“የውድ አዳኛችን ድል፣” ሊያሆና፣ ሚያዝያ 2026 (እ.አ.አ)
ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ሚያዝያ 2026 (እ.አ.አ)
የውድ አዳኛችን ድል
የኢየሱስ ክርስቶስን የከበረ ስጦታ ታላቅነት ለመግለጽ የሚችሉ ቃላት የሉም። ይህም እንደገና ከሌላ ሰው አይጠየቅም። "አንዴ ለሁሉ" ተሰቃየ።
ዓመታት ሲያልፉ፣ ስለ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማይለካ ስጦታ ስለሆነው የኃጢያት ክፍያው ባሰብኩ፣ ባጠናሁ እና ታላቅ መጽናናትን ባገኘሁ መጠን ይበልጥ ትሑት ሆኛለሁ። በጌቴሴማኒ፣ በመስቀል ላይ፣ እና በመቃብር በሆነው ነገር ምክንያት የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ምን ያህል ሙሉ በሙሉ እንደተለወጠ የሰው አእምሮ መገንዘብ ሊጀምር ፈጽሞ አይችልም።
ሁላችንም የልብ ስብራትን እና መከራን እናገኛለን።
በሐዋርያዊ ጥሪዬ፣ ብዙ ተጉዣለሁ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ያሉ ልጆችን፣ ወጣቶችንና አዋቂዎችን የመገናኘት ዕድል አግኝቻለሁ። በህይወት ውስጥ የታላቅ ደስታ ጊዜያት አሉ፤ ነገር ግን በገዛ ዓይኖቼ ያየሁትና በልቤ ጥልቀት የተሰማኝ አንድ ነገር ቢኖር፣ ህይወት ከደስታ እና ሀሴት በተጨማሪ የልብ ስብራትና የመከራ ጊዜያትም እንዳሉት ነው።
ልጆቹ ተኝተው ሳሉ በገዛ ቤታቸው ውስጥ ወላጆቻቸው በአሰቃቂ ሁኔታ በወራሪ ከተገደሉባቸው አራት ትንንሽ ልጆች ጋር መቀመጤን፣ ወይም በታመነ ዘመድ በልጅነቷ ከተበደለች ሴት ጋር መገናኘቴን፣ ወይም በብስክሌት ወድቃ ጭንቅላቷ ላይ ጉዳት ደርሶባት ለጥቂት ጊዜ ቆይታ ከምትሞት አንዲት ወጣት ልጅ አልጋ አጠገብ መቀመጤን፣ ወይም ባሏ ለብዙ ዓመታት የእርሷን ታማኝነት እና የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኑን በክፉ መንገድ የጣሰባትን ሴት ለቅሶ ማዳመጤን መቼም አልረሳውም።
የወንጌልን እውነት ማመኑን አቁሞ በቤተሰብ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎችን እምነት ለማዳከም የሚፈልግ አዋቂ ልጅ ያላቸው ባልና ሚስት የሚሰማቸው ሥቃይም ተሰምቶኛል። ተስፋ የሞላው የነበረና ቢሆንም የገዛ ህይወቱን ያጠፋ ወጣትን ልብ የተሰበረባቸው ወላጆችንና ጓደኞችን ጎብኝቻለሁ። ኃጢአት ሰርተውም በእውነት ንስሐ ለመግባት የሚፈልጉ ሰዎችን እንደ እግዚአብሔር አይነት ኀዘንን እንዲሁም በኃጢአቱ ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን መደቆስ ተመልክቻለሁ።
የአእምሮ ሕመም ለታካሚውም ሆነ ለመርዳት አቅም አጥተው በዝምታ ለሚሰቃዩ ተመልካቾች የሚያስከትለውን የልብ ስብራት አይቻለሁ። በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በጎርፍ፣ በማዕበል፣ በእሳት እና በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የደረሰውን ከፍተኛ የግል ኪሳራ ተመልክቻለሁ። በፖለቲካዊ ማዕበል፣ በጦርነትና በጥፋት በሀገራት ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ፣ እንዲሁም ንጹሐንና ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ በሚጥሩ ሰዎች ላይ ያልተጠበቀ ነገር ሲደርስ የሚሰማውን ሥቃይ አይቻለሁ።
የፈውስ እጆች፣ በኮልቢ ላርሰን፣ ግልባጭ መስራት አይፈቀድም
አዳኙ ይረዳናል
የቀድሞው ቀዳሚ አመራር ሁለተኛ አማካሪ የነበሩት ፕሬዚዳንት ጄምስ ኢ. ፋውስት [1920-2007 (እ.አ.አ)] ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የተጎዱት ፈተናዎቻቸውን ለማሸነፍ የቻሉትን ሁሉ ማድረግ አለባቸው፣ አዳኙም ‘ህዝቡን በድካሙ [ይረዳል]’ [ አልማ 7፥12]። ሸክማችንን እንድንሸከም ይረዳናል። አንዳንድ ጉዳቶች በጣም የሚያምሙና ጥልቅ በመሆናቸው ከበላይ ኃይል እርዳታ ውጪ እና በሚቀጥለው ህይወት ውስጥ ፍጹም ፍትህ እና ካሳ ይገኛል ካለሚል ተስፋ ሊፈወሱ አይችሉም። … እርሱ ሥቃያችንን ይረዳል እንዲሁም በጨለመው ጊዜአችንም እንኳ ከእኛ ጋር ይጓዛል።”
ወደ አዳኙ ፍቅር እና በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ቃል ወደ ተገቡልን መጨረሻ ወደሌላቸው በረከቶች ይበልጥ እየተሳብኩ እንደሆንኩኝ ይሰማኛል። ሊለካ የማይችል ሥቃይ ከሚያመጡ የህይወት አስቸጋሪ ተሞክሮዎች አልጋለለንም፣ ነገር ግን ከዘለአለማዊ ሥቃይና ከሰማይ አባት መለየት ጠብቆናል፤ እንዲሁም ሁሉንም በሚሸፍን ሥቃዩ በኩል በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም ደስታና የዘለአለም ሐሴት የማግኘት ዕድል ሰጥቶናል።
ፕሬዚዳንት ዳለን ኤች. ኦክስ እንዲህ በማለት አስታውሰውናል፦ “ከሁሉ በላይ፣ የእግዚአብሔር ጠንካራው የሟች እርዳታ፣ ዋጋውን ለመክፈል የሚሰቃይና ንስሐ ለገቡ ኃጢአቶች ይቅርታን የሚሰጥ አዳኝ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ማቅረቡ ነው። ያ መሀሪና ክቡር የኃጢያት ክፍያ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ለምን የወንጌል የመጀመሪያው መመሪያ እንደሆነ ያብራራል። የእርሱ ቤዛነት ‘የሙታን ትንሣኤን ያመጣል’ (አልማ 42፥23)፣ እና ‘ለዓለም ኃጢአት ክፍያን [ይከፍላል]’ (አልማ 34፥8)፣ ይህም ንስሐ የገባንባቸውን ኃጢአቶቻችንን ሁሉ ይደመስሣል እንዲሁም አዳኛችን በምድራዊ ድካማችን ውስጥ እንዲረዳን ኃይል ይሰጠዋል።”
ጸሎት በጌቴሴማኒ" የተወሰደ፣ በዴል ፓርሰን፣ ለቤተክርስቲያኗ አገልግሎት ብቻ ግልባጭ መስራት ይቻላል።
የዘለአለም ወሳኝ ክስተት
በምድር ላይ ከኖሩት ወይም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ የሆነውን እኔ በግል ያየሁትን ሥቃይ ሳስብ፣ ስለ ሁሉም የሰው ልጅ ኃጢአትና ሥቃይ በዚያ በቅዱስ የሥቃይ ሰዓት በአዳኙ ልብ፣ አእምሮ፣ አካልና ነፍስ ውስጥ ምን ተከስቶ መሆን እንዳለበት በምንም ዓይነት ቃላት ልገልጸው አልችልም።
የመላው የዘለአለም ወሳኝ ክስተት የጀመረው ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጭ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደሚገኘው "ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ" በሄደ ጊዜ ነው (ማቴዎስ 26፥36)። ደቀ መዛሙርቱን፦ "ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች" አላቸው (ማቴዎስ 26፥38)።
እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ “አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን” (ማቴዎስ 26፥39)። ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመለሰ፣ ተኝተውም አገኛቸው፣ እንደገናም ሄዶ ለሁለተኛ ጊዜ ጸለየ። “አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን። … ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ” (ማቴዎስ 26፥42፣ 44)።
ኢየሱስ መራራውን ጽዋ ጠጣ እንዲሁም በአትክልት ስፍራውም ሆነ በመስቀል ላይ ከሰው ልጅ ግንዛቤ በላይ በሆነ ሁኔታ ተሰቃየ። ያለ ምንም ኃጢአት፣ ወደ እርሱ ስንመጣና ንስሐ ስንገባ ኃጢአታችንና ሸክማችን ከእኛ ላይ እንዲነሳ ዘንድ፣ የሁላችንን ኃጢአት በራሱ ላይ ወሰደ (2 ቆሮንቶስ 5፥21 ተመልከቱ)።
የኢየሱስ ሥቃይ፣ ሞት እና የኃጢአት ክፍያ መሥዋዕትነት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ ነው። ኢየሱስ ከመወለዱ 700 ዓመታት በፊት በመናገር፣ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሯል፦ “እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” (ኢሳይያስ 53፥6)። ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑና ከኃጢአታቸው ንስሐ ለሚገቡ ሁሉ ህይወቱን “ለብዙዎች ቤዛ” (ማቴዎስ 20፥28፤ እንዲሁም 1 ጢሞቴዎስ 2፥6 ተመልከቱ) ይሆን ዘንድ እንደሚሰጥ፣ እናም ይህም “ለኃጢአት ይቅርታ” (ማቴዎስ 26፥28) እንዲያገኙ እንደሆነ ተናግሯል። ጴጥሮስ “በኃጢአ[ታችን] ምክንያት ሞቶአልና” (1 ጴጥሮስ 3፥18)፣ ይህን ያደረገውም በእርሱ ቁስል እኛ እንድንፈወስ (1 ጴጥሮስ 2፥24 ተመልከቱ) ነው። ወደ አባታችን ፊት እንድንመለስ ሌላ ማንም ሊያደርገው የማይችለውን አደረገ። እርሱ “ስለ መተላለፋችን ቆሰለ” (ኢሳይያስ 53፥5)።
በጌቴሴማኒ ከነበረው ሥቃይ በኋላ፣ አብሮት በሄደው ሰው በመከዳቱ፣ በዓመፀኛ ገዥዎች ፊት በመሳለቁ፣ አካሉ ላይ በመገረፉ በመጣው ሥቃይ፣ በጨካኝና ምሕረት በሌላቸው ወታደሮች የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ በመጫኑ (ዮሐንስ 18፥2–3፣ 12–14፤ ማርቆስ 15፥15–20 ተመልከቱ) እና ወደ ጎልጎታ ሲሄድ በተቀደደው የጀርባው ሥጋ ላይ በተጫነው ከባድ እንጨት (ዮሐንስ 19፥16–17 ተመልከቱ) ጭንቀቱ ቀጠሎ ነበር።
በመስቀል ላይ፣ በጌቴሴማኒ ተሰምቶት የነበረው ከፍተኛ ጭንቀት የትኛውም ሰው ሊቋቋመው በማይችል ሁኔታ ተመለሰ። የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ህይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ከአባቱ የተሰጠውን መለኮታዊ ተልእኮ ብቻውን ተወጣ። ወታደሮቹና ገዥዎቹ ይህን ከእርሱ ሊወስዱት አልቻሉም (ዮሐንስ 10፥18 ተመልከቱ)። በክብርና በትህትና፣ ኢየሱስ ራሱን አዘንብሎ፦ “ተፈጸመ” አለ (ዮሐንስ 19፥30)።
የምድራዊ ህይወቱ የመጨረሻ ቅጽበት ተጠናቀቀ። የእርሱን የከበረ ስጦታ ታላቅነት ለመግለጽ የሚችሉ ቃላት የሉም። ይህም እንደገና ከሌላ ሰው አይጠየቅም። ኢየሱስ ክርስቶስ “አንድ ጊዜ ፈጽሞ” ተሰቃይቷል (ዕብራውያን 10፥10)።
ተነስቷል !
መለኮታዊ ተልእኮውን በማጠናቀቅ፣ አሁን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከመቃብር ተነስቶ ወደማይሞት ህይወት የተሸጋገረ የመጀመሪያው ሆነ (1 ቆሮንቶስ 15፥21–23 ተመልከቱ)።
በመቃብሩ አጠገብ ለነበሩት ሴቶች መላእክቱ እንዲህ አሏቸው፦
“ህያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?
“ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም” (ሉቃስ 24፥5–6)።
ለሐዋርያቱ፦ “እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ” አላቸው (ሉቃስ 24፥39)። ከጊዜ በኋላም፣ “ከአምስት መቶ ለሚበዙ … በአንድ ጊዜ ታየ” (1 ቆሮንቶስ 15፥6)። የዓይን ምስክሮች ከሞት የተነሳውን አዳኝ አዩት። እርሱ አልሞተም ነበር። በህይወት ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለኖሩት ወይም ለሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የዘለአለም የሞት ባርነት ሰንሰለትን ሰበረ (1 ቆሮንቶስ 15፥22 ተመልከቱ)። ሁሉን አቀፍ ጠላታችንን ድል አደረገ፤ የሞት ጠላት ለዘለአለም ተሸነፈ።
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን [1924–2025 (እ.አ.አ)] እንዲህ ብለዋል፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእናንተን ኃጢአት፣ የእናንተን ሥቃይ፣ የእናንተን የልብ ስብራት እና የእናንተን ድካም በራሱ ላይ ወስዷል። ብቻችሁን መሸከም አያስፈልጋችሁም! ንስሐ ስትገቡ ይቅር ይላችኋል። በሚያስፈልጋችሁ ነገር ይባርካችኋል። የቆሰለች ነፍሳችሁን ይፈውሳል። ራሳችሁን ከእርሱ ጋር ስታቆራኙ፣ ሸክማችሁ ይቀልላችኋል። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ቃል ኪዳኖችን ከገባችሁና ካከበራችሁ፣ በህይወታችሁ ውስጥ ያሉ አስቸጋሪ ጊዜያት ጊዜያዊ መሆናቸውን ትረዳላችሁ። መከራችሁ ‘በክርስቶስ ደስታ [ይዋጣል]’ [አልማ 31፥38]።”
ከተሾሙት ሐዋርያቱ አንዱ እንደመሆኔ መጠን፣ እርሱ ህያው ስለመሆኑ እርግጠኛና የታመነ ምስክርነት የሰጡኝን መንፈሳዊና ግላዊ ቅጽበቶች አግኝቻለሁ። በዚህ የፋሲካ ወቅት፣ “አዳኝ ሆይ፣ ለእኔ ብለህ ደምህን እንዳፈሰስክና እንደሞትክ እንዳልረሳ” እያልን በደስታ ስንዘምር፣ እነኚህን ቃላት በአእምሮአችንና በልባችን ውስጥ በዝግታ ይኑሩ፦
© 2026 by Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. በዩ.ኤስ.ኤ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። Monthly Liahona Message, April 2026 ትርጉም። Amharic. 20038 506