ወርሀዊ የ ለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ የካቲት 2026 (እ.አ.አ)
ይበልጥ ደስተኞች መሆን ትፈልጋላችሁን? አመስጋኝነትን ሞክሩ
ህይወታችሁ በፈተና የተሞላ በሆነበት ጊዜ፣ አመስጋኝነት በበጎ ነገር ላይ እንድታተኩሩ እና ተስፋን የተሞላችሁ እንድትሆኑ ሊረዳችሁ ይችላል።
ገለጻ በማጊ ስቲቨንሰን
‘’አመስጋኝ መሆን ከምትችለው በላይ ይበልጥ ደስተና መሆን አትችልም።’’
ልክ ከሰባዎቹ አንዱ የሆኑት ሽማግሌ ጌሪ ቢ ሳቢን የሰጡት ጥቅስ እንደሚያመለክተው፣ ደስተናነታችሁ የሚወሰነው ምን ያህል አመስጋኝ በመሆናችሁ ነው። ትርጉም የሚሰጥ ነው--አመስጋኝ ስትሆኑ፣ ከአሉታዊ ነገሮች ይልቅ በአዎንታዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ትጀምራላችሁ።
አሁንም ህይወት እንደጠበቃችሁት አይሄድም። ያልተጠበቁ ነገሮች ይበልጥ እንድትጨነቁ፣ እንድታዝኑ፣ ወይም ደስተኛ ከመሆን ይልቅ ተስፋ የቆረጣችሁ እንድትሆኑ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ነገር ግን ነገሮች ሲከብዱ፣ አመስጋኝነት ተስፋ የተሞላችሁ እንድትሆኑ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ወደ ሕይወታችሁ አመስጋኝነትን የሚያመጡትን እነዚህን ሶስት ነገሮች ሞክሩ።
1. መልካሙን ተመልከቱ
አብዛኛውን ጊዜ፣ አንድ ነገር እንደጎደላችሁ በተሰማችሁ ጊዜ አመስጋኝነትን ማግነት በጣም ይከብዳል። ነገር ግን ካላችሁ ነገር ይልቅ በሌላችሁ ነገር ስታተኩሩ የትኞቹን በረከቶች የምታጡ ይመስላችኋል?
በህይወታችሁ መልካሙን በፈለጋችሁ ጊዜ፣ በጊዜ ሂደት ለማግኘት ቀላል ይሆናል።
2. ለሰጪው ምስጋናን አቅርቡ
በረከታችሁን ስትቆጥሩ፣ ከየት እንደመጡ እንዳትዘነጉ።
የሰማዩ አባትን ስለስጦታው ማመስገን--የልጁን ስጦታ ጨምሮ--ለእርሱ ያላችሁን ፍቅር እና እምነት የጠለቀ ሊያደርገው ይችላል። ፕሬዘዳንት ዲ ቶድ ክሪስቶፈርሰን፣ በቀዳሚ አመራር ሁለተኛ አማካሪ፣ እንዲሁ እንደሚከተለው ገልጸዋል፣ ”ለእግዚአብሄር አመስጋኝነት እንዲሰማን ማድረግ እና መግለጽ … በሃሴት መታደስ የተሞላበትን አምልኮ ያሰርጻል፣” ደስታን እና ብርታትን በማምጣት እንዲሁም ምስክርነታችሁ አስተማማኝ እንዲሆን ያደርጋል።
3. በሰማዩ አባት እቅድ ላይ ማተኮር
በግልጽ፣ አመስጋኝ መሆን ማለት በህይወት ውስጥ ያሉትን ከባድ ነገሮች መርሳት ማለት ወይም ሁል ጊዜ ደስተኛ መሆን ማለት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ ህመምን ያውቅ እና ተሰምቶት ነበር ( አልማ 7፥11፤ ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 19፥18-19)። የሃዘን ስሜት የምድራዊነት የተለመደ ክፍል ነው።
ምንም ይሁን ምን፣ አንድ ነገር በፍጹም አይቀየርም፤ የሰማይ አባት የምህረት እቅድ። በህይወት የምትለማመዱት ሃዘንም ሆነ ጉዳት ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በሃጢያት ክፍያው ምክንያት ይስተካከላል ( ራእይ 21፥4ተመልከቱ)።
የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ቡድን ሽማግሌ ዲይተር ኤፍ. ኡክዶርፍ፤ “በጭንቀት ጊዜ አመስጋኝ መሆን ማለት በሁኔታዎቻችን ሁሉ ደስተኛ መሆን አይደለም በማለት ገልጸዋል። በእምነት አይኖች አማካይነት በዚህ ወቅት ከሚገጥሙን ችግሮች ባሻገር እንመለከታለን ማለት ነው።’’
© 2026 by Intellectual Reserve, Inc. መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ ታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፤ 6/19። ወርሀዊ የ ለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ የካቲት 2026 (እ.አ.አ)ትርጉም። Amharic. 19935 506