድ ዘወትር ጸል[ዩ]’ ያሉትን ነቢዩን ይበልጥ መከተል እንደሚያስፈልገን ማስጠንቀቂያ የሰጠን [ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10፥5፤ አትኩሮት ይጨመርበታል]።”

የማንታይ ዩታ ቤተመቅደስ ዳግም መመረቅ።

ባለፈው ሚያዝያ፣ እህት ራዝባንድ እና እኔ የምንወዳቸውን ነቢያችንን እና እህት ኔልሰንን በማንቲ ዩታ ቤተመቅደስ ዳግም መመረቅ ላይ ስናገኛቸው ክብር ተሰምቶን ነበር።

ፕሬዚዳንት ኔልሰን ወደ ክፍል ሲገቡ ሁሉንም ሰዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ አስገርመው ነበር። እንደሚመጡ እናውቅ የነበርነው በጣም ጥቂቶቻችን ብቻ ነበርን። የእሳቸው በእዛ መገኘት፣ የተሸከሙት የብርሃን እና የትንቢት መጎናጽውፊያ ወዲያውኑ ተሰማኝ። ነቢዩን ሲያዩ ሰዎች ፊት ላይ የነበረው የደስታ ስሜት፣ በግሌ ከእኔ ጋር ለዘለአለም ይኖራል።

ፕሬዚዳንት ኔልሰን ቤተመቅደሱ እንደገና በሚቀደስበት ጸሎት ላይ “ቅዱስ በረከቶችን እንዲቀበሉ እና ለቃል ኪዳኖቻቸው ብቁ እና ታማኝ እንዲሆኑ”ወደ ቤተመቅደስ የገቡትን በሙሉ እዲያግዝ … ወደእነዚህ ደጆች ብቁ ሆነው ለሚገቡ ሁሉ የሰላም ቤት፣ የመጽናናትም ቤት፣ እንዲሁም የግል ራዕይም የሚገለጥበት ቤት ይሆን ዘንድ”ጌታን ለምነዋል።

ሁላችንም በሰላም፣ በምቾት፣ እና ከሁሉም በላይ በግል ራዕይ አለምን የከበበውን ፍርሃት፣ ጨለማ፣ እና ብጥብጥ ለማምከን በእግዚአብሔር ሀይል ከፍ ማለት አለብን።

ከስነ ስርዓቱ በፊት፣ የሚያምረውን የውጭውን አቀማመጥ ለመቃኘት እኔ እና ባለቤቴ ከፕሬዚዳንት እና ከእህት ኔልሰን ጋር ውጭ ፀሐይ ላይ ቆመን ነበር። የፕሬዚዳንት ኔልሰን ቅደመ አያቶች ከአካባቢው ጋር ጠለቅ ያለ ትስስር አላችው። አንዳንዶቹ የእኔ አያቶች እንዳደረጉት፣ ስምንቱም አያቶቻቸው በቤተመቅደሱ ዙሪያ ባሉት ሸለቆዎች ውስጥ ሰፍረው ነበር። ቅድመ አያቴ አንድሩ አንደርሰን በሮኪ ተራሮች ሦስተኛው የሆነውን የማንታይ ቤተ መቅደስ ለማጠናቀቅ 11 ዓመት በፈጀው የቀድሞ አባላት የግንባታ ቡድን ውስጥ በበላይነት ተሳትፏል።

ከፕሬዚዳንት ኔልሰን ጋር አብረን ስንቆም፣ የጌታን ቅዱስ ቤት እንደገና በመቀደስ ስንደሰት የእግዚአብሔርን ነቢይ የመደገፍ እና የማገዝ እድል ነበረን። ፈጽሞ የማልረሳው ቀን ነበር።

በዚያ ቅዱስ ቀን ላይ ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ አሉ፣ “ጌታን ለማክበር ቤተመቅደሶችን እንገነባለን።” “የተገነቡት ለአምልኮ እንጂ ለዕይታ አይደለም። በእነዚህ ቅዱስ ግድግዳዎች ውስጥ ዘለአለማዊ ትርጉም ያላቸውን ቅዱስ ቃል ኪዳኖች እንገባለን።” እስራኤልን እየሰበሰብን ነን።

ፕሬዚዳንት ኔልሰን እና ከእሳቸው በፊት የነበሩት ነቢያት በሙሉ በእጆቻቸው የነበሩትን ቅዱስ ቤተመቅደሶች ተንከባክበዋል። በዛሬው ዕለት፣ በአለም ዙሪያ እየሰሩ ያሉ፣ የታወጁ ወይም እየተገነቡ ያሉ 350 የእግዚአብሔር ቅዱስ ቤቶች፣ አሉን። ፕሬዚዳንት ኔልሰን ነቢይ ከሆኑ፣ ከ2018 (እ.አ.አ) ጀምሮ፣ 168 ቤተመቅደሶችን አስታውቀዋል።

እንዲህም ብለዋል፣ “በጊዜያችን፣ የተሟላ፣ የተደራጀ እና ሁሉንም ዓይነት ፍፁም የሆኑ ዘመናትን፣ ቁልፎችና ኃይላትን በአንድ ላይ ማጣበቅ ያስፈልጋል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 128፥18 ይመልከቱ)። ቅዱስ ቤተ መቅደሶች ለእነዚሁ ቅዱስ ዓላማዎች በምድር ላይ ሰፍረዋል። የእነዚህ ቤተመቅደሶች መገንባት ህይወታችሁን የሚቀይር አይሆንም፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የምታሳልፉት አገልግሎት ግን በእርግጥ ይቀይራል።”

“አዳኙ እና ትምህርቶቹ የቤተመቅደስ ማዕከለኛ ክፍል ነው፣” ይላሉ ፕሬዚዳንቱ። “በመመሪያ እና በመንፈስ አማካኝነት፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የሚስተላለፈው ሁሉም ትምህርት ስለኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖረንን መረዳት ይጨምራል። በቅዱስ የክህነት ቃል ኪዳኖች አማካኝነት አስፈላጊዎቹ የእርሱ ስርዓቶች ከእርሱ ጋር ያጣምሩናል። ከዚያም በኋላ፣ ቃል ኪዳኖቻችንን ስንጠብቅ፣ በእርሱ ፈዋሽ፣ አጠንካሪ ኃይል ይባርከናል።”

ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳሉት፣ “በቤተመቅደሥ ውስጥ የሚያመልኩ ሁሉ በእግዚአብሔር ሃይል ይታጠቃሉ እንዲሁም የመላዕክት ‘ጥበቃን’ ያገኛሉ [ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 109፥22]። የእግዚአብሔር ሃይል የታጠቃችሁ የቤተመቅደሥ ቡራኬን የተቀበላችሁ ሴት ወይም ወንድ፣ ወይም በቤተመቅደስ የምትሄዱ ወጣቶች በመሆናችሁ፣ ህይወትን ለብቻችሁ መጋፈጥ እንደሌለባችሁ ማወቃችሁ ምን ያህል በራስ መተማመናችሁን ይጨምራል? በእርግጥ መላዕክት እንደሚረዷችሁ ማወቃችሁ ምን ዓይነት ድፍረት ይሰጣችኋል?”

ኢየሱስ ከርስቶስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ በትህትና ተንበርክኮ በነበረበት ወቅት፣ መላዕክት እኛን ከፍ ለማድረግ እጃቸውን ይዘረጋሉ የሚለው፣ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ተገልጿል። በእርሱ ስቃይ የተነሳ የማያልቀውን የኃጢያት ክፍያን አመጣ። “በዚያም” አሉ ፕሬዚዳንት ኔልሰን፣ “በታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ የፍቅር ድርጊት ተፈጽሟል። በዚያ በጌቴሴማኒ፣ ‘ሰዎች ንስሀ ገብተው ወደ እርሱ ይመጡ’ ዘንድ የሰዎችን ሁሉ ህመም ተሰቃየ [ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 18፥11]።”

“ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፣” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ጠየቀ፣ “ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ እንጂ።

ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው።”

ዛሬም መላእክት በዙሪያችን አሉ። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ ብለዋል፣ “[በቤተመቅደስ ውስጥ] በሰማይና በምድር መካከል ያለውን መጋረጃ እንዴት መክፈት እንደምትችሉ እና፣ የእግዚአብሔር መላእክት ያገለግሏችሁ ዘንድ እንዴት እግዚአብሔርን እንደምትጠይቁ ትማራላችሁ።”

መላእክት ብርሀንን ያመጣሉ። የአምላክን ብርሃን። ለኔፋውያን ሐዋርያቱ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል “እነሆ፣ እናንተ ከፍ የምታደርጉት ብርሃን ነኝ።” ነቢያችንን ስንደግፍ፣ “የአለም ብርሃን” በሆነው አዳኛችን እንደተጠሩ እንመሰክራለን።

ውድ ፕሬዚዳንት ኔልሰን፣ በአለም ሁሉ ባሉት የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን አባሎች እና ጓደኞች በመወከል፣ ትምህርቶን ከፍ ለማድረግ፣ የክርስቶስ አይነት አኗኗር ተምሳሌነትዎን ከፍ ለማድረግ፣ እናም የሁላችንም ቤዛ የሆነውን የጌታችንን እና የአዳኛችንን ታላቅ ምስክርነት ከፍ ለማድረግ እንደተባረክን ይሰማናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ “የዓለም ብርሃን” እንደሆነ ሐዋርያዊ ምስክርነቴን እሰጣለሁ። ሁላችንም እንደ ደቀመዛሙርቱ የእርሱን ብርሀን፣ “ከፍ እናደርጋለን”። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥38ተመልከቱ።

  2. 2 ኔፊ 4፥20-21

  3. ሮናልድ ኤ ራዝባንድ፣ “ቃላት ዋጋ አላቸው፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2024 (እ.አ.አ)፣ 70–76 ተመልከቱ።

  4. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 81፥5

  5. ሞዛያ 18፥8–9

  6. 3 ኔፊ 18፥24፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል።

  7. ራስል ኤ. ኔልሰን፣ “ነቢያትን መደገፍ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2014 (እ.አ.አ)፣ 75።

  8. ሞዛያ 2፥11

  9. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 21፥681፥5 ይመልከቱ።

  10. ሔሮልድ ቢ. ሊ፣ በጉባኤ ዘገባ፣ ጥቅምት 1970 (እ.አ.አ)፣ 153።

  11. የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሙላት በዳግም መመለስ፦ የሁለት መቶኛ አመት መታሰቢያ ለአለም የተላለፈ አዋጅ” እንደሚለው፣ “ቃል የተገባለት ዳግም መመለስም በሚቀጥል ራዕይ ወደፊት እንደሚሄድ በደስታ እናውጃለን። ምድርም እንደገና አንድ አይነት አትሆንም፣ እግዚአብሔር ‘ያለውን ሁሉ በክርስቶስ [ይጠቀልላልና]’ (ኤፌሶን 1፡10)።”

  12. ራስል ኤም ኔልሰን፣ “የቤተክርስቲያን የወደፊት ሁኔታ፦ ዓለምን ለአዳኝ ዳግም ምጽዓት ማዘጋጀት፣” ሊያሆና፣ ሚያዝያ 2020 (እ.አ.አ)፣6–7።

  13. ራስል ኤም. ኔልሰን. “ንጹህ እውነት፣ ንጹህ ትምህርት፣ እና ንጹህ ራዕይ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2021 (እ.አ.አ)፣ 6።

  14. ረስል ኤም. ኔልሰን፣ “የመንፈሳዊ ፍጥነት ሃይል፣,” ሊያሆና፣ ግንቦት 2022 (እ.አ.አ) 99።

  15. የመመረቂያ ጸሎት፣ የማንታይ፣ ዩታ ቤተመቅደስ፣ 21 ሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ)፣” ChurchofJesusChrist.org።

  16. በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ፣ ነቢዩ ሞሮኒ በጠላት ሲታደንና ብቻውን በነበረበት ጊዜ ልጁን ሞሮኒን በደብዳቤ ሊያጽናናው ሞከረ። እንዲህም ጻፈ፣ “ነገር ግን ክርስቶስ ከፍ ያድርግህ፣ እናም ስቃዩ፣ እናም ሞቱ፣ … ለዘለዓለም በአዕምሮህ ይኑር” (ሞሮኒ 9፥25)።

  17. በ1888 (እ.አ.አ) የማንቲ ዩታህ ቤተመቅደስ ቡራኬ በፊት፣ በዩታህ ውስጥ የነበሩ ሁለት ሌሎች ሁለት ቤተመቅደሶች ቀድሞውኑ ተቀድሰው ነበር፦ የሴንት ጆርጅ ዩታ ቤተመቅደስ በ1887 (እ.አ.አ) እና የሎገን ዩታ ቤተመቅደስ በ1884። የዚህ ዘመን የመጀመሪያው ቤተመቅደስ የተገነባው በከርትላንድ፣ ኦሀዮ ነበር እናም የተቀደሰውም በ1836 (እ.አ.አ) ነበር። የቤተመቅደስ ስራ እና የእስራኤል መሰባሰብ በትጋት እንዲጀመር ከሙሴ፣ ኤልያ እና ከኤልያስ ጋር ታላቅ መንፈሳዊ መገለጦች ነበሩ፣ እናም የክህነት ቁልፎች በዳግም ተመለሱ።

    ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ሲል መዘገበ፣ “በእርግጥም የባዓለ ኀምሳ እና የመፈሳዊ ስጦታ ጊዜ ነበር፣ ድምጽ ከዚህ ቦታ ወደ አለም ሁሉ ይወጣልና፣ እናም የዚህ ቀን ክስተት በቅዱስ ታሪክ ገጾች ላይ ለትውልድ ሁሉ ይወርዳል፣ እንደ የባዓለ ኀምሳ ቀን፣ ስለዚህ ይህ ቀን እንደ ኢዮቤልዩ እና እንደ የልዑል እግዚአብሔር የቅዱሳን የደስታ ጊዜ ይቆጠራል እና ይከበራል።” (Joseph Smith, Journal, 1835–1836 [ጆሴፍ ስሚዝ መፅሔቶች፣ መጋቢት 30፣ 1836 (እ.አ.አ)]፣ ገጽ 190፣ የጆሴፍ ስሚዝ ወረቀቶች፣ የቤተክርስቲያን ታሪኮች ቤተመጽሐፍት፣ ሶልት ሌክ ሲቲ፣ ዩታ።) የናቩ ቤተመቅደስ በግንቦት 1846 (እ.አ.አ) ላይ በይፋ የተቀደሰው አብዛኞቹ ቅዱሳን ቤቶቻቸውንና ማኅበረሰባቸውን ትተው ከሄዱ በኋላ ነበር። ከ6 ሺህ የሚበልጡ ቅዱሳን ወደ ምዕራቡ ዓለም ከመሸሻቸው በፊት የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን ገብተዋል። Church History Topics [የቤተክርስቲያን ታሪክ ርዕሶች]፣ “Nauvoo Temple [የናቩ ቤተመቅደስ]፣” በወንጌል ቤተመጻህፍት ይመልከቱ።

  18. Russell M. Nelson, in “President Nelson Rededicates Manti Utah Temple,” Apr. 21, 2024, newsroom.ChurchofJesusChrist.org.

  19. ስኮት ቴይለር፣ “በፕሬዚዳንት ኔልሰን የታወጁትን 168 ቤተመቅደሶች በቁጥር መመልከት፣” Church News፣ ሚያዝያ 14፣ 2024 (እ.አ.አ)።

  20. ራስል ኤም.ኔልሰን፣ “የቤተክርስቲያኒቷ የወደፊት ዕጣ፣” 8–9።

  21. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ቤተመቅደስ እና መንፈሳዊ መሰረታችሁ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2021 (እ.አ.አ)፣ 93–94።

  22. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “Rejoice in the Gift of Priesthood Keys [በክህነት ቁልፎች ስጦታ ደስ ይበላችሁ]፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2024 (እ.አ.አ)።

  23. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “The Atonement [የኃጢአት ክፍያው]፣” ኤንዛይን፣ ህዳር 1996 (እ.አ.አ)፣ 35።

  24. ሉቃስ 22፥42–43

  25. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ቤተመቅደስ እና መንፈሳዊ መሰረታችሁ፣” 96-94።

  26. 3 ኔፊ18፥24.

  27. 3 ኔፊ 11፥11

  28. 3 ኔፊ 11፥11