“ሰኔ 15–21 (እ.አ.አ) ‘ሰልፉ ለእግዚአብሄር ነው”፡ 1 ሳሙኤል 17-18፤ 24-26፤ 2 ሳሙኤል 5-7” .ኑ፥ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ብሉይ ኪዳን 2026 (እ.አ.አ) [2026 (እ.አ.አ)]
“ሰኔ 15–21 (እ.አ.አ) ‘ሰልፉ ለእግዚአብሄር ነው፣’” ኑ፣ ተከተሉኝ፡ ብሉይ ኪዳን 2026 (እ.አ.አ)
ዳዊት እና ጎልያድ፣፣ በስቲቭ ኔዘርኮት
ሰኔ 15-21 (እ.አ.አ)፡ “ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነው”
1 ሳሙኤል 17–18፤ 24–26፤ 2 ሳሙኤል 5–7
የእስራኤል ነገዶች በተስፋው ምድር ላይ ከተቀመጡበት ጊዜ አንስቶ ፍልስጤማውያን ለደህንነታቸው ቀጣይ ሥጋት ነበሩ። ከዚህ ቀደም ጌታ ብዙ ጊዜ አድኗቸዋል አሁን ግን የእስራኤል ሽማግሌዎች “ንጉሥ ይሁንልን፥ … በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል” (1 ሳሙኤል 8፥19–20) በማለት ግድ አሉ። ሳኦልም ንጉሥ ሆኖ ተቀባ። ሆኖም አስፈሪው ግዙፍ ጎልያድ የእስራኤልን ጭፍሮች ለመዋጋት በመጣ ጊዜ፣ ሳኦልም ልክ እንደሌሎቹ ሰራዊቱ “እጅግ ፈራ” (1 ሳሙኤል 17፥11)። በዚያ ቀን እስራኤልን ያዳነው ንጉስ ሳኦል ሳይሆን፣ ምንም ትጥቅ ያልለበሰው ነገር ግን የማይደፈር እምነትን በጌታ የለበሰ ትሁት እረኛ ልጅ ዳዊት ነበር። ይህም ውጊያ ለእስራኤላዊያን እና መንፈሳዊ ውጊያ ላለበት ሁሉ የሚያሳየው “እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳልሆነ” እና “ሰልፉ የእግዚአብሔር [እንደሆነ]” ነው (1 ሳሙኤል 17፥47)።
በቤት እና በቤተክርስቲያን ለመማር የሚረዱ ሃሳቦች
1 ሳሙኤል 17
በጌታ እርዳታ ማንኛውንም ተግዳሮት ማሸነፍ እችላለሁ።
የዳዊት እና የጎልያድ ታሪክ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከሚታወቁ ታሪኮች መሃል አንዱ ነው። እርግጥ ነው፣ አብዛኛውን ጊዜ የምናተኩረው በዳዊት ላይ ነው። ነገር ግን በዚህ ጊዜ፣ 1 ሳሙኤል 17ን ስታጠኑ፣ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስላሉት ሌሎች ሰዎች ቃልም አስቡ (ከዚህ በታች ያለውን ዝርዝር ተመልከቱ)። ስለእነሱ እና ስለምክንያቶቻቸው ምን ትማራላችሁ? ስለ ዳዊት ምን ትማራላችሁ? እሱ የሚለየው እንዴት ነው?
-
ጎልያድ፥ ቁጥሮች 8–10፣ 43–44
-
ኤልያብ፥ ቁጥር 28
-
ሳኦል፥ ቁጥር 33
-
ዳዊት፥ ቁጥሮች 26፣ 32፣ 34–37፣ 39፣ 45–47
ምንም እንኳን ታሪካችሁ እንደ ዳዊት በደንብ ባይታወቅም፣ ማሸነፍ ያለባችሁ ጎልያድን የሚያክሉ ፈተናዎችን እና በጌታ ላይ እምነትን ለመለማመድ አጋጣሚዎችን እንደሚጨምር እርግጥ ነው። የዳዊት ምሳሌ በታሪካችሁ ውስጥ የሚያጋጥሟችሁን ችግሮች ለመቋቋም ምን ያስተምራችኋል? እንዲሁም የፕሬዘዳንት ካሚል ኤን ጆንሰንን “Invite Christ to Author Your Story” (ሊያሆና፣ ህዳር 2021 (እ.አ.አ)፣ 80–82) መልዕክት ከችግሮቻችሁ አንዱን በማሰብ ማንበብ ትችላላችሁ። እንደዚህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ፈልጉ፡ ጌታ ፈተናዎቼን እንድመለከት የሚፈልገው እንዴት ነው? ከዚህ በፊት የረዳኝስ እንዴት ነው? ታሪኬን እንዲጽፍ እርሱን እንደማምነው እንዴት ማሳየት እችላለሁ?
በዳዊት ታሪክ ውስጥ በኋላ ላይ አንዳንድ አሳዛኝ ምዕራፎች እንዳሉ አስቀድማችሁ ታውቁ ይሆናል (ለምሳሌ፣ 2 ሳሙኤል 11 ይመልከቱ)። ዳዊት ከጎልያድ ጋር ከተዋጋ በኋላ ምክር ለመስጠት እድሉ ቢሰጣችሁ ምን ትሉታላችሁ? ይህ ምክር በሕይወታችሁ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል?
በተጨማሪም “The Lord Will Deliver Me” (ቪዲዮ)፣ የወንጌል ላይብረሪ ይመልከቱ።
The Lord Will Deliver Me
1 1 ሳሙኤል 17፡26–50
በክርስቶስ የሚያምን አንድ ሰው ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።
ግላዊ ከሆኑ ተግዳሮቶች በተጨማሪ፣ ዓለምን በሙሉ የሚነኩ ትልቅና ውስብስብ ችግሮችም ያጋጥሙናል። የክፉ ኃይሎች በጎ ኃይሎችን “[ለመዋጋት ሲከማቹ]” (1 ሳሙኤል 17፡1)፣ የእኛ ጥረት እንዴት ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል እንጠይቅ ይሆናል። በዳዊት ታሪክ ውስጥ ተስፋ የሚሰጣችሁን ምን ታገኛላችሁ?
በተጨማሪም “Let Us All Press On ፣” መዝሙር፣ ቁጥር 243።
እውነተኛ ጓደኝነት እና ራስን ማክበር፣ በዊልሰን ኦንግ (ዝርዝር)
1 ሳሙኤል 18
“ዮናታን [ዳዊትን] እንደ ነፍሱ ወደደው።”
1 ሳሙኤል 18ን በምታነቡበት ጊዜ፣ ሳኦልን እና ልጁን ዮናታንን (ዳዊት ባይኖር ኖሮ እሱ ቀጣዩ ንጉስ እንደሚሆን መገመት ይችል የነበረውን) ለማነፃፀር አስቡ። ሳኦልና ዮናታን ለዳዊት ስኬት እንዴት ምላሽ ሰጡ? ከዚህ ተሞክሮ ምን መማር ትችላላችሁ?
በዮናታን አመለካከትና ድርጊት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያስታውሳችሁን ምን ታገኛላችሁ?
“ሁሉንም ጥቅሶች… አመሳስ[ሉ]” (1 ኔፊ 19፡23)። ቅዱሳት መጻህፍት እንደ ዳዊት፣ ዮናታን እና ሳኦል ካሉ ሰዎች ተነሳሽነት እና ድርጊት ለመማር ታላቅ እድል ይሰጣሉ። በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ማንም እንከን የለሽ እንዳልሆነ ታገኛላችሁ። ስለዚህ፣ ለምሳሌ ስለ ዳዊት ትክክለኛ ምርጫዎች በምታነብበት ጊዜ ከስህተቶቹም ለመማር ዝግጁ ሁኑ። ይህን ማድረግ የራሳችን ሊሆኑ የሚችሉ ድክመቶችን ለይተን እንድናውቅ እና “[ሌሎች] ከነበ[ሩት] የበለጠ ብልህ ለመሆን [እንድንማር]” ይረዳናል (ሞርሞን 9፡31)።
1 ሳሙኤል 24–26
ይቅርታ ወደ ሰላምና ፈውስ የሚወስደው ትክክለኛው መንገድ ነው።
በ1 ሳሙኤል 24–26 ስለ ትእቢት፣ ይቅርታ እና ራስን መግዛት ትምህርቶችን ፈልጉ። እንዲሁም የሽማግሌ ማርክ ኤ. ብራግ “Christlike Poise” የሚለውን መልእክት እንደ ጥናታችሁ አካል (ሊያሆና፣ ግንቦት 2023 (እ.አ.አ)፣ 60–63) ለማንበብ ልታስቡ ትችላላችሁ። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ዳዊት፣ አቢግያ እና ሌሎች የክርስቶስ ዓይነት እርጋታን ያሳዩት ወይም ያላሳዩት እንዴት ነው? የክርስቶስን ዓይነት እርጋታ ለማሳየት ምን አጋጣሚዎች አሏችሁ?
የእህት ክሪስቴን ዪ መልእክት “Beauty for Ashes: The Healing Path of Forgiveness” (ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 36–39) 1 ሳሙኤል 25ን እንድታጠኑ ሊረዳችሁ ይችላል። አቢግያ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስን የሆነችው እንዴት ነው?
2 ሳሙኤል 5፥17–25
ጌታ ምሪትን ሊሰጠኝ ይችላል።
ዳዊት ጎልያድን ካሸነፈም በኋላ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበረው ችግር አላበቃም ነበር። እናንተ 2 ሳሙኤል 5፥17–25ን ስታነቡ፣ የዳዊት ምሳሌ በሚያጋጥማችሁ ችግሮች ውስጥ እንዴት ሊረዳችሁ እንደሚችል አስቡ (በተጨማሪም 1 ሳሙኤል 23፥2፣ 10–11፤ 30፥8፤ 2 ሳሙኤል 2፥1 ይመልከቱ)። በምትቀበሉት መገለጥ ላይ በመተግበራችሁ እንዴት ተባርካችኋል?
2 ሳሙኤል 7
ጌታ ለዳዊት ቃል የገባለት “ቤት” ምንድን ነው?
ዳዊት ቤት፣ ማለትም ቤተመቅደስ፣ ለጌታ ለመገንባት ሲጠይቅ (2 ሳሙኤል 7፥1–3ን ይመልከቱ)፣ የዳዊት ልጅ እንደሚገነባው ጌታ ምላሽ ሰጠ (ቁጥር 12–15፤ በተጨማሪም 1 ዜና 17፥1–15ን ይመልከቱ)። ጌታም እርሱ በበኩሉ ለዳዊት “ቤት” ማለትም ትውልድ እንደሚሰራለት እንዲሁም ዙፋኑ ለዘለአለም እንደሚኖር ተናግሯል (2 ሳሙኤል 7፥11፣ 16፥25–29)፤ መዝሙር 89፥3–4፣ 35–37ን ይመልከቱ)። ይህ ቃል ኪዳን የዳዊት ዘር በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በዘለአለማዊው ንጉሳችን ተፈጽሟል (ማቴዎስ 1፥1፤ ሉቃስ 1፥32–33፤ ዮሃነስ 18፥33–37ን ይመልከቱ)።
ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት የዚህን ወር የሊያሆና እና የለወጣቶች ጥንካሬ መጽሔቶች ዕትሞችን ይመልከቱ።
ልጆችን ለማስተማር የሚረዱ ሀሳቦች
1 ሳሙኤል 17:20–54
በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ድፍረት እንዲኖረኝ ይረዳኛል።
-
ልጆቻችሁ በ1ሳሙኤል 17፡20–54 የሆነውን ነገር እንዲያውቁ ለመርዳት “ዳዊት እና ጎልያድ”ን በየብሉይ ኪዳን ታሪኮች፣ 112–16 ልትጠቀሙ ትችላላችሁ። ከዚያም በዚህ ንድፍ ውስጥ ያሉትን ምስሎች ወይም የመስመር ሥዕሎችን በመጠቀም ታሪኩን እንደገና እንዲናገሩ ማድረግ ትችላላችሁ። ጌታ ከዚህ ታሪክ እንዲማሩ የሚፈልገው ምን እንደሆነ እንደሚያስቡ ጠይቋቸው።
2:36David and Goliath
-
እናንተ እና ልጆቻችሁ በሕይወታችሁ ሊያጋጥሟችሁ የሚችሉ አንዳንድ አስቸጋሪ ፈተናዎችን ዝርዝር ማውጣት ትችላላችሁ። ከዚያም በእነዚህ ፈተናዎች ሊረዱ የሚችሉ ዳዊት የተናገራቸውን ነገሮች እንዲያገኙ እርዷቸው (1ሳሙኤል 17፡26፣ 32፣ 34–37፣ 45–47 ይመልከቱ)። በችግር ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደረዳችሁ አካፍሉ።
-
ልጆቻችሁ ዳዊት ጎልያድን ለመውዋጋት እንደሚሀዱ በማስመሰል መዝመት እና እንደ “I Will Be Valiant” (የልጆች የመዝሙር መጽሐፍ፣ 162) ደፋር ስለመሆን መዝሙር መዘመር ይችላሉ።
1 ሳሙኤል 18:1–4
መልካም ጓደኞች የእግዚአብሄር በረከት ሊሆኑ ይችላሉ።
-
ልጆቻችሁ ከዮናታንና ከዳዊት ጓደኝነት እንዲማሩ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ለእያንዳንዱ ልጅ፣ አንዱ ዳዊትን ሌላኛው ደግሞ ዮናታንን የሚወክል ሁለት የወረቀት ልብ መስጠት ነው። ከዚያም እነዚህ ሁለቱ ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላቸው ያላቸውን ፍቅር አጉልተው የሚያሳዩ ጥቂት ሀረጎችን ከ1ሳሙኤል 18፡1-4 አንብቡ። ልጆቻችሁ ለጓደኛቸው ፍቅርን እንዴት ማሳየት እንደሚችሉ በወረቀት ልባቸው ላይ መጻፍ ወይም መሳል ይችላሉ።
2 ሳሙኤል 5፥19፣ 23።
ምሪት ካስፈለገኝ የሰማይ አባትን መጠየቅ እችላለሁ።
-
በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ይሆናል። ልጆቻችሁ ንጉሥ ወይም ንግሥት መስሎ መተወን ሊያስደሳቸው ይችላል። ምን ዓይነት ሕጎች ሊያወጡ ይችላሉ? እርዳታስ ለማግኘት የት ይሄዳሉ? ዳዊት እርዳታ በሚፈልግበት ጊዜ መልስ ለማግኘት “[እንደጠየቀ]” ወይም እንደጸለየ ልጆቻችሁ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። ለምሳሌ፣ 2 ሳሙኤል 5:19፣ 23ን ስታነቡ ልጆቻችሁ “ጠየቀ” የሚለውን ቃል እንዲያዳምጡ እና ሲሰሙ እጃቸውን እንዲያጣምሩ ጋብዟቸው። ዳዊት በአዲሱ ሥራው የጌታን እርዳታ ለምን አስፈለገው?
-
የሰማይ አባትን እርዳታ ለማግኘት ስለጸለያችሁባቸው ጊዜያት እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ። እርሱ እንዲረዳችሁ ማድረጋችሁ ምን ለውጥ አመጣላችሁ?
2 ሳሙኤል 7:16–17
ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ንጉሴ ነው።
-
በብሉይ ኪዳን ያነበብናቸው ነገሥታት ሁሉ ጉድለቶች ነበሩባቸው፣ መንግሥታቸውም ሁሉ አብቅተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ፍጹም ንጉሥ ነው፣ ለዘላለምም ይነግሣል። ይህን እንዲያውቁ በ2ሳሙኤል 7፡16–17 ላይ ነቢዩ ናታን ለንጉሥ ዳዊት የነገረውን አንድ ላይ በማንበብ ልጆቻችሁን መርዳት ትችላላችሁ። የዳዊት መንግሥት መጨረሻ የማይኖረው እንዴት ነው? የዳዊት ዘር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣችን መሆኑን የሚያስተምሩ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶችን እንዲያገኙ ልጆቻችሁ እንደ ሉቃስ 1፡32–33፤ ዮሐንስ 18:33–37 እና ራእይ 19:16 እንዲያነቡ እርዷቸው። ኢየሱስ ከምድራዊ ነገሥታት የሚለየው እንዴት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ዘላለማዊ ንጉሣችን የምናከብረው እንዴት ነው?
ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት የዚህን ወር የጓደኛ መጽሔት ዕትም ይመልከቱ።