“የህይወቶቻችን እውነት፣” ሊያሆና፣ ነሐሴ 2025 (እ.አ.አ)
ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ነሐሴ 2025 (እ.አ.አ)
የህይወቶቻችን እውነት
አፍቃሪ የሰማይ አባታችን ከስጦታዎች ሁሉ የላቀውን ስጦታ እንዴት መቀበል እንደሚቻልም ጨምሮ የቀደመውን፣ የአሁኑን እና የወደፊታችንን የተመለከቱ እውነቶችን ገልጧል።
ጥር 22፣ 1833(እ.አ.አ) በከርትላንድ ኦሃዮ በሚገኘው ከኑውል ኬ ዊትኒ መደብር በላይ ባለው ትንሽ የተጣበበ ክፍል ውስጥ የቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች ከነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ጋር ተሰበሰቡ። በቀደመው ዓመት በታህሳስ ወር፣ ጆሴፍ በዋናነት ወንድሞችን ለሚስዮን አገልግሎት ለማዘጋጀት ትምህርት ቤት ለማቋቋም የመራውን ራዕይ ተቀበለ።
ጌታ እንዲህ ሲል ተናግሯል “እናም የመንግስቱን ትምህርት እርስ በርስ ትማማሩም ዘንድ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።
“በትጋት አስተምሩ እናም፣ ጸጋዬ ከእናንተ ጋር ይሆናል፣ ይህም በፅንሰ ሀሳብ፣ በመሰረታዊ መርሆች፣ በትምህርት፣ በወንጌሉ ህግ፣ ከእግዚአብሔር መንግስት ጋር ግኑኝነት ባላቸው ሁሉም ነገሮች፣ ለእውቀታችሁ አስፈላጊ የሆኑትን ፈጽማችሁ እንድትማሩ ዘንድ…
“በተጠራችሁበት ጥሪ፣ እና በልዩ ሀላፊነት በሰጠኋችሁ ተልዕኮ፣ ጥሪዎቻችሁን እንድታጎሉ በምልካችሁ ጊዜ በሁሉም ነገሮች ትዘጋጁ ዘንድ ጸጋዬ ከእናንተ ጋር ይሆናል” (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 88፥77–78፣ 80)።
ይህ ቀድሞ “የነቢያት ትምህርት ቤት” ተብሎ የሚጠራው ድንቅ መንፈሳዊ ስጦታዎችን እና ልምዶችን ያቀርብ ነበር። ብዙ ቀደምት የቤተክርስቲያን መሪዎች እዚያ ተምረዋል። በዛሬው ጊዜ ዓለም ፍጹም የተለየች ቦታ ነች፣ ነገር ግን ጌታ በዚያን ጊዜ የሰጠው መመሪያ አሁንም በሚያስደንቅ ሁኔታ ይሰራል። እኛም “እውነት ነገሮች እንዳሉ፣ እንደነበሩ፣ እናም ወደፊት እንደሚሆኑት የሚታወቅበትን” እውቀት መሻት አለብን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥24)።
የእውነት ፍለጋችን
ይህ የምንኖርበት ዘመን ከማንኛውም ጊዜ በላይ ለእኛ ብዙ እውቀት ያለበት ነው። በቀደመው ጊዜ አንድ ነገር ለማወቅ ብትፈልጉ ወደ ቤተመጻሕፍት ሄዳችሁ መፈለግ ይኖርባችሁ ነበር። በዛሬው ጊዜ በይነመረብን እና በእጅ የሚያዙ መሳሪያዎችን በመጠቀም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መረጃዎች ወዲያውኑ ማግኘት እንችላለን።
ጌታ መረጃን በጥበብ ስንጠቀም ይደሰታል፤ ሆኖም ይህንን ጊዜ የማይሽረው ምክር ሰጥቶናል፦“ተግታችሁ ፈልጉ እና እርስ በርሳችሁም የጥበብ ቃላትን ተማማሩ፤ አዎን፣ ከተመረጡት መጽሀፍትም የጥበብን ቃላት ፈልጉ፤ እውቀትን፣ እንዲሁም በጥናትና ደግሞም በእምነት፣ እሹ”(ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥118)። በዙሪያችን ስላለው ዓለም እንድናውቅ ያበረታታናል ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥79; 93፥53 ይመልከቱ) ሆኖም እውነትን ስንፈልግ “ሁሉንም ነገሮች [የሚረዳውን]፣ እና ሁሉም ነገሮች በፊቱ [የሆኑትን]…በሁሉም ነገሮች ከዳር እስከ ዳር [የሆነውን] እና ሁሉም ነገሮች በእርሱ እና በርሱ በኩል [የሆነውን]” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88:41)እግዚአብሄርን መጠየቅ ይኖርብናል።
እግዚአብሔር ከሰጠን እውነቶች መካከል፣ በምድራዊ ህይወታችን ከሁሉም ይበልጥ መሠረት ከሆኑት እውነቶች አንዱ እርሱ የሰማይ አባታችን መሆኑ ነው። እኛ የእርሱ የተወደድን የመንፈስ ወንድና ሴት ልጆቹ ነን። እርሱ ያውቀናል እንዲሁም ፍጹም በሆነ ሁኔታ ይወደናል። የእግዚአብሔር የመንፈስ ልጆች እንደመሆናችን መለኮታዊ ተፈጥሮ እና መለኮታዊ ፍፃሜ አለን። እነዚህን ዘለአለማዊ እውነቶች መረዳታችን እና መቀበላችን በቅድመ ምድር ህይወታችን የባረከን እና የመራን እንዲሁም አሁን እና ለዘለአለም በሚቀጥል ማንነት፣ ዋጋ እና አላማ ይህንኑ ያደርጋል።
በመጀመሪያ ከአብ ጋር ነበርን
የነገሮችን እውነት “እንዳሉ፣” ስንፈልግ የሚከተለውን ቃል ከአዳኛችን እናገኛለን፦ “አሁንም፣ እውነት እላችኋለሁ በመጀመሪያም ከአብ ዘንድ ነበርኩኝ፣እና በኩርም ነኝ፤ እንዲሁም “ እናንተም አስቀድማችሁ ከአብ ጋር ነበራችሁ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93:21, 23)።
ከምድራዊ ህይወታችን በፊት፣ የሰማይ አባታችን ታላቁን የደስታ እቅዱን ባቀረበበት በሰማይ በተደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝተናል። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ፣ እግዚአብሔር እቅዱን ለማዘጋጀት ያነሳሳው “እንደ እርሱ እንድናድግ [እና] በዘለአለማዊ ህይወት ከእርሱ ጋር ከፍ ከፍ እንድንል ልዩ መብት” ሊሰጠን እንደሆነ አስተምሯል። ስራው እና ክብሩ “የሰውን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ሕይወት ማምጣት ነው”(ሙሴ 1፥39)።
የመምረጥ ነፃነታችንን ተጠቅመን የሰማይ አባትን እቅድ ለመከተል መረጥን። የመምረጥ ነፃነታችንን መጠቀም በምንቀጥልበት እና ሟችነትን በምንለማመድበት፣ በምንማርበት እና ወደ ዘላለማዊ ህይወት በምናድግበት በዚህ ህይወት ለመወለድ ተባርከናል።
በምድራዊ ጉዟችን ፈተናዎች እና እንቅፋቶች ያጋጥሙናል። ሆኖም የህይወትን መከራዎች ብቻችንን መጋፈጥ አይኖርብንም። ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ሲል አስተምሯል፣ “ታላቁ የአለም ወላጅ መላውን የሰው ቤተሰብ በአባታዊ እንክብካቤ እና ወላጃዊ ዕይታ ይመለከታል።”
የሰማይ አባታችን፣”የምህረት አባት፣ የመጽናናት ሁሉ አምላክ፣ እኛ በእግዚአብሄር በተጽናናንበት መጽናናት በችግር ያሉትን ሁሉ እናጽናና ዘንድ፣ በመከራችን ሁሉ ያጽናናን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እና አባት ይባረክ።”(2ኛ ቆሮንጦስ 1፥3-4)። የእቅዱ አስፈላጊ ክፍል በማድረግ፣ የሰማይ አባት ወደ እርሱ የምንመለስበትን መንገድ አዘጋጅቶልናል።
ወደ አባታችን የምንመለስበት መንገድ
“ነገሮች በርግጥ እንዳሉ”(ያዕቆብ 4፣13) እውነታው ግልፅ ነው፦የሰማይ አባታችን ልጆች በመሆናችን ብቻ ወደ ሙሉ አቅማችን መድረስ አንችልም። በመንፈስ የአብ የበኩር ልጅ የሆነው ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አዳኛችን እና ቤዛችን ሊሆን ቃል ኪዳን ገብቷል ።
ኢየሱስ ክርስቶስ “በጸጋ እና በእውነት፣ እንዲሁም የመጣ እና በስጋም የኖረ፣ እና በመካከላችን የኖረ፣ በእውነት መንፈስ የተሞላ፣ የአብ አንድያ ልጅ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥11).ነው። በዚህ እና በዘላለማዊ ህይወት ውስጥ ደስታን፣ ትርጉምን፣ እና ሃሴትን የምናገኝበትን መንገድ ሊያሳየን መጥቷል።
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል።
“ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።”(ዮሐንስ 3፥16–17)።
የአዳኙ ምድራዊ ተሞክሮ አስፈላጊ ነው። “ሙላትን በመጀመሪያ አልተቀበለም፣ ነገር ግን ሙላትን እስከሚቀበል ድረስ ከጸጋ ወደ ጸጋ ቀጠለ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥12)። “ሀይልን ሁሉ፣ በሰማይ እና በምድር ላይ [እስከሚቀበል]፣ እና የአብ ክብርም ከእርሱ ጋር [እስኪሆን]፣ በእርሱ ውስጥም [እስከሚሆን]” ድረስ ያድግ ነበር(ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥16–17)። አዳኙ እንዲህ አስተማረ፦
“እነዚህን አባባል የምሰጣችሁ እንድትረዱ እና እንዴት እንደምታመልኩ እንድታውቁ፣ እና ምን እንደምታመልኩ እንድታውቁ፣ በስሜ ወደ አብ እንድትመጡ፣ እና በጊዜም ሙላትን ትቀበሉ ዘንድ ነው።
“ትእዛዛቴን የምታከብሩ ከሆናችሁም ሙላቱን ትቀበላላችሁና፣ እና እኔ በአብ እንደሆንኩ እናንት በእኔ ትከብራላችሁ፤ ስለዚህ፣ እላችኋለሁ፣ በጸጋ ላይ ጸጋን ትቀበላላችሁ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥19–20)።
በጌተሴማኒ የአትክልት ስፍራ እና በመስቀል ላይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በእራሱ ላይ የአለምን ሃጢያት ወሰደ፣ሁሉንም ስቃይ እንዲሁም “በመከራ እናም በሁሉም አይነት ህመም እና ፈተናዎች” ተሰቃየ (አልማ 7፥11)። ይህ “ከስቃዩ የተነሳ እን[ዲ]ንቀጠቀጥ እናም ከእያንዳንዱ ቀዳዳ እን[ዲ]ደማ” አደረገው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፥18)። ደህንነት እና በዘላለማዊ ህይወት ከፍ ከፍ መደረግ የሚቻለውበኢየሱስ ክርስቶስ እና በኃጢያት ክፍያው እንዲሁም በትንሳኤው ብቻ ነው።
በአዳኙ ጸጋ እና የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት ሙላት እስክንቀበል እና አንድ ቀን ወደ ፍፁምነት እስክንደርስ ድረስ ማደግ እንችላለን። የአዳኙን ምሳሌ ከተከተልን እና ትዕዛዛቱን የምንጠብቅ ከሆነ ይመራናል እንዲሁም ወደ ሰማይ አባታችን የክብር መገኘት በምንጓዝበት መንገዳችን ላይ ይመራናል።
ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ እየተጓዘ፣ በማይክል ኮልማን፣ ቅጂ አይፈቀድም
የእርሱን ስጦታ ትቀበላላችሁን?
“ነገሮች በርግጥ እንደሚሆኑ” (ያዕቆብ 4፥13)፣ ከሚታዩት እውነቶች መካከል በዘለአለማዊ ህይወት የሚኖረን ተሞክሮ የሚወሰነው ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል እና የሚሰጠንን ስጦታዎች ለመቀበል በምናደርገው ምርጫ እንደሆነ እንማራለን። ቅዱሳት መፃህፍት “ለመቀበል ፍቃደኛ የሆነውን እንደምናጣጥም” ያስተምሩናል። በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንዶች “በተቀበሉት ለመደሰት ፈቃደኛ አይሆኑም”(ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥32)።
የሰባዎቹ አጠቃላይ ባለስልጣን በመሆን ያገለገሉት፣ የእኔ የሚሲዮን ፕሬዚዳንት፣ ሽማግሌ ማሪዮን ዲ.ሃንክስ (1921–2011(እ.አ.አ))፣ ለመቀበል ፍቃደኛ የሆንነውን መጠየቅ እና በዚያም መደሰት በመንፈሳዊ ጉዟችን ውስጥ የት ላይ እንደሆንን የምንወስንበት መንገድ እንደሆነ ለሚስዮናውያን አስተምረዋል። “ለሰው ስጦታ ቢሰጠው እና ስጦታውን ባይቀበለው ምን ይጠቅመዋል?” እርሱን በትጋት በመፈለግ እና በመከተል የአዳኙን ስጦታዎች ስንቀበል፣ በዘለአለም ህይወት ተስፋ እና “በስጦታ ሰጪውም ” እንደሰታለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥33)። ይህ በፍቅር የተሰጠ ስጦታ “ከእግዚአብሔር ስጦታዎች ሁሉ የበለጠ ነው” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 14፥7)።
እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን ነው። እርሱ ያውቀናል እንዲሁም ይወደናል። በእውነት ፍለጋችን ላይ ወደ እርሱ ስንመለስ፣ ከመረዳት ችሎታ ጋር እንጣበቃለን፣ ጥበብን እንቀበላለን፣ እውነትን እናቅፋለን፣ በጎነትን እናፈቅራለን፣እንዲሁም ከእርሱ በሚጣው ብርሃን እንታቀፋለን ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88:40ይመልከቱ)። ከዚያም “በእርሱ ውስጥ እና በእርሱ ህይወት ተሰጥቷችሁ እግዚአብሔርን የምትረዱበት ቀን [እስኪመጣ ድረስ]” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88:49) በመላው ህይወታችን እንቀጥላለን።
ያ ቀን እጅግ የከበረ እና አስደሳች ይሆናል።
© 2025 by Intellectual Reserve, Inc. መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ ታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፤ 6/19። Monthly Liahona Message, August 2025 ትርጉም።Amharic. 19613 506