2025
ቃል ኪዳኖች፣ ሀይል እና የተስፋ ቃላት
ጥቅምት 2025 (እ.አ.አ) ሊያሆና


“ቃል ኪዳኖች፣ ሀይል እና የተስፋ ቃላት፣” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2025 (እ.አ.አ)።

ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ጥቅምት 2025 (እ.አ.አ)

ቃል ኪዳኖች፣ ሀይል እና የተስፋ ቃላት

ቤተመቅደስ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት በፊት ለምእመናን ቃል የተገባው ኃይል እና ጥበቃ ማዕከል ነው።

ጆሴፍ ስሚዝ በከርትላንድ ቤተመቅደስ ፊት ለፊት ቆሞ የሚያሳይ ስዕል

የጆሴፍ ስሚዝ ስዕል በዳን በር

በግንቦት 1833 (እ.አ.አ)፣ የቅድመ አያቴ አሼል ፔሪ እና አንዳንድ ጓደኞቹ ከሰሜን ኒው ዮርክ ወደ ከርትላንድ ኦሀዮ ተጓዙ። እነርሱ በዳግም የተመለሰችው ቤተክርስቲያን አባል አልነበሩም፣ ነገር ግን ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝን ለመገናኘት ፈልገው ነበር። የከርትላንድ ቤተመቅደስን ስለመገንባት በነበረው የሸንጎ ውይይት ለመሳተፍ በሰዓት ደረሱ።

ሸንጎውን ከጀመረ በኋላ፣ ነቢዩ ቤተመቅደስን ስለመገንባት ጉዳይ አቀረበ። ከዚያም በዚያ የሚገኙት ይህን ታላቅ ስራ ስለመጀመር ያላቸውን ስሜት እንዲገልጹ ጠየቃቸው። አብዛኛዎቹ እንዲህ አይነት ድርጊት ለማከናወን ቤተክርስቲያኗ በጣም ደሀ ነች በማለት መለሱ። ትንሽ፣ ብዙ ወጪ የማያስፈልገው ህንጻ ለመገንባትም ሀሳብ አቀረቡ።

በቀጠለው ውይይት፣ አያቴ ፔሪ እና ጓደኞቹ ያላቸውን ገንዘብ አወጡ እናም ደመሩት። ለመመለሻ ጉዞአቸው እና ለቤተመቅደስ መገንባት አስተዋጽዖ ለማድረግ የሚበቃ ገንዘብ አላቸውን? ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ አያቴ ወደ ጆሴፍ ስሚዝ ቀረበ፣ የአምስት ዶላር የወርቅ ሳንቲም አወጣ፣ እና ለነቢዩ ሰጠው። (እንደዚህ አይነት ሳንቲም በዚህ ቀን ብዙ መቶ ዶላሮች ያህል ዋጋ አለው!)

ጆሴፍ በሸንጎው ፊት ቆመ እናም ሳንቲሙን ከፍ አድርጎ አሳየ። ከዚያም በትጋት በመናገር፣ “ሥራው ተጀምሯል እናም [የጌታ] ቤትም" ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ "ባቀረበው ንድፍ መሠረት ይገነባል።"

የፔሪ ቤተሰብም ወዲያውኑ በከርትላንድ ውስጥ ከምትገኘው ቤተክርስቲያን ጋር ተቀላቀሉ፣ ከትንሽ አመታት በኋላ በናቩ ቤተመቅደስ ውስጥ የቤተመቅደስ በረከታቸውን ተቀበሉ፣ ከዚያ በኋላም ወደ ዩታ ተጓዙ።

በ1836 (እ.አ.አ) የከርትላንድ ቤተመቅደስ በተቀደሰበት ጊዜ፣ ለመገኘት የፈለጉትን የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ሁሉ በምርቃቱ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ቦታው በጣም ትንሽ ነበር። ቤተክርስቲያኗ ስታድግ፣ ስብሰባዎችን በውጪ የሚሳተፉ ቅዱሳን ቁጥርም አደገ። በወጣትነቴ እንደ ካስማ ፕሬዚደንት እና በ2007 (እ.አ.አ) እንደ አጠቅቃላይ ባለስልጣን ስጠራ እንደ አማካሪ ያገለገሉት ፕሬዚዳንት ጄምስ ኢ. ፋውስት፣ ስለቤተክርስቲያኗ ሁለተኛ ቤተመቅደስ ይህን አስተያየት ሰጡ፦

“በ1846 የናቩ ቤተመቅደስ ከመጠናቀቁ በፊት ቅዱሳን ጆሴፍ እና ሌሎች የቤተክርስትያን መሪዎች ሲናገሩ ለመስማት በውጭ፣ ብዙ ጊዜ በቤተመቅደስ አቅራቢያ፣ ሆነው ይሰበሰባሉ። አንዳንድ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ በእነዚያ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ነበር”—አንዳንድ ጊዜ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥም ጭምር።

“እንደ [ሽማግሌ] ጆርጅ ኤ. ስሚዝ በአስቂኝ ሁኔታ እንዳስተዋሉት፣ ‘በነቢዩ ጆሴፍ ዘመን … [ቤተክርስቲያኗ በበር ውጭ በልጽጋ ነበር።’”

በዘመናችን፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከቤት ውጭ፣ በቤት ውስጥ እና በመላው አለም እያደገች በመሆኗ አመስጋኞች ነን። ያ እድገት ቤተመቅደሶችን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት “እንደቀረበው ንድፍ” መገንባትን ያጠቃልላል—ሁልጊዜም በረከቶችን፣ መቀደስን፣ እምነትን፣ እና መስዋዕትን የሚያካትተው ንድፍ።

የከርትላንድ ቤተመቅደስ ስዕል

A Glorious Light—Kirtland Temple [ግርማዊ ብርሀን—የከርትላንድ ቤተመቅደስ]፣ በግሌን ኤስ. ሆፕኪንሰን፣ ቅጂ ለመስራት አይፈቀድም

ለምን ብዙ ቤተመቅደሶች?

ፕሬዚዳንት ኧዝራ ታፍት ቤንሰን [1899–1994 (እ.አ.አ)] ከብዙ አስር አመታት በፊት እንዳሉት፣ “ቤተመቅደሶች የሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ፣ የፓስፊክ ደሴቶች፣ አውሮፓ እና ሌሎች ቦታዎችን እንደሚሸፍኑ የቀድሞ አባቶቻችን ተንብየዋል። “ይህ የማዳኑ ሥራ በሚፈለገው መጠን መከናወን ካለበት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተመቅደሶች ያስፈልጋሉ።”

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳሉት፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ቤተመቅደስን የምንገነባበት "ምክንያት ጌታ እንድናደርገው መመሪያ ስለሰጠን ነው። የቤተመቅደስ በረከቶች በመጋራጃው በሁለቱም በኩል እስራኤልን ለመሰብሰብ ይረዳሉ። እነዚህ በረከቶችም አለምን ለጌታ ዳግም ምጽዓት የሚያዘጋጁትን ሰዎች ለማዘጋጀት ይረዳሉ።

በከርትላንድ ቤተመቅደስ ምርቃት ባደረገው ጸሎት ላይ፣ ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ጽለየ፣ “በጌታ ቤት መግቢያ በር ላይ የሚገቡት ህዝብ ሁሉ ሀይልህ እንዲሰማቸው። …

“እና ቅዱስ አባት ሆይ፣ አገልጋዮችህ ከዚህ ቤት በሀይልህ ይታጠቁ ዘንድ፣ እና ስምህም በእነርሱ ላይ እንዲሆን፣ እና ክብርህም በዙሪያቸው፣ እና መላእክትህም ይጠብቋቸው ዘንድ እንጠይቅሀለን” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 109፥13፣ 22፤ ትኩረት ተጨምሯል፤ ደግሞም ቁጥር 23ን ተመልከቱ)።

እነዚህን ጥቅሶች ሳነብ፣ ኔፊ ስለኋለኛው ቀናት ያየውን ራዕይ አስብበታለሁ። የቃላቱን ተመሳሳይነት ተመልከቱ፦ “እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ በበጉ ቤተክርስቲያን ቅዱሳንና በምድር ገፅ ላይ ሁሉ በተበተኑት የጌታ የቃል ኪዳን ህዝቦች ላይ የእግዚአብሔር በግ ኃይል ሲወርድ ተመለከትኩ፤ እነርሱም ፅድቅንና የእግዚአብሔርን ኃይል በታላቅ ክብር የታጠቁ ነበሩ።” (1 ኔፊ 14፥14፤ ትኩረት ተጨምሯል)።

የኋለኛው ቀን ቤተመቅደሶች የኔፊን ትንቢት መፈጸም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ አምናለሁ እናም ከዳግም ምጽአቱ በፊት ለምእመናን ቃል የተገባላቸው ጥበቃ እና ሀይል ማእከላዊ ናቸው።

ከበርካታ አመታት በፊት፣ እንደ የዩኒቨርሲቲ ኤጲስ ቆጶስ ሆኜ ሳገለግል፣ በተለይ በአጥቢያዬ ውስጥ ባለች አንዲት ወጣት ተደንቄ ነበር። አሁንም ታስደንቀኛለች። አሁን እርሷን እንደ አሁን እርሷን እንደ ወጣት ሴቶች አጠቃላይ ፕሬዚዳንት፣ ፕሬዚዳንት ኤምሊ ቤል ፍሪማን ታውቃታላችሁ። በቅርብ አጠቃላይ ጉባኤ ንግግር ላይ፣ በቤተመቅደስ በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ከፍተኛ የመንፈስ ቦታ ከፍ እንደሚያደርገን አስተምራለች

ፕሬዚዳንት ፍሪማን እንዳለችው፣ “ቤተመቅደስ በገባሁኝ ቁጥር ከእርሱ ጋር ጥልቅ የሆነ የቃል ኪዳን ግንኙነት ይኖረኛል።” “በመንፈሱ ተቀድሻለሁ፣ የእርሱ ሀይል ተሰጥተውኛል እንዲሁም መንግስቱን ለመገንባት ተለይቻለሁ።”

ቃል የተገባለት ሀይል

ፕሬዚዳንት ኔልሰን በቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች በኩል ሊገኙ ስለሚችሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ሀይል በብዛት ተናግረዋል። “ራስችሁን ከአዳኝ ጋር ማጣመር ማለት የእሱን ጥንካሬ እና የመቤዠት ሃይል ማግኘት ትችላላችሁ ማለት ነው” አሉ። ፕሬዚዳንት ኔልሰን ደግመው እንዳስተማሩት፦

“የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖቻችንን ስናከብር፣ የጌታን የሚያጠነክር ኃይል ይበልጥ እናገኛለን። በቤተመቅደስ ውስጥ፣ በዓለም ካሉት ጫናዎች ጥበቃን እናገኛለን።”

“በቅዱስ የክህነት ቃል ኪዳኖች አማካኝነት አስፈላጊዎቹ [የአዳኝ] ስርዓቶች ከእርሱ ጋር ያጣምሩናል። ከዚያም በኋላ፣ ቃል ኪዳኖቻችንን ስንጠብቅ፣ የእርሱን ፈዋሽ፣ አጠንካሪ ኃይል ስጦታ ይሰጠናል። እና አቤቱ፣ የእርሱ ኃይል በወደፊት ቀናት እንዴት እንደሚያስፈልገን።”

“ህዝባችን አሁን እና ወደፊት ለሚመጡት ቀናት የሚያስፈልገው የስነምግባር እና የመንፈሳዊ ሀይል የእግዚአብሔር አብ እና የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ነው። ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኖችን በመፈፀም እና በመጠበቅ ሀይላቸውን ማግኘት እንችላለን።”

ወንድሞች እና እህቶች፣ የምንኖረው በጣም ክፉ በሆነ ዓለም ውስጥ ስለሆነ የሰማይ ኃይል አስፈላጊ ነው። ያለዚያ ኃይል፣ “የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል” እና “እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም” (ሚልክያ 3፥2) ለመሆን አንችልም። ያ ቀን መቼ እንደሆነ አናውቅም፣ ነገር ግን ለእርሱ መመለስ “[መንገዱን በፊቱ እንዲያስተካክሉ]” የእርሱ መልእክተኞች ተልከዋል (ሚልክያ 3፥1)። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዓለም ወደዚያ ቀን በእርጋታ እየተንሸራተተች አይደለም።

እኛን ለመርዳት ለታማኞች ቃል የተገባለት ኃይል ያስፈልገናል፦

  • እግዚአብሔር በህይወታችን እንዲያሸንፍ እናድርግ።

  • ንስሀ ግቡ እንዲሁም ወደ ጌታ ቅረቡ።

  • ባርኩ፣ አፅናኑ፣ ምሩ፣ እንዲሁም አገልግሉ።

  • “መከራዎቻችንን፣ ፈተናዎቻችንን እና ልባችንን የሚሰብረውን በተሻለ ሁኔታ እንቋቋመው” (ሞዛያ 3፥19 ተመልከቱ)።

  • በቃል ኪዳን መንገድ ስንጓዝ በክርስቶስ ሰላም እና ደስታ እናግኝ።

  • “[ለ]ክፉዎች አሰቃቂ አደጋ” እና “[ለ]መቃጠል ቀን” ተዘጋጁ(ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 109፥46)።

  • የጌታን ስራ ከእርሱ ዳግም ምፅዓት በፊት አከናውኑ።

የቱሳን አሪዞና ቤተመቅደስ

የቱሳን አሪዞና ቤተመቅደስ ጉልላት በ ጄምስ ዊትኒ ያንግ

የደህንነት ጠባቂዎች

የሰማይ አባት ስራ እና ክብር “የሰውን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት ለማምጣት” ነው (ሙሴ 1፥39)። እያንዳንዱ ቤተመቅደስ እንደ እግዚአብሔር የማዳን እቅድ ምድራዊ ጠባቂ ሆኖ ይቆማል፣ ይህም አዳኝ በስራ እና በክብር ውስጥ ያለውን ማዕከላዊ ሚና ያመለክታል።

በኃይሉ የታጠቁ—ያገቡም ቢሆን ያላገቡ—የቤተመቅደስን ቃል ኪዳኖች በታማኝነት የሚጠብቁ፣ ቃል ኪዳን ጠባቂ ወንድ እና ሴት፣ በዚህ ህይወት እና በሚመጣው ህይወት ይባረካሉ።

ፕሬዚዳንት ኔልሰን ቃል እንደገቡት፣ “ለእያንዳንዳችን የምንጥርበት ፍጻሜ በጌታ ቤት ሃይል መሰጠት፣ እንደ ቤተሰብ መታተም፣ በቤተመቅደስ ውስጥ ለተገባ ቃል ኪዳኖች ታማኝ በመሆን ለታላቁ የእግዚአብሔር ስጦታ፣ ለዘለአለም ህይወት ብቁ እንድንሆን ነው። የቤተመቅደስ ስርዓቶች እና በዚያ የምትገቡት ቃል ኪዳኖች ህይወታችሁን፣ ጋብቻችሁን፣ እና ቤተሰባችሁን፣ እናም የጠላትን ጥቃቶች ለመቋቋም ያላችሁን ችሎታ ለማጠናከር ዋና ቁልፎች ናቸው። በቤተመቅደስ ውስጥ በምታመልኩበት እና ለቅድመ ዘመዶቻችሁ የምታደርጉት አገልግሎት በተጨማሪ የግል ራዕይና ሰላም ይባርካችኋል እናም በቃል ኪዳን መንገድ ለመቆየት ያላችሁን የልብ ውሳኔ ያጠነክራል።”

እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ፣ እነዚህ ነገሮች እውነት እንደሆኑ እመሰክራለሁ።