“በእርሱ ስራ ውስጥ በመሳተፍ ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተላለን፣’’ ሊያሆና፣ ሰኔ 2025 (እ.አ.አ.)።
ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ሰኔ 2025 (እ.አ.አ)
በእርሱ ስራ ውስጥ በመሳተፍ ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተላለን
በእርሱ አላማ ላይ ባተኮርን ጊዜ፣ ትእዛዛቱን በጠበቅን ጊዜ፣ እና እርስ በርስ በተዋደድን ጊዜ በጌታ ስራ ላይ እንሳተፋለን።
ዝርዝር ከክርስቶስ እና ሀብታሙ ወጣት አለቃ፣ በሄንሪክ ሆፍማን
ስንጠመቅ የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ስም በራሳችን ላይ የመውሰድን ሂደት እንጀምራለን። የዚህ ሂደት ክፍል የሚያመለክተው ከጌታ ጋር በስራው ላይ እየተሳተፍን መሆኑን ነው። የቀዳሚ አመራር የመጀመሪያ አማካሪ ዳለን ኤች. ኦክስ እንደጻፉት፣ ‘’የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በላያችን ላይ የመውሰዱ መሰረታዊ ትርጉሞች አንደኛው የአዳኙን ስራ እና የእርሱን መንግስት በላያችን ለመውሰድ ያለን ፈቃደኛነት እና ቁርጠኝነት ነው።’’
የአዳኙ ስራ “የሰውን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት ማምጣት” ነው (ሙሴ1፥39)። ዘለአለማዊነት ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው አማካይነት ያረጋገጠው ቅድመ ሁኔታ የሌለው ስጦታ ነው። ይሁን እንጂ ዘለአለማዊ ህይወት፣ እና የሰው ህያውነት አንድ አይነት አይደሉም። ዘለአለማዊ ህይወት እግዚአብሔር ለሰው ዘር ሊሰጥ የሚችለው ከሁሉም የላቀው ስጦታ ነው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 14፥7ን ይመልከቱ)። ይህም እርሱ ባለበት እንደቤተሰብ ለዘለአለም መኖር ነው። የዘለአለምን ሕይወት ለማግኘት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ደቀመዝሙር መሆን አለብን። ይህም ማለት በአዳኙ እና በኃጢያት ክፍያው በማመን ዳግም የተመለሰውን ወንጌል መቀበል፣ ንስሀ መግባት፣ መጠመቅ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን መቀበል፣ የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን መግባት እና መጠበቅ፣ እንዲሁም እስከመጨረሻው መፅናት ነው። እስከ መጨረሻው መጽናትም በጌታ ስራ ውስጥ መሳተፍን ያካትታል።
በጉጉት መሳተፍ
የእግዚአብሔርን ልጆች እንዲሁ ታማኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዝሙር እንዲሆኑ በረዳን ጊዜ በጌታ ስራ ውስጥ እንሳተፋለን። ይህም የሚያካትተው የእርሱን ወንጌል ማካፈል፣ በዚያም የተበተኑትን እስራኤል ማሰባሰብ፣በአዳኙ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሃላፊነትን በመወጣት እና እርሱን ለመምሰል በመጣር ነው። እኛ ‘’[በእርሱ ስራ] ያለን ስኬት ሌሎች ለእኛ ግብዣ ወይም [ለእኛ] ልባዊ የደግነት ስራ ምላሽ ለመስጠት በሚመርጡበት መንገድ የሚወሰን አይደለም።’’ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳረጋግጡት፣ “ለማንኛውንም ሰው —በመጋረጃው በሁለቱም በኩል—የሚረዳ ማንኛውንም ነገር ባደረጋችሁ በማንኛውም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት እና አስፈላጊ የሆነውን የጥምቀት እና የቤተመቅደስ ስነስርዓቶችን ይቀበል ዘንድ ለማገዝ እርምጃ ስትወስዱ፣ እስራኤልን ለመሰብሰብ እየረዳችሁ ነው።’’
የአዳኙን ስራ የራሳችን ስራ ለማድረግ፣ በእርሱ አላማ ላይ እናተኩራለን፣ የእርሱን ትእዛዛት እናከብራለን፣ እና እርስ በርሳችን እንዋደዳለን። በእርሱ መንገድ ስራውን በሰራን ጊዜ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 51፥2 ተመልከቱ)፣ አንዳንድ ነገሮችን በራሳችን ለማድረግ ለእኛው የተተዉ ናቸው። በጃክሰን ካውንቲ፣ በምዙሪ ለተሰበሰቡ ቅዱሳን ጌታ እንዳለው፦
‘’እነሆ፣ በሁሉም ጉዳዮች ትእዛዝ መስጠቴ ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም በሁሉም ነገር መገደድ ያለበት እርሱም ሰነፍ ነው እናም ብልህ አገልጋይ አይደለም፤ ስለዚህ ምንም ዋጋን አይቀበልም።
‘’እውነት እላችኋለሁ፣ ሰዎች መልካም ስራን በጉጉት ማከናወን፣ እናም ብዙ ነገሮችን በራሳቸው ነጻ ምርጫ ማድረግ፣ እናም ብዙ ጽድቅንም መስራት አለባቸው፤
‘’ሀይል በእነርሱ ውስጥ ነውና፣ በዚህም ራሳቸውን ይወክላሉ። እናም ሰዎች መልካም ስራን ከሰሩ ዋጋቸውን አያጡም” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፥26–28)።
ጌታን ስንከተል፣ በስራውም ስንሳተፍ፣ እና ሌሎች የእርሱ ታማኝ ደቀመዛሙርት እንዲሆኑ ስንረዳ፣ እርሱ የሚያስተምረውን እናስተምራለን። ሌላ ምንም አይነት ነገር ለማተማር ስልጣን ስላልተሰጠን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥9፣ 36ተመልከቱ)፣ በማያወላውል ሁኔታ በእርሱ ትምህርት ላይ እናተኩራለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 68፥25ን ተመልከቱ)። በተጨማሪም፣ ድሆች፣ እርዳታ የሚፈልጉ፣ እና አቅመ ደካማ ለሆኑት ልዩ ትኩረት እንሰጣለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥40 ተመልከቱ)። እነዚህ ስረ ነገሮች ጌታ በናዝሬት በምኩራብ ውስጥ ከኢሳያስ ላይ በጠቀሰው ግልጽ ሆኗል፦
“የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ
‘’የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል’’ (ሉቃስ 4፥18–19፤ እንዲሁምኢሳይያስ 61፥1–2 ይመልከቱ)።
የተወደደችው የጌታ አመት የሚያመለክተው የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ በረከቶች ሁሉ በህዝቡ ላይ የሚያርፉበትን ጊዜ ነው። ሌሎች ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳኖች በመግባት እና በማክበር በረከቶችን እንዲቀበሉ እና ድሆች የሆኑትን ወይም እርዳታ የሚፈልጉትን በመንከባከብ ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተላለን።
ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በስራው መሳተፍ የሚያነቃቃ ነው ምክንያቱም የእርሱ ስራዎች፣ ጥበብ፣ እና ዓላማ ‘’ሊከሸፍም ሆነ ከንቱ ሊሆን አይችልም” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 3፥1)። ለእነዚያ ተስፋ ለቆረጡት፣ ጌታ እንዲህ መክሯል፦ ‘’መልካም ሥራን ትሰሩ ዘንድ አትታክቱ፣ የታላቅ ስራን መሰረት እየገነባችሁ ነውና። እናም ከትንንሾቹ ነገሮች ታላቅ ነገሮች ይወጣሉና” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 64፥33)። ጌታ ስለመከሩ እንዲጨነቅ እናደርጋለን፣ እና በቀላሉ የራሳችንን ድርሻ እናደርጋለን።
ልብ እና መልካም ፈቃድ ያለው አዕምሮ
የእኛ ድርሻ ማድረግ ከምናስበው በላይ የቀለለ ነው ምክንያቱም ለጌታ ስራ የተለየ ስጦታን ወይም ችሎታን ማቅረብ አያስፈልገንም። የእርሱ መመዘኛ በቀላሉ ቁርጠኝነት እና ፈቃደኝነት ነው። በከርትላንድ፣ ኦሃዮ ላሉት ቅዱሳን ጌታ እንዲህ ብሏል፣ ”እነሆ፣ ጌታ ልብን እና መልካም ፈቃድ ያለውን አእምሮ ይሻል’’ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 64፥34)፡፡ እግዚአብሔር ፍቃደኛ የሆኑትን ብቁ ያደርጋቸዋል፣ ነገር ግን ችሎታ ያላቸውን ፍቃደኛ ማድረግ አይችልም ወይም አያደርግም። በሌላ አነጋገር፣ እኛ ቁርጠኞች እና ፈቃደኞች ከሆንን፣ እርሱ ሊጠቀምብን ይችላል። ነገር ግን የቱንም ያህል ስጦታ ቢኖረን፣ እርሱን ለመርዳት ለእርሱ ስራ ቁርጠኛ እስካልሆንን እና ፈቃደኛ እስካልሆንን ድረስ ሊጠቀምብን አይችልም።
ሳሙኤል እና አና-ማሪያ ኮይቪስቶ ቁርጠኝነትን እና ፈቃደኝነትን ሁለቱንም አሳይተዋል። ከጋብቻቸው ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ኮይቪስቶስ ከጃይቫስኪያ፣ ፊንላንድ፣ ወደ ጎቴቦርግ፣ ስዊድን የስራ እድሎቻቸውን ለማካሄድ ተዛወሩ። ከደረሱም በኋላ፣ ወንድም ኮይቪስቶ፣ በጎተቦርግ ስዊድን የካስማ አመራር ውስጥ አማካሪ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ሌይፍ ጂ. ማትሰንን እንዲጎበኝ ተጋበዘ። ሳሙኤል ስዊድንኛ ባለመናገሩ፣ ቃለመጠይቁ በእንግሊዝኛ ተከናወነ።
ከጥቂት ጊዜ ጉብኝት በኋላ፣ ፕሬዚዳንት ማትሰን በኡትቢ አጥቢያ ውስጥ የአጥቢያ የሚስዮን መሪ እንዲሆን ሳሙኤልን ጠየቁ። ሳሙኤል ግልጽ የሆነን ነገር ጠቆመ፦ ‘’ነገር ግን እኔ ስዊድኛ አልናገርም።’’
ፕሬዚዳንት ማትሰን በዴስኩ ላይ ደገፍ በማለት እና በመጠቆም እንዲህ ጠየቁት፣ ‘’የጠየቅሁት ስዊድኛ መናገር እንደምትችል ነው ወይስ ጌታን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆንህን ነው?’’
ሳሙኤልም እንዲህ መለሰ፣ ‘’የጠየቁኝ ጌታን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኔን ነው። እና እኔም ፈቃደኛ ነኝ።’’
ሳሙኤል ጥሪውን ተቀበለ። አና-ማሪያም እንዲሁ ጥሪዎችን ተቀበለች። ሁለቱም በታማኝነት አገለገሉ እና እግረመንገዳቸውንም ስዊድንኛ መናገርን ተማሩ።
ጌታን የማገልገል ቁርጠኝነት እና ፈቃደኝነት የሳሙኤልን እና የአና–ማሪያን ህይወት ለውጧል። እነርሱ በቤተክርስቲያኗ የተለመዱ ጀግኖች ነበሩ። በተጠየቁ በማንኛውም ጊዜ በታማኝነት አገልግለዋል። ባገለገልን ጊዜ ያለንን ስጦታ እንደምንጠቀም አስተምረውኛል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 60፥13ን ይመልከቱ)፣ እና ከዚያም ጌታ አላማውን እንድንፈጽም ይረዳናል።
እኛ ለማገልገል ፈቃደኛ ስንሆን፣ ቅር ለመሰኘትም ሆነ ለማጉረምረም አንጥርም፣ ምክንያቱም በየትኛውም መንገድ አገልግሎታችንን ማቋረጥ ስለማንፈልግ ነው። ማጉረምረም የወላዋይነት ምልክት ነው፣ ወይም ለጌታ ያለን ፍቅር መሆን ያለበትን ያህል አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ሳይታይ የሚተው ከሆነ፣ ማጉረምረም በጌታ ላይ የሚደረግን አመጽ የሚያፋጥን ሊሆን ይችላል። ይህ ፍጥነት በምዙሪ ሚስዮናዊ እንዲሆን በተጠራው በኦሃዮ በቀደምትነት ወደ ቤተክርስቲያን በተለወጠው በእዝራ ቡት ህይወት ውስጥ ታይቷል።
በሰኔ 1831 (እ.አ.አ) ኦሃዮን እንደለቀቀ፣ እርሱ በበጋው ሙቀት፣ በእርግር እየተጓዘ በመንገዱ እየሰበከ በነበረበት ጊዜ አንዳንድ ሚስዮናውያን በጋሪ መሄድ በመቻላቸው ተበሳጭቶ ነበር። እርሱ አጉረመረመ። በምዙሪ እንደደረሰም፣ ዝቅ የተደረገ መስሎ ታየው። ምዙሪ እርሱ እንደጠበቀው አልነበረም። ይልቁኑም፣ ዙሪያውን ተመለከተ እና ‘’የተጠበቀው ጭጋጋማ መስሎ እንደነበር’’ አስተዋለ።
እዝራ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠራጣሪ፣ የሚያስመስል፣ እና አሳሳቢ ሆነ። ምዙሪን ትቶ በሄደ ጊዜ፣ እንደተጠየቀ ሄዶ በመስበክ ፈንታ፣ በቻለው ፍጥነት ወደ ኦሃዮ ተመለሰ። ቀድሞ የተጀመረው ማጉረምረም ወደ መወላወል እና በመጨረሻም አስቀድሞ በነበረውን መንፈሳዊ ልምምድ የራስ መተማመኑን እስከሚያጣ ተቀይሯል። ወዲያውኑም እዝራ ቤተክርስቲያኗን ትቶ ሄደ እንዲሁም ‘’ክርስትናን ተወ እና በእግዚአብሔር የማያምን ሆነ።’’
እኛም ካልተጠነቀቅን ተመሳሳይ ነገር ሊከሰትብን ይችላል። ዘለአለማዊ አመለካከትን መያዝ ካልቻልን፣ ይህ ስራ የማን እንደሆነ ራሳችንን ማስታወስ ካልቻልን፣ ልናጉረመርም፣ ልንወላውል፣ እናም በስተመጨረሻም ያለንን እምነት ልናጣ እንችላለን።
በእርሱ ስራ ውስጥ በመሳተፍ ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል እንድንችል እጸልያለሁ። ይህንን ስናደርግ “የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ” ይሰጠናል (2 ጴጥሮስ 1፥4)። እነዚህ በረከቶች የሃጢያት ይቅርታን ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 60፥7 ፤ 61፥2፣ 34፤ 62፥3፤ 64፥3 ተመልከቱ)፣ ደህንነትን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 6፥13፤ 56፥2 ተመልከቱ)፣ እና ከፍ ከፍ ማለትን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፥3–11፤ 59፥23 ተመልከቱ) ያካትታሉ። በእርግጥም፣ እግዚአብሔር ሊሰጥ የሚችለውን ታላቅ ስጦታ– የዘለአለማዊ ህይወት ቃል ተገብቶልናል።
© 2025 by Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። የMonthly Liahona Message, June 2025 ትርጉም።Amharic. 19610 506