2025
እግዚአብሔር ያልሆነው ነገር
ነሐሴ 2025 (እ.አ.አ)


ወርሀዊ የለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ ነሐሴ 2025 (እ.አ.አ)

እግዚአብሔር ያልሆነው ነገር

ስለ ሰማይ አባታችን 5 እውነቶች

እግዚአብሔር ስላልሆነው ነገር ስንረዳ ስለእርሱ ብዙ መማር እንችላለን።

ቅብ እና የብሩሽ ቅብ

ምስል በካሚላ ግሬይ

ከዳግም መመለሱ ትልልቅ በረከቶች አንዱ እግዚአብሔር ራሱን እና እንደ አፍቃሪ የሰማይ አባት ባህሪውን እንደገና መግለጡ ነው። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ስለእግዚአብሔር እውነት ያልሆኑ እሳቤዎች ወይም ሀሳቦች ይኖሩናል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ እግዚአብሔር ስላልሆነው ነገር በመረዳት ስለእርሱ ብዙ መማር እንችላለን።

እግዚአብሔር በርቀት በሚገኝ ዙፋን ላይ ያለ የሆነ የማይታወቅ ግለሠብ አይደለም

እርሱ ከምትገምቱት ምርጥ ምድራዊ አባት የበለጠ ድንቅ የሆነ አባታችን ነው። ምንም እንኳን ከእርሱ ጋር የነበረንን የቅድመ ምድር ህይወት ማስታወስ ባንችልም እርሱ በግለሠብ ደረጃ እና ፍጹም በሆነ ሁኔታ ያውቀናል። የሰማይ አባት የከበረ የስጋና አጥንት አካል አለው፣ እኛም የእርሱ አምሳያ ነን።

እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል ለማየት የምትቸገሩ ከሆነ፣ ፍጹም የሆነው ምሳሌ ይኸውም ልጁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ። ክርስቶስ “እኔ መንገድና እውነት ህይወትም ነኝ፤ ከእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር።” (ዮሐንስ 14፥6–7)። በሌላ አባባል፣ የሰማይ አባት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ከፈለግን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንደሚመስል መማር እንችላለን! እነርሱ በዓላማ ፍጹም አንድ ናቸው።

እግዚአብሔር፣ ለእናንተ በጣም በሥራ የተጠመደ አይደለም

እንደ እውነቱ ከሆነ የዘለአለም ሕይወት እንድታገኙ መርዳት የእርሱ ስራ እና ክብር ነው። እናንተ የእርሱ ቁጥር አንድ ትኩረት ናችሁ። እንደ እኛ በጊዜ የተገደበ አይደለም። በማንኛውም ጊዜ በጸሎት ወደ እርሱ ቅረቡ። ከዚያም የሚመልስባቸውን በርካታ መንገዶች አድምጡ።

እግዚአብሔር፣ እርሱን እንድትከተሉ አያስገድድም

የአስራሁለቱ ሃዋርያት ቡድን አባል የሆኑት ሽማግሌ ዴል ጂ. ረንላንድ፣ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦ “የሰማዩ አባታችን የወላጅነቱ አላማ ልጆቹ ትክክለኛውን እንዲያደርጉ ማስገደድ አይደለም፤ ይልቁንም የእርሱ ልጆች መልካም የሆኑትን ነገሮች ለማድረግ እንዲመርጡ በመጨረሻም እርሱን እንዲመስሉ ነው።” ወደ እውነት ይጋብዛችኋል፣ ያማክራችኋል እንዲሁም እውነትን ያስተምራችኋል፣ ነገር ግን እርሱን እንድትከተሉ በማስገደድ የመምረጥ ነፃነታችሁን አያስወግድም።

እግዚአብሔር ይቀጣችሁ ዘንድ ስህተት ስትሠሩ ለመያዝ የሚሞክር አይደለም።

ከዚያ ይልቅ፣ የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ቡድን አባል የሆኑት ሽማግሌ ፓትሪክ ኬረን እንዳስቀመጡት፣ “እግዚአብሔር ያለማቋረጥ ይፈልጋችኋል፣” ይህም ማለት ወደ እርሱ እንድትመለሱ ለመርዳት በመሞከር አይታክትም። ስህተት በምሠንሠራበት ጊዜ ሁላችንም በተፈጥሮ አስቸጋሪ ነገሮች እንደሚያጋጥሙን ያውቃል። ስለዚህ እርሱ ከኃጢአት የምንነጻበትን እና በልጁ የኃጢያት ክፍያ አማካኝነት ጥንካሬ የምናገኝበትን መንገድ አዘጋጅቷል።

እግዚአብሔር እናንተን ከመውደዱ በፊት “ብቁ” ወይም “ፍጹም” እንድትሆኑ የሚጠብቅ አይደለም።

ለእናንተ ያለው ፍቅር ወሰን የለውም። እርሱ ፍፁም ሳትሆኑ አሁኑኑ ይወዳችኋል! የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት፣ ፕሬዚዳንት ጄፍሪ አር. ሆላንድ ስለዚህ እውነት ሃይለኛ ማብራሪያ ሰጥተዋል፦ “‘አፍቃሪ አባት እያንዳንዳችንን ባላችሁበት ሁኔታ ኑ፣’፣ ነገር ግን አክሎም፣ ‘ባላችሁበት ሁኔታ ለመቆየት አታስቡ’ ይለናል። እግዚአብሔር ልንሆን እንችላለን ብለን ከምናስበው በላይ እንደምንሆን በማሰብ ቁርጠኛ መሆኑን ስናስታውስ ፈገግ እንላለን። የሰማይ አባት ፍፁም ፍቅር እና ማበረታቻ በመስጠት፣ በአንድ ጊዜ አንድ እርምጃ እየወሰዳችሁ እርሱን እንድትመስሉ እና ያለውን ሁሉ እንድትቀበሉ ሊረዳችሁ እየሞከረ ነው።

የእግዚአብሔር ማንነት

የሰማይ አባታችሁን ለማወቅ ከሁሉም የተሻለው መንገድ ከእርሱ ዘንድ ተሞክሮዎችን ማግኘት ነው። እንዴት? ስለእርሱ እና ስለልጁ ከቅዱሳት መጻህፍት እና በህይወት ካሉ ነቢያት ቃላት ተማሩ። ወደ እርሱ ጸልዩ። ትእዛዛቱን ጠብቁ። በቤተክርስቲያን፣ በቤተመቅደስ እና በሌሎች የተቀደሱ ቦታዎች በማምለክ ጸጥ ያለ የግል ጊዜ አሳልፉ። ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳኖችን ግቡ ከዚያም ጠብቋቸው። እርሱ ማን እንደሆነ እና ስለእናንተ የሚሰማውን ስሜት እንድታውቁ ይረዳችኋል።