2025
እርዳታ ከኢየሱስ ክርስቶስ፡ ለምን እና እንዴት
ለወጣቶች ጥንካሬ፣ መጋቢት 2025 (እ.አ.አ)


ወርሀዊ የለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ ሚያዝያ 2025 (እ.አ.አ)

እርዳታ ከኢየሱስ ክርስቶስ: ለምን እና እንዴት

ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን መልስ እንደሆነ እና እንዴት እንደሚረዳችሁ ተረዱ።

ኢየሱስ ክርስቶስ

ምስል በዳን ዊልሰን

“ማበላሸቴን እንደቀጠልኩ ይሰማኛል። መሞከር መቀጠል ከባድ ነው።”

“ሁኔታዬ አስቸጋሪ ነው። እንዴት ወደፊት መቀጠል እንዳለብኝ እርግጠኛ አይደለሁም።”

“ስለወደፊቱ እጨነቃለሁ። ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልገኝ ነገር ይኖረኝ እንደሆን አላውቅም።

“ደክሞኛል፣ ነገር ግን ገና ብዙ መስራት ያለብኝ ነገር አለ።”

ከእነዚህ ችግሮች አንዳቸው ሊመለከቷችሁ ይችሉ ይሆን? ፕሬዘደንት ራስል ኤም ኔልሰን “ምንም አይነት ጥያቄዎች ወይም ችግሮች ቢኖሩባችሁ፣ መልሱ ሁል ጊዜም በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት እና ትምህርቶች ውስጥ ይገኛል” (“መልሱ ሁል ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣” አፕሪል 2023 አጠቃላይ ጉባኤ [ሊያሆና፣ ግንቦት 2023 (እ.አ.አ)፣ 127])።

“ኢየሱስ ክርስቶስ መልስ ነው” ማለት ቀላል ነው። እርሱ መልሱ ለምን እና እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ትንሽ ተጨማሪ ጥረት ይጠይቃል።

ክርስቶስ መልስ የሆነው ለምንድነው?

የኃጢያት ክፍያውን በፈጸመ ጊዜ፣ አዳኙ ሶስት አስፈላጊ ነገሮችን አድርጓል፡-

  1. ሞትን በማሸነፍ ትንሣኤ እንድናደርግ አስችሎናል።

  2. የኃጢአትን ሁሉ ዋጋ በመክፈል ንስሐ እንድንገባ፣ እንድናድግ እና ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ አድርጎናል። ይህ ደግሞ ክርስቶስ ኃጢአታቸውን በራሱ ላይ ወስዷልና ሌሎች ሲበድሉ ይቅር እንድንል ይረዳናል።

  3. ሁሉም አይነት ህመሞች፣ ስቃዮች፣ ፈተናዎች፣ በሽታዎች እና ድክመቶች አጋጥመውታል (አልማ 7፡11–13 ይመልከቱ)። ያ ማለት እንዴት እንደሚረዳችሁ እና እንደሚፈውሳችሁ ያውቃል ማለት ነው እንዲሁም ፈተናዎችን እንድትቋቋሙ እና የተሻለ ለመሆን እንድትጥሩ ሊያበረታታችሁ ይችላል።

ማንኛውንም ችግር ምረጡ፣ መፍትሄውን ከሶስቱ እውነቶች በአንዱ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑት ላይ ማገናኘት ትችላላችሁ።

ድህነት? ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ነገር ስላሳለፈ፣ ምን እንደሚመስል በትክክል ያውቃል። ሁልጊዜ መሰናክልን አያስወግድም፣ ነገር ግን ያንን ሸክም የተሸከሙ ሰዎችን ማጠንከር ይችላል (ሞዛያ 24፡15 ይመልከቱ)።

ውድቀት? ክርስቶስ ኃጢአትን ስላሸነፈ፣ የእኛ ውድቀቶች ዘላቂ አይሆኑም። ንስሃ መግባት ማለት መሻሻል እና እኛ መሆን እንደምንችል የሚያውቀው ሰው መሆንን ይጨምራል።

በሽታ? እርሱ ሞትን ስላሸነፈ፣ ከበሽታና ከሥቃይ ነፃ የሆነ ፍጹም አካል ይዘን ትንሳኤ እናደርጋለን። እንዲሁም ክርስቶስ “በሽታን በራሱ ላይ” (አልማ 7፡11) መውሰዱ ለማጽናናት እና ለመደገፍ የሚሆን ፍጹም ሰው ያደርገዋል።

ክርስቶስ የሚረዳው እንዴት ነው?

አዳኙ ለምን መልስ እንደሆነ ብናውቅም እንኳን (በማንነቱ እና ባደረገልን ምክንያት) አሁንም ከእሱ እርዳታ እና ብርታት እንዴት ማግኘት እንደምንችል ማወቅ ግን ይኖርብናል። ጥቂቶቹ መንገዶች የሚከተለቱ ናቸው፣

ጸሎት። እንደ እኛ ያሉ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመጸለይ ፍጹም ከሆነው እግዚአብሄር ጋር መነጋገር ይችላሉ። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ለሚያስፈልገን ጥንካሬ መጸለይ እንችላለን፣ ሁልጊዜ በምንፈልገው ወይም በምንጠብቀው መንገድ ሳይሆን በሚባርከን መንገድ እግዚአብሔርም መልስ ይሰጣል። የአዳኙ ግብዣ እውነት ነው፡ “ለምኑ፣ ይሰጣችኋል” (ዮሐንስ 16፡243 ኔፊ 27፡29ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 4፡7)።

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሰማይ አባት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እና መንፈስ ቅዱስ በዓላማ አንድ ናቸው። አብረው ይሰራሉ! በማንኛውም ጊዜ ከመንፈስ ቅዱስ መመሪያን ስታገኙ ወይም መጽናናት ሲሰማችሁ ክርስቶስ እየረዳችሁ እንደሆነ መረዳት ትችላላችሁ።

ቃል ኪዳኖችን መጠበቅ። የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ቡድን ሽማግሌ ዴል ጂ. ረንለንድ እንዲህ አስተምረዋል “የቃል ኪዳን መንገድ የሚለው ቃል ወደ ክርስቶስ የምንመጣበትን እና ከእርሱ ጋር የምንገናኝባቸውን ተከታታይ ኪዳኖችን ያመለክታል። በዚህ የቃል ኪዳን ትስስር፣ ዘላለማዊ ኃይሉን ማግኘት እንችላለን።” (ሚያዚያ 2023 አጠቃላይ ጉባኤ [ሊያሆና፣ ግንቦት 2023 (እ.አ.አ)፣ 36])።

ጸጋ። በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ስንለማመድ እና ንስሃ ስንገባ፣ በራሳችን የማንችላቸውን ነገሮች ለማከናወን ተጨማሪ እርዳታ እና ጥንካሬ (ጸጋ ተብሎም ይጠራል) ማግኘት እንችላለን (የቅዱሳት መጻሕፍት መመሪያ፣ “ጸጋ” የሚለውን ይመልከቱ)። ይህ ጥንካሬ ወይም ጸጋ በብዙ መንገዶች ሊመጣ ይችላል፡ ከመንፈስ ቅዱስ፣ ከጓደኛ፣ ከማናውቀው ሰው፣ በሚሰማን ስሜት። በመሠረቱ፣ ማንኛውም መልካም ነገር የሚመጣው ከክርስቶስ ነው (ሞሮኒ 7፡22 ይመልከቱ)። ትንሽ ተጨማሪ ትዕግስት፣ ትንሽ ተጨማሪ ጉልበት፣ ለመታገስ ትንሽ ተጨማሪ ጥንካሬ ስታገኙ ክርስቶስ እየረዳችሁ እንደሆነ አስተውሉ።

ለምን እና እንዴት እንደሆነ አስታውሱ

ስለዚህ በሚቀጥለው ጊዜ ለጥያቄ ወይም ለችግር መልስ በምትፈልጉ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተመልከቱ። በኃጢአት፣ በሞት እና በሌሎች ምድራዊ ፈተናዎች ላይ ባደረገው ድል የተነሳ የማይቻል ነገር እንደሌለ አስታውሱ። እርሱ እንዴት ሊባርካችሁ እንደሚችል ስትፈልጉ በህይወታችሁ ውስጥ የእሱን ተጽዕኖ ታያላችሁ። እርሱ ከልቡ ይወዳችኋል!