2025
ለዘለዓለም ቤተሰብ የሆነው የእግዚአብሔር እቅድ
ታህሳስ 2025 ፟(እ.አ.አ) ሊያሆና


“ለዘለዓለም ቤተሰብ የሆነው የእግዚአብሔር እቅድ፣” ሊያሆና፣ ታህሳስ፣ 2025 (እ.አ.አ)

ወርሀዊ የ ሊያሆና መልዕክት፣ ታህሳስ 2025 (እ.አ.አ)

ለዘለዓለም ቤተሰብ የሆነው የእግዚአብሔር እቅድ

ሽማግሌ ስዋሬዝ ሲያስተምሩ የእግዚአብሔርን እቅድ በደስታ የሚቀበሉ ቤተሰቦች ጌታ እንደወደደ የሚወዱ ናቸው እናም ቃልኪዳናቸውም ወደ ፊት አንድ ቀን “የዘለዓለም ህይወትን እና የተሟላ ደስታን” እንደሚያወርሳቸው በማመን ያከብራሉ።

የሳዎ ፖሎ ብራዚል ቤተመቅደስ ፎቶግራፍ

በሚስዮን አገልግሎቴ ማገባደጃ ወቅት በሳዎ ፖሎ ብራዚል ቤተመቅደስ ለወላጆቼ ቅዱስ ስርዓትን በመፈጸሜ እና ከእነርሱም ጋር በመጣመሬ ሃሴትን አደረግሁ።

ወላጆቼ አፓሬሲዶ እና ሜርሴድስ ከተለያየ የሃይማኖት መደብ የመጡ ቢሆንም የህይወት ልምዶቻቸው ዳግም የተመለሰውን ወንጌል እንዲቀበሉ አዘጋጅቷቸዋል።

አባቴ በመልካም ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ነገር ግን ሃይማኖተኛ ያልነበረ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ፣ ወጣት በነበረ ጊዜ ለሃይማኖት ፍላጎት ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስን አንብቧል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥባቸውን ክፍሎች ተከታትሏል፣ እናም ስለኢየሱስ ክርስቶስ ህይወት አጥንቷል። ጥናቶቹ ለአዳኙ ወንጌል እና ለቤተሰብ ታላቅ ጉጉት እንዲያድርበት አደረገው፣ በመሆኑም ተመሳሳይ አመለካከት ያላትን እንዲያገባ ፍላጎትን አሳደረበት።

በተቃራኒው እናቴ ጥልቅ ሃይማኖተኛ ከሆነ ቤተሰብ የመጣች ናት። መሰረታዊ የወንጌል ትምህርቶችን በደስታ ተቀብለዋል፣ የቤተክርስቲያን አገልግሎቶችን ተከታትለዋል፣ እናም በታማኝነት ሃይማኖታቸውን ይለማመዱ ነበር። ከእንደዚያ ባለ አካባቢ በማደጓ እናቴ የቤተክርስቲያን ስብሰባዎችን በጭራሽ አቋርጦ የማያውቅ አይነት ግለሰብ ሆነች።

በመሆኑም ወላጆቼ ከተጋቡ እንዲሁም እኔ እና ሶስት ወንድሞቼ ከመጣን በኋላ በወንጌል መሰረተ ሃሳቦች የእውቀት ብርሃን ውስጥ እኛን ለማሳደግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ንቁ ተሳታፊ የነበረች አክስቴ አንድ ቀን ለአባቴ እንዲህ አለችው፣ “አራት ወንዶች ልጆች አሉህ፣ ውዴ። በእውነት ክርስቶስን ማእከል ያደረገ ቤተሰብ ለማሳደግ ከፈለግህ እና በቤተሰብህም ውስጥ እግዚአብሄር እንዲገኝ ከፈለግህ ወደ እኔ ቤተክርስቲያን ልትሄድ ያስፈልግሃል።”

አባቴ እርሷ ያለችውን ሰምቷል፣ ነገር ግን የሙሉ ጊዜ ሚስዮናውያን በጎረቤታችን በራሪ ወረቀቶችን እስከሰጡበት፣ በራችንንም እስካንኳኩበት እና እኛንም ማስተማር እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም ነበር። በፍጥነትም እነርሱ አክስቴ እንዲከታተል ያበረታታችውን ቤተክርስቲያን የሚወክሉ እንደነበር አስተዋለ።

ብርሃን እና እውነት

ወላጆቼን ከጅምሩ ዳግም ለተመለሰው ወንጌል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ካደረጓቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ቤተክርስቲያኗ ለቤተሰብ የሰጠችው ቦታ እና ‘’አብዛኞቹ የእግዚአብሔር የማዳን እና የመክበር ስራዎች የሚፈጸሙት በቤተሰብ አማካይነት” በሚሰጡ ትምህርቶች ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ነበር። ከመጠመቃቸው አስቀድሞ፣ ወላጆቼ እየተማሩ በነበሩት ነገሮች በጣም በመደነቃቸው ጎረቤቶቻቸውን ለሚስዮናውያን ትምህርቶች ይጋብዟቸው ነበር።

የሽማግሌ ስዋሬዝ ወላጆች ፎቶግራፍ

ወላጆቼን ከጅምሩ ዳግም ለተመለሰው ወንጌል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ካደረጓቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ቤተክርስቲያኗ ለቤተሰብ የሰጠችው ቦታ ነበር።

ከሚስዮናውያን ጋር እንደተገናኙ እና ከጥምቀታቸው በኋላ ወንጌልን መማር እንደቀጠሉ፣ ወላጆቼ “ልጆቻቸውን በብርሃን እና እውነት ለማሳደግ” እና “ቤታቸውን በስርዓት” እንዴት በመንፈሳዊነት እንደሚያስተዳድሩ መንገዶችን ተምረዋል (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 93፥40፣ 43)።

“ቤተሰብ ፈጣሪ ለልጆቹ ላዘጋጀው የዘለአለም ደስታ እቅድ መካከለኛ’’ እንደሆነ እና “በቤተሰብ ህይወት ደስታ የሚገኘው ቤተሰብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ላይ ሲገነባ እንደሆነ” ተምረዋል።

“የተሳኩ ጋብቻዎች እና ቤተሰቦች የሚመሰረቱት እና የሚጸኑት በእምነት፣ በጸሎት፣ ንስሀ በመግባት፣ በምህረት፣ በክብር፣ በፍቅር፣ በርህራሄ፣ በስራ፣ እና በመልካም መዝናኛ እንቅስቃሴዎች መሰረት በኩል’’ እንደሆነ ተምረዋል።

ቤተሰቦች ዘለዓለማዊ እንደሆኑ እና “አሁን በመካከላችን የሚገኝ ተመሳሳይ ማህበረሰብ በዚያም በመካከላችን የሚሆነው ከዘለዓለም ክብር ጋር ሲጣመር ብቻ’’ እንደሆነ ተምረዋል (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 130፥2)።

“የማንኛውም ትምህርት፣ በቤተክርስቲያን የሚከናወን የማንኛውም ተግባር ዋናው አላማ ወላጆች እና ልጆቻቸው በቤታቸው ውስጥ ደስተኛ እንዲሆኑ፣ በዘለአለም ጋብቻ እንዲጣመሩ እና ከትውልዶቻቸው ጋር እንዲያያዙ ለማድረግ’’ መሆኑን ተምረዋል።

በዚያም እውቀት፣ እንደዘለዓለም ቤተሰብ ለመጣመር ፈልገዋል።

ወደ ዘለዓለማዊነት የሚያይ አይን

ወላጆቼ ከተጠመቁ በኋላ፣ ከዓለም ወደ ወንጌል መንግስት ዘወር በማለት እየተማሩ የነበሩትን ተግባራዊ አድርገዋል። የቤት ምሽት እና የቤተሰብ የቅዱሳን መጻሐፍት ጥናትን በማድረግ፣ በታማኝነት የቤተክርስቲያን ስብሰባዎችን በመካፈል፣ እና የቤተሰብ ታሪክ ስራዎችን በመስራት ቤተሰባችንን አንድ ለማድረግ ሰርተዋል። አንድነትን ለማምጣት ከተደረገው ጥረት ጋር፣ ዘለዓለማዊነትን ለማምጣት በማለም የደህንነትን እቅድ ያማከለ ቤተሰብ ለመፍጠር ተስፋ አድርገው ነበር።

በ1965 (እ.አ.አ)፣ ወላጆቼ በተጠመቁበት ዓመት፣ ለሳዎ ፖሎ ብራዚል በጣም ቅርቡ ቤተመቅደስ በሜሳ አሪዞና በ6000 ማይል (9650 ኪሜ) በሚጠጋ ርቀት ላይ ነበር። ጉዞ ለቤተሰባችን እጅግ ውድ ነበር፣ በመሆኑም ወላጆቼ የቤተመቅደስ ስርዓቶችን ከመቀበላቸው እና ከመጣመራቸው በፊት የሳዎ ፖሎ ብራዚል ቤተመቅደስ በ1978 (እ.አ.አ) እስከሚመረቅ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። በዚያን ወቅት፣ በሪዮ ደዤነሮ ሚስዮኔን እያገለገልኩ ነበር።

በየካቲት 1980 (እ.አ.አ) ሚስዮኔን ከማብቃቴ ሁለት ወራት ቀደም ብሎ፣ የሚስዮን ፕሬዘዳንቴ እኔን እና የሚስዮን ጓደኛዬን በሪዮ ደዤኔሮ ከነበሩ የካስማ አባላት ጋር ለወላጆቼ የተቀደሱ ስርዓቶችን እንዳደርግ እና ከእነርሱም ጋር እንድጣመር ወደ ሳዎ ፖሎ ቤተመቅደስ እንድንጓዝ ፈቀደልን። እንደወላጆቼ ሁሉ፣ ለቤተመቅደስ ስርዓቶች እና ቃልኪዳኖች ቃል የተገቡልኝን በረከቶች ለመቀበል ለዓመታት ጠብቄአለሁ።

ያ ልምድ የወደፊቱን ራእዬን ቀይሮልኛል እናም ስለፕሬዘዳንት ራሰል ኤም ኔልሰን የቅርብ ቃላት እውነተኛነት የመጀመሪያውን ቅኝት ሰጥቶኛል፤ ‘’በቤተመቅደሥ ውስጥ የምታሣልፉት ጊዜ ስለሰለሥቲያል እንድታስቡ እንዲሁም ስለእውነተኛ ማንነታችሁ፣ ወደፊት ማን መሆን እንደምትችሉ እና ለዘለዓለም ልትኖሩት ስለምትችሉት ህይወት እይታ እንድታገኙ ይረዳችኋል።’’

በዚያ አጋጣሚ በቤተመቅደስ የነበረኝ አጭር ጊዜ በቀረው የሚስዮናዊ አገልግሎቴ ላይ በጥልቅ ተጽእኖ አሳድሯል። ከዚያም አዲስ ራእይ ጋር፣ ስለ ቤተመቅደስ እና ስለቤተሰብ የእግዚአብሔር እቅድ አስፈላጊነትን መመስከር እንዲሁ በህይወቴ ዘላቂ የሆነ ተጽእኖ ነበረው።

ባለቤቴ ሮዛና፣ እና እኔ ከሚስዮኔ ሁለት ዓመታት በኋላ ስንጋባ የራሳችንን ዘለዓለማዊ ቤተሰብ ለማፍራት በነበረን ራእይ በቤተመቅደስ ተጣመርን። ይህንንም ለማድረግ ልክ ወላጆቻችን እንዳስተማሩን አይነት የቤተሰብ ባህል ለመፍጠር አብረን ሰርተናል ይህም ያተኮረው በአዳኙ፣ በእርሱ ትምህርቶች፣ እና በዘመናችን ባሉ የእርሱ ነቢያት ትምህርቶች ላይ ነበር።

ዛሬ ልጆቻችን በተመሳሳይ የወንጌል መርህ ላይ ልጆቻቸውን እያሳደጉ ነው። ለእኛ ቤተሰብ ሁሉም ነገር ነው ምክንያቱም በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ የቤተሰብን መካከለኛነት ስለምንረዳ ነው።

እንደ አጠቃላይ ባለስልጣን፣ ሶስቱን ልጆቼን ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር የማጣመር በረከት ተካፋይ ነበርኩኝ። በቤተመቅደሱ መሰዊያ ላይ ሲንበረከኩ አይኖቻቸውን ማየቱ ውብ የሆነ ልምምድ ነበር። ዘሮቼ ወላጆቼ ባስተማሩኝ እንዲሁም ሮዚና እና እኔ ባስተማርናቸው ተመሳሳይ የወንጌል መርህ ሲባረኩ ለማየት ችያለሁ። እነዚህ በረከቶች በመጪዎቹ ትውልዶች ሲቀጥሉ ማየት እችላለሁ። እናም ይህንን ማን እውን እንዳደረገው ትውስታን አግኝቻለሁ።

አያሌ የተውልድ ስብስብ በሼልፎቹ ላይ

የገና ማስታወሻ

ቤተሰብ ለእግዚአብሔር የደስታ እቅድ መካከለኛ ነው፣ ነገር ግን ያለ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያ እቅድ እውን ሊሆን አይችልም። የእርሱ የሃጢያት ክፍያ እና በወንጌሉ የሚገኙት ስርዓቶች እና ቃልኪዳኖች የዘላለም ክብር የተስፋ ቃልን እውን የሚያደርጉ ናቸው።

ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ አውጀዋል፥ “የዘለዓለም ክብር የቤተሰብ ጉዳይ ነው። ቤተሰቦች ከፍ ከፍ መደረግ የሚችሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማዳን ስነስርዓቶች ብቻ ነው። እኛ የምንጥርለት ዋናው መጨረሻው እንደቤተሰብ--የቤተመቅደስ ስርዓቶችን በማከናወን፣ በመጣመር፣ እና በእግዚአብሔር ፊት ለዘለዓለም ህይወት በመዘጋጀት ደስተኛ ለመሆን ነው።’’

ከዚህ በፊት ያላየኋቸውን ስፍራዎች ስጎበኝ፣ ሮሳና እና እኔን ስለ ጌታ የሚያስታውሰንን ትንሽ የትውልድ ሁኔታን ለማግኘት ሞክሪያለሁ። ስብጥሮችን እያዳበርኩ ነው።

እነዚያን ትሁት የሆኑ የትውልድ ስፍራዎች ባሰብን ጊዜ፣ እኔ እና ባለቤቴ በአንድ ወቅት እንዲህ አሰላሰልን፣ “በእውነት በህይወታችን ትርጉም ያለው ነገር ምን ይሆን?” መልሱ በርግጥ አዳኙ፣ የእርሱ ወንጌል፣ እና ቤተሰባችን ነው። የሰማዩ አባታችን ለእኛ ያለውን ፍቅር እና የዘለዓለማዊ ቤተሰብ ቃል ኪዳን በአዳኙ አማካይነት በመሆኑ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በቤታችን በሚገኙ ሁለት የመጽሀፍ መደርደሪያዎች ላይ ሁሉንም የትውልድ ስራዎቻችንን አስቀምጠን ነበር—እናም ከጌታ ልደት በኋላ ከማንሳት ይልቅ እዚያው ልናቆያቸው መርጠናል። ያ ባህል በየዓመቱ የጌታን ልደት መንፈስ እንድናቆይ ረድቶናል።

በየእለቱ እነዚያን የትውልድ ስራዎች ባየን ጊዜ፣ በህይወታችን የጌታን ማእከላዊ ሚና ያስታውሱናል። አሁን በምድር ሰላምን (ሉቃስ 2፥14 ተመልከቱ) እና በሚመጣው ህይወት ያለው ዘለዓለማዊ ህይወት በጌታ ላይ እና ከእርሱ ጋር በገባነው ቃል ኪዳን ላይ የተደገፈ መሁኑን ያስታውሱናል። “እርሱ፣ ኢየሱስ፣ ለአለም ሊሰቀልና የአለም ኃጢአቶችን ሊሸከም፣ እናም አለምንም ሊቀድስና፣ ከርኩሳትም ሊያጸዳ ወደ አለም እንደመጣ፣

“በእርሱም አማካይነት አብ በእርሱ ሀይል ያደረጋቸውን እና በእርሱ የተሰሩት ሁሉ ይድኑ ዘንድ እንደመጣ’’ ያስታውሱናል (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 76፥41–42)።

ልክ እነዚህን እውነቶች ከወላጆቻችን እንደተማርን ሁሉ፣ ሮዛና እና እኔ ለልጆቻችን ለማስተላለፍ ሰርተናል። አሁን ልጆቻችን እነዚህኑ ተመሳሳይ እውነቶች ለልጆቻቸው እያስተመሩ ይገኛሉ። ከ60 ዓመታት በፊት በብራዚል በነበረች ትንሽ ቤታችን ውስጥ በወላጆቼ ልብ ውስጥ ተተክለው የነበሩ ፍሬዎች “እነሆ፣ የተከበረውን፣ ከጣፋጮች ሁሉ ጣፋጭ የሆነውንና ከነጡት ሁሉ በላይ ነጭ፣ አዎን ከንፁህ ሁሉ በላይ ንፁህ የሆነውን” አፍርተዋል እናም ሰጥተዋል። (አልማ 32፥42)።

ለቤተሰቦቻቸው የእግዚአብሔርን እቅድ በደስታ የሚቀበሉ፣ አዳኙ እንደወደደው የሚወዱ፣ እና ቃልኪዳናቸውን የሚያከብሩ “የዘለዓለምን ህይወት በረከት እና የደስታን ሙላት” ከሚወዷቸው እንዲሁም ከአብ እና ከወልድ ጋር አንድ ቀን እንደሚወርሱ እመሰክራለሁ።

ማስታወሻዎች

  1. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፦ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል፣ 2.0፣ የወንጌል ቤተ መፃህፍት ውስጥ ይመልከቱ።

  2. ቤተሰብ፦ ለአለም አዋጅ፣” የወንጌል ላይብረሪ።

  3. ቤተሰብ፥ ለአለም የተላለፈ አዋጅ።”

  4. ቦይድ ኬ ፓከር፣ “A Tribute to the Rank and File of the Church [ለቤተ ክርስቲያን እናንዳንዱ አገልጋዮች የተሰጠ ክብር]፣” ኤንዛይን፣ ግንቦት 1994 (እ.አ.አ)፣ 19።

  5. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “Rejoice in the Gift of Priesthood Keys [በክህነት ቁልፎች ስጦታ ደስ ይበላችሁ]፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2024 (እ.አ.አ)።

  6. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ሰማያትን በቤተመቅደስ እና በቤተሰብ ዘር ሃረግ ስራዎች ሰማያትን መክፈት፣” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2017 (እ.አ.አ)፣ 18።

  7. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፣ 2.0።