‘’በወንጌል ጉዞአችሁ ውስጥ ሃሴትን ፈልጉ፣’’ ሊያሆና፣ ሀምሌ 2025 (እ.አ.አ)።
ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ሐምሌ 2025 (እ.አ.አ)
በወንጌል ጉዞአችሁ ውስጥ ሃሴትን ፈልጉ።
ትእዛዛቱን በመጠበቅ ለጌታ ፍቅራችንን የማሣየት የመጨረሻው ውጤት ደስታን እና ሃሴትን የሚያመጡት በረከቶች ናቸው።
በታይላንድ ያሉ በሃሴት የተሞሉ የቤተክርስቲያን አባላት ፎቶ በክርስቲና ስሚዝ
ከጥቂት ዓመታት በፊት በጃፓን ሚስዮናዊ ሆኜ ሳገለግል በነበረበት ጊዜ፣ በሚስዮናችን በሩቅ ጫፍ ላይ ከነበሩ የገጠር ከተሞች መካከል በአንዷ የሰንበት ጉባኤ ተካፍዬ ነበር። የአውራጃው ፕሬዘዳንት ከአንድ ዓመት በፊት ቤተክርስቲያኗን ተቀላቅሎ የነበረን እና የቤተመቅደስ መግቢያ ካርድ ለመቀበል ይፈልግ የነበረን አንድ ሰው ቃለመጠይቅ እንዳደርግለት ሁኔታዎችን አመቻችቶልኝ ነበር። እርሱም ጥምቀቱ አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበበት ወቅት ወይም አንድ ዓመት በሞላው ጊዜ የቤተመቅደስ ቡራኬውን ለመቀበል ተስፋ አድርጎ ነበር።
በንግግራችን ወቅት፣ ይህ አዲስ አባል ከተጠመቀ ጀምሮ በነበረው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለተቀበላቸው አያሌ በረከቶች ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆነ ገልጾልኛል። በየሳምንቱ የሚደረጉትን የቅዱስ ቁርባን እና ሌሎች ስብሰባዎች መሣተፍ ያስደስተዋል። በእርሱ ቅርንጫፍ ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በጥልቀት ተሳታፊ ሆኗል። ለእኔ፣ አሁን የእርሱ ታላቅ ክፍል የሆነውን የወንጌሉን ዓላማ ከመረዳቱ የመነጨውን የቃልኪዳን ልበ ሙሉነት ያንፀባርቃል። እርሱ ታላቅ የልብ ለውጥ ያደረገ የተለወጠ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ነው (ሞዛያ 5፥2 ይመልከቱ)።
የቀሩት ንግግሮቻችን ተስፋ የተሞላበት አካሄድን የተከተሉ ነበሩ። የእርሱ የቤተመቅደስ ልምምዶች አካል ስለሚሆት ስርአቶች እና ቃል ኪዳኖች ተወያይተናል። የቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃድ ከማግኘት ጋር የተያያዙትን እያንዳንዱን መመዘኛ ጥያቄዎች በሚስማማ ሁኔታ መልሷል።
ቃለመጠይቁን ተከትሎ፣ እንዲህ አይነቱን ተወዳዳሪ የሌለውን ሰው በማግኘቴ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆንኩ ለአውራጃው ፕሬዘዳንት አስተያየቴን መስጠቴን አስታውሳለሁ። ሚስዮናውያን እና አባላት እንዲህ አይነቱን ብቃት እና ተስፋ ያለውን ሰው በማግኘታቸው እና በመንፈሳዊ በመበንከባከባቸው የተደነቅሁ መሆኔን ነገርኩት።
የአውራጃው ፕሬዘዳንት በንግግሩ ይህ ሰው ከሚስዮናውያን ትምህርቱን መቀበል በጀመረበት ጊዜ እና ከአንድ ዓመት በፊት ቤተክርስቲያን መምጣት በጀመረበት ጊዜ፣ ተስፋ በሚያስቆርጥ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የነበረ መሆኑን ባካፈለበት ወቅት ተደንቄአለሁ። ከዚያም የአውራጃው ፕሬዘዳንት የዚህ ወንድም በወራት ጊዜዎች ውስጥ የነበረው የወንጌል ጥናቱ እና መለወጡ በመንፈሳዊም በስጋዊም ራስን የመቻል ጎዳና ላይ እንዳስቀመጠው እናም የዓላማ እና የሃሴት ስሜትን በመፍጠር ወደ ተዓምራዊ ለውጥ እንደመራው ገልጿል።
ወንጌል ለህይወቱ ዓላማ የጠራ ምስልን ሰጥቶታል። ግልጽ እና ውድ የሆኑት የወንጌል እውነቶች “እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን ነው እኛም የእርሱ ልጆች ነን። … እግዚአብሔር በግል ያውቀናል እንዲሁም ይወደናል።’’ በእቅዱም ውስጥ ‘’ወደ እርሱ መገኘት እንድንመለስ የሚረዱንን ብዙ ስጦታዎች እና መመሪያዎች ሰጥቶናል።’’ ከሚለው እውቀት ጀምሮ አስፈላጊ ለሆኑ ምድራዊ ጥያቄዎቹ መልሶችን አምጥተዋል።
በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አማካይነት ለእግዚአብሄር ልጆች ሁሉ በእኩል የቀረበው የዚህ ሰው በረከት ይህ ነበር።
የሕይወት ዓላማ
ኢየሱስ ክርስቶስ በጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ወንጌሉን ዳግም በመመለሱ፣ “ስለህይወት ዓላማ፣ ስለማንነታችን ግንዛቤ አለን፣” በማለት ፕሬዘዳንት ኤም ራሰል ባላርድ ገልጸዋል (1928-2023 እ.አ.አ)። በዚያን ወቅት የአስራሁለቱ ሃዋርያት ቡድን ተጠባባቂ ፕሬዘዳንት የነበሩት ፕሬዘዳንት ባላርድ፣ ለቤተክርስቲያን ባደረጉት የመጨረሻ ምስክርነት እንዲህ ብለዋል፦
“በልጅነቱ ወደ ዛፎች ቁጥቋጦ በመግባት፣ ለኃጢአቱ ይቅርታን ፈልጎ በነበረው …በጆሴፍ ምክንያት እግዚአብሔር ማን እንደሆነ እናውቃለን፤ አዳኙ ማን እንደሆነ እናውቃለን፣
“እንደብዙዎቻችሁ፣ ስለ ህይወታችን አላማ፣ ለምን እዚህ እንዳለን፣ በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ ምን ለማድረግ እና ለማከናወን መሞከር እንዳለብን የምናውቀውን በማወቃችን ያን ያህል በመባረካችን እገረማለሁ።”
ለኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት፣ ያ እውቀት የእግዚአብሄርን “ፍጹም” የደህንነት እቅድ መረዳትን ያካትታል። “ታላቁ የደስታ እቅድ፣” “የቤዛነት እቅድ፣” እና “የምህረት እቅድ” (አልማ 42፥8፣ 11፣ 15) በመባልም ይታወቃል፣ ይህም “ከህይወት ውስጥ ሚስጥርን እና ከወደፊታችን ውስጥ ደግሞ እርግጠኛ አለመሆንን የሚያስወጣ ነው።” የህይወት ዓላማ ማእከል የሆነው “የክርስቶስ ትምህርት፣” ለዚያ እቅድ አስፈላጊ ነው።
ወንጌል ያለን በመሆኑ ምክንያት፣ ልንፈተን፣ ልንቀረጽ፣ እና “በበጉ ድል እና ክብር አማካይነት በሙታን ትንሳኤ ወደ ፊት ለመምጣት” እየተዘጋጀን ያለን የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆንን እናውቃለን (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 76፥39)። እኛ ትእዛዛቱን እናውቃለን እናም “መልካሙን ከክፉ በበቂ ሁኔታ ለይተን እንድናውቅ” ትምህርት ተሠጥቶናል (2ኛ ኔፊ 2፥5)። እኛ በምድር ላይ ያለነው ለመውደድ እና ለማገልገል እንደሆነ እናውቃለን። እንዲሁም ለዳግም ምጽዓቱ ለመዘጋጀት ዓለምን እንድናሸንፍ እና ሌሎችም ይህንኑ እንዲያደርጉ ለመርዳት አዳኙ የጠራን እንደሆንን እናውቃለን (ዮሐንስ 16፥33፣ ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 64፥2) ።
በእርሱ ላይ ትኩረትን ባደረግን ጊዜ፣ ጆሴፍ ስሚዝ እንዳለው “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የደስታ ድምጽ” በአስቸጋሪ ቀናት ያበረታናል እንዲሁም ወደ ህይወታችን እና ወደ ሌሎችም ህይወት ትርጉምን እና ዓላማን ያመጣል።
ጉልበት ሁሉ ይንበረከካል፣ በዳን ዊልሰን፣ ለቅጂ ያልሆነ
ታዛዥነት፣ በረከቶች፣ ሃሴት
እግዚአብሔር በምናደርጋቸው ምርጫዎች ተጠያቂ እንሆን ዘንድ የሞራል ነጻነት ሰጥቶናል ( ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 101፥78; 2ኛ ኔፊ 2፥16 ተመልከቱ)። “ለሁሉ ነገሮች ተቃራኒ የመኖር አስፈላጊነት” ክፍል በመሆን (2ኛ ኔፊ 2፥11)፣ ሰይጣን ነጻነታችንን በአግባቡ እንዳንጠቀም እንዲፈትነን ተፈቅዶለታል።
ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “በምድር ነዎሪዎች ላይ የሚመጣውን መቅሰፍት በማወ[ቁ]” በዘመናችን ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊን ጠራ[ው] እናም “ከሰማይም ተናገ[ረው] እንዲሁም ትእዛዛትን ሰጠ[ው]” (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 1፥17)። ጌታም ትእዛዛቶቹን እና ፈቃዱን ለነቢያቱ የገለጸባቸው ያ ንድፍ ለተመሳሳይ ምክንያት ዛሬም በእኛ ጊዜ በፕሬዘዳንት ራሰል ኤም ኔልሰን ይቀጥላል። እግዚአብሔር በዚህ ህይወት ወደ ደስታ እንዲሁም በሚቀጥለው ህይወት ወደሰለስቲያል ክብር ሊመራን ይወዳል።
ለእግዚአብሄር ትእዛዝት መታዘዝ ለእርሱ ካለን መሰጠት እና ፍቅር የሚመነጭ መሆን አለበት። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ እግዚአብሔርን መውደድ ‘’የመጀመሪያይቱ እና ታላቂቱ ትእዛዝ’’ እንደሆነች አውጇል (ማቴዎስ 22፥37-38 ተመልከቱ)። “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” በማለት ሲያውጅ ተጨማሪ ሃሳብን ሰጥቷል (ዮሐንስ 14፥15)።
ጌታን በመውደድ እና ትእዛዛቱን በመጠበቅ በጎ ምላሽ አለ። በዚህ ዘመን “ሁሉም በረከቶች የሚመረኮዙበት በሰማያት ውስጥ ሊሻር የማይችል የታወጀ ህግ አለ—
“እና የትኛውንም ዓይነት በረከት ከእግዚአብሔር ስናገኝ፣ ሁሉም ነገር ለተመረኮዘበት ለዚያ ህግ ታዛዥ በመሆን ነው”(ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 130፥20–21)።
ስለዚህ፣ ትእዛዛቱን በመጠበቅ ለጌታ ፍቅራችንን የማሣየት የመጨረሻው ውጤት ደስታን እና ሃሴትን የሚያመጡ በረከቶች ናቸው።
ህይወትን ዳግም በተመለሰው ወንጌል እና በዘመኑ ራዕይ መነጽር ውስጥ ማየት የጠራ እይታን ይሰጠናል። ከመለኮታዊ መገኛችን እና እጣ ፈንታችን የጠራ እይታ ጋር፣ “ዋናዎቹ ምድራዊ ህይወታችንን ሊሆን የሚችለውን ያህል ከሁሉ የተሻለ የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ህይወታችንን በዘለአለምም የተሻለ የሚያደርጉት ተመሳሳይ ነገሮች እንደሆኑ!” እናውቃለን።
መደምደሚያ
በጃፓን አዲስ አባል ከነበረ ግለሠብ ጋር ከዓመታት በፊት የነበረ ልምዴን በማስታወስ ከጀመርኩበት እጨርሳለሁ። በእርሱ ታታሪነት እና በሚስዮናውያን እንዲሁም በአባላት ታታሪነትም ጭምር፣ ዳግም የተመለሰውን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል አግኝቷል። ወንጌሉን በማግኘቱ፣ ራዕዩን ያሰፋለትን ዓላማውንም እንዲሁ ሊያገኝ ችሏል። ታላቁን የደስታ እቅድም አግኝቷል። ለእቅዱ የወንጌል ቃልኪዳኖች መታዘዝ፣ በሥጋዊ እና በመንፈሳዊ የሚያነሳሡ በረከቶችን እና ሃሴትን አምጥቶለታል።
ወደ ኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የመራው ጉዞ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር እንዲሆን አስችሎታል። የአስራ ሁለቱ ሃዋርያት ቡድን አባል የሆኑት ሽማግሌ ፓትሪክ ኬሮን ተከትሎ የሚመጣውን ሃሴት እንዲህ ይገልጹታል፦
“የሰማይ አባታችን ለእያንዳንዱ ልጆቹ ባለው የፍቅር ዕቅድ እንዲሁም በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ህይወት እና ተልዕኮ የተነሣ በምድር ላይ እጅግ ደስተኞቹ ሰዎች ለመሆን እንችላለን —እንዲሁም መሆን— አለብን! ብዙ ጊዜ መከራ በበዛበት ዓለም ውስጥ ያሉ አስቸጋሪ የህይወት ፈተናዎች ጥልቅ ተፅዕኖ ሲያሳድሩብንም እንኳን፣ በክርስቶስ ምክንያት ባለን ተስፋ እና መልካም በሆነው የደሥታ ዕቅድ ውስጥ ያለንን የራሣችንን ቦታ በማወቃችን ምክንያት እያደገ የሚሄድ እንዲሁም ዘላቂ የሆነ የደስታ ሥሜትን እና ውስጣዊ ሠላምን ማዳበር እንችላለን።”
በውስጡ በጥልቀት ተሳስሮ ስላለው ስለታላቁ የደስታ እቅድ ጨምሮ፣ ዳግም ስለተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና ለዚያም ስላለኝ ምስክርነት ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ወደዘለአለም ህይወት በምታደርጉት ጉዞ ላይ የወንጌልን ፍሬዎች እንድትመገቡ እና በዚህ ህይወት ይበጥል ሃሴት እንድታደርጉ እጋብዛችኋለሁ።
© 2025 by Intellectual Reserve, Inc. መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፤ 6/19። የ Monthly Liahona Message, July 2025. Amharic. 19601 506