2020–2024
ክርስቶስን መከተል
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


13:31

ክርስቶስን መከተል

እንደ ክርስቶስ ተከታይነታችን፣ ፍጹም ምስሌያችን ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እናስተምራለን እንዲሁም እንመስክራለን። ስለዚህ ጸብን በመተው እርሱን እንከተል።

በዚህ ዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ “ኑ፣ ተከተሉኝ” በተሰኘው በአዳኙ ግብዣ በሚታወቀው የወንጌል ጥናት እቅድ ተነሳስተዋል።” ክርስቶስን መከተል ተራ የሆነ ወይም አልፎ አልፎ የሚደረግ ነገር አይደለም። በማንኛውም ጊዜ እና በሁሉም ቦታ ሊመራን የሚገባ ዘላቂ ቁርጠኝነት እና የአኗኗር ዘይቤ ነው። ትምህርቶቹ እና የእርሱ ምሳሌ ለእያንዳንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መንገዱን ይደነግጋል። ሁሉም ወደዚህ መንገድ ተጋብዘዋል ምክንያቱም ሁሉንም ወደ እርሱ እንዲመጡ ጋብዟልና—“ጥቁርም ነጭም፣ ባሪያ እና ነፃ፤ ወንድ እና ሴት፤ … በእግዚአብሔር ፊት ሁሉም አንድ ነው።”

1.

ክርስቶስን ለመከተል የመጀመሪያው እርምጃ፣ “ታላቂቱ … ትእዛዝ” ብሎ የገለጸውን መታዘዝ ነው።

“ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።

“ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

“ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።

“በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።”

አባትና ልጅ ወላንዳን እያበረሩ

የእግዚአብሔር ትዕዛዛት በህይወታችን ውስጥ ምሪትን እና ቋሚ ኃይልን ይሰጣሉ። በምድራዊ ህይወታችን ያለን ተሞክሮ ልክ በነፋሻማ ቀን ካይት እንደሚያበሩ ትንሽ ልጅ እና አባት ነው። ካይቱ ወደ ላይ ከፍ ሲል በትንሹ ልጅ እጅ ያለውን የሚያገናኘውን ገመድ ንፋሱ መጎተት ጀመረ። ስለ ምድራዊ ንፋስ ሃይል ልምድ ስላልነበረው ካይቱ ወደ ላይ ከፍ ማለት እንዲችል ገመዱን እንዲቆርጥ ልጁ ሀሳብ አቀረበ። አዋቂው አባቱ ገመዱ ካይቱ ምድራዊ ነፋስን እንዲቋቋም በቦታው የሚይዘው መሆኑን በማብራራት አይሆንም በማለት መከረ። ገመዱን ከለቀቅን ካይቱ ወደላይ ከፍ አይልም። በምድራዊ ንፋስ ተወስዶ ወደ ምድር መውደቁ የማይቀር ነው።

ያ አስፈላጊ ገመድ እኛን ከሰማይ አባታችን እግዚአብሔር እና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያገናኝን ቃል ኪዳን ይወክላል። ትእዛዛቶቻቸውን በመጠበቅ የእነርሱን ቃል ኪዳኖች ስናከብር እና የማዳን እቅዳቸውን ስንከተል፣ ቃል የገቡልን በረከቶች ወደ ሰማያዊ ከፍታ እንድንወጣ ያስችሉናል።

መፅሐፈ ሞርሞን ክርስቶስ “የዓለም … ብርሃን” እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራል። ለኔፋውያን በተገለጠ ወቅት፣ የተነሣው ጌታ ያንን ትምህርት “ምሳሌ ትቼላችኋለሁ” ብሎ ለእነርሱ በመንገር ገለጸላቸው። “እኔ ሳደርግ የተመለከታችሁትም፣ እናንተ ከፍ የምታደርጉት ብርሃን ነኝ።” እርሱ የእኛ ምሳሌ ነው። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንድናደርግ እንዳበረታቱን፣ ቅዱሳት መጻህፍትን በማጥናት እና ትንቢታዊ ትምህርቶችን በመከተል የተናገረውን እና ያደረገውን እንማራለን። በቅዱስ ቁርባን ስርአት ወቅት፣ “ሁልጊዜ እርሱን [ለማስታወስና] … ትእዛዛ[ቱን ለመጠበቅ]” በእያንዳንዱ ሰንበት ቀን ቃል ኪዳን እንገባለን።

2.

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ጌታ “የክርስቶስ ትምህርት” ብሎ በጠራው መሰረት መሰረታዊ ነገሮችን ሰጥቶናል። እነዚህም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን፣ ንስሐ መግባት፣ መጠመቅ፣ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበል፣ እስከ መጨረሻው መጽናት እና እንደ ትንሽ ልጅ መሆን ናቸው፣ ይህም ማለት በጌታ መታመን እና እርሱ ለሚፈልገው ሁሉ መገዛት ማለት ነው።

የጌታ ትእዛዛት ሁለት አይነት ናቸው፣ ቋሚ ልክ እንደ ክርስቶስ ትምህርት እና ጊዜያዊ። ጊዜያዊ ትእዛዛት ለጌታ ቤተክርስቲያን ወይም ለታማኞች ፍላጎቶች በጊዜያዊ ሁኔታ የሚያስፈልጉ ሲሆኑ ፍላጎቱ ሲሟላ የሚቀሩ ናቸው። የጊዜያዊ ትእዛዛት ምሳሌ ቅዱሳን ከኒውዮርክ ወደ ኦሃዮ፣ ወደ ምዙሪ፣ ወደ ኢሊኖይ ለማዘዋወር በስተመጨረሻም የአቅኚዎቹን ስደት ወደ ተራራ ተከባቢው ውዕራብ ለመምራት ጌታ ለቀደመው የቤተክርስቲያኗ አመራር የሰጠው መመሪያ ነው። ምንም እንኳን ጊዜያዊ ቢሆኑም፣ ተግባራዊ በሆኑበት ጊዜ ትዕዛዛቱ ይጠበቁ ዘንድ ተሰጥተዋል።

አንዳንድ ቋሚ ትእዛዛት በአጠቃላይ ለመከበር ብዙ ጊዜ ወስደዋል። ለምሳሌ፣ የፕሬዚዳንት ሎሬንዞ ስኖው የአስራት ህግ ስብከት ቀደም ሲል የተሰጠውን ነገር ግን በአጠቃላይ በቤተክርስቲያኗ አባላት ሲከበር ላልነበረው ትእዛዝ አጽንዖት ሰጥተው ነበር። በጊዜው ቤተክርስቲያኗ እና አባላቶቿ በተጋፈጡት ሁኔታ ምክንያት እንደገና አጽንኦት መስጠት አስፈልጎ ነበር። በኋለኛው ቀን ቅዱሳን ወይም በቤተክርስቲያን በተጋፈጡ ወቅታዊ ሁኔታዎች ምክንያት ተጨማሪ የቅርብ ጊዜ የድጋሚ ምሳሌዎች ያስፈልጋሉ። እነዚህ የሚያካትቱትም በፕሬዚዳንት ጎርደን ቢ. ሂንክሊ ስለ ቤተሰብ የወጣው አዋጅ፣ እና በቅርቡ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን ቤተክርስቲያኗ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በመባል በተከበረ ስሟ እንድትጠራ የሚል ጥሪ የሰጡባቸው ናቸው።

3.

ሌሎቹ የአዳኛችን አስተምህሮዎች በዘመናችን ሁኔታዎች እንደገና ትኩረትን የሚሹ ይመስላል።

ይህ በህዝባዊ ግንኙነት፣ አንዳንዴ ደግሞ በቤተሰባችን ውስጥ ጭምር፣ የብዙ አስከፊ እና ጎጂ ቃላት ጊዜ ነው። በሕዝብ ፖሊሲ ጉዳዮች ዙሪያ ያለው ከፍተኛ ልዩነት ብዙውን ጊዜ በሕዝብ እና በግላዊ ግንኙነቶች ውስጥ የጥላቻ ድርጊቶችን አልፎ ተርፎም ጥላቻን ያስከትላል። ይህ የጥላቻ ድባብ አንዳንድ ጊዜ ለህዝብ የሚሆን አጣዳፊ መልስ በሚያስፈልጋቸው ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ህግ የማውጣት አቅምን ሽባ ያደርጋል።

በዚህ መርዛማ የሆነ የሃሳብ ልውውጥ ወቅት፣ የክርስቶስ ተከታዮች ምን ማስተማር እና ማድረግ አለባቸው? የእርሱ ትምህርቶች እና ምሳሌዎች ምን ነበሩ?

አዳኝ ኔፋውያንን ሲያስተምር።

ኢየሱስ ለኔፋውያን በተገለጠበት ወቅት ካስተማራቸው የመጀመሪያ መርሆች መካከል ክርክርን ማስወገድ መሆኑ ትርጉም አለው። ይህንን በሃይማኖታዊ አስተምህሮ አለመግባባት አውድ ውስጥ ቢያስተምርም የሰጣቸው ምክንያቶች ግን በፖለቲካ፣ በሕዝብ ፖሊሲ እና በቤተሰብ ግንኙነት ውስጥ ባሉ ግንኙነቶች እና የሃሳብ ልውውጦች ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ ናቸው። ኢየሱስ እንዲህ አስተማር፦

“የፀብ መንፈስ ያለበት፣ የፀብ አባት ከሆነ እናም የሰዎችን ልብ እርስ በርስ እንዲጣሉ በቁጣ ከሚያነሳሳው ከዲያብሎስ እንጂ፤ ከእኔ አይደለም።

“እነሆ፣ ሰዎችን አንዳቸውን ከሌላኛው ልባቸውን ለቁጣ የሚያነሳሳ ይህ የእኔ ትምህርት አይደለም፤ ነገር ግን እንደነዚህ ያሉ ነገሮች እንዲወገዱ ማድረግ ይህ የእኔ ትምህርት ነው።”

በኔፋውያን መካከል ባደረገው በተቀረው አገልግሎቱ፣ ክርክር ከመከልከል ጋር በቅርበት የተያያዙ ሌሎች ትእዛዛትንም ኢየሱስ አስተምሯል። በመፅሐፍ ቅዱስ እንደተማርነው፣ ቀደም ሲል እነዚህን እያንዳንዳቸውን በታላቁ የተራራ ላይ ስብከቱ ወቅት፣ በኋላ ላይ ደግሞ ለኔፋውያን በግልጽ በተጠቀመው ተመሳሳይ ቋንቋ አስተምሯል። የተለመደውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ እጠቅሳለሁ።

አዳኝ በኢየሩሳሌም ሲያስተምር።

“ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ።”

ይህ ከክርስቶስ በጣም ከታወቁ አብዮታዊ እና ለመከተል በጣም ከባድ ከሆኑ ትእዛዛት መካከል አንዱ ነው። ሆኖም ግን ሁሉም እርሱን እንዲከተሉት ካደረገው ግብዣ ዋና አካል ነው። ፕሬዚዳንት ዴቪድ ኦ. መኬይ እንዳስተማሩት፣ “ለሰዎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርን ከማሳየት የበለጠ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለማሳየት የተሻለ ምንም አይነት መንገድ የለም።”

በሽምግልና ላይ ያሉ ተቃዋሚ ወገኖች።

ምሳሌያችን የሆነው የእርሱ ሌላ መሠረታዊ ትምህርት ይህ ነው፦ “የሚያስተራርቁ ሁሉ ብፁአን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።”

የሚያስታርቁ! የክርስቶስ ተከታዮች በሁሉም ንግግሮቻቸው ውስጥ መጥፎ እና ጎጂ ቃላትን ቢተዉ ግላዊ ግንኙነቶች እንዴት የሚቀየሩ ይሆኑ ነበር።

ባለፈው አመት አጠቃላይ ጓኤ ውስጥ፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እነዚህን ማበረታቻዎች ሰጡን፦

“የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታይን ለመለየት ከሚቻልባቸው እጅግ ቀላል መንገዶች አንዱ ያ ሰው ለሌሎች ሰዎች ያለው ርህራሄ ነው። …

“… የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት አስታራቂዎች ናቸው።

… አዳኙን ማክበር ከምንችልባቸው ከተመረጡ መንገዶች አንዱ አስታራቂ መሆን ነው።”

ትምህርታቸውን ሲያጠቃልሉ፡- “ክርክር ምርጫ ነው። ማስታረቅ የምርጫ ጉዳይ ነው። ከጸብ እና ከእርቅ አንዱን የመምረጥ ነጻነት አላችሁ። አሁን እና ሁሌም አስታራቂዎች ለመሆን እንድትመርጡ አሳስባችኋለሁ።”

የማይስማሙ ቡድኖች ሁሉም የሚስማሙበትን የጋራ ነጥቦችን በመለየት መጀመር አለባቸው።

የእኛን ፍጹም ምሳሌ እና የእርሱን ነቢይ ለመከተል ወርቃማው ህግ በመባል የሚታወቀውን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፦ “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።” ሁሉንም መውደድ እንዲሁም ለሁሉም መልካም ማድረግ አለብን። በሁሉም ግንኙነቶቻችን ውስጥ አለመግባባቶችን ማስወገድ እና አስታራቂዎች መሆን አለብን። ይህ የእኛን መርሆችን እና ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች ማላላት ሳይሆን ሌሎችን በኃይል ማጥቃት ማቆም ማለት ነው። ፍጹሙ ምሳሌያችን በአገልግሎቱ ያደረገው ይህንኑ ነው። እርሱን እንድንከተለው ሲጋብዘን ለእኛ የተወው ምሳሌ ይህ ነው።

ከአራት አመት በፊት በዚህ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ለዘመናችን ትንቢታዊ ጥሪ አስተላልፈው ነበር፦

“እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ እናንተ ፍቃደኞች ናችሁን? እግዚአብሔር በህይወታቸው በጣም ሃይለኛ ተጽዕኖ እንዲሆን እናንተ ፈቃደኞች ናችሁን? የእርሱ ቃላት፣ ትዕዛዛት፣ እና ቃል ኪዳኖች በየዕለቱ በምታደርጉት ነገር ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ ትፈቅዳላችሁን? ድምጹ ከሌሎች ድምጽች በላይ ቅድሚያውን እንዲያገኝ ትፈቅዱለታላችሁን?”

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ።

እንደ ክርስቶስ ተከታይነታችን፣ ፍጹም ምስሌያችን ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እናስተምራለን እንዲሁም እንመስክራለን። ስለዚህ ጸብን በመተው እርሱን እንከተል። በህዝባዊ ተግባራት የምንመርጣቸውን ፖሊሲዎች ስንከተል፣ የአስታራቂዎችን ቋንቋ እና ዘዴ በመጠቀም ለበረከቱ ብቁ እንሁን። በቤተሰባችን እንዲሁም በሌሎች ግላዊ ግንኙነቶች ውስጥ የሃይል እና የጥላቻ ነገሮችን እናስወግድ። ቅዱሳን እንድንሆን እንዲረዳን የእርሱን በረከት እንድናገኝ ስለ ቅዱስ ስሙ የምመሰክርለት እና በረከትን የምጠራበት እንደ አዳኛችን ቅዱስ ለመሆን እንፈልግ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።