ለወጣቶች ጥንካሬ
ከስህተታችሁ በኋላ—ታላላቅ ለሆኑትም እንኳን
ለወጣቶች ጥንካሬ ሚያዝያ 2026 (እ.አ.አ)


ወርሀዊ የለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ ሚያዝያ 2026 (እ.አ.አ)

ከስህተታችሁ በኋላ—ታላላቅ ለሆኑትም እንኳን

ከጴጥሮች ስለአዳኝ፣ ስለኃጢአት ክፍያው እና እንደገና ስለመመኮር ብዙ ለመማር እንችላለን።

ጴጥሮስ ክርስቶስን ሲክድ

የጤትሮስ ክህደት፣ በካርል ብሎክ

አብዛኞቻችን በቀላሉ ልንረሳው የምንመኘው ቢያንስ አንድ ትውስታ ይኖረናል። በጣም የሚያሳፍር ጊዜ፣ የሚያም አካላዊ አደጋ፣ ወይም ልትመልሷቸው የምትፈልጓቸውን ቃላት የተናገራችሁበት ክርክር ይሁን፣ በህይወት ውስጥ “እንደገና ብጀምረው” ወይም “ልሰርዘው” የሚል ስሜት እጅግ ማራኪ ሆኖ የሚሰማበት ጊዜ ብዙ ነው።

መራራ ትንቢት ተፈጸመ

ሐዋርያው ጴጥሮስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኝ አስደናቂ ሰው ነበር። ወደ ኢየሱስ በውኃ ላይ ለመሄድ እምነትና ድፍረት ነበረው፣ ነገር ግን ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ፍርሃቱ እንዲያሸንፈው ፈቀደና ለጌታ እርዳታ እየጮኸ መስጠም ጀመረ (ማቴዎስ 14፥28–31 ተመልከቱ)። ስለ ጴጥሮስ ህይወት ሁሉንም ዝርዝሮች ባናውቅም፣ በአንድ ወቅት ምርር ብሎ ማልቀሱን ግን እናውቃለን።

ኢየሱስ ክርስቶስ ከመታሰሩ ጥቂት ሰዓታት በፊት፣ ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮህ ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ እርሱን እንደሚክደው ትንቢት ተናገረ። ጴጥሮስ እንዲህ ያለውን ትንቢት ለማመን ፈቃደኛ አልሆነም እንዲሁም "እርሱም ቃሉን አበርትቶ፣ ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም” አለ (ማርቆስ 14፥31)።

በእርግጥ፣ የአዳኙ ትንቢት እውነት ሆነ። በአዳኙ መታሰር ምክንያት በነበረው ሽብርና ፍርሃት፣ የጴጥሮስ ድፍረት ከዳው። አዳኙን እንደሚያውቅ ሁለት ጊዜ ከካደ በኋላ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ሲጫኑበት፣ ጴጥሮስ፦ “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር” (ማርቆስ 14፥71)።

ዶሮ ሁለት ጊዜ በጮኸ ጊዜ እና ጴጥሮስ የአዳኙን ትንቢት ሲያስታውስ፣ “መራራ ልቅሶ አለቀሰ” (ማቴዎስ 26፥75)።

ነገር ግን የዚህ ታሪክ መጨረሻ ይህ አይደለም!

ለዘለአለም የተለወጠ አቅጣጫ

በቅዱሳት መጻህፍ ውስጥ ልንማር ከምንችለው ሁሉ፣ የጴጥሮስ ፍርሃት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለውን ምስክርነት ዳግመኛ አልሸፈነውም። ይህን በማድረግ በግሉ አደጋ ቢኖርም እንኳን፣ በእያንዳንዱ አጋጣሚ ስለ አዳኙ በድፍረት መሰከረ። አስታውሱ፣ ጴጥሮስ ያስተምራቸው የነበሩት ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርቡ የሰቀሉት ነበሩ! አደጋው እውን ነበር።

ጴጥሮስ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ የሆነን ሰው “በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ” (የሐዋርያት ሥራ 3፥6) ብሎ በፈወሰ ጊዜ፣ ከዮሐንስ ጋር ታሰረና ይህን ተአምር እንዴት እንዳደረገ ተጠየቀ።

ጴጥሮስም በድፍረት እንዲህ መለሰ፦ “እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን።

“እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” (የሐዋርያት ሥራ 4፥10–12)።

እንዴት ያለ ደፋር መልስ ነው! እንዲሁም ስለ እምነቱ ግልጽ ማስረጃ ነው።

ፍጹም በሆነ መንገድ ለማገልገል የሚችሉ ፍጽምና የሌላቸው አገልጋዮች

በዚህ ህይወት ውስጥ እያንዳንዳችን ኃጢአት እንሠራለን። የተቻለንን ሁሉ ጥረት ብናደርግም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተስፋችን እና በዓላማችን እንደናቀፋለን። የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሬዚዳንት ጄፍሪ አር. ሆላንድ [1940-2025 (እ.አ.አ)] በአንድ ወቅት እንዳስተማሩት፣ "ፍጹም አንድያ ልጅን ሳይጨምር፣ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ስራውን ለመስራት ያሉት ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ናቸው።”

መንፈሳዊ ዋጋችሁ የሚወሰነው ወይም የሚገደበው በስህተቶቻችሁ አይደለም—ታላላቅ ለሆኑትም እንኳን! ንስሐ ስለገባና ክርስቶስ ይቅር ስላለው፣ የጴጥሮስ ክህደት በኋላ ላይ በታላቅ ኃይል ከመመስከር፣ ከማስተማርና ከመለወጥ አላገደውም። ቅዱሳት መጻሕፍት ኃጢአት ስለሠሩ፣ ንስሐ ስለገቡና በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው እምነት ስለቀጠሉ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ምሳሌዎች የተሞሉ ናቸው።

ሰይጣን ሁልጊዜ ስህተቶቻችሁ እየበዙ እንደሆነና እነሱን ፈጽሞ ማሸነፍ እንደማትችሉ ሊያሳምናችሁ ይሞክራል። ውሸቱን ችላ በሉ!

የወጣት ሴቶች አጠቃላይ ፕሬዚዳንት የመጀመሪያ አማካሪ የሆኑት እህት ታማራ ደብሊው. ሩኒያ እንዲህ አስተምረዋል፦ “ይህንን መስማት ያስፈልጋችኋል፤ ስለዚህ እነዚህን ቃላት ድምፄን ከፍ አድርጌ እናገራለሁ፦ እናንተ በጭንቅላታችሁ ውስጥ የሚሠማው ድምጽ ወይም የፈፀማችኋቸው ስህተቶች አይደላችሁም። እናንተም ያንን ጮክ ብላችሁ መናገር ያስፈልጋችሁ ይሆናል። ሰይጣንን ‘ለዛሬ አልተሣካልህም’ በሉት። ወደ ኋላም እርሡት።

“ያ ወደ አዳኛችሁ የሚመልሣችሁ አምላካዊ ሀዘን ይሠማችሁ ከዚያም የእርሱ ፀጋ ወደ እናንተ እና ወደምትወዷቸው ሰዎች ህይወት ውስጥ ሲገባ ተመልከቱ። የተሰበረ ልብን በድፍረት ወደ እርሱ ባቀረብንበት ደቂቃ፣ ወዲያውኑ እዚያ [ይገኛል]።”

ኢየሱስ ክርስቶስ

Christus Consolator [አጽናኝ ክርስቶስ]፣ በካርል ብሎክ

ከፊታችሁ ያሉ ብሩህ ቀናቶቻችሁ

በዚህ የትንሣኤ ወቅት፣ ስለ አዳኙ የኃጢአት ክፍያ በጥልቀት ስታስቡ፣ ንስሐ የመግባትና እንደገና የመሞከር ችሎታችሁ ልትቀበሏቸው ከምትችሏቸው ታላላቅ ስጦታዎች አንዱ መሆኑን አስታውሱ። በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት፣ የባሰ ስህተቶቻችሁ ይቅርታ ሊደረግላቸውና እንደ ከባድ ሰንሰለት ሊወገዱ ይችላሉ።

እህት ሩኒያ እንዳስተማሩት፣ “አዳኙ ለዘለዓለም ከሃፍረት ጨለማ የበለጠ ብሩህ ነው።”

በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት፣ በእርሱ ላይ ትኩረት እስካደረጋችሁ ድረስ ተስፋ ሁልጊዜ ከፊት ለፊታችሁ በደምቅ ሁኔታ ሊያበራ ይችላል።