“ዘላለማዊው ቃል ኪዳን፣“ ሊያሆና፣ የካቲት 2026 (እ.አ.አ)
ወርሃዊ የ ሊያሆና መልዕክት፣ የካቲት 2026 (እ.አ.አ)
አስደሳቹ የቃል ኪዳን መንገድ
የቤተሰብ አባላት በአብ እና በወልድ ፊት በአንድነት የመጣመራቸው አስደናቂነት እና ታላቅነት ለነፍሴ ከልክ ያለፈ ግርምትን እና ሃሴትን የሚያመጣልኝ እና በምስጋናም መንፈስ እንድሞላ የሚያደርገኝ ነው።
ሽማግሌ ፓትሪክ ኪረን እና ባለቤታቸው፣ ጄኒፈር
በ1848 (እ.አ.አ) እስራኤል እና ኤልሳቤጥ ሃቨን ባርሎው ናቩ፣ ኤሊኖስን ትተው ወደ ሶልት ሌክ ሸለቆ በሄዱበት ጊዜ፣ በትንሿ የናቩ የቀብር ስፍራ አንድን ህጻን ቀብረው ነበር የሄዱት። ጨቅላው ጄምስ ናትናኤል ባርሎው፣ የመጀመሪያ ልጃቸው፣ በ ግንቦት1841 (እ.አ.አ) ከተወለደ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነበር በሞት የተለየው።
ወደ ሶልት ሌክ ሸለቆ እንደተጓዙ፣ እስራኤል እና ኤልሳቤጥ በፍጹም ወደ ልጃቸው መቃብር ለማተኮር አልፈቀዱም። ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ እስራኤል በእንግሊዝ ለሚስዮን አገልግሎት እንደተጠራ፣ ወደ ምስራቅ እየተጓዘ በነበረበት ጊዜ በናቩ በኩል አልፏል። በኤልሳቤጥ ጥያቄ የልጃቸውን መቃብር ለማመልከት እናም አስከሬኑንም በከተማው በስተምስራቅ ወዳለው ዋና የመቃብር ስፍራ ለማዘዋወር ቆሟል።
ፍሬ አልባ ከነበረው የአንድ ቀን ፍለጋ በኋላ፣ እስራኤል ከአካባቢው ቤት ጠባቂ ዘንድ እርዳታን ፈልጓል። በቀጣዩ ቀን፣ የጄምስ ዘመድ ከነበረችው ከማሪያም አጠገብ መቃብሩን አግኝተውታል። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ሳጥኖቹ በስብሰው እና ተሰባብረው ነበር። እስራኤልም ለባለቤቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ‘’በመሆኑም እስከ መጪዎቹ ጊዜያቶች በዚያው ልተዋቸው እና ተመልሼ ልሄድ ወሰንኩኝ’’ ብሏል።
ድምጽ እንደሰማ ከመቃብሩ ብዙ ርቆ አልሄደም። ሁኔታውን በማስታወስ ይህንን ጽፏል፣ ‘’በደንብ የሚሰማ አልነበረም፣ ነገር ግን ልቋቋመው በማልችለው ሁኔታ ለአእምሮዬ ጉልህ ነበር፤ ‘አባዬ፣ እዚህ ጥለኸኝ አትሄድ።’’ ትንሽ ልጁን ለማንሳት በመወሰን፣ እስራኤል ወደ መቃብሩ ተመልሷል። “አስቀድሞ ያልተሰማኝ በጣም እንግዳ የሆነ ጸጥታ እና ሰላም ተሰምቶኛል።… በህይወቴ ካከናወንኳቸው ስራዎች እንደዚህ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቼ የሰራሁት አልነበረም፤ መናገር የምችለው ይህን ያህል ነው።’’
በመስከረም 2፣ 1853 (እ.አ.አ)፣ እስራኤል ባርሎው እና ቤት ጠባቂው የጄምስን እና የማሪያምን አስከሬን ናቩ ወደሚገኘው ዋና የመቃብር ስፍራ አዘዋውረውታል፣ በፍስራውም ‘’በመቃብሩ ራስጌ እና ግርጌ ላይ የድንጋይ’’ ምልክት በማድረግ ነበር።
እስራኤል በመቃብሩ አጠገብ እንደቆየ ለኤልሳቤጥ እንዲህ ሲል ነገራት፣ ‘’ከጄምስ ጋር በፊተኛው ትንሳኤ ማለዳ ለመነሳት ብቁ እሆን ዘንድ ራሴን እና የራሴ ያልኩትን በሙሉ በጌታ እጅ አሳልፎ የመስጠት ፍላጎት ተሰማኝ። ‘’
ቅዱስ ቃልኪዳኖችን ከማክበር ጋር ተጣምሮ እስራኤል ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ያለው መሰጠት—ከበረከቶች ሁሉ ታላቅ የሆነውን—ለእርሱ፣ ለዘሮቹ፣ እና ለትውልዱ ክርስቶስ የዘለአለምን ህይወት እንዲሰጣቸው አድርጓል።
ይህም በእያንዳንዳችን ላይ ተመሳሳይ ነው።
የጀሪ ጋርንስ ፎቶግራፍ፣ ምናልባት ለቤተክርስቲያን ጥቅም ብቻ እንዲውል ኮፒ የተደረገ
ቅዱስ የሆኑ ቃል ኪዳኖች
ከምናልመው ከምንም ነገር በላይ የሰማይ አባታችን እና ልጁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እያንዳንዳችንን ይወዱናል። ፍቅራቸው በጥምቀጥ እና በጌታ ቤት ውስጥ ለእኛ በቃልኪዳኑ አማካይነት ከቀረበልን የተስፋ በረከቶች ውጪ በየትኛውም ስፍራ ይበልጥ አልተገለጠልንም።
ፕሬዘዳንት ራሰል ኤም ኔልሰን እንዳስተማሩት (1924—2025 እ.አ.አ)፣ ‘’ከተገለጠው ሃይማኖት እጅግ አስፈላጊ አስተሳሰቦች አንዱ የተቀደሰ ቃልኪዳን ነው።’’ ‘’ህጋዊ በሆነ ቋንቋ፣ ቃልኪዳን በአጠቃላይ የሚያመለክተው ሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ አካላት የሚደረግ ስምምነት ነው። ነገር ግን ሃይማኖታዊ በሆነው አባባል፣ ቃልኪዳን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ የተቀደሰ ቃልኪዳን ነው።’’
የምናደርገው እና የምንጠብቀው እያንዳንዱ የተቀደሰ ቃልኪዳን ይባርከናል። የሰማይ አባት እና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ እንድንቀርብ ይፈልጋሉ። በእምነት እና በመረዳት እንድንማር እና እንድናድግ ሊረዱን ይፈልጋሉ። በሰማያዊ ሃይል ሊያላብሱን ይፈልጋሉ። እንደዚህ አይነት በረከቶች የማይጨበጡ በሚመስሉበት በዚህ ዓለም ፈውስን እና ሰላምን እንድናገኝ ይፈልጋሉ። በዚህ እና በሚመጣው ሕይወት ሃሴትን እንድንለማመድ ይፈልጋሉ። ከዚህ ፍጹም ከሆነ ፍቅር የሚመነጨውን ከእነርሱ ጋር በቃልኪዳን ውስጥ የሚያጣምረንን እድል ያቀርቡልናል። በየሳምንቱ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ወቅት ከእነዚያ ቃልኪዳኖች ጋር በቁርጠኝነት የምንሄድበትን በረከት እናገኛለን።
የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በላያችን ላይ የምንወስድበትን፣ እርሱን እና በሃጢያት ክፍያው ስጦታ አማካይነት ለእኛ የተገለጠውን የእርሱን ፍቅር--እርሱ ለእኛ እንደተሰቃየ፣ እንደደማ፣ እና እንደሞተ የምናስታውስበትን ቅዱስ ቁርባን በአመስጋኝነት መንፈስ እንቀበላለን። ቅዱስ ቁርባን በየሳምነቱ የእርሱን ትእዛዛት ለመጠበቅ፣ ቃልኪዳናችንን ለማደስ፣ እና አዲስ ቃልኪዳን ለማድረግ ፈቃደኝነታችንን በምናሳይበት እድልም እንዲሁ ይባርከናል። ( ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 20፥77፣ 79)።
ፕሬዘደንት ራስል ኤም.ኔልሰን “ብዙ ጊዜ ቅዱስ ቁርባን የምንካፈለው በጥምቀት ወቅት የገባነውን ቃል ኪዳን ለማደስ ነው ሲባል እሰማለሁ። ይህ እውነት ቢሆንም ከዚያ የበለጠ ነው’’ በማለት ተናግረዋል። ‘’እኔ አዲስ ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። እናንተም አዲስ ቃል ኪዳን ገብታችኋል።… በተራውም [ጌታ] ሁልጊዜ መንፈሱ ከእኛጋ እንደሚሆን ቃል የገባበትን ነግሮናል። እንዴት ያለ በረከት ነው!’’
በንጹህ ልብ ንሰሃ ስንገባ እና ቅዱስ ቁርባንን ስንወስድ፣ መንፈስ ቅዱስን እንቀበላለን እናም ‘’ልክ እንደገና የተጠመቅን ያህል ከኃጢያታችን እንነጻለን። ይህ ኢየሱስ ለእያንዳንዳችን የሰጠን ተስፋ እና ምህረት ነው።’’
በኢየሱስ የቤዛነት ፍቅር አማካይነት ንሰሃ መግባት እና ይቅርታን ማግኘት እንዴት ያለ ደስታ ነው!
የናቩ ኢለኖይ ቤተመቅደስ ፎቶ በጄኒፈር ሮዝ ማዲ
የእርሱ የደስታ ቤት
የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፕሬዘዳንት ከሆኑ በኋላ ፕሬዘዳንት ኔልሰን የቤተክርስቲያኑ የመጀመሪያ ፕሬዘደንት በመሆን ለህዝብ የመጀመሪያ መልእክታቸውን ሲጀምሩ፣ በአብዛኛው ስለቃልኪዳኑ መንገድ ተናግረዋል። ወደዚያም መንገድ የምንገባው ‘’በንሰሃ እና በውሃ ጥምቀት ነው’’ (2 ኔፊ 31፥17)፣ በሌላ አጋጣሚ ሲናገሩ፣ እንዲሁ ‘’ይበልጥ ወደዚያ የምንገባው በቤተመቅደስ ነው’’ ብለዋል።
ልክ ቅዱስ ቁርባን ቃልኪዳናችንን እና ተያይዘው የሚመጡትን በረከቶች እንደሚያስታውሰን፣ በመቅደስም የምናከናውነው የውክልና ስራም እንዲሁ ነው። ላለፉት ለእነዚያ የውክልና ስርዓትን ባከናወንን ጊዜ፣ ያደረግናቸውን ቅዱስ የተስፋ ቃሎች እና የምንቀበላቸውን ተስፋ የተደረጉልንን በረከቶች እናስታውሳለን።
በቃልኪዳኑ መንገድ አማካይነት፣ ለአብርሃም፣ ለይስሃቅ፣ እና ለያእቆብ እንዲሁም ለትውልዳቸው ቃል የተገቡትን በረከቶች ሁሉ ወራሾች እንሆናለን። ምንም እንኳ እነዚያ ቃል የተገቡ በረከቶች ቢኖሩም፣ እንደእኛው ሁሉ አብርሃም፣ ይስሃቅ፣ እና ያእቆብ ቀላል የሆነን ህይወት አልመሩም። ‘’በሁሉም ነገር በተፈተንን’’ ጊዜ እንደእነርሱ፣ ችግሮችን፣ ቅጣትን፣ እና ማጣትን እንጋፈጣለን (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 136፥31፤ በተጨማሪ 101፥4-5 ተመልከቱ)። ነገር ግን እንደጥንቶቹ ነቢያት እና ጻድቃን ቅዱሳን የታመንንበትን እናውቃለን ( 2 ኔፊ 4፥19ተመልከቱ)።
ምድራዊው ህይወታችን የአፈጣጠራችን ትንሹ ጊዜ ነው፣ ነገር ግን ያ ጊዜ--አንዳንዴ በጣም ከባድ ቢመስልም—ዘለዓለማዊ ጥቅም ያለው ነው። አዎን፣ የሰማይ አባታችን እንድንማር እና እንድናድግ ይፈልጋል። እና አዎን፣ ያ እድገት አንዳንድ ጊዜ ሃዘንን እና ስቃይን የሚፈጥር ይሆናል። ነገር ግን እርሱ ህይወታችን የተዋበ እና ተስፋ የተሞላበት እንዲሆን ይሻል። ለዚያም ሲባል፣ እና ዳግም ወደ እርሱ የሚያመራንን ጉዞ ሊያቀልልን ከአባቱ ጋር ለገባነው ቃልኪዳን ‘’ዋስ’’ የሚሆንልንን አዳኝ አዘጋጅቶልናል። በኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢያት ክፍያ አማካይነት፣ አብ በቤተመቅደስ ለልጆቹ የገባውን ቃልኪዳን ይፈጽማል።
በእርሱ ፍቅር እና የሃጢያት ክፍያ አማካይነት፣ አዳኛችን በህይወት ለሚያጋጥመን ሁሉ ዋጋ ከፍሏል እናም ፈውስንም አምጥቶልናል። እና በእርሱ የተቀደሰ ቤት ምክንያት--በእርሱ የሃሴት ቤት--መከራ ቢኖርም ሁሉ መልካም ይሆናል። ቃልኪዳንን ለመጠበቅ መድሃኒት በሆነው ቅባት አማካይነት ሃዘን፣ ህመም፣ ስቃይ፣ እና ብስጭት ይወገዳል። ልንጨነቅም ሆነ ልንፈራ አይገባም። ይልቁኑም፣ የቤዛነታችን ዋጋ የተከፈለ ( 1ኛ ቆሮንቶስ 6:20ተመልከቱ) እና ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት የሚመራው ጎዳና የተዘረጋ በመሆኑ ሃሴት ልናደርግ ይገባል።
የቃልኪዳኑ መንገድ በርግጥም የቤዛነት ፍቅር መንገድ ነው። በቤተመቅደስ የገባነውን ቃልኪዳን ባከበርን ጊዜ፣ ታላቅ የሆነ የሃይል፣ የታላቅ ፍቅር፣ የታላቅ ምህረት፣ የታላቅ መረዳት፣ እና የታላቅ ተስፋ በረከቶችን እንቀበላለን። የቤተሰብ አባላት በአብ እና በወልድ ፊት በአንድነት የመጣመራቸው አስደናቂነት እና ታላቅነት ለነፍሴ ከልክ ያለፈ ግርምትን እና ሃሴትን የሚያመጣልኝ እና በምስጋናም መንፈስ እንድሞላ የሚያደርገኝ ነው።
‘’በሕይወታችሁ ውስጥ ሁከት ሲከሰት፣ በመንፈስ በደህንነት ውስጥ ለመሆን የምትችሉበት ስፍራ ቢኖር በቤተመቅደስ ቃል ኪዳናችሁ ውስጥ መኖር ነው!’’ ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ ሲሉ መክረዋል። ከራሴ ጣፋጭ እና አንዳንድ ጊዜም መራራ ከሆነው የምድራዊ ህይወት ልምዴ የእነዚያን ቃላት እውነተኛነት አውቃለሁ።
ጨቅላው ጄምስ ናትናኤል ባርሎው፣ የእስራኤል እና የኤልሳቤጥ የመጀመሪያ ልጃቸው፣ በ ግንቦት1841 (እ.አ.አ) ከተወለደ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነበር በሞት የተለየው። ከዓመታት በኋላ፣ በሎጋን ዩታ ቤተመቅደስ ከወላጆቹ ጋር በውክልና ተጣምሯል።
ምስል በአለን ጋርንስ
ወደ ቤት ሰብስቧቸው
እስራኤል ባርሎው ህጻን ልጁን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሲሰናበተው፣ ለባለቤቱ እንዲህ ሲል ጽፏል፣ ‘’ ራሴን ሩቅ አድርጌ ማሰቤ፣ ወደ ጄምስ መቃብር ዳግም ከዚህ በኋላ በጭራሽ ያለመመለሴ፣ በእርሱ መቃብር ላይ ከእንባ ጋር እስኪበጠስ ድረስ የመጨረሻውን የፍቅር ክር አልጠመዘዘውም።’’
ብዙ እንባ--በዚህ ጊዜ የሃሴት እንባ-- በታህሳስ 4፣ 1889 (እ.አ.አ) ፈሷል። በዚያ ቀን፣ ጨቅላው ናትናኤል ባርሎ፣ በሎጋን ዩታ ቤተመቅደስ ከወላጆቹ ጋር ተጣምሯል። ያን ጊዜ፣ እስራኤል በሞት ተለይቷል፣ በመሆኑም ሌሎች ለእርሱ እና ለጄምስ ለውክልና ቆመው ነበር።
እህት ኬሮን እና እኔ ለእስራኤል እና ለኤልሳቤጥ ልዩ የሆነ ስሜት እና ርህራሄ አለን። የመጀመሪያ ልጃችን፣ ሲየን የተባለው ወንድ ልጅ፣ ገና የሶስት ወር እድሜ እያለ እየተደረገለት በነበረ የልብ ቀዶ ጥገና ምክንያት ህይወቱ አልፏል። ይህም ለእኛ ምድርን የሚበጠብጥ ሃዘን ነበር። በጊዜው፣ የመኖራችን ነገር አጠራጥሮን ነበር። በእንግሊዝ በነበረ በሚያሳዝን አንድ ትንሽ መቃብር ውስጥ ቀበርነው። ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ፣ ቤተሰባችን በዩናይትድ ኪንግደም ከነበርንበት በመዛወር የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን በቤተክርስቲያን እንንዲያገለግል ተጠራ እናም ያችን ትንሿን መቃብር ወደኋላ ትተን ሄድን።
በምእራቡ ጉዞ ልጃችንን አላጣንም፣ የእነባርሎው የማይታመን አሰቃቂ ፈተና አላጋጠመንም፣ ነገር ግን እነርሱ እያለፉ የነበሩበትን ለመረዳት ጀምረናል። የህጻኑ ልጃችን መቃብር እጅግ የራቀ ነው፣ ይሁን እንጂ እንደነባርሎው በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ እና በተቀደሰው የመጣመር ቃልኪዳን አማካይነት በቤተሰባችን ዘለዓለማዊነት ታላቅ እምነት አለን።
ሁላችንም ከመቃብር ባሻገር ሆነው ‘’እባክህ በዚህ አትተወኝ’’ የሚሉን ቅድመ አያቶች እና የምንወዳቸው አሉን። በቤተመቅደስ ቃልኪዳን ምክንያት ማንም ሰው ወደ ኋላ የሚቀር አይሆንም። የእኛ ጥሪ እነርሱን መውደድ፣ ማገልገል፣ እና ለማሰባሰብ መርዳት ነው።
የሰማይ አባታችን እናንተን እና እኔን ይወደናል። ‘’በምድር ያሰርነው በሰማይ የታሰረ ይሆን ዘንድ’’ ቤተመቅደሶችን ሰጥቶናል (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 128፥8፤ እንዲሁም ማቴዎስ 18፥18ተመልከቱ)። የሞትን ቀንበር ይሰብር፣ ለዘለዓለም ግንኙነት እና ለዘለዓለማዊው የቤተሰብ አንድነት መንገድን ይጠርግልን ዘንድ ልጁን ልኳል።
ለዚህም ነው ቅዱስ ስርአቶች ያሉን። ለዚህም ነው ቃልኪዳኖችን የምንገባው። ለዚህም ነው ቤተመቅደሶችን የምንገነባው። ለዚህም ነው ራሳችንን ለእግዚአብሄር ስራ እና ክብር የሰጠነው ( ሙሴ 1፥39ተመልከቱ)። እና ለዚህም ነው የደስታ እንባ የምናነባው፣ በአብ እና በወልድ ፊት ከምንወዳቸው ጋር ዘለዓለማዊ ጥምረት እንዳለን በማወቃችን ነው።
ቃልኪዳናችንን በጠበቅን እና ከጌታም ጋር በማዳን ስራው ስንተባበር ደስታ እና ሰላም እናገኝ ዘንድ እመኛለሁ።
© 2026 (እ.አ.አ) በ Intellectual Reserve, Inc. መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ ታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፤ 6/19። ወርሃዊ ሊያሆና መልዕክት፣ የካቲት 2026 (እ.አ.አ)ትርጉም። Amharic. 19933 506