ኢየሱስ ክርስቶስ “የሕያው፣” “የመልካም” እና “የላቀ ተስፋ” ምንጭ ነው ሊያሆና፣ ታህሳስ 2024 (እ.አ.አ)።
ወርሀዊ የ ሊያሆና መልዕክት፣ ታህሳስ 2024 (እ.አ.አ)
ኢየሱስ ክርስቶስ “የሕያው፣” “የመልካም” እና “የላቀ ተስፋ” ምንጭ ነው።
በቤተልሔም የተወለደውን ሕፃን ልደት በሚከበርበት በዚህ ልዩ ወቅት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችን ሊሆን ወደ ዓለም እንደመጣ ሁልጊዜ እናስታውስ።
The Nativity (ውልደቱ) በሻርሎት አንድሩስ
ሐዋሪያው ጴጥሮስ እና የመፅሐፈ ሞርሞን ነብያት ያዕቆብ እና ሞሮኒ በክርስቶስ ያለውን የተስፋን ስጦታ፣ መመሪያ ሰጪ በሆኑ ተመሳሳይ መንገዶች አፅንዖትን ይሰጣሉ።
ለምሳሌ፦ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።” (1 ጴጥሮስ 1፥3፣ አጽንዖት ተጨምሯል)። እባካችሁ “ሕያው” የሚለውን ቃል “ተስፋ”ን ለመግለጽ መጠቀሙን ልብ ይበሉ።
ያዕቆብም እንዲህ ሲል ተናገረ፡- “ስለሆነም፣ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናም በክርስቶስ ባለው የትንሳኤ ኃይል መሰረት፣ ትንሳኤን ታገኙ ዘንድ፣ እናም እምነት በማግኘትና እራሱን በስጋ ከመግለጡ በፊት መልካም የሆነውን የክብሩን ተስፋ በማግኘት ለእግዚአብሔር የክርስቶስ የመጀመሪያው ፍሬ ሆናችሁ ትቀርቡ ዘንድ በአንድያ ልጁ፣ በክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ከእርሱ ታረቁ።” (ያዕቆብ 4፡11፣ አጽንዖት ተጨምሯል)። እባካችሁ “መልካም” የሚለውን ቃል “ተስፋ”ን ለመግለጽ መጠቀሙን ልብ ይበሉ።
ሞሮኒም እንዲህ አለ፡-“እናም ደግሞ ለሰዎች ቤት፣ አዎን፣ በአባትህም ቤት እንኳን ማዘጋጀትህን መናገርህን አስታውሳለሁ፤ በዚህም ሰው የላቀ ተስፋ፣ ይኖረው ዘንድ ነው፤ ስለሆነም ሰው ተስፋ ማድረግ ይገባዋል፣ አለበለዚያ አንተ ያዘጋጀኸውን ሥፍራ በውርስ ሊቀበል አይችልም።” (ኤተር 12፥3፣ አጽንዖት ተጨምሯል)። እባካችሁ “የላቀ” የሚለውን ቃል “ተስፋ”ን ለመግለጽ መጠቀሙን ልብ በሉ።
በክርስቶስ ያለው ተስፋ ምንድን ነው?
በክርስቶስ ያለው መንፈሳዊ የተስፋ ስጦታ “በቅዱስ መሲህ ብቃት፣ ምሕረት እና ጸጋ” በኩል የሚገኝ የዘላለም ሕይወት አስደሳች የሆነ መጠባበቅ (2 ኔፊ 2፥8) እና ለተስፋው የጽድቅ በረከቶች ጠንካራ ፍላጎት ነው። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ፣ “ሕያው”፣ “መልካም” እና “የላቀ” የሚሉት ቅፅሎች የሚጠቁሙት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለ እምነት በኩል እየተስፋፋ ስላለው የትንሣኤ እና የዘላለም ሕይወት ንቁ የሆነ ማረጋገጫን ነው።
ነብዩ ሞርሞን እንደገለጸው፦
“እናም የተወደዳችሁ ወንድሞቼ በድጋሚ ተስፋን በተመለከተ እናገራችኋለሁ። ተስፋ ከሌላችሁ እምነትን እንዴት ለማግኘት ይቻላችኋል?
“እናም ተስፋ የምታደርጉት ምንድን ነው? እነሆ በክርስቶስ የኃጢአት ክፍያ እናም በትንሳኤው ኃይል ለዘለዓለም ህይወት እንዲኖራችሁ ተስፋ ይኑራችሁ እላችኋለሁ፤ እናም ይህም በእርሱ ባላችሁ እምነት ለእናንተ በገባላችሁ ቃል ኪዳን መሰረት ነው።
“ስለሆነም፣ አንድ ሰው እምነት ካለው ተስፋ ሊኖረው ይገባል፤ ያለ እምነት ምንም ዓይነት ተስፋ ሊኖር አይችልምና።” (ሞሮኒ 7፥40–42)።
የአብ የደስታ እቅድ
ሕያው፣ መልካም እና የላቀ ተስፋን በክርስቶስ ላይ ማድረግ የሚጀምረው እግዚአብሔር የዘላለም አባት እንደሚኖር በማወቅ ነው። እርሱ አባታችን ነው እኛም የመንፈስ ልጆቹ ነን። እኛ በትክክል የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ወንድ እና ሴት ልጆች ነን እንዲሁም ከእርሱ መለኮታዊ ባህሪያትን ወርሰናል።
አብ የደስታ እቅዱ ደራሲ ነው ( አብርሃም 3፥22-28ይመልከቱ)። እንደ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ወንድ ልጆች እና ሴት ልጆች፣ “ልጆቹ ሥጋዊ አካል የሚያገኙበትን እና ወደ ፍጽምና ምድራዊ ልምድን የሚያገኙበትን እና በመጨረሻም የዘላለም ሕይወት ወራሾች መሆን እንዲችሉ መለኮታዊ እጣ ፈንታቸውን የሚያገኙበትን እቅዱን ተቀበልን። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ፣ የሚከተለውን እንማራለን፡- “አብ እንደ ሰው የሚዳሰስ ሥጋና የአጥንት አካል እዳለው፣ ወልድም እንዲሁ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 130፡22)። ስለዚህ፣ በመለኮታዊ እጣ ፋንታችን ሂደት ላይ ሳለን ስጋዊዊ አካልን ማግኘት አስፈላጊ ነው።
እኛ መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ፍጡራን ነን። መንፈሳችን፣ የእኛ ዘላለማዊ የሆነው ክፍል፣ ለምድራዊ ህይወት ፍላጎቶች ተገዚ በሆነው ሥጋዊ አካል ተሸፍኗል። የአብ የደስታ እቅድ፣ ልጆቹትንሳኤን ባደረጉ እና ከፍ ከፍ የተደረጉ (አክሊልልን የተላበሱ) አካላትን ይዘው በደህና ወደ ቤቱ እንዲመለሱ ለመርዳት እና ዘላለማዊ ሐሴትን እና ደስታ በረከቶች እንዲያገኙ ለመርዳት መመሪያን እንዲሰጥ የተዘጋጀ እቅድ ነው።
The Christ Child [ሕጻኑ ክርስቶስ ]፤ በሻርሎት አንድረስ
በአብ እቅድ ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሚና
ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም አባት አንድያ ልጅ ነው። ወደ ዓለም የመጣው የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ነው ( 3 ኔፊ 27፥13ይመልከቱ)። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን በሚሆኑ ነገሮች ሁሉ የግል ተወካይ እንዲሆን በአብ የተቀባ ነው። እርሱ አዳኛችን እና ቤዛችን ነው ምክንያቱም ሞት እና ኃጢአትን አሸንፏል።
አልማ ስለ መሲሑ የማዳን ሥራ ለጌዴዎን ሰዎች ተነበየ፡-
“እናም በመከራና በሁሉም ዓይነት ህመምና ፈተናዎች በመሰቃየት ይሄዳል፤ የህዝቡን ህመምና በሽታ በራሱ ላይ ይወስዳል የሚለውን ቃል ይፈፀም ዘንድ ይህ ይሆናል።
“እናም ህዝቡን ያሰረውን የሞት እስር ይፈታ ዘንድ ሞትን በራሱ ላይ ይወስዳል፣ እናም በስጋ አንጀቱ በምህረት ይሞላ ዘንድ፣ በስጋ ህዝቡን ከድካማቸው እንዴት እንደሚረዳ ያውቅ ዘንድ ድካማቸውን በራሱ ላይ ያደርጋል።
“እንግዲህ መንፈስ ሁሉን ነገር ያውቃል፤ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ ሰዎችን በማዳን ኃይሉ መተላለፋቸውን ይሰርይላቸው ዘንድ የህዝቡንም ኃጢያት በራሱ ላይ ያደርግ ዘንድ በስጋው ይሰቃያል፤ እናም አሁን እነሆ በእኔ ያለው ምስክርነት ይህ ነው።”(አልማ 7፥11–13)።
ከወንጌል መሰረታዊ መርሆች መካከል የመጀመሪያው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው። እውነተኛ እምነት በአዳኝ ላይ ያተኩራል እናም በእርሱ እንድንታመን እና ከሞት ሊያድነን በኃይሉ ሙሉ እምነት እንዲኖረን፣ ከኃጢአት ሊያነጻን እና ከራሳችን በላይ በሆነ ኃይል እንዲባርከን ያስችለናል።
ሞሮኒ እንዲ ሲል መስክሯል፣ “እናም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለሰዎች ቤዛነት በመምጣቱ፣ ወደ ጌታም ፊት ተመልሰዋል፤ አዎን፣ ሁሉም ሰዎች የዳኑበት በዚህም ነው፥ የክርስቶስ ሞት ትንሣኤን አመጣ፣ ይህም መጨረሻ ከሌለው እንቅልፍ ቤዛነት አመጣ፣ መለከቱ ሲነፋ ሰዎች ሁሉ ከዚህ እንቅልፍ በእግዚአብሔር ኃይል ይነቃሉ፣ እናም ትልልቆችም ሆኑ ትንንሾች የሆኑት ይመጣሉ፣ እናም ዘላለማዊ ከሆነው የሞት ሰንሰለት በመዳንና በመፈታት፣ ይህም ሞት ጊዜአዊው ሞት ነው፣ በፍርዱ ወንበር ፊት ሁሉም ይቆማሉ።” (ሞርሞን 9፥13)
አዳኝ የሞትን እስራት እንደሰበረ እመሰክራለሁ። ከሞት ተነስቷል፣ ይኖራል፣ እናም ብቸኛው የሕያው፣ መልካም እና የላቀ የተስፋ ምንጭ ነው።
ለነፍስ መልህቅ (አጥብቆ መያዣ)
ነቢዩ ኤተር እንዲህ ሲል መስክሯል፣ “ስለሆነም፣ በእግዚአብሔር የሚያምን በእርግጥ ለተሻለ ዓለም፣ አዎን፣ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ በኩል ያለውን ስፍራ እንኳ ለማግኘት ተስፋ ይኖረዋል፤ ይኸውም ተስፋ በእምነት የሚመጣ ነው፤ ተስፋም ለሰዎች ነፍስ እንደ መልሕቅ ነው፤ እነርሱንም ፅኑ እና የማይነቃነቁ እንዲሆኑ እናም ሁልጊዜም በርካታ መልካም ነገሮችን እንዲሰሩ፤ እግዚአብሔርንም እንዲያከብሩ ያደርጋቸዋል።” (ኤተር 12፥4; አጽንዖት ተጨምሯል)።
በቤተልሔም የተወለደውን ሕፃን ልደት በሚከበርበት በዚህ ልዩ ወቅት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችን ሊሆን ወደ ዓለም እንደ መጣ ሁልጊዜ እናስታውስ። በዋጋ የማይተመን የህይወት፣ የብርሃን፣ የመታደስ፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአመለካከት፣ የደስታ እና የተስፋ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይሰጠናል።
የጥንት እና በአሁን ጊዜ ያሉ ነቢያት ስለእርሱ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት እና ስለ ትንሳኤው ያስተማሩትን ትምህርት እና ምስክርነት በማጥናት በአዳኝ ላይ ያለውን የተስፋ መንፈሳዊ ስጦታ በአግባቡ እንድትፈልጉ እጋብዛችኋለሁ። ይህን ስታደርጉ፣ ስለ ቤዛው መለኮታዊነትነት ያላችሁ ምስክርነት እንደሚጠናከር ቃል እገባለሁ፣ ወደ እርሱ መለወጣችሁ ይበልጥ ይጠናከራል፣ ስለ እርሱ ስትሉ በጀግንነት ምስክር ሆናችሁለመቆም ያላችሁ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ይጨምራል እንዲሁም ለነፍሳችሁ መልህቅ (አጥብቆ መያዣ) —ሕያው እናመልካም በሆነ እንዲሁም በላቀ ተስፋ እንኳን ትባረካላችሁ።
በዘመናት ሁሉ ስለ እርሱ ከመሰከሩት ሐዋርያት ጋር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ምስክርነቴን በደስታ አውጃለሁ። የከበረ፣ የሚዳሰስ ሥጋና አጥንት ያለው ትንሣኤን ያደረገው ቤዛችን ነው። ጌታም ለሰው ልጆች ሁሉ ባደረገው ቤዛነት እና እርቅ የተነሳ፣ መንፈሳዊ ዋስትናን እና ሕያው እና መልካም የሆነን እንዲሁም የላቀ ተስፋን ልንቀበል እንችላለን፣ “ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና” (1 ቆሮንቶስ 15፥22)።
© 2024 (እ.አ.አ) በ Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። Monthly Liahona Message, December 2024 ትርጉም። Amharic. 19296 506